No summary available.
ህዳር 8 ቀን 2007 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመሰል አመልካች፡-
አሳመነው ከበደ
ወ/ሮ ፍቅርተ ከበደ ጠበቃ አቶ ፍሰሀ አለማየሁ ቀረቡ።
አቶ ምንተስኖት ከበደ - ቀረቡ
ተማሪ ቀንአየሁ ከበደ
ተማሪ ብሩክ ከበደ ተጠሪ፡- አቶ ዳንኤል ከበደ- ጠበቃ አቶ በየነ ታደሰ ቀረቡ።
መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካቾች የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ግንቦት 21 ቀን 2005 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔና የፍድራል የከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ጥር 14 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልን በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው።
ጉዳዩ የውርስ ንብረት ጥያቄን የሚመለከት ነው። በሥር ፍርድ ቤት ተጠሪ አመልካች አመልካችዎች ተጠሪ በመሆን ተከራክረዋል።
አመልካቾች ውርስ አጣሪ ቢመደብና የውርሱ ንብረት ተጣርቶ ቢቀርብ አንቃወምም በማለት መልስ ሰጥተዋል። ፍርድ ቤቱም ውርስ አጣሪ ከመደበ በኋላ ውርሱ ሲጣራ ተጠሪ ሟች በ 24/11/1980 ዓ.ም በተፃፈ የስጦታ ውል በ210 ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ አንድ ክፍል ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት ሰጥቶኝ አባታችን በህይወት እያለ ቆርቆሮ ቤቱን በማፍረስ ሁለት ክፍል የጭቃ ቤት ሰርቼ እየኖርኩበት እገኛለሁ። ቤቱ ዋናውን 568 ካሬ ሜትር ግቢው ውሰጥ የሚገኝና ቦታውም ራሱን የቻለ ካርታ የልለው በመሆኑ ሁለት ክፍል የጭቃ ቤት 210 ካሬ ሜትርይዞታ ከውርስ ንብረቱ ተለይቶ እንድያዝልኝ በማለት ለውርስ አጣሪው ጥያቄ አቅርቧል።አመልካቾች የይርጋ መቃወሚያ አቅርበዋል።
ስጦታው በፍትሐበሕር ሕግ ቁጥር 2443 እና የፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 881 መስፈርቶች የማያሟላ በመሆኑ ህጋዊ ውጤት የለውም በማለት ተከራክረዋል። የሥር ፍርድ ቤት ስጦታው በፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 2443 እና በፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 881 የተደነገገውን መስፈረት ስለማያሟላ፣ ስጦታው ፈራሽ ነው በማለት ወስኗል።
ሆኖም ሁለት ክፍል ጭቃ ቤት የሥር አመልካቹ የአሁን ተጠሪ ያሰራው መሆኑን በሰውና በፅሑፍ ማሥረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ በ201 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ የተሰራው ሁለት ክፍል ቤት የውርስ ንብረት ሣይሆን የአመልካች /የተጠሪ/ የግል ንብረት ነው በማለት ውሣኔ ሰጥቷል።
አመልካቾች በዚሁ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዋል። የከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኙን በፍ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 337 መሰረት ሰርዞታል። አመልካቾች ጥር 8 ቀን 2006 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ በ210 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አንድ ክፍል ቤት እንድሰራ በሰጦታ ተሰጥቶኝ ቤቱን አፍርሸ ሁለት ክፍል ቤት ሰርቻለሁ በማለት ክስ አቅርቧል። የስጦታ ውሉ የሕጉን ፎርም አያሟላም ተብሎ ውድቅ ተደርጓል። ይህ ከሆነ ተጠሪ አማራጭ የዳኝነት ጥያቄ ያላቀረበበትን የፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 1179 ጠቅሶ መወሰኑ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት። ተጠሪ ቤቱን መሥራቱን አመልካቾች አላመኑም። ቤቱን መስራቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አላቀረበም። ስለዚህ ቤቱን ያሰራው ተጠሪ ነው መባሉ ስህተት ነው። ተጠሪ ሰራሁ የሚለውን ቤት ከ30 ካሬ ሜትር በማይበልጥ ቦታ ላይ ያረፈ ሆኖ እያለ 210 ካሬ ሜትር የይዞታ ቦታ የውርስ ንብረት ክፍል እንዳልሆነ የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክተዋል።
ተጠሪ የካቲት 21 ቀን 2006 ዓ.ም በተፃፈ መልስ አመልካቾች ቤቱንና ሽንት ቤቱን በግል የሰራሁት መሆኔን ገልጬ ያቀረብኩትን ክስ በግልፅ ክደው ክርክር አላቀረቡም።
