በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 74(2) መሰረት ፍ/ቤቱ የተዘጋን የይግባኝ አቤቱታን እንደገና ስለሚያይበት እነ ወ/ሮ ብዙ ሰንበታ (ሁለት ሰዎች) እና አቶ ታደሰ ሰንበታ
No summary available.
መጋቢት 16 ቀን 2007 ዓ.ም.
ዳኞች፡- አልማው ወል ዓላ መሐመድ ሱልጣን አባተማም ሙስጠፋ አህመድ ተኽላት ይመሰል አመልካች፡- አቶ ባካፋ አንለይ -- ራሳቸው ቀረቡ።
ተጠሪ፡- አቶ ቴዎድሮስ አንለይ - ጠበቃ ጌትነት አየለ ቀረቡ።
**
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ ያለአግባብ የተያዘ የመኖሪያ ቤት ይለቀቅልኝ ጥያቄን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው በምዕራብ ጎጃም አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአሁን ተጠሪ በአመልካች ላይ በመሰረተው ክስ መነሻነት ነው። የክሱ ይዘትም ባጭሩ፡- በባህር ዳር ከተማ ቀበል 08 ክልል ውስጥ የሚገኘውን፣ በካርታ ቁጥር 10/00/93 የሚታወቀውንና በ660 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሰፍሮ በስማቸው ተመዝግቦ ያለውን መኖሪያ ቤት ተከሳሽ ምንም መብት ሳይኖራቸው ከህዳር ወር 1998 ዓ.ም ጀምሮ በመያዝ እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ገልፀው ቤቱ እንዲለቀቅላቸውና ያላግባብ ቤቱን ለተጠቀሙበት ጊዜ ደግሞ በወር ብር 2000.00(ሁለት ሺህ) ኪራይ ታስቦ እንዲከፈላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።
ተከሳሽ የሰጡት የመከላከያ መልስም፡- ከሳሽ ቦታውን የተመራበት ካርኒ አላቀረበም። ቤቱ በ1963 ዓ.ም የተሰራ ሲሆን ውሃና መብራት የገባው በወላጅ አባታችን በደጃዝማች አንለይ ኃይል ስም በመሆኑ ቤቱ የአባታችን ቤት ነው። በአባታችን ስም የተከፈተው የማህደር ቁጥር 1224 የአባታችን ቤት መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ማህደሩ በሙሉ ተዘርፏል። ግብርበአባታችን ስም የተገበረ ለመሆኑ የባህር መዝገብ ቁጥር 202 ስለሚያስረዳ ቀርቦ መታየት ይችላል። ቤቱ ከአባታችን ሞት በኋላ ከእናታችን ጋር የምንገለገልበት እንጅ ተከራይቶ አያውቅም። ከሳሽ ከአከራካሪው ቤት ጐን በላዝ የተመራውን ቦታ አንድ ላይ በማድረግ የሟች አባታችንን ቤትና ቦታ አጠቃሎ ካርታ እና ፕላን አወጣበት እንጅ የእሱ አይደለም። ስለዚህ የወራሽነት ድርሻውን ከሚጠይቅ ውጪ የግል ነው በማለት ያቀረበው ክርክር ሐሰት ነው በማለት ተከራክረዋል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከሰማ በኋላ አከራካሪው ቤት የከሳሽ ለመሆኑ ከተከሳሽ በተሻለ አስረድተዋል በማለት በአብላጫ ድምጽ ተከሳሹ ቤቱን ለከሳሽ ላያስረክብ ይገባል በማለት ውሣኔ ሰጥቷል። በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ባለመስማማት ይግባኛቸው ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣የሰበር አቤቱታቸውን ደግሞ ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ተቀባይነት ሲያጡ ጉዳዩን ለዚህ ችሎት አቅርበው ይህ ችሎትም ግራ ቀኙን በመ/ አከራክሮ የበታች ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ውሳኔ በመሻር ጉዳዩ በአግባቡ ተጣርቶ ላወሰን ይገባል ሲል ላጣሩ የሚገባቸውን ነጥቦች ለይቶና ላቀርቡ የሚችሉትን ማስረጃዎችን ጭምር ጠቁሞ ጉዳዩን ለስር ፍርድ ቤት መልሶ ልኮለታል።
