No summary available.
የሰ/መ/ ታህሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሡልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመሰል አመልካቾች፡- 1.አቶ ብርሃኑ ቢኔ 2. አቶ ሞላ ደሴ 3. አቶ ተስፋዬ ሐበና 4. ወ/ሮ ጀማነሽ መንገሻ 5. አቶ ጉልትነህ ታደሰ 6. አቶ ወርቁ አይድ 7. አቶ መኮንን ሙሉ 8. ወ/ሮ ክብነሽ ዋጤሮ 9. ወ/ሮ ታየች አሰፋ 10. አቶ አጫ አይሳሮ 11. ወ/ሮ ፀዳለ ቸችሮ 12. አቶ ሐይል አረጋዊ 13. አቶ ጠብቀው ሳንፎ 14. ወ/ሮ ለተብርሃን መኮንን 15. አቶ ዘሪሁን ደግፍ 16. አቶ በርሕ አሰፋ 17. ወ/ሮ አቦነሽ ሳካሎ 18. አቶ ዋህድ ካሳዬ 19. አቶ ግዛቸው ካሳ 20. አቶ አበራ ሐይል 21.አቶ ደምመላሽ ካሳዬ ደመነ ቱኔ 22. ወ/ሮ መስከረም ካንኮ የ34ቱም 23. አቶ ሙሉጌታ መቺሶ ጠበቃ 24. አቶ ሱልጣን ሐሰን 25. አቶ ጌታሁን ሐይል 26. ወ/ሮ ዓለሚቱ ገብሬ 27. ወ/ሮ ባዩሽ በቀለ 28. አቶ ደሳለኝ ትንታግ 29. አቶ እንግዳ እሸቱ 30. ወ/ሮ ጀማነሽ መንገሻ 31. ወ/ሮ አየለች ባልቻ 32. አቶ መንበረ ጌታቸው 33. አቶ መተኪያ ፀጋዬ 34. አቶ አብዮት ጌታሁን ተጠሪ፡- የአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካአ/ማ- ነ/ፈጅ ሹፋያን ሱልጣን ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካቾች የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ግንቦት 25 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልን በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ የስራ ውል መቋረጥን የሚመለከት ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በደቡብ ክልል የሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ነው። በክልሉ የሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ አመልካቾች ከሳሽ ተጠሪ ተከሳሽ በመሆን ተከራክረዋል።
አመልካቾች በተጠሪ ድርጅት ከሃያ ዓመት በላይ በታማኝነት ያገለገሉ መሆኑን ገልፀው ተከሳሽ (ተጠሪ) አዲስ መዋቅር አስጠንቻለሁ በማለት የስራ መደባችሁ ታጥፏል በሚል ሰበብ በሕግ አግባብ የሰራተኛ ድልድልና ምደባ ሳያደርግ ቅነሳ በሚል ሀሰተኛ ምክንያት መጋቢት 10 ቀን 2005 ዓ/ም እና ሚያዝያ 10 ቀን 2005 ዓ/ም በተፃፈ ደብዳቤ የስራ ውላችንን ከሕግ ውጭ ያቋረጠ በመሆኑ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ ይወሰንልን በማለት አመልክተዋል። ተጠሪ በተከሳሽነት ቀርቦ ጉዳዩ በመደበኛ ፍርድ ቤት የሚታይ ነው በማለት የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያ ያቀረበ ሲሆን፣ በአማራጭ ሰራተኞቹ የተቀነሱት የድርጅቱ መዋቅር በገለልተኛ ባለሙያ ከተጠና በኋላ ከሳሾች መዋቅሩ የሚጠይቀውን መስፈርት ባለማሟላታቸው ያልተደለደሉ በመሆኑና ድልድሉ የሰራተኞች ተወካይ ባለበት በግልጽ መስፈርት ሰራተኞች ተወዳድረው የተመደቡ በመሆኑ ስንብቱ ሕጋዊ ነው በማለት ተከራክሯል።
የክልሉ ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከሰማ በኋላ ተጠሪ አመልካችዎችን ከስራ ያሰናበተበት አግባብ የአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 29 የተደነገጉትን መስፈርቶች የማያሟላና ከሕግ ውጭ በመሆኑ ተጠሪ በሕጉ መሰረት ሁሉንም ሰራተኞች ባሳተፈ መልኩ እንደገና የሰራተኛ ድልደላ ይፈፅም። ተጠሪ እንደገና ለመደልደል ካልፈለገ ስንብቱ ሕግን ያልተከተለ በመሆኑ ከሳሾችን/ አመልካቾችን/ ወደ ስራ ይመልስ።
ተጠሪ ከሳሾችን ወደ ስራ ካልመለሰ በሕግ አግባብ ካሳ በመክፈል እንዲያሰናብታቸው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል። ተጠሪ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል። የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ይግባኝ ባይ (ተጠሪ) ሰራተኞችን የደለደለው በትምህርት ደረጃ፣ በስራ ልምድ፣ በማህደር ጥራትና የስራ አፈፃፀም ውጤት በመሆኑ ስንብቱ በህግ አግባብ የተፈፀመ ነው በማለት የክልሉ ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል።
