No summary available.
ህዳር 24 ቀን 2007 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመስል አመልካቾች፡-
**
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
የሰበር አቤቱታው የቀረበው የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍ/ብ/ይ/መ/ ታህሳስ 7 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ.96927 ግንቦት 05 ቀን 2006 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተሽሮ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በማለት አመልካቾች የሰበር አቤቱታ ስላቀረቡ ነው። ጉዳዩ የጡረታ ደመወዝ ማስተካከያ አስተዳደራዊ ውሳኔ ተግባራዊ ይሁንልን ጥያቄ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው። በዚህ ፍርድ ቤት የአሁኑ አመልካቾች ከሳሾች ተጠሪ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ተከሳሾች ነበሩ።
የአመልካቾች የክስ ይዘትም፡- መንግስት ለመንግስት ሰራተኞች እና ጡረተኞች ህዳር 23 ቀን 2003 ዓ/ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ የደመወዝ ማስተካከያ ማድረጉን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርተዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅድስ ሲኖዶስም በስሩ ላሉት ሰራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ እንዲደረግ ወስኖ ባለበት ሁኔታ የአሁኑ ተጠሪ እምቢተኛ መሆኑን ዘርዝረው የጡረታ ደመወዝ ማስተካከያ እንዲከፈል ይወሰንልን የሚል ነው። የስር ተከሳሾች ጉዳዩ በፍርድ ላታይ የማይችልበትን ምክንያትና አመልካቾች ክሱን ለማቅረብ መብትና ጥቅም የልላቸው መሆኑን የሚያሳዩ ነጥቦችን በመጥቀስ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት የተከራከሩ ሲሆን በፍሬ ነገር ደረጃም ለአመልካቾች የጡረታ ደመወዝ እንዲስተካከል የሚደረግበት የህግ ወይም የህብረት ስምምነት የልለ መሆኑን ዘርዝረው ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ተከራክረዋል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኃላ ጉዳዩን መርምሮ የአመልካቾች ጥያቄ ተቀባይነት የለውም ሲል ወስኗል። በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካቾች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ከሰማ በኃላ ጉዳዩን መርምሮ የአመልካቾች ጥያቄ በፍርድ ቤት ላታይ እንደሚችል፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ/ም ባደረገው ስብሰባ ማስተካከያውን ለሰራተኞችና ለጡረተኞች በወሰነው መሰረት የአሁኑ ተጠሪም ለአሁኑ አመልካቾች ማስተካከያው ላከፍል ይገባል በማለት ደምድሞና ላጨመር የሚገባውን ማስተካከያ በመቶኛ ገልጾና ይኼው ማስተካከያ የሚመለከተውን የጡረታ ደመወዝ መጠን ለይቶ ለአመልካቾች ተጠሪ የጡረታ ማስተካከያውን ላከፍል ይገደዳል በማለት ወስኗል። በዚህ ውሳኔ የአሁኑ ተጠሪ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቦ ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኃላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ተጠሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስር የሚተዳደር ነገር ግን በራሱ ገቢ ራሱን የሚያስተዳድር ስለመሆኑ ግራ ቀኙን ያላከራከረ ጉዳይ መሆኑን፣ ለአመልካቾች ክስም ሆነ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሰራተኞቹና ጡረተኞቹ የደሞዝ ማስተካከያ አስመልክቶ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ.ም ያስተላለፈው ውሳኔ መሆኑን በዚህ ውሳኔ ጥናት ተደርጐ የቀረበውን ጉባኤው ያፀደቀላቸው ሲሆን ልሎቹ ማለትም በትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤትና ጐፋ ጥበበ እድ ካህናት ማሰልጠኛ ለሚገኙት ሰራተኞችና ጡረተኞች እንደየገቢያቸው መጠን እየወሰኑ ለአስተዳደሩ አቅርበው እያስፀደቁ ተግባራዊ እንዲሆን ሲል ቋሚ ሲኖዶሱ መወሰኑን የስብሰባ ቃለ ጉባኤ ይዘት በግድታ የማያመላክት መሆኑን ከዚህ መረዳት የሚቻለው የጉባኤው ውሳኔ የአሁኑን ተጠሪን በተመለከተ ቀጥተኛ ተፈጻሚነት እና አስገዳጅነት ያለው የደመወዝ ማስተካከያ ያለማድረጉ መሆኑን ይልቁንም ተጠሪ በራሱ ገቢ የሚተዳደር ከመሆኑ አንፃር እንደራሱ ገቢ መጠን ጥናት አድርጐ በአስተዳደሩ አፅድቆ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ የተቀመጠለት መሆኑን እንጂ አስገዳጅ የሆነ ውሳኔ ያልተሰጠ መሆኑን የሚያስገነዝብ መሆኑን ደምድሞ አመልካቾች ባለው የቤተክርስቲያን መዋቅር መሰረት አቤቱታቸውን ከማቅረብ ውጪ በፍርድ ሃይል ተፈጻሚ የሚሆን ውሳኔ የላቸውም በማለት የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮ የፍደራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በውጤት ደረጃ በመቀበል አፅንቶታል ። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
No topics extracted.
የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ/ም ያሳለፈው ውሳኔ ተጠሪ ገቢውን መሰረት በአደረገ መልኩ ለሰራተኞቹም ሆነ ለጡረተኞቹ በተሰራው ስኬል መሰረት ማስተካከያውን እንዲያደርግ የሚል ሁኖ እያለ ተጠሪ ለሰራተኞቹ ብቻ ማስተካከያውን አድርጐ ለጡረተኞቹ ሳያደርግ ሲቀር የቀረበውን ክስ የፍደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያላግባብ ተርጐሞ ተጠሪ የሚገደድበት ውሳኔ የለም በማለት መወሰኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ነው የሚል ሲሆን ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ ግራ ቀኙ በፅሁፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል ።እንደመረመረውም ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ሲቀርብ በጭብጥነት የተያዘው ነጥብ ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ/ም በሰጠው ውሳኔ የአሁኑን ተጠሪ በስም ጠቅሶ ለሰራተኞቹና ጡረተኞቹ እንደየገቢያቸው መጠን እየወሰኑ ለአስተዳደሩ እያስፀደቁ ክፍያው እንዲፈፀም በማለት በሰጠው ውሳኔ መሰረት ለሰራተኞቹ የጭማሪውን ክፍያ እንደአደረገ ተጠሪ ግንቦት 27 ቀን 2005 ዓ/ም በሰጠው መልስ ማመኑ ከተረጋገጠ የሲኖዶሱ ውሳኔ ለጡረተኞች ብቻ ተፈፃሚነት የለውም በሚል የተሰጠውን ውሳኔ አግባብነት ለመመርመር ተብሎ ነው። እኛም ጉዳዩን ከዚሁ ጭብጥ አንፃር ብቻ መመርመሩን ተገቢነት ያለው ሆኖ አግኝተናል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ተጠሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥር የሚተዳደር ነገር ግን በራሱ ገቢ ራሱን የሚያስተዳድር ስለመሆኑ ግራ ቀኙን ያላከራከ ጉዳይ መሆኑን፣ ለአመልካቾች ክስም ሆነ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሰራተኞቹና ጡረተኞቹ የደሞዝ ማስተካከያ አስመልክቶ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ.ም ያስተላለፈው ውሳኔ መሆኑን፣ በዚህ ውሳኔ ጥናት ተደርጎ የቀረበውን ጉባኤው ያፀደቀላቸው ሲሆን ልሎቹ ማለትም በትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤትና በጎፋ ጥበብ እድ ካህናት ማሰልጠኛ ለሚገኙት ሰራተኞችና ጡረተኞች እንደየገቢያቸው መጠን እየወሰኑ ለአስተዳደሩ አቅርበው እያፀደቁ ተግባራዊ እንዲሆን ሲል ቋሚ ሲኖዶሱ መወሰኑና ይህንኑ ተከትሎም ተጠሪ ለሰራተኞቹ የጭማሪውን አስተካክሎ ክፍያውን ሲፈፅም ለአሁኑ አመልካቾች፤ የድርጅቱ ጡረተኞች ግን ማስተካከያውን ሳያደርግ የቀረ መሆኑን አምኖ የሚከራከር መሆኑን ነው። የፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተጠሪ ለክሱ ኃላፊነት የለበትም ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰው የሲኖዶሱ የስብሰባ ቃለ ጉባኤ ይዘት ተጠሪ ለጡረተኞች ማስተካከያ እንዲያደርግ በግድታየሚያመላክት አይደለም የሚለውን ምክንያት በመያዝ መሆኑን ከውሳኔው ይዘት ተረድተናል።
