ከዳኝነት ስራ ጋር ያልተያያዙ እና የአስተዳደር ስራ ሲያከናውኑ የሚፈፀሙ የወንጀል ጥፋቶች ዳኛውን ከተጠያቂነት የማያስቀሩ ስለመሆኑ፣ የወ/ህ/ቁ. 402(1) እና (2) በትግራይ ክልል ዳኞች እና ሬጂስትራሮችን ለማስተዳደር ተሻሽሎ የወጣው ደንብ ቁጥር 1/2003
No summary available.
መስከረም 26 ቀን 2007 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል መኮንን ገ/ህይወት ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ ተኸላት ይመስል አመልካች፡- አቶ ሐጐስ ገ/ሄር መኮንን ተጠሪ፡- የትግራይ ክልል የስነ/ፀ/ሙ/ኮ - ዐ/ሕግ መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ወስነናል።
የአሁኑ አመልካች በወንጀል ህጉ አንቀጽ 407(2) የተመለከተውን በመተላለፍ የማይገባውን ብልፅግና ለራሱ ወይም ለልላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ በትግራይ ክልል በደቡብ ዞን አሰላ ወረዳ ፍ/ቤት ዳኛ ሆኖ ሲሰራ ሥልጣኑን አላግባብ በመጠቀም የመንግስት የአበል አከፋፈል ሥርዓት በመጣስ ለራሱና ለሥራ ባልደረቦች ላከፈል የማይገባውን ብር 7653.4 እንዲከፈል በማድረጉ በፈፀመው በሥልጣን ያለአግባብ መጠቀም ወንጀል ተከሷል ሲል የአሁን ተጠሪ ክስ አቅርቦበታል።
ጉዳዩን በቅድሚያ የተመለከተው የአላማጣ ማዕከላዊ ፍ/ቤት የግራ ቀኙን ክርክር እና ማስረጃ ከሰማ በኋላ አመልካች በተዘዋዋሪ ችሎት ስም ከሥራ ቦታዬ ወደ ቀበልዎች ሄጃለው በማለት በተሞክሮ ልውውጥ ስም፤ በመሀበራዊ ፍ/ቤትና የመሬት ዳኞች ሥልጠና ስም አበል አላግባብ መውሰዱ ፤ዳኞች ስልጠና ሰጥተዋል በማለት በፔሮል ወደ ቀበል እንደወጡ አሰመስሎ አበል መክፈሉ ፤ የሂሳብ መደብ በማይፈቅድበት ሁኔታ በራሱ ስም አበል ወጪ በማድረግ የፅሕፈት መሣሪያ መግዛት እና ከፋይናንስ ደንብ እና መመሪያ ውጭ ስለመስራቱ በራሱ በዝርዝር የተመለከተውን እና የቀረበበትን የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ እንደ ክሱ አቀራረብ ጥፋተኛ ነው በማለት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶችን ተቀብሎ በ1(አንድ) ዓመት ፅኑ እስራት እና በብር 2000 /ሁለት ሺህ /መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።
ጉዳዩ በይግባኝ የቀረበለት የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤትም ሆነ የሰበር አቤቱታ የቀረበለት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔው የሚነቀፍበት ምክንያት የለም በማለት ቅሬታውን ውድቅ አድርገዋል።
የሰበር አቤቱታው ለዚህ ፍ/ቤት የቀረበው ይህን ውሳኔ በመቃወም ነው። አመልካቹ የካቲት 24 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በተፃፈ 5 (አምስት) ገጽ ዝርዝር ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን ተጠቃሎ ሲታይ የፍርድ ቤቱ ሥራ እንዳይጐዳ ብሎ የፈፀምኩት መሆኑ እየታወቀ፤በአግባቡም ሣይጣራ ተድበስብሶ የታለፈ በመሆኑ፤የቀረቡት ማስረጃዎች ከሚመለከታቸው ህጐች ሳይገናዘብ የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑና ፤ የፍድራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በሰበር መዝገብ ባሳለፈው ውሳኔ የዳኝነት ሥራ በሚያከውኑበት ጊዜ የሚፈፅሙ ጥፋቶች እና ስህተቶች ዳኞች በስልጣን ያለ አግባብ መጠቀም በሚል ወንጀል ላከሰሱ አይገባም በማለት የሰጠው ውሳኔ ተሻሽሎ ተተርጉሞ የሥር ፍ/ቤቶች ውሣኔ ተሽሮ በነፃ ልሰናበት ብለዋል።
ቅሬታቸው ተመርምሮ ፈፀሙት የተባለው ድርጊት ጥፋተኛ በተባሉበት የህግ አንቀጽ ሥር የሚወድቅ መሆኑን ወይም ጉዳዩ ከዳኝነት ሥነ ምግባርና ዲሲፕላን አኳያ የሚታይ መሆኑን ለማጣራት ተብሎ ተጠሪ መልስ እንዲሰጡበት ተደርጓል።
ተጠሪ ሚያዚያ 9/2ዐዐ6 ዓ.ም በተፃፈ መልስ በወ/ህ/ቁ.407(2) መከሰሱ እና ጥፋተኛ መባሉ የህግ ስህተት የልለበት በመሆኑ፤አስቀድሞ በ
የተሰጠው ውሳኔም የዳኝነት ሥራ በመከናወን ላይ እያለ የሚፈፀሙ ጥፋትና ሥህተትን እንጅ መሰል ተግባርን የሚመለከት ባለመሆኑ የሥር ፍ/ቤቶች ያሳለፉት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት አልተፈፀመበትም ተብሎ እንዲፀና ጠይቀዋል። አመልካቹም ግንቦት 2/2006 ዓ.ም የተፃፈ ክርክራቸውን የሚያጠናክር የመ/መልስ አቅርበዋል።