አመልካቾች ሰኔ 27 ቀን 2006 ዓ/ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተጠሪ ያስጠናው መዋቅር ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 20 የስራ መደብ ያለው ቢሆንም ሰራተኛ ድልድል የፈፀመው ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 12 ባለው የሥራ መደብ ላይ ብቻ መሆኑ ተረጋግጧል። ተጠሪ ካሉት 674 ሰራተኞች አስር ፐርሰንት የሚሆኑ አልቀነሰም። መዋቅሩ ሰራተኞች ቁጥር እንዲጨምር የሚያደርግ ነው። ተጠሪ እኛን በሕግ አግባብ በማወዳደር ሰራተኞችን ያልደለደለ መሆኑን በማረጋገጥ ቦርዱ የሰጠውን ውሳኔ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አላግባብ መሻሩ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት አመልክተዋል። ተጠሪ ጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ/ም በተፃፈ መልስ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 12 ባለው የስራ መደብ ሰራተኞች በአግባቡ ተወዳድረው ተመድበዋል። ከደረጃ 13 እስከ ደረጃ 20 ያለው የስራ መደብ የስራ መሪዎችን የሚመለከት ነው። ከስራ የተሰናበቱት ሰራተኞች 10% በታች መሆኑ ስንብቱን ህገ ወጥ አያደርገውም የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ የሕግ ስህተት የልለበት በመሆኑ እንዲፀናልኝ በማለት ተከራክረዋል። አመልካቾች ጥቅምት 14 ቀን 2007 ዓ/ም በተፃፈ የመልስ መልስ ተጠሪ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 12 ሰራተኞች ተወዳድረው ተመድበዋል ያለው ሀሰት ነው። ምክንያቱም በድርጅቱ ንብረትና ፋይናንስ ዘርፍ የሥራ መደቦች ላይ የተሰማሩ ሰራተኞች በድልድል አልተካተቱም። ተጠሪ ከደረጃ 13 እስከ ደረጃ 20 ያሉት የስራ መደቦች የስራ መሪ የስራ መደብ ነው በማለት ያቀረበው ክርክር እውነትነት የልለው ነው። ስለዚህ ስንብቱ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ እንዲወስንልን በማለት ተከራክረዋል።
ከስር የክርክሩ አመጣጥና በሰበር ግራ ቀኙ ያቀረቡት የፅሁፍ ክርክር ከላይ የተገለፀው ሲሆን እኛም የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ የአመልካቾችን የስራ ውል ያቋረጠው በሕግ አግባብ ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ ሕጋዊ መሰረት አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን መርምረናል።
ጉዳዩን እንደመረመርነው ከላይ የተገለፀውን ጭብጥ ለመወሰን፣ በመጀመሪያ ፍሬ ጉዳይ የማጥራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን በሕግ የተሰጠው የሰራተኞች ጉዳዮች ወሳኝ ቦርድ የግራ ቀኙን የሰውና የፅሁፍ ማስረጃ ሰምቶ፣ መርምሮና መዝኖ የደረሰባቸውን የፍሬ ጉዳይ መደምደሚያዎች ከሕጉ ድንጋጌ ጋር ማገናዘብ አስፈላጊ ነው። የክልሉ ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ተጠሪ ምርታማነትን ለማሳደግና አሰራር ለመለወጥ አዲስ መዋቅር ያስጠና መሆኑና በአዲሱ መዋቅር መነሻ በማድረግ አመልካቾችን ከስራ የቀነሰ መሆኑን አረጋግጧል። ሆኖም ተጠሪ ካሉት 674 ሰራተኞች ቅነሳ በሚል ምክንያት ከስራ ያሰናበተው ከአስር ፐርሰንት የማይሆኑ ሰራተኞችን እንደሆነ አረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪ የስራ ምደባው ከተወዳደሩ በኋላ በውድድሩ ያላለፉ ሰራተኞችን ተጠሪ ከደረጃቸው ዝቅ አድርጎ የመደበና ያላሰናበተ መሆኑን በማስረጃ መረጋገጡንና የሥራ ድልድሉ ሁሉንም ሰራተኞች የማይመለከት በተለይ ንብረትና ፋይናንስ ክፍል የሚሰሩ ሰራተኞችን የማይመለከት መሆኑን በማስረጃ እንደተረጋገጠ ቦርዱ በግልጽ በውሳኔው ውስጥ አስፍሯል። ከዚህ በተጨማሪ ከደረጃ 13 እስከ ደረጃ 20 ያሉ የስራ መደቦች ሰራተኞች በውድድር ያልተመደቡባቸው መሆኑን፣ በማስረጃ እንደተረጋገጠ በውሳኔው አስፍሯል። ይህም የሰራተኛ ቅነሳ ነው በማለት ተጠሪ ያከነወነው ተግባር የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት አያሟላም በማለት የሰራተኛ ውሳኝ ቦርዱ መደምደሚያ ላይ ደርሷል።
