አንድ አሰሪ ለሙከራ የቀጠረውን ሰራተኛ በቀጠረው በ46ኛው ቀን ለስራው ብቁ አይደለም ብሎ የስንብት ደብዳቤ ቢጽፍለት ድርጊቱ ህገ ወጥ ነው ላባል የማይችል ስለመሆኑ፣ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 11(2)፣(3) 101890 የኢትዮጵያ አየር መነግድ እና ወ/ት ፍፁም ሀይሉ ጥቅምት 24/2007 69 19. “ስለሰራተኛ ዕድገት አሰጣጥ ስርዓት” በሚል በአዋጁ የተገለፀው ሀረግ ላተረጎም የሚገባው ከአንድ የሰራተኛ የስራ መደብ ወደ ልላ የሰራተኛ የስራ መደብ የሚፈፀም የዕድገት አሰጣጥ ስርዓት በሚል መልኩ ስለመሆኑ፣ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 142(1)(ሰ)
No summary available.
መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ሡልጣን አባተማም መኮንን ገ/ሕይወት ሙስጠፋ አህመድ ተፈሪ ገብሩ አመልካች፡- የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት ነገረ ፈጅ ፈለቀ እንግዳሸት- ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ አድማሱ አበበ ከጠበቃ ጥላሁን ጋር ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 መሰረት የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ነው በሚል የተነሳ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን የተጀመረውም በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ከሳሽ የነበሩት የአሁኑ ተጠሪ በአሁኑ አመልካች ላይ ባቀረቡት ክስ ነው።
በ08/02/2006 ዓ.ም አዘጋጅተው ያቀረቡት ክስ ይዘትም ባጭሩ፡-ተከሳሽ ድርጅት ለሕዝብ ግንኙነት ደጋፊ የስራ ሂደት ላወጣው ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ የድርጅቱ ደንብ፣መመሪያ እና የህብረት ስምምነት በሚፈቅደው መሰረት ከሳሽ መስፈርቶቹን አሟልተው ለውድድር መመዝገባቸውን፣ይሁን እንጂ ድርጅቱ በማስታወቂያ የወጣውን የመወዳደሪያ መስፈርት በመተው መስፈርቱን የማያሟሉትን አቶ አወቀ በለጠ የተባሉትን የድርጅቱ ባልደረባ ለውድድር አቅርቦ እንዲያልፉ ማድረጉን፣ከሳሽ ይህንን በመቃወም ለድርጅቱ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ያቀረቡት ቅሬታ ተቀባይነት አግኝቶ መስፈርቱን የማያሟሉት አቶ አወቀ በለጠ ለውድድር እንዲቀርቡም ሆነ እንዲያልፉ የተደረገው አላግባብ መሆኑን ገልጾ ኮሚቴው በ13/01/2006 ዓ.ም. የተጻፈ የውሳኔ ሀሳብ ያቀረበ ቢሆንም ድርጅቱ ለውድድር በቀረበው የስራ መደብ ላይ ከሳሽን ለመመደብ ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን በዝርዝር የሚገልጽ ሆኖ መስፈርቱን ላላሟሉ ሰራተኛ የተሰጠው ምደባ ተሰርዞ በቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሀሳብ መሰረት የስራ መደቡ መስፈርቶቹን ላሟሉት ለከሳሽ እንዲሰጥ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት የተጠየቀበት ነው።