ከላይ ባጭሩ ለመግለፅ የሞከርነው የጉዳዩን አመጣጥ ሲሆን የሰበር አቤቱታው ያስቀርባል የተባለበትን ጭብጥ ይዘን መዝገቡን መርምረናል።
እንደመረመርነው ፍሬ ነገሩን የማጣራት እና ማስረጃ ለመመዘን ሥልጣኑ የተሰጠው የሥር ፍ/ቤት አመልካቹ መንግስት የፋይናንስ ህጐች እና ደንቦች ከተፈቀደው ውጭ በአጠቃላይ ብር 7,650.40 እንዲወጣ በማድረግ ለራሱም ሆነ ለሥራ ባልደረቦቹ መጠቀሚያ በማድረግ በኃላፊነቱ አላግባብ መገልገሉን አረጋግጧል።
ይኸው በማስረጃ ተረጋግጧል የተባለው አድራጐት በመንግስት ሥራ ላይ የተፈፀመ ከዳኝነት ሥራ ጋር ተቀላቅሎ ላታይ የማይገባ የወንጀል ጥፋት ነው።
አመልካቹ በዳኝነት ተሹመው በቋሚት የዳኝነት የመንግሰት ሥራን የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኛ በመሆናቸው እና ይሰሩበት የነበረው የወረዳ ፍ/ቤትም በመንግስት በጀት ተመድቦለት የዳኝነት መንግስታዊ ሥራ የሚከናወንበት መስሪያ ቤት በመሆኑ በመንግስት ሥራ ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን የሚመለከቱ የወንጀል ህጉ ድንጋጌዎች በመሰል ጥፋቶች ላይም በተመሳሳይ ተፈፃሚነት የሚሆኑ ናቸው። /የወ/ህ/ቁ. 402(1) እና (2) ይመለከታል።
ልላው መከራከሪያ እና የሰበር አቤቱታው ያስቀርባል ለመባሉ ምክንያት የሆነው ጉዳዩን ከዳኝነት ሥነ ምግባር እና ዲሲፕላን አኳያ የሚታይ መሆኑን የተመለከተ ነው ።
በትግራይ ክልል ዳኞች እና ሬጅስትራሮችን ለማስተዳደር ተሻሽሎ የወጣው ደንብ ቁጥር 1/2003 በመንግስት ገንዘብ ወይም ንብረት በዳኞች የሚፈፀምን ያላግባብ መጠቀም እና መውሰድ የዲስፒላን ጥፋት አድርጐ ይዟል። ነገር ግን የዲስፒላን ደንቡ መሰል ድንጋጌ መያዙ በወንጀል ገረድ የሚኖረን ኃላፊነት የሚያስቀር አይደለም።
የዲስፕላን ጉዳዩች የሚቋቋሙበት፣ የሚመሩበት ሥርዓት እና ከሚሰጠው ውሳኔ የወንጀል ጥፋቶች ከሚቋቋሙበት፣ከሚመሩበት ሥርዓት እና ከሚሰጠው ውሣኔ ተለይቶ ላታይ ይገባል።
ስለሆነም የተፈፀመው ጥፋት የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆን አለመሆኑ ከዲስፒላን ጉዳዩ ጋር ላያታይ አይገባም።
የፍድራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ ዳኛ ብርቁ ባላዬ እና የአማራ ክልል ስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በተከራከሩበት ጉዳይ ጥር 13/2001 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ የዳኝነት ሥራን በሚያከናውኑበት ወቅት የሚፈፅሙ ስህተቶች እና ጥፋቶች ሁሉ ዳኛን በሥልጣን አላግባብ መገልገል ወንጀል ላያስጠይቁ የማይችሉ ስለመሆናቸው መወሰኑ የዳኞችን ህገ መንግስታዊ የውሳኔ ነፃነት ለማጠናከር እንጅ በእጃችን እንዳለው ጉዳይ ከዳኝነት ሥራ ጋር ያልተያያዙ እና የአስተዳደር ስራ ሲያከናውኑ የሚፈፀሙ የወንጀል ጥፋቶች ሁሉ ተጠያቂነትን የሚያስቀር ትርጉም የሚሰጠው ባለመሆኑ አመልካቾች ይኸው ውሳኔ በማመሳሰል ለተያዘው ጉዳይ ተፈፃሚ እንዲሆን ያቀረቡት ጥያቄ በህጉ ተቀባይነት የለውም ብለናል።
በአጠቃላይ አመልካቾች በነበራቸው የሥራ ኃላፊነት ምክንያት ላጠብቅ እና ላከላከሉት የሚገባን የህዝብ እና የመንግስት ንብረት ከህግ ውጭ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ለፈፀሙት ጥፋት በስር ፍ/ቤቶች የተላለፈባቸው ውሣኔ የህግ ሥህተት የተፈፀመበት አይደለም ብለናል ተከታዩንም ወስነናል።
የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በሰጠው መ/ቁ. 6111/06 ታህሳስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም ያሳለፈው ትዕዛዝ ፤የጠቅላይ ፍ/ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ.58434 ግንቦት 13 ቀን 2005 ዓ.ም ያሳለፈው ትዕዛዝ እና በደቡባዊ ዞን ማዕከላዊ ፍ/ቤት የአላማጣ ምድብ ችሎት በወ/መ/ቁ.02867/05 የካቲት 26/2005 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.195(2)(ለ)(2) መሰረት ፀንቷል።
No topics extracted.