No summary available.
ታህሳስ 21 ቀን 2007 ዓ/ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመሰል አመልካች፡- ወ/ሪት ሄለን ተክል - ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ ዘይድ አብርሃ - የቀረበ የለም **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የውርስ ንብረት ይጣራልኝ ጥያቄን የሚመለከት ነው።ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች የሟች አባታቸው የአቶ ተክል ነጋሽ የውርስ ንብረት እንዲጣራላቸው ባቀረቡት አቤቱታ መነሻ ነው። የውርስ አጣሪው በፍርድ ቤቱ ተቋቁሞ የማጣራት ስራውን ከአጠናቀቀ በኋላ ሪፖርቱ ለፍርድ ቤቱ ቀርቦ ግራ ቀኙ አስተያየት ከሰጡበት በኋላ የውርስ አጣሪው ሪፖርት ተሻሽሎ በስር ፍርድ ቤት ፀድቋል።በዚህ ውሳኔ የአሁኗ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አፅንቶታል።የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- አመልካች ሶፋውን ከእነ ሙሉ ጠረጴዛ የግል ንብረቴ ነው በማለት ጠይቀው እያለ በንብረቱ ላይ የግል ወይም የጋራ ነው ተብሎ ዳኝነት ሳይሰጥበት መታለፉ እና የቀበል ቤት የተከራይነት መብትን በተመለከተም አመልካች በወራሽነታቸው የሚገባቸው ስለመሆኑ በፍርድ ቤት መወሰን ሲገባው በቤቱ አካራይ የሚወሰን ነው ተብሎ መታለፉ ያላግባብ ነው በማለት መከራከራቸውን የሚያሳይ ነው።አቤቱታቸው ተመርምሮም በዚህ ችሎት ላታይ የሚገባው ነው ተብሎ ተጠሪ እንዲቀርቡ ተደርጎ ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም የችሎቱን ምላሽ የሚያስፈልጋቸው አበይት ነጥቦች፡-
የሚሉ ሁነው ተገኝተዋል።
የመጀመሪያውን ጭብጥ በተመለከተ፡-አመልካች የሟች አቶ ተክል ነጋሽ ወራሽ መሆናቸውን ጠቅሰውና የሟቹ ንብረት እንዲጣራ የውርስ አጣሪ በፍርድ ቤት እንዲሾም ጠይቀው ፍርድ ቤቱም የውርስ አጣሪው እንዲቋቋም አድርጎ አመልካች ላጣራ የሚገባቸውን የውርስ ንብረቶች ህዳር 05 ቀን 2005 ዓ/ም በፃፉት ማመልከቻ ዘርዝረው ያቀረቡ መሆናቸውን፣በዚህ የንብረት ዝርዝርም ከሟቹ መኖሪያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ንብረቶች ናቸው በሚል ወደ 48 የሚሆኑ የቤት መገልገለያ እቃዎችን መጥቀሳቸው የውርስ አጣሪው ከአቀረበው የውርስ ማጣራት ሪፖርት መጠቀሱን ከስር ፍርድ ቤት የውሳኔ ግልባጭ የተመለከተን ሲሆን በዚህ የንብረት ዝርዝር ውስጥ አመልካች በሟቹ መኖሪያ ቤት ሶፋ ከእነ ሙሉ ጠረጴዛ አለ በማለት የጠቀሱት ነገር እንደልለ ግልባጩ የሚያሳይ ሁኖ አግኝተናል።ከዚህም መረዳት የሚቻለው አመልካች ይህንኑ ንብረት የውርስ ንብረት ነው በማለት በዚህ ረገድ ተገቢው መጣራት እንዲደረግላቸው የማጣራት ስራውን እንዲያከናውን በፍርድ ቤት ለተሾመው የውርስ አጣሪ ጥያቄ ያላቀረቡ ከመሆኑም በላይ የማጣራት ስራውን ሲከታተል ለነበረው ፍርድ ቤትም በተገቢው ጊዜ በዚህ ረገድ ያቀረቡት ጥያቄ ያለመኖሩን የክርክሩ ሂደት ያሳያል።እንዲህ ከሆነ አመልካች ሶፋው ከእነ ሙሉ ጠረጴዛ ዳኝነት ተጠይቆበት የግል ወይም የጋራ ነው ተብሎ ውሳኔ ሳያርፍበት ቀርቷል በማለት የሚያቀርቡት ቅሬታ በስር ፍርድ ቤት የዳኝነት ጥያቄ ያልቀረበበት በመሆኑ እና የስር ፍርድ ቤት ደግሞ ባልተጠየቀ ጉዳይ ዳኝነት የሚሰጥበት አግባብ የልለ ስለመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 182 (1) ድንጋጌ ስር የተመለከተ በመሆኑ ይህ ችሎት በዚህ ረገድ አመልካች የሚያቀርቡትን ቅሬታ የሚቀበለው ሁኖ አልተገኘም።