ጉዳዩ የተመለሰለት የምዕራብ ጐጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም እንደገና ግራ ቀኙን በመጥራት አለኝ የሚሉትን የሰውና የሰነድ ማስረጃ አስቀርቦ በመስማትና ለጉዳዩ አግባብነት አላቸው ያላቸውን የሰነድ ማስረጃዎችን ከሚመለከታቸው አካለት እንዲቀርቡና ማብራሪያም እንዲሰጥበት ጭምር ከአደረገ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ ከ660 ካ/ሜትር ቤትና ቦታ ውስጥ በ440 ካ/ሜትር ክልል ውስጥ ያለው ቤት የአሁኑ ተጠሪ አይደለም፣ 220 ካ/ሜትር ቦታ ግን ተጠሪ በላዝ የገዙት በመሆኑ የአሁኑ አመልካች ለቀው ላያስረክቡ ይገባል በማለት ወስኗል።
የአሁን ተጠሪ በዚህ ውሣኔ ቅር በመሰኘት ጉዳዩን በይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት አቅርበው ችሎቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሣኔ 440 ካ/ሜትር ቤትና ቦታ የአሁን ተጠሪ ስለመሆኑ በሰውም ሆነ በሰነድ ማስረጃ ከአሁኑ አመልካች ክርክርና ማስረጃ በተሻለ መልኩ ተረጋግጧል የሚል ድምዳሜ ይዞ የአሁን አመልካች ቤትና ቦታውን ሙሉ በሙሉ ለቀው ለተጠሪው ላያስረክቡ ይገባል፣ ያላግባብ ለተጠቀመበት የቤት ኪራይም በወር 2000.00 ታስቦ በድምሩ ብር 62,000 /ስልሳ ሁለት ሺህ ብር/አመልካች ለተጠሪ ላከፍሉ ይገባል በማለት ውሣኔ ሰጥቷል። ከዚህ በኋላ የአሁኑ አመልካች ለፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኛቸውን አቅርበው ችሎቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ አመልካች 440 ካ/ሜትር ቤትና ቦታ ጭምር እንዲለቁ መወሰኑ ባግባቡ ነው፣ የኪራይ ገንዘቡን በተመለከተ ግን ለተጠሪ ቀድሞ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያልወሰነው እና ጉዳዩ ከፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሲመለስም እንዲጣራ ያልታዘዘ በመሆኑ አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍሉ የሚወስንበት የዳኝነት አሰጣጥ ስርዓት የለም ብሎ በጉዳዩ ላይ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተሰጠውን ውሳኔ አሻሽሎ ወስኗል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- አከራካሪው ቤትና ቦታ የሟች አባታችን ለመሆኑ በተገቢው መንገድና ማስረጃ ተረጋግጦ እያለ የተጠሪው ነው ተብሎ እንዳስረክብ የተወሰነው ያለአግባብ ነው፣ተጠሪው አለኝ ያሉት የኑዛዜ ሰነድም የማስረጃ አቀራረብ ስርዓትን ተከትሎ ያልቀረበና ሕጋዊ አይደለም፣በጉዳዩ ላይ ዳኝነት የተሰጠው በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲጣሩ የተለዩት ነጥቦችንና ጉዳዩ ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከተመለሰ በኋላ ከሚመለከታቸው አካላት የቀረቡትን የሰነድ ማስረጃዎችን ባለገናዘበ መልኩ ነው የሚል ሁኖ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ እንዲሻር ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው። የሰበር አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉ ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው ቀርበው ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከለተው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም አመልካች 440 ካ/ሜትር ቤትና ቦታ ለተጠሪ ላለቁ ይገባል ተብሎ መወሰኑ ባግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ አግኝተናል።
በቅድሚያ ተጠሪ ጉዳዩ የፍሬ ነገር ክርክር ነው በማለት ያቀረቡትን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ተመልክተናል። በአመልካችና በተጠሪ መካከል ያለው ክርክር ከማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ጋር የተያየዘ ሲሆን በዚህ ችሎት ጉዳዩ የቀረበው ጉዳዩ በሕጉ አግባብ ተጣርቶ የተወሰነ መሆን ያለመሆኑንና የማስረጃ አቀራረብ ስርዓትን እንዲሁም የምዝና መርሁን ባገናዘበ መልኩ ነው። በመሆኑም ይህ ጭብጥ የፍሬ ነገር ማጣራት ወይም የማስረጃ ምዘና ጉዳይ ባለመሆኑ በዚህ ችሎት የማይታይበት አግባብ ስላላገኘን በዚህ ረገድ የቀረበውን የተጠሪን ተቃውሞ አልተቀበልነውም።
ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመለስም፡- ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው ይህ ችሎት ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ሲመልስ ላጣሩ የሚገባቸውን ነጥቦችን የለየ መሆኑን ነው።ይህ ችሎት ጉዳዩን ወደ ታች ሲመልሰው ለክርክሩ መነሻ የነበረውን ይዞታ ማነው የተመራው ፣ ቤቱን ማነው የሰራው፣በማን ገንዘብ ተሰራ የፅሁፍ ማስረጃዎችን በተመለከተ ካርታ በከሳሽ (የአሁን ተጠሪ) ስም የተሰጠ መሆኑ ከማስረዳት ባለፈ የከተማው አስተዳደርየቤቱንና የይዘታውን አመጣጥ በአግባቡ ያውቃል ተብሎ ስለሚገመት በስር ፍርድ ቤቱ በኩል ታዞ ተጨማሪ ማብራሪያዎችንእንዲሰጥበት ላደረግ እንደሚገባ፣ ማብራሪያ ከሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች መካከልም በከተማ አስተዳደሩ የነበረውን የማህደር ቁጥሩ 1224 የሆነውና በደጃዝማች አንለይ ሃይል ስም የነበረው/ የተከፈተው ለየትኛው ይዞታና ቤት ነበር የውሃና መብራት ውል በስማቸው ላዋዋሉ የቻሉበትን አግባብ እንድት እንደነበር፣ ከማህደሩ ውስጥ ጠፍቷል የተባሉት ገፆች እንድት ላጠፉ እንደቻሉ ፣ጠፍተውም ከሆነ መጥፋታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የጠፉት ገፆች ይዘታቸው ምን እንደነበር ያሁን ተጠሪ ካርታ 660 ካሬ ሜትር ላይ የወጣላቸው በአንድ ጊዜ ነው ወይስ አሁን ክርክር ካስነሳው ይዞታ ጎን የነበረውን 220ካሬ ሜትር ከተመሩ በኋላ ነው፣ አሁን ክርክር የተነሳበት ይዞታ ከ220 ካሬ ሜትር ጋር ተጠቃሎ የተሰራ ነው ወይስ አይደለም፣ ሒደቱስ እንድት ነበር የሚሉት ነጥቦች ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው ናቸው በማለት ዘርዝሯል እንዲሁም ሰበር ችሎቱ የግብር አከፋፈል ሂደቱ በተካራካሪዎች አባት ሲከፈል የነበረበትና በተጠሪም ሲከፈልበት የነበረበት አግባብ ላጠራ የሚገባው ነጥብ መሆኑን በመግለፅ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በባህርዳር ከተማ ገቢ ፅ/ቤት የባህር መዝገብ ተራ ቁጥር 202 በአባታቸው ስም ይገበር የነበረ በመሆኑ ቀርቦ ይታይልኝ በሚል ጥያቄ ቀርቦ ፍ/ቤቱ ስለማየቱ በፍርዱ ውስጥ የተባለ ነገር ባለመኖሩ ማስረጃው ቀርቦ ላታይ እንደሚገባ ለስር ፍርድ ቤት መመሪያ ሰጥቷል።