No summary available.
መጋቢት 17 ቀን 2007 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመሰል አመልካች፡- ንብ ኢንሹራንስ (አ.ማ) - ነገረ ፈጅ ተስፋሁን ሽብሩ - ቀረቡ ተጠሪ፡- ራዲካል ኢንጅነሪንግ ኃላ/የተ/የግል ማህበር - አልቀረበም።
መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ መጋቢት 22 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው የአፈፃፀም ትዕዛዝና የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት በመዝገብ ሚያዝያ 3 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ ፍርድ አፈፃፀም የሚመለከት ነው።
የክርክሩ መነሻ ተጠሪ ያቀረበው የአፈፃፀም ክስ ነው። ተጠሪ አመልካች ወጪና ኪሣራን ጨምሮ አመልካች በፍርድ የተወሰነበትን / አምስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ሺ ስምንት መቶ ሰማኒያ ብር / እንዲከፍል የአፈፃፀም ትዕዛዝ ይሰጥልኝ በማለት ለሥር ፍርድ ቤት የአፈፃፀም ክስ አቅርቧል። የሥር ፍርድ ቤት አመልካች በፍርዱ መሰረት የማይፈፀምበትን ምክንያት ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቶ አመልካች የፍርድ ባለመብት /ተጠሪ/ የሚከናወን ቅሪት ለመሸጥ የሚያስፈልግ ላብሬና ውክልና እንዲሰጠን ብንጠይቀው ፈቃደኛ ባለመሆኑ በፍርድ የተወሰነብኝን ገንዘብ አልከፈልኩም የሚል መከራከሪያ አቅርቧል። የስር ፍርድ ቤት አመልካች ያቀረበው መከራከሪያ በፍርድ የተወሰነበትን ገንዘብ ባለመክፈል በቂ ምክንያት ላሆን አይችልም በማለት አመልካች እንደ ፍርዱ እንዲፈፅም ትዕዛዝ ሰጥቷል። አመልካች በዚህ ትዕዛዝ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቧል። ይግባኝ ሰሚው ችሎት የአመልካችን ይግባኝ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 መሰረት ሰርዞታል።
አመልካች በዚህ ትዕዛዝ ቅር በመሰኘት ሚያዝያ 6 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ የሰበር አቤቱታ አቅርቧል። አመልካች በመኪናው ላይ የደረሰውን ጠቅላላ ጉዳት ብር 450,000 በመክፈል ተሽከርካሪውን የማስቀረት መብት በመድን ውሉ ውስጥ ተሰጥቷል። ስለዚህ ተጠሪ በፍርድ የተወሰነበትን ገንዘብ እንዲከፈለው ጉዳት የደረሰበትን ተሽከርካሪ ለአመልካች እንዲያስረክብ፣ጉዳት የደረሰበትን ተሽከርካሪ አስጠግኖ ለመሸጥ፣ለመለወጥ የሚያስችል ውክልና የመኪና ላብሬና ተሽከርካሪ ከዕዳና እገዳ እንዲሁም ከግብር ዕዳ ነፃ መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃና ክላራንስ ለአመልካች የመስጠት ግድታውን መወጣት ይገባዋል።
ተጠሪ ይህንን ሳይፈፅም ገንዘቡን ክፈል መባሉ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክቷል።
ተጠሪ ግንቦት 5 ቀን 2006 ዓ.ም በተፃፈ መልስ፣ፍርድ የሚፈፀመው የተሰጠው ፍርድ ይዘት መሰረት በማድረግ ነው። አመልካች በአፈፃፀም ወቅት ካነሳቸው መከራከሪያዎች በዋናው ጉዳይ ስንከራከር አንስቶ ፍርድ አላረፈበትም ይህ ከሆነ አመልካች በፍርድ የተወሰነበትን እንድፈጽም ስጠይቅ በፍርድ ተረጋግጦ ውሣኔ ያላረፈበትን ቅድመ ሁኔታ በመደርደር ፍርዱን ለመፈፀም እንቢተኛ መሆኑ የሕግ መሰረት ያለው አይደለም። ስለዚህ የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ችሎት የሰጡት ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክሯል። አመልካች ግንቦት 27 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር የቀረበው ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡት የአፈፃፀም ትዕዛዝ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው አመልካች በተጠሪ ብር 589,850 / አምስት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ሺ ስምንት መቶ ሃምሳ ብር/ ለተጠሪ እንድከፍል በፍርድ ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑንና የፍርድ ባለመብቱ ተጠሪ በፍርድ የተወሰነለትን ገንዘብ አመልካች እንዲከፍለውና ፍርዱ እንዲፈጽምለት ጥያቄ ያቀረበ መሆኑን ግራቀኙ በሥርና በሰበር ደረጃ ካቀረቡት ክርክር ተረድተናል። አመልካች በፍርዱ መሰረት ፍርድ የማይፈፀምበትን ቀርቦ እንዲያስረዳ በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 383 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት እንዲያቀርብ የተጠሪው አመልካች ከተጠሪ ጋር ባለው የመድን ውል መሰረት በመኪናው ላይ የደረሰው ጉዳት ሰባ አምስት ፐርሰንት ከሆነ የመኪናውን በመድን ውሉ የተመለከተውን ሙሉ ዋጋ ከፍሎ የመረከብ መብት እንዳለው ገልፆ፣ገንዘቡን ለመክፈል በመጀመሪያ የመኪናውን ቅሪት፣ተጠሪ ላያስረክበኝ ይገባል። የመኪናውን ላብሬና ውክልና ላሰጠኝ ይገባል የሚል መቃወሚያ አቅርቧል። አመልካች በመድን ውሉና አግባብነት ባላቸው ሕጎች መሰረት አለኝ የሚለው የመኪናውን ቅሪትና ልሎች መኪናውን ለማስጠገንና ለሶስተኛ ወገን ለማስተላለፍ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች የመረከብ መብት፣የፍታብሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 30 እና የፍታብሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 215(2) መሰረት የተከሳሽ ከሳሽነት ክስ በማቅረብ በፍርድ ያስወሰነ ስለመሆኑ ያቀረበው የፍርድ ቤት ውሣኔ የለም። ከዚህ በተጨማሪ አመልካች በአፈፃፀም ወቅት መከራከሪያ አድርጎ ያቀረባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች የክስ መከላከያ አድርጎ አቅርቦ፣ፍርዱን የሰጠው ፍርድ ቤት በጭብጥነት ይዞ፣ውሣኔ የሰጠባቸውና ፍርድ ያረፈባቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ የፍርድ ቤት ውሣኔ አላቀረበም።
ፍርድ የሚፈፀመው በፍርድ ውስጥ በተገለፀው ውሳኔ መሰረት መሆኑን የፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 378 ንዑስ አንቀጽ 1 ደንግጓል። ከዚህ በተጨማሪ የፍርድ ባለመብት ፍርዱን እንዲፈፀምለት ሲጠይቅ፣የፍርድ ባለዕዳው፣የፍርድ ባለመብቱ ተነጻጻሪ የሆነ ግድታውን እንዲወጣ ትዕዛዝ ይስጥልኝ በማለት ጥያቄ ለማቅረብ የሚችለው በአንድ ፍርድ ውስጥ ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች የፍርድ ባለመብት መሆናቸው ተረጋግጦ ውሳኔ ተሰጥቶበት እንደሆነ መሆኑን ከፍትሐብሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 398 ድንጋጌ ለመረዳት ይቻላል። በያዝነው ጉዳይ አመልካች ከመድን ውሉና አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ተጠሪ ላፈፅምልኝ የሚገባው ግድታ አለ በማለት በአፈፃፀም መከራከሪያ አድርጎ ያቀረባቸው ነጥቦች በዋናው ጉዳይ መከራከሪያ ሆነው ቀርበው ፍርድ የተሰጠባቸው አይደሉም ይህ ከሆነ አመልካች ከተጠሪ የሚጠይቀው መብት ካለ፣በሕግ አግባብ ክስ አቅርቦ በፍርድ ተረጋግጦ እንድንወስንለት ከሚጠይቅ በስተቀር፣ፍርድ ያላረፈበትን ቅድመ ሁኔታ በአፈፃፀም ክርክር በመደርደር ፍርዱን የመፈፀም ግድታ የለብኝም በማለት ያቀረበው መቃወሚያ የሕግ መሰረት ያለው አይደለም። በመሆኑም አመልካች ፍርዱን የማይፈፅምበት በቂ አሳማኝና ህጋዊ ምክንያት አላቀረበም በማለት የሥር ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚው ችሎት የሰጡት የአፈፃፀም ትዕዛዝ ከላይ የጠቀስናቸውን የሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገና መሰረታዊ የሕግ ስህተት የልለበት ነው በማለት ወስነናል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጡት ትዕዛዝ ፀንቷል።
በዚህ ፍርድ ቤት
No topics extracted.