ሁለተኛውን ጭብጥ በተመለከተ፡- አመልካች የሟች አቶ ተክል ነጋሽ ወራሽ መሆናቸውንና ሟቹ ከቀበል ተከራይተው ይኖሩበት የነበረ መኖሪያ ቤት እንዳላቸው ጠቅሰው የሟች አባታቸው የተከራይነት መብት እንዲተላለፍላቸው ዳኝነት እንዲያርፍበት ጥያቄ ማቅረባቸውን የክርክሩ ሂደት ያሳያል።የበታች ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ የቀረበውን የአመልካችን የዳኝነት ጥያቄ ያለፉት ጉዳዩ በቤቱ ባለቤት የሚወሰን እንጂ በፍርድ ቤት የሚወሰን አይደለም በሚል ነው።ይሁን እንጂ የቀበል ቤት የተከራይነት መብት ተከራይ ሲሞት ለወራሾቹ ወይም ለቤተሰቦቹ የሚተላለፍ መሆን ያለመሆኑ በፍ/ብ/ሕጉ ስለማይንቀሳቀስ ንብረት የኪራይ ውል የተመለከቱትን ድንጋጌዎች፣የቀበል ቤትን የኪራይ መብትና ግድታ ለመግዛት በሚመለከተው አካል በወጡት ደንብና መመሪያዎች አንጻር ታይቶ በፍርድ ቤት ዳኝነት የሚሰጥበት እንጂ የቤቱ አስተዳዳሪ የሆነ ቀበል ለፈለገው ሰው የሚያከራየው ነው ተብሎ በፍርድ እንዳያልቅ የሚደረግ ጉዳይ አይደለም።የቀበል ቤት የተከራይነት መብት የሚሰጥበት አግባብ በሕግ ስርዓት የሚዘረጋለትና የራሱ የሆነ አስራር ያለ መሆኑ የሚታወቅ ነው።መብቱ በሕጉ በተዘረጋው ስርዓትና አሰራር መሰረት መፈፀሙ ያለመፈፀሙ ላይ ክርክር ሲነሳ ደግሞ ነፃና ገለልተኛ በሆነ አካል፤በፍርድ ቤት ታይቶ አግባብነት ያላቸውን ማስረጃዎችን፣ህጎችንና አሰራሮችን መሰረት በማድረግ ዳኝነት የሚሰጥበት እንጂ ጉዳዩ የቤቱ አስተዳዳሪ ለሆነው አካል የሚተው አይደለም።የቀበል ቤት የተከራይነት መብት ላይ ክርክር ሲነሳ ጉዳዩ ለቤቱ አስተዳዳሪ ለሆነው ለቀበል የሚተው ነው ከተባለ የቀበል ቤት የተከራይነት መብት ማግኘት ያለባቸው ግለሰቦችም መብታቸውን በአግባቡ ለማስከበር የሚችሉበት አግባብ ይኖራል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም።በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች አንድ የቀበል ቤትን ተከራይቶ የነበረ ሰው ከዚህ አለም በሞት ሲለይ ወራሾቹ ወይም ቤተሰቦቹ የተከራይነት መብቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አግባብ ከኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ህገ መንግስት አንቀጽ 37፣ከፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 826(2) እና 2928 ድንጋጌዎች እንዲሁም በዚህ ረገድ የወጣውን መመሪያና ተቀባይነት ያለውን አሰራር በመመልከት የራሳቸው በቂ መተዳደሪያ የልላቸው ዜጎች ከመንግስት ላደረግላቸው ከሚገባው ድጋፍ ጭምር በመመርመር ዳኝነት መስጠት ሲገባቸው ጉዳዩ በፍርድ ቤት የሚያልቅ አይደለም በማለት የአመልካችን የቀበል ቤቱን የተከራይነት መብት የውርስ ጥያቄ ማለፋቸው መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል።በአጠቃላይ ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች ተከታዩን ወስነናል።
No topics extracted.
ው ሣ ኔ
በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ መጋቢት 10 ቀን 2005 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ታህሳስ 22 ቀን 2006 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሐል።
በየካ ክፍለ ከተማ በወረዳ 06 ክልል ውስጥ በሚገኘው ቁጥሩ 009 በሆነው የቀበል ቤት ላይ አመልካች ተከራይ የነበሩትን ሟች አባታቸውን አቶ ተክል ነጋሽ መብት ለመውረስ ያቀረቡት ጥያቄ በፍርድ ቤት የሚወሰን አይደለም ተብሎ በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ተሸሯል።በቤቱ ላይ የቀረበው የተከራይነት መብት የውርስ ጥያቄ በፍርድ ቤት የሚያልቅ ነው በማለት በዚህ ነጥብ ላይ የፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክርክሩን ቀጥሎ በፍርድ ሐተታው ላይ በተመለከተው አግባብ ጉዳዩን አጣርቶና ተገቢውን የክርክር አመራር ሁሉ በመከተል ተገቢውን ዳኝነት ላሰጥበት ይገባል በማለት ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 341(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል።ይጻፍ።
ሶፋን ከእነ ሙሉ ጠረጴዛ በተመለከተ የበታች ፍርድ ቤቶች ማለፋቸውም ሆነ በልሎች ንብረቶች ላይ የሰጡት የውሳኔ ክፍል ላይ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውንወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።