ተጠሪ 1179 ድንጋጌን በመጥቀስ በቃል ክርክርና በፅሑፍ ለሥር ፍርድ ቤት አማራጭ ክርክር አቅርቤያለሁ። አመልካቾች ቤት ያረፈበት በ3ዐ ካሬ ሜትር የሚሆነው ይዞታ እንጅ 21ዐ ካሬ ሜትር አይደለም በማለት ያቀረቡት ክርክር በሥር ፍርድ ቤት ያልቀረበ አዲስ የፍሬ ነገር ክርክር ነው። ስለዚህ የበታች ፍርድ ቤት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የልለበት በመሆኑ እንዲፀናልኝ በማለት መልስ ሰጥቷል። አመልካቾች የመልስ መልስ አቅርበዋል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ግራ ቀኙ ያቀረቡት የፅሑፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የበታች ፍርድ ቤቶች በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 የቤት ቁጥር 429 ግቢና ስፋቱ 568 ካሬ ሜትር ቦታ ውስጥ የሚገኘው ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤትና አንድ ክፍል ሽንት ቤትና ቤቶቹ የተሰሩት 21ዐ ካሬ ሜትር የይዞታ ቦታ የውርስ ንብረት ሣይሆን የተጠሪ የግል ቤትና ይዞታ ነው በማለት የሰጡት ውሣኔ የሕግ መሰረት አለው ወይስ የለውም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው ከላይ የተያዘውን ጭብጥ ለመወሰን ተጠሪ ለሥር ፍርድ ቤት ያቀረበውን የዳኝነት ጥያቄ መሰረታዊ ይዞታና በተጠሪና በአመልካቾች ክርክር ማስረጃ የተረጋገጡትን መሰረታዊ ፍሬ ጉዳዩች መመርመር ያስፈልጋል።ተጠሪ ለሥር ፍርድ ቤትና ለውርስ አጣሪው ያቀረበው የዳኝነት ጥያቄ ሁለት መሰረታዊ መብቶች ተረጋግጠው በፍርድ እንዲወሰንለት የሚጠይቅ ነው። የመጀመሪያው ሟች ወላጅ አባቴ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 የቤት ቁጥር 429 ግቢ ውስጥ ሰርቶት የነበረውን አንድ ክፍል ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት ሐምል 24 ቀን 1980 ዓ.ም ባደረገው የስጦታ ውል ሰጥቶኛል። ከዚህ በኂላ ሰጭው ወላጅ አባቴ በህይወት እያለ የሰጠኝን አንድ ክፍል ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት በማፍረስ ፣ በራሴ ወጪ ሁለት ክፍል ሰርቪስ የጭቃ ቤትና አንድ ክፍል ሽንት ቤት ገንብቼ የኖርኩበት ስለሆነ ሁለቱ ክፍል ሰርቪስ ቤቶችና አንድ ክፍል ሽንት ቤት የሟች የውርስ ንብረት ክፍል አለመሆኑ ተረጋግጦ ይወሰንልኝ የሚል ይዘት ያለው ነው። ሁለተኛ የዳኝነት ጥያቄ ወላጅ አባቴ ሐምል 24 ቀን 1980 ዓ.ም ባደረገው የስጦታ ውል አንድ ክፍል ቆርቆር በቆርቆሮ የተሰራ ቤት ሣይሆን ሟች ከነበረው 568 ካሬ ሜትር የይዞታ መሬት210 ካሬ ሜትር ይዞታ በስጦታ ያስተላለፈልኝና ይህ የይዞታ መሬት ከጠቅላላው 568 ካሬሜትር ይዞታ ያልተለየ በመሆኑ ተለይቶና ተከልሎ እንዲሰጠኝ ይወሰንልኝ የሚል ይዘት ያለው ነው።
ተጠሪ መብት አግኝበታለሁ የሚሉት የስጦታ ውል በፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 2443 እና በፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 881 የተደነገጉትን መስፈርቶች የማያሟላ መሆኑ ፍሬ ነገር የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው ፍርድ ቤቶች ተረጋግጧል።
በዚህ ምክንያት ተጠሪ የግል ንብረቴ ናቸው የሚላቸውን ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤቶችና አንድ ክፍል ሽንት ቤት ላይ መብት ያላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ የሥጦታ ውሉ መሰረት እንደማይሆንና የሥጦታ ውሉ ህጋዊ መብት እንደልለው የበታች ፍርድ ቤቶች ወስነዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪ የውርስ ንብረት ከሆነው የቤት ቁጥር 429 አጠቃላይ 568 ካሬ ሜትር ስኩየር የይዞታ ቦታ 21ዐ ካሬ ሜትር ስኩዌር በስጦታ ይተላለፍልኝ የግል ይዞታዬ ነው በማለት ያቀረበው ክርክር የስጦታ ውሉ ፈራሽ ነው በመባሉ ምክንያት የሕግ መሰረት የልለው መሆኑን ለመረዳት ይቻላል። በአጠቃላይ ሲታይ ተጠሪ የስጦታ ውሉን መነሻ በማድረግ ሰርቪስና ሽንት ቤቱ በ 21ዐ ካሬ ሜትር የይዞታ ቦታ ላይ ያቀረበው የመብት ጥያቄ፣የስጦታ ውሉ የሕጉን ፎርም ያላሟላ ፈራሽ ነው በመባሉ ምክንያት ውሉ በሙሉ ውድቅ የተደረገ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል።
በአንድ ሰው የይዞታ መሬት ላይ ባለይዞታው ሣይቃወም ህንፃ የገነባ ሰው የህንፃው ባለቤት እንደሚሆን፣ በፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 1179 ንዑስ አንቀጽ 1 ይደነግጋል።