በመሰረቱ ተጠሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስር የሚተዳደር ከሆነ የቤተክርስቲያኗ የበላይ የሆነው አካል የሰጠውን ውሳኔ ያለምንም ልዩነት ተግባራዊ ማድረግ አለበት። ተጠሪ ለአመልካቾች የጡረታ ደመወዝ የሚከፍለው በግራ ቀኙ መካከል በነበረው የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ሲሆን ይህ ክፍያ የሚፈፀመውም የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነቱ በጡረታ ምክንያት በመቋረጡ ምክንያት በመሆኑና ገንዘቡም ከአሰሪውና ከሰራተኞቹ ደመወዝ ተቆርጦ ሲጠራቀም ከነበረው መሆኑ ግልፅ ነው። የጡረታ ደመወዝ ሕጋዊ በሆነ የአስተዳደራዊ ውሳኔ መሰረት እንዲስተካከል ሲደረግ በሰራተኛው ስም የተቀመጠው ገንዘብ መኖሩን ብቻ በማረጋገጥ ነው ተብሎ አይታሰብም። ጡረታ አግባብነት ላላቸው የህብረተሰቡ ክፍሎች የኑሮ ዋስትና ለመስጠት እንዲያስችል ተብሎ ተግባራዊ የሚደረግ ማህበራዊ መድህን መሆኑ ግልፅ ነው።
የኑሮ ዋስትና የመስጠት መሰረታዊ አላማው የሚሳካው ደግሞ ተጨባጭነት ያለውን ወይም የሕብረተሰቡን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ማስተካከያው ሲደረግ መሆኑ የሚታመን ነው።
በዚህ አግባብ የጡረታም ሆነ የደመወዝ ማስተካከያም ተግባራዊ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ መኖሩም ግንዛቤ የሚወሰድበት ነው። የተጠሪ መስሪያ ቤት ባለቤት የሆነውና የበላይ የአስተዳደር አካሉ መንግስት ለሰራተኞቹና ለጡረተኞቹ ያደረገውን ማስተካከያ መነሻ በማድረግና በራሱ ፍላጎት ለተጠሪ ሰራተኞቹና ጡረተኞች ማስተካከያውን እንዲያደርግ፣ ማስተካከያው ደግሞ የተጠሪን ገቢ መሰረት አድርጎ ላሰራእንደሚገባና በሚመለከተው አካል እየጸደቀ ተግባሪዊ እንዲሆን የሚገልፅ ውሳኔ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ/ም መወሰኑም ይህንኑ የሚያሳይ ነው ።
ተጠሪ የሲኖዶሱ ውሳኔ በተጠሪ ላይ አስገዳጅነት የለውም በማለት የሚያቀርበውና በፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ተቀባይነት ያገኘው መከራከሪያ ነጥብ ሲታይም ተጠሪው ገቢውን መሰረት ያደረገ ጥናት አደርጎ ለቋሚ እና ለኮንትራት ሰራተኞቹ ማስተካከያውን አድርጎ ክፍያውን መፈጸሙን ያመነበትን አግባብ ክፍያውን ለጡረተኞቹ ላለማድረግ ህጋዊ ምክንያት የነበረው መሆን ያለመሆኑን አጣምሮ ያላገናዘበ ሆኖ አግኝተናል።ምክንያቱም የተጠሪ የበላይ አስተዳደር የሆነው አካል ለተጠሪ የሰጠው አስተዳደራዊ አቅጣጫ የማስተካከያው ክፍያ ተጠቃሚዎችን ሰራተኞች ወይም ጡረተኞች በሚል ጭምር ተለይቶ እንዲፈፀም የሚያሳይ ሳይሆን ለሰራተኞቹም ሆነ ለጡረተኞቹ ልዩነት ሳይደርግ የድርጅቱን ገቢ መሰረት አድረጎ ማስተካከያውን እንዲሰራና ተግባራዊ እንዲያደርግ የሚያስገነዝብ ነው። ስለሆነም ተጠሪ የበላይ አካልን ውሳኔ ተግባራዊ ላለማድረግ ሕጋዊ መከራከሪያ ላሆነው የሚችለው የድርጅቱ የገቢ ሁኔታ ብቻ ነው።ሆኖም ተጠሪ ለሰራተኞቹ ማስተካከያውን ያደረግው የድርጅቱን ገቢ መሰረት አድርጎ ስላለመሆኑ ያቀረበው ክርክርና ማስርጃ የለም።