በሰራተኛው የሚጠየቅ የውዝፍ ደመወዝ ክፍያ ጥያቄ በአሰሪው የይርጋ መቃወሚያ ካልቀረበበት በስተቀር ተከፋይ ስለመሆኑ።-
No summary available.
መስከረም 29 ቀን 2007 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ሱልጣን አባተማም መኰንን ገ/ህይወት ሙስጠፋ አህመድ ተኸላት ይመስል አመልካች፡- አቶ ዳዊት ገ/ማርያም - የቀረበ የለም።
ተጠሪ፡- አቶ ሣህለማርያም ደግፍ - የቀረበ የለም።
መዝገቡ ተመርምሯል።
የሰበር አቤቱታው የሶማል ክልል መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.05-0- 60/06 መጋቢት 19 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈፅሟል ይታረምልን የሚል ሲሆን፤ይግባኝ ባይ በጠበቃቸው በኩል ግንቦት 18 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ጽፈው ባቀረቡት ሦስት ገጽ ቅሬታ፡በሥር ፍርድ ቤት ከሳሽ የአሁኑ የሰበር አመልካች በተጠሪ ላይ በ17/10/2005 ዓ.ም በተፃፈ ክስ ከተጠሪ ጋር በ3ዐ/09/2004 ዓ.ም በተዋዋሉት የሥራ ቅጥር ውል መሰረት አመልካች ሲሰሩ የቆዩ ቢሆንም ተጠሪ ክፍያ ባለመፈፀማቸው እና አመልካችን ከሥራ አላግባብ በማሰናበታቸው ተጠሪ ውዝፍ ደመወዝ፣ ካሣ እና ልሎች ጥቅማ ጥቅም ለአመልካች እንዲከፍሉ ይወሰንላቸው ዘንድ ጠይቀዋል።
ተጠሪ ለቀረበባቸው ክስ ከአመልካች ጋር የሥራ ቅጥር ውል የለንም ከማለት አልፈው በፍሬ ነገር ክርክሩ መልስ ባለመስጠታቸው ክሱ የቀረበለት የጅጅጋ ወረዳ ፍርድ ቤት በግራ ቀኙ መካከል የሥራ ቅጥር ውል አለ ተጠሪ ውዝፍ ደመወዝ ብር 42,000 /አርባ ሁለት ሺህ/ አመልካች ይክፈሉ ሲል ወስኗል።
ተጠሪ በውሣኔው ቅር በመሰኘት ለፋፈን ዞን ከፍተኛ ፍ ርድ ቤት ይግባኝ የጠየቁት ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙ አከራክሮና ማስረጃ ሰምቶ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን በማፅናት ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት ወስኗል።
የአሁኑ ተጠሪ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቅርበው ግራ ቀኙን ያከራከረ ቢሆንም በሥር ፍርድ ቤት ያልቀረበ የይርጋ ክርክር በማንሳት የአመልካች ክስ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 162/3 መሰረት በይርጋ ቀሪ ሆኗል በማለት የሥር ፍርድ ቤቶች ውሣኔ በመሻር መሰረታዊ የሕግ ሥህተት የፈፀመ በመሆኑ ችሎቱ የሥር ሰበር ችሎት ስህተት በማረም የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲያፀናልኝ እና ወጪና ኪሣራዬን ይተካልኝ ዘንድ በመወሰን ያስናብተኝ የሚል ነው።
የሰበር አቤቱታ አጣሪ ችሎቱ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ሰኔ 20 ቀን 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት መርምሮ።
“የሱማል ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በይርጋ ላይ ተመርኩዞ የሰጠው ዳኝነት አግባብነት ከፍ.ሥ.ሥ.ሕግ ቁጥር 244/3 አንፃር ለመመርመር ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ይቅረብ” ሲል አዟል።