ከዚህ በተጨማሪ ቤቱ ተሰራ ከተባለበት ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ ግራ ቀኙም ሆኑ ልሎች የቤተሰብ አባላት በተለይም እናትና አባት ከቤቱ ጋር ያላቸውና የነበራቸው ቁርኝት መታየትና መጣራት እንዳለበትም በውሳኔው ላይ አስፍሮ ጉዳዩን ለስር ፍርድ ቤት የመለሰለት መሆኑን ተረድተናል።
ከላይ የተመለከቱት ነጥቦች ይህ ችሎት በስር ፍርድ ቤት እንዲጣሩ የለያቸው ሲሆን የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩ ከተመለሰለት በኋላ ፍሬ ነገሩን ያጣራበትን መንገድ መመልከቱ ተገቢነት ይኖረዋል።
የስር ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ምስክሮች የሰማ ሲሆን በሥር ፍ/ቤት የተሰሙት የተጠሪ ምስክሮች ቤቱን ከ1961 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1965 ድረስ ባለው ጊዜ ተመርቶ የሰራው ተጠሪ መሆኑን፣ ቤቱን ሲሰራም ከተለያዩ ሰዎች ገንዘቡን ተበድሮ መስራቱን የሚያውቁ መሆኑን አስረድተው ቤቱን ሰርቶ ከጨረሰ በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲሄድ አባቱ እንዲኖሩበት ፈቅዶላቸው ይኖሩበት እንደነበር፣ በዚሁ ሁኔታ ውሀና መብራት በእሳቸው ስም መግባቱን መስክረዋል። ባንቺ ዓለም አንለይ የተባለችው የግራ ቀኙ እህት በሰጠችው ምስክርነትም ቤቱ የታላቅ ወንድማችን የቴዎድሮስ አንለይ ነው፣ አባታችን በሕይወት እያሉ ሁሉን ነገር ያንቀሳቅሱ የነበሩ እሳቸው ናቸው፣ በኑዛዜያቸውም ቤቱን የተጠሪ መሆኑን ገልፀዋል፣ እሳቸው በ1990 ዓ.ም ከሞቱ በኋላ ቤቱ በብር 2000 ተከራይቶ ነበር፣ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ቤቱ በአሁኑ አመልካች ይዞታ ስር መቆየቱንም ሁሉም ምስክሮች አስረድተዋል። የአመልካች ምስክሮች በበኩላቸው ቤቱን የሰሩት የግራ ቀኙ አባት ደጃዝማች አንለይ ኃይል ናቸው፣ ቦታውን የተመሩት ደግሞ በተጠሪው ስም ነው፣ ግብር ይከፈል የነበረው ደግሞ በደጃዝማች አንለይ ስም ነበር በማለት መመስከራቸውን የውሳኔው ግልባጭ ያሳያል።
ከክፍሉ ማዘጋጃ ቤት የቀረበው የሙያ ምስክር የሰጠው ምስክርነትም የደጃዝማች አንለይ በልጃቸው ቴዎድሮስ አንለይ ስም ቦታ ተመርተው በራሳቸው ስም ሲገብሩ ቢኖሩም በኋላ ግን ቦታው በስሙ በተመራው ልጃቸው /በተጠሪ ስም/ ግብሩ ተስተካክሎ ሲገበር መቆየቱን፣ በፊት የነበረው ቦታ 440 ካሬ ሜትር ሲሆን በኋላ 220 ካሬ ሜትር ቦታ ላዝ ገዝቶ ጨምሮበት 660 ካሬ ሜትር ቦታ በተጠሪ ስም ተጠቃሎ መስጠቱን መግለጹን የስር ፍርድ ቤት መዝግቧል።
የስር ፍርድ ቤት በሰነድ ማስረጃነት ያስቀረበው የባህር ዳር ከተማ አስተዳዳር ገቢዎች ጽ/ቤት ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ ቁጥር አዘል ደብዳቤ በባህር መዝገብ ቁጥር 202 በሆነ ግብር በተጠሪው ስም የማይገበር መሆኑንና መዝገቡ በደጃዝማች አንለይ ኃይል ስም መሆኑን የሚያሳየውን ሰነድ፣ በባህር ዳር ከተማ ውሀና ፍሳሽ አገልግሎት ጽ/ቤት ጥቅምት 10 ቀን 2004 ዓ.