ከላይ የሰራተኛ ወሳኝ ቦርዱ በማስረጃ ያረጋገጣቸው ጉዳዬች አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች አንጻር መርምረናል። በመጀመሪያ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 2(ሐ) አሰሪው የድርጅቱን አቋም ወይም የስራ እንቅስቃሴ ምክንያት በማድረግ በተለይም የድርጅቱን ምርታማነት የማሳደግ አሰራር ዘድዎች ለመለወጥ ወይም አዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ሲባል ሰራተኞችን የመቀነስ ውሳኔ ላያስተላልፍ እንደሚችልና ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ሰራተኞችን ላያሰናብት እንደሚችል ይደነግጋል። በዚህ መስረት የስራ መደብ መሰረዝ ሰራተኞችን የሚነካ ሲሆንና በአዋጁ አንቀጽ 29(1) መሰረት የሰራተኛ ቅነሳ የሚያስከትል ሲሆን የስራ ውሉ የሚቋረጠው በአዋጅ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 3 ሁኔታዎች በማሟላት መሆን እንዳለበት በአዋጁ አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 3 ተደንግጓል።
ከዚህ አንፃር ሲታይ አመልካች ባስጠናው አዲስ መዋቅር ምክንያት ካሉት ሰራተኞች አስር ፐርሰንት የሚሆኑትን የስራ ውል ያላቋረጠና ይህም በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 29(1) የተቀመጠውን መስፈርት የማያሟላ መሆኑ ተረጋግጧል። አመልካች ካሉት ሰራተኞች አምስት ፐርሰንት የማይሆኑትን የስራ ውል ለማቋረጥ በአዋጅ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 3 የተደነገገውን አስገዳጅ መስፈርት የመከተል ግድታ አለበት። ሆኖም አመልካች በመጀመሪያ ደረጃ ከአመልካቾች ያነሰና ዝቅተኛ የሥራ አፈጻጸም ያላቸውን ሰራተኞች በተጠሪ ኃላፊዎች ትዕዛዝ በስራ እንዲቀጥሉ አድርጎ አመልካቾችን ያሰናበተ መሆኑ የሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ የግራ ቀኙን ምስክሮች የሰራተኛ ደልዳይ ኮሜቴ አባላት የምስክርነት ቃል በመስማትና በመመዘን አረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪ የስራ ድልድልና ቅነሳው ተጠሪ ያሉትን ሁሉንም የስራ መደቦች የማያካትትና ሁሉንም የስራ ክፍሎች የማይመለከት መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል።በአጠቃላይ ተጠሪ የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 29/3/ የተደነገጉትን መስፈርቶች በመጠቀም የአመልካቾችን የስራ ውል ያላቋረጠ መሆኑ ፍሬ ጉዳይ የማጣራት እና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ባለው የሰራተኛ ጉዳይ ቦርድ ተረጋግጧል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ያረጋገጣቸውን ፍሬ ጉዳዮች እና የደረሰበትን የፍሬ ጉዳይ እና የማስረጃ መደምደሚያ በመቀበል፤ሕጉን መሰረት ያደረገ መሆኑን ከመመዘን ያለፈ፣ የፍሬ ጉዳይና የማስረጃ ምዘና ስህተት በይግባኝ የማየትን የማረም ሥልጣን ከአዋጅ አንቀጽ 140 ንዑስ አንቀጽ 1 አልተሰጠውም። ከዚህ አንፃር ሲታይ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ተጠሪ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 12 ሰራተኞች ለመደልደል በተጠቀማቸው አራት መስፈርት ከአመልካቾች ጋር ተወዳድረው ዝቅተኛ ነጥብ ያመጡ ሰዎች በስራ እንዲቀጥሉ ያደረገና የተሻለ ውጤት ያመጡትን አመልካቾች ያሰናበተ መሆኑን በማስረጃ እንዳረጋገጠ የገለጸውን የፍሬ ጉዳይ መደምደሚያ የሚያስከትለውን ሕጋዊ ውጤት ሳይመረምርና ሳይመዝን በማለፍ ተጠሪ ሰራተኞችን የደለደለው አራት መስፈርቶች ተጠቅሞ ነው በማለት ስንብቱ ህጋዊነው በማለት መወሰኑ በመዝገቡ የሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ በማስረጃ ያረጋገጣቸውን ፍሬ ጉዳዮች በማለፍ የተሰጠና የአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 2(ሐ) እና ንዑስ አንቀጽ 3 እንዲሁም የአዋጁን አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 3 እና አንቀጽ 40(1) ድንጋጌዎችን የሚጥስና መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነው በማለት ወስነናል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ተሽሯል።
የደቡብ ብሕር ብሕረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሰራተኞች ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ በመዝገብ ቁጥር 0002/05 መሰከረም 24 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ ፀንቷል።
በዚህ ፍርድ ቤት ያወጡትን ወጭና ኪሳራ ግራ ቀኙ ለየራሳቸው ይቻሉ።
መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.