ተከሳሽ ድርጅት በበኩሉ በ25/02/2006 ዓ.ም በሰጠው መልስ የመቃወሚያ እና የፍሬ ነገር የክርክር ነጥቦችን አቅርቧል።የቀረቡት ሁለት የመቃወሚያ ነጥቦችም ክሱ የግል የስራ ክርክርን የሚመለከት በመሆኑ እና ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያው የወጣበት የስራ መደብም የሚመለከተው የስራ መሪን እንጂ ሰራተኛን ባለመሆኑ ቦርዱ ጉዳዩን ለማየት የሚያስችል ስልጣን የለውም የሚሉ ሲሆኑ በፍሬ ጉዳዩ ረገድ የተሰጠው መልስ ይዘት ደግሞ ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂው የወጣው በስራ መሪዎች ምደባ መመሪያ መሰረት መሆኑን፣ጉዳዩም የሚመለከተው ምደባን እንጂ የደረጃ ዕድገትን አለመሆኑን፣ የከሳሽ የምደባ ጥያቄ ተቀባይነት ያጣው የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ የመንግስትን ፖላሲ እና መመሪያ በማስፈጸም ረገድ በከሳሽ ላይ እምነት ባለመጣላቸው መሆኑንየሚገልጽ ነው።ቦርዱም በቅድሚያ የመቃወሚያ ነጥቦቹን ከመረመረ በኃላ ከሳሽ ክሱን ያቀረቡት የዕድገት አሰጣጥ ስርዓት ተጥሶብኛል በማለት በመሆኑ እና የሰራተኛ አቀጣጠር እና ዕድገት አሰጣጥ ስርዓትን አስመልክቶ የሚነሱ ክርክሮችን የማየት ስልጣን ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 142(1)(ሰ) ድንጋጌ መሰረት የተሰጠው ለቦርድ በመሆኑ ክሱ የግል የስራ ክርክርን የሚመለከት መሆኑን ጠቅሶ ተከሳሽ ያቀረበው የስልጣን መቃወሚያ ተቀባይነት የልለው መሆኑን እና ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያው የወጣበት የስራ መደብየሚመለከተው የስራ መሪን እንጂ ሰራተኛን ባለመሆኑ ቦርዱ ጉዳዩን ለማየት የሚያስችል ስልጣን የለውም በሚል የቀረበውን መቃወሚያ በተመለከተም በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 3(2)(ሐ) ድንጋጌ መሰረት ለስራ መሪ የተሰጠው ትርጉም ቀድሞውንም ቢሆን የስራ መሪ ሆኖ በአንቀጹ ላይ የተዘረዘሩትን የስራ መሪ ተግባሮች ሲያከናውን የነበረን ሰው የሚመለከት እንጂ ሰራተኛ ሆኖ ለስራ መሪ በወጣ ክፍት የስራ መደብ ላይ ለውድድር የቀረበን እንደ ከሳሽ ዓይነት ሰውን የሚያጠቃልል ባለመሆኑ በዚህ ረገድ የቀረበው መቃወሚያም ተቀባይነት የልለው መሆኑን ገልጾ መቃወሚያዎቹን በ11/03/2006 ዓ.ም በብይን ካለፋቸው በኃላ ፍሬ ጉዳዩን በተመለከተ ጉዳዩን ለክፍት የስራ ቦታው በወጣው ማስታወቂያ ላይ ከተዘረዘሩት መስፈርቶች እና ከስራ መሪዎች ምደባ መመሪያ አንጻር መመርመሩን ገልጾ በውድድሩ 84.50% ውጤት አግኝተዋል የተባሉት አቶአወቀ በለጠ ወደ ውድድሩ የገቡት ተገቢ መመዘኛዎችን ሳያሟሉ በመሆኑ ለእርሳቸው የተሰጠው ምደባ ውድቅ ተደርጎ የስራ መደቡ እና የስራ መደቡ የሚያስገኘው ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ተገቢ የመወዳደሪያ መስፈርቶቹን አሟልተው ወደ ውድድሩ ለገቡት እና በውድድሩ 71% ውጤት ላገኙት ለከሳሽ ላሰጥ ይገባል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።
አመልካች አቤቱታውን ለዚህ ችሎት ያቀረበው የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኙን ዘግቶ በማሰናበቱ ሲሆን የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ በዚህ ጉዳይ ለስራ መሪ የስራ መደብ ብቁ ሆኜ ሳለ ቦታው ለሶስተኛ ወገን የተሰጠው አላግባብ ነው በማለት ተጠሪ ለአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ያቀረቡትን ክስ ቦርዱ የማየት ስልጣን የለውም በማለት አመልካች ያቀረበው መቃወሚያ በስር ፍርድ ቤቶች ተቀባይነት የማጣቱን አግባብነት ተጠሪው ባሉበት ለማጣራት ይቻል ዘንድ ጉዳዩ ለሰበር ክርክር እንዲቀርብ በመደረጉ ግራ ቀኙ የጽሁፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምረናል።
