No summary available.
የሰ/መ/ ጥቅምት 14 ቀን 2007 ዓ/ም ዳኞች፡- አልማው ወል ሱልጣን አባተማም መኮንን ገ/ህይወት ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመሰል አመልካች፡- የደቡብ ክልል ዐ/ህግ ተጠሪ፡- ዓለማየሁ አስፋው መዝገቡ የተቀጠረው የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ነው። በዚህም መሰረት መዝገቡን መርምረን ተከታዩን የቅጣት ውሳኔ ሰጥተናል።
ቅ ጣ ት
እንደ ቅጣት መመሪያው መወሰን እንዲቻል ደግሞ በተጠሪ ላይ የተሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔከግራ ቀኙ ቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ምክንያቶች ጋር ተገናዝቦ ላታይ የሚገባው ነው። በዚህ አግባብ ቅጣቱ ከመሰላቱ በፊት ግን ተጠሪ ጥፋተኛ የተባሉበት ድንጋጌ ክሱ ሲመሰረትም ሆነ በበታች ፍርድ ቤቶች ክርክሩ ሲካሄድ ደረጃ ያልወጣለት ቢሆንም በዚህ ችሎት ጉዳዩ በመታየት ላይ እያለና የጥፋተኛነት ውሳኔ በተሰጠበት ጊዜ በስራ ላይ ያለው የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 በመሆኑ በዚሁ መመሪያ መሰረት የወንጀል ህጉ አንቀጽ 543 ደረጃ ድንጋጌ ነው። ተጠሪ ድርጊቱን የፈጸሙት በታወቀ ቸልተኝነት ከመሆኑም በላይ የሟች አስተዋጽኦ ስለልለና ተጠሪም በሙያቸው ሹፍር በመሆናቸው የወንጀሉ ደረጃ አራት ሆኖ የእስራት ቅጣት መነሻ እርከን 16 ነው። በዚህ እርከን የፍርድ ቤቱ የተተወው ፍቃደ ስልጣን ከሶስት አመት እስከ ሶስት አመት ከሰባት ወር ነው። መነሻ ቅጣቱም በዚሁ ሬንጅ ውስጥ የሚያዝ ሲሆን ተጠሪ ላይ መጨረሻ ላይ የሚጣለው የቅጣት መጠን የሚታወቀው ግን የማክበጃ እና የማቅለያ ምክንያቶች ታይተው ስልቱ ከተሰራ በኃላ ነው። በዚህም አግባብ የቅጣት መጠኑን ማስላት የግድ ሲሆን በተጠሪ ላይ በዓቃቤ ህግ በኩል የቀረበ የቅጣት ማክበጃው ምክንያት የለም።
አቃቤ ህግ ጥፋተኝነት ውሳኔ ሲሰጥም ሆነ የቅጣት አስተያየቱን የማቅረብ እድሉን ለመጠበቅ ቀጠሮ ሲያዝለት አልቀረበምና። በልላ በኩል ተጠሪ ሪኮርድ ያልቀረበባቸው መሆኑን የክርክሩ ሂደት ማሳየቱ ይኼው ምክንያት በማቅለያነት እንዲያዝላቸው የሚያደርግ ነው። ይህ ማቅለያ ምክንያት ደግሞ በመመሪያው አንቀጽ 23(4) ድንጋጌ መሰረት በተጠሪ ላይ የሚጣለውን ቅጣት ከእርከን 16 ወደ እርከን 15 ዝቅ የሚደረገው ነው። በዚሁ መጨረሻ እርከን ስር የተመለከተው የቅጣት ዓይነትና የእስራት መጠን ሬንጅ ከሁለት አመት ከዘጠኝ ወር እስከ ሶስት አመት ከስምንት ወር በመሆኑ በዚሁ ለፍ/ቤቱ በተሰጠው ፈቃድ ስልጣን መሰረት የአሁኑ ተጠሪ ለፈጸመው ጥፋት በሁለት አመት ከዘጠኝ ወር ቀላል እስራት ላቀጣ የሚገባ ሆኖ ስለገኘነው ተጠሪ በጉዳዩ ላይ የታሰረው ካለ ማናቸውም ጊዜ የሚታሰብለት ሁኖ በሁለት አመት ከዘጠኝ ወር ቀላል እስራት ላቀጣ ይገባል ብለናል።
የገንዘብ መቀጮን በተመለከተ ደግሞ ተጠሪ ላቀጡ የሚገባው ብር በእርከን 4 ሁኖ ስለአገኘነው በብር 3500.00 (ሶስት ሺህ አምስት መቶ ብር) ነው ብለናል።
በአመልካች የሰበር አቤቱታ ላይ የተጠሪ መኖሪያ አድራሻ አዲስ አበባ መሆኑ ስለተጠቀሰ የፍድራል ፖላስ ከደቡብ ክልል ፖላስ ጋር በመሆን ተጠሪን አፈላልጎ በመያዝ ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ፣የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤትም ተጠሪን ተረክቦ በዚህ ችሎት ውሳኔ መሰረት ቅጣቱን ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ብለናል። ይጻፍ።
No topics extracted.