ተጠሪ የአመልካች የሰበር አቤቱታ ደርሷቸው በጠበቃቸው በኩል ሐምል 7 ቀን 2006 ዓ.ም ጽፈው ያቀረቡት መልስ፤ ተጠሪ በሥር ፍርድ ቤት የቀረበባቸው ክስ ችግር የተሞላበት የነበር ቢሆንም በይግባኝ ደረጃ የሥር ፍርድ ቤት ውሣኔ ህገወጥነት ከመግለጽ አልፎ በቃል ክርክር ስለይርጋ በማንሳት ተከራክረዋል። ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሥር ፍር ድ ቤት ውሣኔ ቢያጸናውም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የአመልካች ክስ በይርጋ ቀሪ ነው በማለት መወሰኑ የሚነቀፍ ባለመሆኑ ውሳኔው ስህተት የለበትም ተብሎ ችሎቱ ከበቂ ወጪና ኪሣራ ጋር ያሰናብተን የሚል ነው።
አመልካች ሀምል 25 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ ያቀረቡ ሲሆን የሰበር አቤቱታውን በሚያጠናክር መልክ የቀረበ ነው።
እኛም በሰበር አቤቱታው ያስቀርባል ሲባል የተያዘውን ጭብጥ መሰረት በማድረግ የግራ ቀኙ ክርክር አግባብ ካላቸው ህጐች አንፃር መርምረናል ።
አመልካች ለሰበር አቤቱታቸው ምክንያት ያደረጉት በሥር ፍርድ ቤት በተጠሪ ላይ ያቀረብኩት ክስ በይርጋ ቀሪ አይሆንም፣ በሥር ፍርድ ቤትም ያልቀረበ መቃወሚያ በሰበር ደረጃ ላቀርብ አይገባም በሚል ሲሆን ተጠሪ መቃወሚያ በቃል ክርክር አቅርቤያለሁ ውሳኔው አግባብ ነው ባይ ናቸው።
በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 244/3 መሰረት መቅረብ ከሚገባቸው መቃወሚያዎች ውስጥ ተጠቃለው ካልቀረቡ ያልቀረበው መቃወሚያ ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት የሚያሰናክል ከሆነ ባለጉዳዩ ራሱ ሆነ ብሎ ለማቅረብ ባለመፈለግ እንደተወው የሚቆጠር ለመሆኑ ተመልክቷል።
ተጠሪ መቃወሚያ በመጀመሪያ ቀነ ቀጠሮ አጠቃለው አለማቅረባቸው አሁን በሰበር ክርክር ያመኑ ሲሆን በሥር መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና ውሳኔም ስለመቅረቡም አልተመዘገበም።
መቃወሚያ ካልቀረበም ተከሳሹ ሆነ ብሎ እንደተወው የሚቆጠር ከመሆኑም በላይ በሥር ፍርድ ቤት ያልተነሳ ክርክር ኋላ በማንሣት ለውሣኔ መሰረት ማድረግ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁጥር 329/1 የሚፃረር ነው።
የክልሉ ሰበር በሥር ፍርድ ቤት ያልቀረበውን መቃወሚያ በማንሳት የአመልካች ክስ በይርጋ ቀሪ ሆኗል ሲል መወሰኑ የህግ ስህተት ሲሆን፤ አመልካች ሥራ ከተቀጠርኩ ጊዜ ጀምሮ ደመወዝ አልተከፈለኝም ውዝፍ ደመወዜ ይከፈለኝ በሚል ነው። አመልካች አስራ ሦስት ወር ለተጠሪ መስራታቸው ተረጋግጧል። አመልካች የጠየቁት የውዝፍ ደመወዝ ክፍያ የይርጋ መቃወም በተጠሪ ካልቀረበበት የማይከፈልበት ምክንያት የለም።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአሁኑ ተጠሪ የተነሳ የይርጋ ጥያቄ ሳይኖር የአመልካች ክስ በይርጋ ቀሪ ማድረጉ የሕግ ስህተት ስለሆነ የሚከተለው ውሣኔ ተሰጥቷል።
ው ሣ ኔ
በሱማል ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቁጥር 05/1/60/06 ግንቦት ዐ5 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጠው ፍርድ በፍ.ብ.ሥ.ሥ.ሕግ ቁጥር 348/1 መሰረት ተሽሯል።
የሱማል ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት የፈፋን ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ.ቁ.19-05-06 ጥር 29 ቀን 2006 ዓ.ም የሰጡት ውሳኔ እና የጅጅጋ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ.ቁ.M/D/J746/05 ሐምል ዐ4 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ በፍ.ብ.ሥ.ሥ.ሕግ ቁጥር 348/1 መሰረት ፀንቷል።
ግራ ቀኙ ወጪና ኪሣራቸው ይቻሉ መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.