በዚህም መሰረት አመልካች ላወጣው ክፍት የስራ መደብ ለውድደር በቀረቡበት ጊዜ ተጠሪ ይሰሩ የነበረው በሰራተኛነት መሆኑ፣ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያው የወጣው ለስራ መሪ የስራ መደብ መሆኑ፣በማስታወቂያው መሰረት በሰራተኞች እና በስራ መሪዎች መካከል ልዩነት ሳይደረግ ለውድድር የተጋበዙት በሁለቱም የስራ ዘርፍ የሚገኙ የድርጅቱ የሰው ኃይል አባላት መሆናቸው፣በመወዳደሪያ መስፈርቶቹ መሰረት ውድድሩ እና አሸናፊውን ተወዳዳሪ የመምረጡ ስርዓት የሚከናወነው በድርጅቱ የስራ መሪዎች ምደባ መመሪያ መሰረት መሆኑ እና በዚህ ረገድ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 “ም” ሆነ የድርጅቱ የህብረት ስምምነት ተፈጻሚነት የማይኖራቸው መሆኑ በግራ ቀኙ ክርክር ያልቀረበበት እና ቦርዱም ቢሆን የተቀበለው ጉዳይ መሆኑን የመዝገቡ ግልባጭ ያመለክታል።ቀደም ሲል እንደተገለጸው ቦርዱ በስረ ነገር ስልጣን ረገድ ከአመልካች የቀረበለትን የመቃወሚያ ነጥብ ውድቅ ያደረገው ክሱ የቀረበው የዕድገት አሰጣጥ ስርዓት ተጥሶብኛል በማለት መሆኑን፣የሰራተኛ አቀጣጠር እና ዕድገት አሰጣጥ ስርዓትን አስመልክቶ የሚነሱ ክርክሮችን የማየት ስልጣን ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 142(1)(ሰ) ድንጋጌ መሰረት የተሰጠው ለቦርድ መሆኑን እና የስራ መሪ የስራ መደብም ተጠሪው የሚወዳደሩበት እንጂ ይዘው የሚገኙት የስራ መደብ አለመሆኑን በመግለጽ ነው።
እንደሚታወቀው አዋጅ ቁጥር 377/1996 "ን" መሰረት አድርገው የሚነሱ የስራ ክርክር ጉዳዮች የሚታዩት እንደ ጉዳዩ ዓይነት በክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ወይም በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ሲሆን በክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሚታዩት በአዋጁ አንቀጽ 138(1) ስር ከፊደል (ሀ) እስከ (ረ) የተዘረዘሩ የግል የስራ ክርክር ጉዳዮች መሆናቸውን እና በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቋሚ ቦርድ የሚታዩት ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 142(1) ከፊደል (ለ) እስከ (ሸ) የተዘረዘሩ የወል የስራ ክርክር ጉዳዮች መሆናቸውን ከላይ የተጠቀሱት እንዲሁም የአዋጁ አንቀጽ 142(3) እና 147(1)(ሀ) እና (ለ) ድንጋጌዎች ያመለክታሉ።ተጠሪ ክሳቸውን ለቦርዱ ያቀረቡትም የዕድገት አሰጣጥ ስርዓት ተጥሶብኛል በማለት ነው።የዚህ ዓይነቱ የስራ ክርክር ደግሞ በባህርይው የወል እንጂ የግል የስራ ክርክር አይደለም።በዚህም ሁኔታ ከላይ የተጠቀሱትን የአዋጁን ድንጋጌዎች መሰረት በማድረግ ክሱ የቀረበው የዕድገት አሰጣጥ ስርዓት ተጥሶብኛል በማለት መሆኑን እና የሰራተኛ አቀጣጠር እና ዕድገት አሰጣጥ ስርዓትን አስመልክቶ የሚነሱ ክርክሮችን የማየት ስልጣን በአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 142(1)(ሰ) ድንጋጌ መሰረት የተሰጠው ለቦርድ መሆኑን በመግለጽ ቦርዱ የያዘው አቋም በራሱ የሚነቀፍ ባይሆንም ከጉዳዩ ልዩ ባህርይ አንጻር ለክርክር የቀረበው የዳኝነት ጥያቄ በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 የሚሸፈን መሆን አለመሆኑ እና በዚህም ምክንያት በቦርዱ ስልጣን ስር የሚወድቅ መሆን አለመሆኑ በአግባቡ መጤን የሚገባው መሆኑን ተገንዝበናል።