ም. በተፃፈ ቁጥር የያዘ ደብዳቤ ውሀ የገባው በደጃዝማች አንለይ ኃይል ስም መሆኑንና በመሥሪያ ቤቱ አሰራር ውሀ በስም ለማስገባት የሚቻለው ባለይዞታ መሆኑን ገልፆ በወቅቱ ደጃዝማች አንለይ ባለይዞታ ስለሆኑ ውሃው የገባላቸው መሆኑን በማረጋገጥ የሰጠው ሰነድ፣በባህር ዳር ከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት ጥቅምት 10 ቀን 2004 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የማህደር ቁጥር 1224 የሆነውን በደጃዝማች አንለይ ኃይል ስም የነበረው ቦታ የሚያሳየው የተለያዩ ቦታዎችን ከሰዎች መግዛታቸውን፣ ይሁን እንጂ እነዚህ ቦታዎች የተወረሱባቸውና በተለያየ ምክንያት የፈረሱ መሆኑን፣ ህዳር 19 ቀን 1984 ዓ.ም በፃፉት ማመልከቻ ቦታ እንዳልላቸውና በልጃቸው በቴዎድሮስ አንለይ ቤት በጢሰኝነት እንደሚኖሩና ቦታ እንዲሰጣቸው ያመለከቱበት ማመልከቻ መኖሩንና አቶ ቴዎድሮስ ፋይል ላይ ደግሞ ግንቦት 11 ቀን 1992 ዓ.ም በተዘጋጀ ሳይት ፕላን ባህር ዳር ከተማ 08 ቀበል የ440 ካሬ ሜትር ቦታ እንደነበራቸውና 220 ካሬ ሜትር ቦታ በላዝ ጠይቀው ከሚያዚያ 24 ቀን 1993 እስከ ግንቦት 02 ቀን 1993 ዓ.ም እንዲወስዱ ተወሰኖላቸው የ660 ካሬ ሜትር ቦታ ካርታ መውሰዳቸውን የሚገልፅ ሰነድ ፣ የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በባህር ዳር ዲስትሪክት ቁጥር 2 አገልግሎት ማዕከል ጥቅምት 06 ቀን 2004 ዓ.ም የተፃፈ ደብዳቤ መብራት በደጃዝማች አንለይ ኃይል ስም መግባቱን የሚያሳይ ሰነድ፣ የባህር ዳር ከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት ጥቅምት 26 ቀን 2001 ዓ.ም የፃፈው ደብዳቤ በደጃዝማች አንለይ ኃይል ስም ይገበርበት የነበረ ምንም ዓይነት ካርታና ፕላን የለም ሲል የገለጸበት ሰነድ፣የባህር ዳር ከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት ጥቅምት 07 ቀን 2001 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ አከራካሪው ቤትና ቦታ በአቶ ቴዎድሮስ አንለይ ስም በካርታ /93 በፋይል ቁጥር 291 ተመዝግቦ የሚገኝ መሆኑን እንደሚያሳይ የገለፀበት ሰነድ ናቸው። ከእነዚህ የሰነድ ማስረጃዎች በተጨማሪ የስር ፍርድ ቤት በማስረጃነት የያዘው ሰነድ የአሁኑ ተጠሪ ጉዳዩ ወደ ስር ፍርድ ቤት ከተመለሰ በኋላ አገኘሁ ብለው በተጨማሪ ማስረጃነት እንዲታይላቸው ያቀረቡት ሰነድ ሲሆን ይህም ሟች ደጃዝማች አንለይ ኃይል መስከረም 06 ቀን 1984 ዓ.ም. አደረጉ የተባለው ኑዛዜ ሁኖ ለጉዳዩ አግባብነት አለው የተባለው የኑዛዜው ክፍል ሟቹ "…..አሁን ያለንበት መኖሪያ ቤት በልጄ በቴዎድሮስ አንለይ ስም የተሰራ ነው፣ቤቱም የተሰራበት ቦታ በራሱ ስም የተገኘና የተያዘ ሥለሆነ ቤቱን ከነቦታው መረከብ ይችላል…." በማለት ማስፈራቸውን ያሳያል ተብሎ በስር ፍርድ ቤቶች ተመዝግቧል። ከዚህ የሰውና ሰነድ ማስረጃ መገንዘብ የሚቻለው በአከራካሪው ቤትና ቦታ ውሀና መብራት በደጃዝማት አንለይ ኃይል ስም መግባቱንና በቤቱም ውስጥ እየኖሩ ግብር በህይወት እስከነበሩ ድረስ በእሳቸው ስም ይገበሩ የነበረ መሆኑን ሲሆን የቤቱን ካርታ እና ፕላን ግን በእሳቸው ስም የተመዘገበ አለመሆኑንና በተጠሪው ስም የተመዘገበ መሆኑን ነው።በተጠሪው ስም የተመዘገበበት ጊዜ በ1993 ዓ/ም ስለመሆኑ ክርክር የቀረበበት የፍሬ ነገር ነጥብ አይደለም።