የተጠሪ የበላይ አካል የሆነው ሲኖዶሱ ማስተካከያው ለተጠሪ ድርጅት ሰራተኞች ጡረተኞች እንዲደረግ ውሳኔ ከሰጠና ለሰራተኞቹ የተጠሪን ገቢ መሰረት ባደረግ መልኩ ማስተካከያው መደረጉ እስከተረጋገጠ ድረስ ደግሞ ተጠሪ ጡረተኞችን ብቻ በመለየት የማስተካከያው ተጠቃሚ ላሆኑ አይችሉም የሚልበት አግባብ የለም።ተጠሪ የበላይ አካሉን ውሳኔ ተቀብሎ ለሰራተኞቹ ብቻ ማስተካከያ አድርጎ ለጡረተኞቹ ብቻ ማስተካከያውን የተወበት አካሄድ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ በውጤት የጡረታ መብት ለኑሮ ዋስትና ያለው ሕጋዊ ፋይዳ ዋጋ የሚያሳጣው ነው።
አመልካቾች ተጠሪ ላይ በመደበኛ ፍርድ ቤት ክስ የመሰረቱት ከተጠሪ ጋር መስርተው የነበሩት ሕጋዊ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ተቋርጦ የአመልካቾች የጡረታ መብት ተከብሮላቸው የጡረታ መብት ተካፋይ ሁነው ባሉበት ሁኔታ በአስተዳደራዊ ውሳኔ መሰረት የተከበረላቸው የጡረታ ማስተካከያ ክፍያ ተግባራዊ ላሆን አልቻለም በሚል በመሆኑ ጉዳዩ ኃይማኖታዊ ስርዓትን ተከትሎ ትርጉም የማያስፈልገው በመሆኑ ጉዳዩ በፍርድ ቤት መታየቱ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 11 ስር የተደነገገውን መርህ የማይነካ መሆኑን ተገንዝበናል።ሕጋዊ የሆነ አስተዳደራዊ ውሳኔ ተግባሪዊ ሳይሆን ሲቀር በፍርድ ቤት ውሳኔ አስገዳጅነትእንዲኖረውማድረግም በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 37 እና 25 የተረጋገጡትን ፍትህ የማግኘት መብትና የእኩልት መብት ውጤታማ የሚያደረግ ነው ተብሎ ይታሰባል።ስለሆነም የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተጠሪ የበላይ አካል የሆነው ሲኖዶስ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ.ም በሰጠው ውሰኔ የአሁኑን ተጠሪ በስም ጠቅሶ ለሰራተኞቹና ጠረተኞቹ እንደየገቢያቸው መጠን እየወሱነ ለአስተዳደሩ እያስፀደቁ ክፍያው እንዲፈፀም በማለት በሰጠው ውሳኔ መሰረት ተጠሪ ለሰራተኞቹ የጭማሪው ክፍያ እንደ አደረገ ግንቦት 27 ቀን 2005 ዓ/ም በሰጠው መልስ ማመኑ በተረጋገጠበት ሁኔታ የሲኖዶሱ ውሳኔ ለጡረተኞች ብቻ ተፈፃሚነት የለውም የሚል ትርጉም የሚያሰጥ ውሳኔ መስጠቱ በክርክሩ ሂደት የተረጋገጡትን ፍሬ ነገሮችን ያላገናዘበ ሆኖ ስለአገኘነው በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ያለበት ነው በማለት ተከታዩን ወስነናል።
የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ ግንቦት 05 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ታህሳስ 07 ቀን 2006 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል።
ተጠሪ ለአመልካች ጥያቄ ኃላፊ ነው ተብሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ መጋቢት 20 ቀን 2003 ዓ/ም በወሰነው መሰረት ከጥር ወር 2003 ዓ/ም ጀምሮ የጡረታ ማስተካከያ አበል ላከፈላቸው ይገባል በማለት ወስነናል። ስልቱን በተመለከተ የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባስቀመጠው መሰረት ነው ብለናል።
ለክርክሩ የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።