ከዚህ አንፃር ሲታይ ሁለቱ ክፍል ሰርቪስ ቤቶችና አንድ ክፍል ሽንት ቤት ከጅምሩ የአመልካቾች አውራሽ የግል ሀብት ሣይሆኑ የተጠሪ የግል ንብረት መሆናቸውን ፍሬ ጉዳይ የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ሥልጣን ባላቸው የበታች ፍርድ ቤቶች የደረሱበትን የፍሬ ጉዳይ መደምደሚያ በፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 1179 ንዑስ አንቀጽ 1 ድንጋጌ በማጣመር ለመገንዘብ ይቻላል። ሟች ሲሞት ለሟች ወራሾች የሚተላለፈው በሟች መሞት ምክንያት የማይቋርጡ መብቶችና ግድታዎች መሆናቸው በፍትሐበሕር ሕግ ቁጥር 826 ንዑስ አንቀጽ 2 ይደነግጋል። ከዚህ አንፃር የአመልካችዎች አውራሽ ተጠሪ በራሱ ወጭ በሰራቸው ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤቶች እና አንድ ክፍል ሽንት ቤት ላይ የባለሀብትነት መብት የልለው በመሆኑ፣ አውራሻቸው የልለው መብት ለአመልካች ወራሾች ላተላለፍ የሚችልበት የሕግ መሰረት የለም። ከዚህ አንፃር ተጠሪ የሰራቸው ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤትና አንድ ክፍል ሰርቪስ ቤት የውርስ ንብረት ክፍል ሣይሆን የተጠሪ የግል ንብረት ነው በማለት የሰጡት ውሣኔ የፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 826 ንዑስ አንቀጽ 2 እና የፍትሐበሕር ሕግ ቁጥር 1179(1) ድንጋጌ መሰረት ያደረገ በመሆኑ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያልተፈፀመበት ሆኖ አግኝተነዋል። ተጠሪ ቤቶቹን የሰራኃቸው እኔ ነኝ የሚል ጥያቄ ያቀረበ በመሆኑ የበታች ፍርድ ቤቶች ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን የሕግ ድንጋጌ ማለትም የፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 1179(1) በመጥቀስ የሰጡት ውሳኔ የፍትሐብሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 182(2) ድንጋጌ የሚጥስ ነው በማለት አመልካቾች ያቀረቡት ክርክር የሕግ መሰረት የልለው በመሆኑ አልተቀበልነውም ።
ከዚህ አንፃር የበታቸ ፍርድ ቤቶች ተጠሪ በግቢው ውስጥ በ 210 ካሬ ሜትር የይዞታ ቦታ ላይ መብት አግኝቼበታለሁ የሚለው የስጦታ ውል ፈራሽነው በማለት ከወሰኑ በኃላ ተጠሪ 210 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የይዞታ መብት እንዳለው ገልፀው የሰጡት ውሳኔ የፍታብሕር ሕግ ቁጥር 1179(1) እና የፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 826(2) ድንጋጌ መሰረት ያላደረገና መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ አግኝተነዋል።
ውሣኔ
የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና የፍደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጡት ውሣኔ ተሻሽሐል።
የበታች ፍርድ ቤቶች ተጠሪ በራሱ ውጭ የሰራቸው ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤትና አንድ ክፍል ሽንት ቤት የውርስ ንብረት ክፍል ሣይሆኑ የተጠሪ የግል ንብረት ናቸው በማለት የሰጡት ውሣኔ የፍትሐብሕር ሕግ ቁጥር 1179(1) መሰረት ያደረገ በመሆኑ ፀንቷል።
ተጠሪ በቤት ቁጥር 429 ግቢ ውስጥ 210 ካሬ ሜትር ቦታ ባለ ይዞታ ሆኜበታለሁ የሚለው የስጦታ ውል ፈራሽ የሆነ በመሆኑና ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤትና አንድ ክፍል ሽንት ቤት ከገነባበትና ቤቱ ካረፈበት ውጭ ያለው 210 ካሬ ሜትር ቦታ የውርስ ንብረት ክፍል አይደለም በማለት የበታች ፍርድ ቤቶች የሰጡት የውሣኔ ክፍል ተሽሯል።
ተጠሪ ሰርቪስ ቤቱና ሽንት ቤቱ ከገነባበትና ቤቱ ካረፈበት ቦታ ውጭ ባለው ይዞታ ቦታ ላይ የይዞታ መብት የለውም ብለናል። ተጠሪ ሰርቪስ ቤትና ሽንት ቤት ከገነባበትና ቤቱ ካረፈበት ቦታ ውጭ ያለው የቤት ቁጥር 429 ይዞታና ቤቱ ላይ አመልካችና ተጠሪ እኩል የወራሽነት መብት አላቸው በማለት ወስነናል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
ይህ ውሣኔ ተጠሪ በአፈፃፀም ወቅት የመውጭያና የመግቢያ መብት ይከበርልኝ የሚለበትን ጥያቄ ከማቅረብ አያግደውም።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
የማይነበብ አምስት ዳኞች ፊርማ አለበት።
No topics extracted.