ከስራ በቅነሳ ምክንያት ለሚሰናበት ሰራተኛ የስራ ስንብት ክፍያ የሚከፈል ስለመሆኑ፡አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 39(1)(ሐ)፣40(1)(3)፣28(2)(ሀ)(3)
No summary available.
ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመሰል አመልካቾች፡-
ጉዳዩ የቀረበው አመልካቾች መዝገብ ሐምል 3 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልን በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የሥራ ስንብት የሁለት ወር ደመወዝ ይከፈለን በማለት የቀረበ ጥያቄ የሚመለከት ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው። በሥር ፍርድ ቤት አመልካቾች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
ስለዚህ ተከሳሾች የስራ ስንብት ክፍያ የምንከፍልበት ምክንያት የለም በማለት ተከራክሯል።
የሥር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኃላ ተከሳሽ ኪሣራ አልደረሰበትም። ኪሳራ የደረሰበት ራሱን የቻለ የህግ ሰውነት ያለው የቡና ላኪ ድርጅት ላይ ነው። ከሳሾች የሚያሽከረክሯቸው መኪኖች የተሸጡትም የቡና ላኪ ድርጅት ዕዳ መክፈያነት ነው። ተከሳሽ የሥራ ውሉን ከሳሾች የሚያሽከረክሯቸው መኪኖች በቡና ላኪ ድርጅት ላይ በደረሰው ኪሣራ ምክንያት በዕዳ መክፈያነት በመሸጣቸው የሥራ ውሉን ያቋረጠ በመሆኑ፣የሥራ ውሉ የተቋረጠው በቅነሳ እንጂ የሥራ መደብ በመሰረዙ ምክንያት አይደለም። ይህም በመሆኑ ከሳሽ በተከሳሾች የሁለት ወር ደመወዝና አገልግሎት ጊዜአቸውን አስልቶ የሥራ ስንብት ክፍያ የመክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት ውሣኔ ሰጥቷል።
አመልካች በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ መልስ ሰጭዎች ያሽከረከሯቸውየነበሩት መኪናዎች መሸጣቸው ተረጋግጧል። መልስሰጭዎች ያሽከረክሯቸው የነበሩ መኪናዎች መሸጣቸው ከተረጋገጠ ይግባኝ ባይ ልላ መኪና ገዝቶ እስኪተካ ድረስ የሹፍርነት የሥራ መደብ ተሰርዟል ለማለት ይቻላል። ይግባኝ ባይ መልስ ሰጭዎችን የሥራ መደብ በመሰረዙ ምክንያት ከሥራ ያሰናብታቸው በመሆኑ የሥራ ስንብት ክፍያ ላከፍል አይገባም በማለት የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ ሽሮታል።
አመልካቾች መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ ካሉት ከመቶ በላይ ከሚሆኑ ሹፍሮች ዝቅተኛ አገልግሎትና የሥራ ልምድ በመምረጥ ቀንሶ ከሥራ አሰናብቶናል። ከዚህ አንፃር የተጠሪ አድራጎት ቅነሳ እንጂ የሥራ መደብ መሰረዝ ነው ላባል አይገባውም። ከዚህ በተጨማሪ አሰሪው ሰራተኛውን ከሥራ ሲያሰናብት የአገልግሎት ክፍያ የመክፈል ሃላፊነት አለበት። በመሆኑም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የስራ ስንብት ክፍያ አይገባችሁም በማለት የሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር እንዲታይልን በማለት አመልክተዋል። ተጠሪ ጥር 28 ቀን 2007 ዓ.ም በተፃፈ መልስ አመልካቾች የተሰናበቱት የሥራ መደቡ የተሰረዘ በመሆኑ ምክንያት ነው። ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ይህንን በማገናዘብ የሥራ ስንብት ክፍያ ተጠሪ የመክፈል ኃላፊነት የለበትም በማለት የሰጠው ውሣኔ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክሯል። አመልካችዎች የካቲት 14 ቀን 2007 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርበዋል።
ከሥር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ግራ ቀኙ ያቀረቡት ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ተጠሪ ለአመልካቾች የሥራ ስንብት ክፍያ ላከፍል አይገባም በማለት የሰጠው ውሣኔ የሕግ መሰረት አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
አሰሪው ማስጠንቀቂያ በመስጠት የሥራ ውል ለማቋረጥ የሚችልባቸውን መሰረታዊ ምክንያቶች አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 28 በሁለት ከፍሎ አስቀምጧቸዋል።
የመጀመሪያው ከሰራተኛው ችሎታ ማጣት ወይም ሁኔታ የሚመለከቱ ምክንያቶችም ሲሆኑ በአዋጅ አንቀፅ 28 ንዑስ አንቀጽ 1 ከ’’ሀ’’ እስከ ‘’መ’’ በዝርዝር ደንግጓል። ሁለተኛው ከአሰሪው ድርጅታዊ አቋም ወይም የሥራ እንቅስቃሴ የሚመለከቱ ምክንያቶች የሥራ ውል ሲቋረጥ መሆኑ በአዋጅ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 2 ተመልክቷል። ተጠሪ አመልካቾች የሚያሽከረክሯቸው መኪኖች በዕዳ ምክንያት በመሸጣቸው የአመልካችዎች የሥራ መደብ በአዋጅ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 1 (መ) መሰረት ተሰርዟል በማለት የሚያቀርበው ክርክር ተጠሪ ከፈፀመው ተግባር አግባብነት ያለው ሆኖ አላገኘነውም።
አመልካችዎች የሚያሽከረክሯቸው መኪኖች የተሸጡት በተጠሪ ድርጅታዊ አቋምና የሥራ እንቅስቃሴ ምክንያት በመሆኑና በተለይም ቡና የሚልከው የንግድ ድርጅት ኪሣራ ስለደረሰበት መኪኖቹ ተሸጠው ዕዳ መክፈያነት የዋሉ መሆኑ በሥር ፍርድ ቤት ተረጋግጧል። አንድ ድርጅት ሰራተኞች የተሰማሩባቸው ሥራዎች በከፊልም ሆነ በሙሉ በቀጥታና በልላ ቦታው የሚያስቆምና የሰራተኞች ቅነሳ የሚያስከትል ሁኔታ ሲያጋጥመው ማስጠንቀቂያ በመስጠት የሥራ ውሉን ላያቋርጥ እንደሚችል በአዋጅ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 2(ሀ) ተደንግጓል። የተጠሪም አድራጎት በዚህ ድንጋጌ ሥር የሚሸፈን ሆኖ አግኝተነዋል።
ሰለ ሥራ ስንብት ክፍያ የሚደነግገው የአዋጅ ቁጥር 377/96 ምዕራፍ ሶስት በክፍል ሁለት የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ ሰራተኛ በዚህ አዋጅ በተመለከቱት ሁኔታዎች መሰረት ከሥራ ሲቀነስ የሥራ ስንብት ክፍያ የማግኘት መብት ያለው መሆኑ በአንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1(ሐ) በግልፅ ይደነግጋል። ከዚህ አንፃር ሲታይ በተጠሪ ድርጅታዊ አቋምና የሥራ እንቅስቃሴ ምክንያት ከሥራ የተቀነሱት አመልካቾች በአዋጁ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 1 እና ንዑስ አንቀጽ 3 የተመለከቱትን የሥራ ስንብት ክፍያዎች የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑ ከድንጋጌዎቹ ይዘት መንፈስና ዓላማ የምንረዳው ጉዳይ ሆኖ እያለ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አመልካችዎች የሚያሽከረክሯቸው መኪናዎች በዕዳ ምክንያት መሸጥ ከተጠሪ ድርጅታዊ አቋምና የሥራ እንቅስቃሴ ነጥሎ በማየት ተጠሪ ለአመልካችዎች የሥራ ስንብት ክፍያ የመክፈል ግድታ የለበትም በማለት የሰጠው ውሣኔ የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 2(ሀ) ና ንዑስ አንቀጽ 3 አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 (ሐ) እና የአዋጁን አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 1 እና ንዑስ አንቀጽ 3 ያላገናዘበና መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ወስነናል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሣኔ ተሽሯል።
ተጠሪ ለአመልካችዎች የሥራ ስንብት ክፍያ የመክፈል ኃላፊነት አለበት በማለት ወስነናል።
ተጠሪ ለአመልካችዎች በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 1 ንዑስ አንቀጽ 2 እና ንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት በማስላት የሥራ ስንብት ክፍያ ይክፈላቸው በማለት ወስነናል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሣራ ግራቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።