በመሰረቱ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 የተፈፃሚነት ወሰን በአሰሪና ሰራተኛ መካከል በሚደረግ በቅጥር ላይ በተመሰረተ የስራ ግንኙነት ጉዳዮች የተገደበ ስለመሆኑ እና በተለይም ከስራ መሪ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት የማይኖረው ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 3(1) እና (2)(ሐ) ስር የተመለከተ ሲሆን ተጠሪ የስራ መሪ ባይሆኑም ለውድድር የቀረቡት በስራ መሪ በሚሸፈን የስራ መደብ ላይ ለመመደብ ነው።ዋነኛ አከራካሪ ነጥብ ሆኖ የቀረበውም በአዋጁ መሰረት የተጠሪው ሰራተኛ የመሆን አለመሆን ጉዳይ ሳይሆን በስራ መሪ ለሚሸፈን የስራ መደብ የሚደረግ ውድድር የሚመራበት ስርዓት ነው።በመወዳደሪያ መስፈርቶቹ መሰረት ውድድሩ እና አሸናፊውን ተወዳዳሪ የመምረጡ ስርዓት የሚከናወነው በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ እና በህብረት ስምምነቱ መሰረት ሳይሆን በድርጅቱ የስራ መሪዎች ምደባ መመሪያ መሰረት መሆኑ አላከራከረም።የስራ መሪዎችን የምደባ መመሪያ መሰረት በማድረግ የሚነሱ ክርክሮችን የማየት ስልጣን ደግሞ በአዋጁ መሰረት ለፍርድ ቤት የስራ ክርክር ችሎቶችም ሆነ ለአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ አልተሰጠም።እንዲህ ከሆነ ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 142(1)(ሰ) ድንጋጌ ስር “…ስለሰራተኛ…ዕድገት አሰጣጥ ስርዓት” በሚል የተገለጸው ሐረግ ላተረጎም የሚገባው ከአንድ የሰራተኛ የስራ መደብ ወደ ልላ የሰራተኛ የስራ መደብ የሚፈጸም የዕድገት አሰጣጥ ስርዓት ተደርጎ እንጂ ከአንድ የሰራተኛ የስራ መደብ በስራ መሪ ወደሚሸፈን ልላ የስራ መደብ የሚፈጸም የዕድገት አሰጣጥ ስርዓትን በሚያጠቃልል አግባብ አለመሆኑን ከድንጋጌው አጠቃላይ ይዘትና መንፈስ መገንዘብ ይቻላል።በመሆኑም በአዋጁ አንቀጽ 142(1)(ሰ) ድንጋጌ ስር “…ስለሰራተኛ…ዕድገት አሰጣጥ ስርዓት” በሚል የተገለጸውን ሐረግ ከአንድ የሰራተኛ የስራ መደብ በስራ መሪ ወደሚሸፈን ልላ የስራ መደብ የሚፈጸም የዕድገት አሰጣጥ ስርዓትን እንደሚያጠቃልል አድርጎ በመተርጎም ቦርዱ በስረ ነገር ስልጣን ረገድ በአመልካች የቀረበውን መቃወሚያ በብይን አልፎ በፍሬ ጉዳዩ ረገድ የሰጠው ውሳኔ በሕግ አተረጓጎም ረገድ መሰረታዊ ስህተት የተፈጸመበት እና ላታረም የሚገባው መሆኑን ተገንዝበናል።
ሲጠቃለል በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ተሰጥቶ በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በትዕዛዝ የጸናው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ በመዝገብ ቁጥር 498/ቀወ2/06 በ12/06/2006 ዓ.ም. ተሰጥቶ በፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ በ22/09/2006 ዓ.ም. በትዕዛዝ የጸናው ውሳኔ በፍትሐብሕር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 348(1) መሰረት ተሽሯል።
ክርክር ያስነሳው ጉዳይ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/1996 የሚሸፈን ባለመሆኑ ቦርዱ ጉዳዩን ተቀብሎ በማስተናገድ ውሳኔ የሰጠው ጉዳዩን ለማየት የሚያስችል የስረ ነገር ስልጣን ሳይኖረው ነው በማለት ወስነናል።
በዚህ መዝገብ በ12/10/2006 ዓ.ም. ተሰጥቶ የነበረው የአፈጻጸም ዕግድ ተነስቷል።
እንዲያውቁት የውሳኔው ቅጂ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ እና ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይላክ።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
ውሳኔ ያገኘ ሰለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።
No topics extracted.