ይህ ምዝገባ የተከናወነው ቦታው በተጠሪው ስም የተመራ ነው በሚል ምክንያት ስለመሆኑ ማዘጋጃ ቤቱ የሚከተለውን አሰራርን መሰረት በማድረግ ለስር ፍርድ ቤቱ ማብራሪያ እንደሰጡ የቀረቡት ሰራተኞች ከሰጡት የምስክርነት ቃል መገንዘብ የሚቻል ቢሆንም በቤቱ ማህደር ውስጥ ሰነዶች እንደነበሩ ሳይካድ ሰነዶቹ የጠፉት ህጋዊ ምክንያት ግን በማስረጃ ያለመረጋገጡን የክርክሩ ሂደት ያሳያል። ማዘጋጃ ቤት ያለው የቤቱ ማህደር የአመልካችን አባት ስም የማይጠቀስ ነው የተባለ ቢሆንም ተመሳሳዩን ቤትና ቦታ በተመለከተ በግብር አስገቢው መስሪያ ቤት ይገኛል የተባለው ማህደር ደግሞ የአሁኑን ተጠሪ ስም የማይገልፅ፣ይልቁንም የሟች ደጃዝማች አንለይ ኃይልን ስም የሚገልፅ መሆኑን የሚመለከተው አካል ለፍርድ ቤቱ አረጋግጦ ልኳል።ይህ ማህደር ሰነዶቹ የጠፉት ስለመሆኑ በተጠሪ ክርክር ያልቀረበበትና ሕጋዊ ተቀባይነቱም ጥያቄ ውስጥ ያልገባ የሰነድ ማስረጃ መሆኑን ክርክሩ በግልጽ ያሳያል።
በመሰረቱ አንድ ሰው በፍ/ብ/ህ/ቁ 1195 ድንጋጌ መሰረት የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብትነትን በማወቅ በአስተዳደር ክፍልየምስክር ወረቀት ሲሰጥ የምስክር ወረቀቱን ያገኘው ሰው የማይንቀሳቀሰው ንብረት ባለሃብት ሁኖ ላገመት እንደሚገባ ተመልክቷል። ይህ ድንጋጌ በግልጽ የሚያሳየው በአስተዳደር አካሉ የሚሰጥ ማስረጃ የመብቱ ባለቤት የሆነውን ሰው ለመለየት ግምት የሚወስድበት እንጂ አሳሪ ወይም ድምዳሜ ማስረጃ /conclusive evidence/ ያለመሆኑን ይልቁንም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1196 ስር በተመለከቱት ውስን ምክንያቶች አግባብ ላሰተባበል የሚችል ሕጋዊ ግምት /rebuttable legal presumption/ መሆኑን ነው። በመሆኑም በፍ/ብ/ህ/ቁ 1195 ስር የተመለከተው የህግ ግምት ፍጹም የሆነ ወይም ድምዳሜ ማስረጃ ሳይሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1196 ስር የተመለከቱት ሁኔታዎች ስለመኖራቸው በማናቸውም ማስረጃ በማረጋገጥ ላስተባብል የሚችል የሕግ ግምት ነው። በመሆኑም አንድ ስው በአስተዳደር አካል የተሰጠ ካርታ በመያዙ ብቻ በካርታው የተጠቀሰው የማይንቀሳቀስ ንብረት ህጋዊ ባለሃብት እንደሆነ ህጉ ግምት ቢወስድለትም ይህ ግምት ግን ካርታው የተሰጠበትን አግባብ ከደንቡ ከአስራሩና ከሰልጣኑ ውጪ እንዲሁም በማይረጋ የምስከር ወረቀት መሰረት ማስረጃው ተሰጥቶ ከሆነ ይህንኑ በማናቸውም ማስረጃ በማረጋገጥ የህጉን ሕላናዊ ግምት ማፍረስ እንደሚቻል ፍ/ብ/ሕ/ቁ 1196 ድንጋጌ በግልጽ ያሳያል። ይህንኑ የህጉን ይዘትና መንፈስ ካርታው ከመሰረዝ ጋር አስተሳስረን ስንመለከተውም አንድ የአስተዳደር አካል በሕጉ አግባብ የተሰጠን የባለቤትነት ማስረጃ በሕጉ የተመለከቱት ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ዋጋ አልባ የሚያደርገው ሕጋዊ አግባብ የልለ መሆኑን በቀላሉ የምንረዳው ጉዳይ ነው። አንድ ሰው በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የባለቤትን መብት አቋቁሟል ለማለት የሚቻለው በህግ አግባብ የተገኘውን ማስረጃ መሰረት አድርጎ የመፋለም ክስ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት አቅርቦ በጉዳዩ የሚቀርቡት ማስረጃዎች በሕጉ የተዘረጋውን የማስረጃ አቀራረብ ስርዓት ተከትለው ሲቀርቡና ማስረጃዎቹ ለጉዳዩ ተፈጻሚነት ባለው የማስረጃ ምዘና መርህ መሰረት ክሱን ማስረዳታቸው ሲረጋገጥ ነው።
ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ ተጠሪ በ1993 ዓ/ም ከአስተዳደር አካሉ የባለቤትን ማረጋገጫ ደብተር አግኝተዋል ተብሎ ማስረጃው መቅረቡ በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1195 መሰረት ማስረጃው የተሰጠበትን ንብረት ባለሃብት ናቸው ተብሎ የሚገመቱት ተጠሪ ናቸው ተብሎ ግምት ለመውሰድ የሚያስችል ቢሆንም የክርክሩ ልዩ ባህርይ ሲታይ በተለይም የአከራካሪው ቤት ማህደር ውስጥ ነበሩ የተባሉ ሰነዶች ከጠፉ በኋላ ማስረጃው ለተጠሪ መሰጠቱ በፍሬ ነገር ደረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ ተጠሪ አለኝ በማለት ያቀረቡት ይኼው የባለቤትነት የምስክር ወረቀት ሕጋዊ ተቀባይነት እንዲሰጠው የማያደርገው ሁኖ እያለ የበታች ፍርድ ቤቶች አመልካች ይህንን ለማስተባበል በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1196 በተደነገገው አግባብ ለተጠሪውየተሰጠው የባለቤትነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ከደንብ ውጪ በሆነ አሰራር ወይም ሥልጣን በልለው አስተዳዳር ክፍል ስለመሆኑ በሰውም ሆነ በሰነድ ማስረጃው ያስረዱት ነገር የለም በማለት መደምደማቸው በክርክሩ ሂደት የቀረቡትን ሁሉንም ማስረጃዎች ያገናዘበ ሁኖ አልተገኘም። ሟች ደጃዝማች አንለይ ኃይል ግብር በስማቸው መገበራቸው ወይም ውሃና መብራት በስም ማስገባታቸው ከሚመለከታቸው አካላት በቀረቡት ማስረጃዎች የተረጋገጠ ሲሆን እነዚህ ማስረጃዎች በአመልካችና በተጠሪ መካከል አይነት በተነሳው ክርክር የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነትን ለማረጋገጥ አይችሉም ተብሎ ማስረጃዎቹ ውድቅ የሚሆኑበት የማስረጃ ምዝና መርህ የለም። የበታች ፍርድ ቤቶች የባህር ዳር ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽ/ቤት ውሃ በስም ላገባ የሚችለው የይዞታ ባለቤትነት ሲረጋገጥ ነው በማለት የሰጠውን የሰነድ ማስረጃም በደፈናው በምን እንዳረጋገጠው የገለፀው ነገር ባለመኖሩ የሰጠው ማረጋገጫ ተቀባይነት አለው ብሎ ለመውሰድ የሚቻል አይደለም በማለት ከማለፋቸው በስተቀር የመስሪያ ቤቱ የተለመደ አሰራር አለመሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲቀርብ ያላደረጉ በመሆኑ ማስረጃው ተቀባይነት ያጣበት አግባብ ሕጋዊ ምክንያትን መሰረት አድርጎ አለመሆኑን ተገንዝበናል።
ከዚህ በተጨማሪ አመልካች አጥብቀው የሚከራከሩት ቤትና ቦታው የሟች አባታችን ነው በማለት ሲሆን ሟች አባታቸው መስከረም 06 ቀን 1984 ዓ.ም ባላደረጉትና ስርዓቱን ጠብቆ ባልቀረበው የኑዛዜ ሰነድ ክርክር ያስነሳው ቤት የተጠሪ ነው መባሉ ያላግባብ ነው በሚል ነው።
የስር ፍርድ ቤቶች ይህ የኑዛዜ ሰነድ ለማስረጃነት የቀረበበትን አግባብ በውሳኔውአቸው ላይ በግልጽ ባያሰፍሩም የአሁኑ ተጠሪ በዚህ የሰበር ደረጃ በዚህ ረገድ የሚያቀርቡት ክርክር ሰነዱ ቀድሞ ላገኝ ባለመቻሉ የቀረበና ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን ለስር ፍርድ ቤት ሲመልስም ጉዳዩ አግባብነት ባላቸው ልሎች ማስረጃዎች ጭምር እንዲጣራ ብሎ ስለአዘዘ ማስረጃው መቅረቡ ተገቢ ነው በሚል ነው። ይሁን እንጂ ይህ ችሎት የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን አግባብነት ባላቸው ማስረጃዎች ሁሉ አጣርቶ እንዲወስን በማለት የሰጠው ውሳኔ ስለማስረጃ አቀራረብ በህጉ የተመለከቱትን ድንጋጌዎችን ሁሉ ባላገናዘበ መልኩ ማስረጃው እንዲቀርብ በማሰብ ነው ተብሎ ላወሰድ የሚገባ አይደለም። በመሆኑም ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸው ማስረጃዎች መቅረብ ያለባቸው በሕጉ የተዘረጋውን ስርዓት ጠብቀው ላሆን ይገባል። ከዚህ አንጻር ተጠሪ አለኝ የሚሉትን የኑዛዜ ሰነድ በተመለከተ ለማስረጃነት ያቀረቡት ጉዳዩ ከዚህ ችሎት ከተመለሰ በኋላ ሲሆን ሰነዱ በማስረጃነት እንዲቀርብ የጠየቁበት አግባብም ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 137(3) እና 256 ድንጋጌዎች ይዘት ጋር የተገናዘበ መሆኑን ያረጋገጡት ነገር የልለ መሆኑን የክርክሩ ሂደት ያሳያል። የተጠሪ ምስክር የሆኑት እህታቸው ቀድሞ ክርክሩ ላይ የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን በዚህ ጊዜ ስለኑዛዜ ሰነዱ የሰጡት የምስክርነት ቃል ሳይኖር ጉዳዩ ወደ ዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲመለስ ቤቱ የተጠሪ መሆኑን ሟች ደጃዝማች በኑዛዜ አረጋግጠውላቸዋል የሚለው ምስክርነታቸው ቀድሞውንም ኑዛዜ መኖሩ ይታወቅ የነበረ መሆኑን የሚያሳይ ምስክርነት ነው ላባል የሚችልና ተጠሪ ሰነዱን በጊዜው ተገቢውን ጥረት አድርገው ማቅረብ ይችሉ የነበረ፣ ማቅረብ የማይችሉበት ምክንያት ካለውም ይህንኑ ለፍርድ ቤቱ ማሳወቅና በልላ አግባብ ማስረዳት ይችሉ የነበረ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው። በመሆኑም የኑዛዜው ሰነድ ለማስረጃነት የቀረበበት አግባብ ከተጨማሪ ማስረጃ አቀራረብ ስርዓት ውጪ ነው። በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች ሰነዱን ውድቅ ማድረግ ሲገባቸው ሟቹ በኑዛዜው ላይ ቤቱ የልጅ ቴዎድሮስ አንለይ በስሙ ቦታ ተመርቶ የሰራው ስለሆነ ቤቱ ከነቦታው መረከብ ይችላልብለው ማስፈራቸውን፣የኑዛዜው ቃል ይዘት ቤቱ የሟች ነው ተብሎ አሁን የተከሰተው ዓይነት ክርክር እንዳይፈጠር አስቀድመው አስበው ያደረጉት መሆኑን ነው በሚል ምክንያት ሰነዱ የማስረጃነት ዋጋ መስጠታቸው ተገቢነት የልለውን የማስረጃ አቀራረብ ስርዓት ተፈጻሚ በማድረግ የደረሱበት ድምዳሜ በመሆኑ በሕግ ተቀባይነት ላሰጠው የማይገባ ሁኖ አግኝተናል።
ሲጠቃለልም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትና የፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አከራካሪው 440 ካ/ሜትር ቤትና ቦታ የተጠሪ ሃብት ነው በማለት የሰጡት ውሳኔ ጉዳዩ እንዲጣራ ሲመለስ በክርክሩ ላይ በህግ አግባብ የቀረቡትን የሰነድ ማስረጃዎችን ይዘት ከክርክሩ ልዩ ባህሪና ተገቢነት ካለው የማስረጃ ምዘና መርህ ጋር ባለማገናዘብ ሁኖ ስለአገኘው በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሁኖ አግኝተናል። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስናል።
ው ሣ ኔ
የአማራ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ቁ. 34051 የካቲት 20 ቀን 2005 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተሰጥቶ በፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ ታህሳስ 02 ቀን 2006 ዓ/ም ተሻሽሎ የጸናው ውሣኔ በፍ/ብ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ. 348/1/ መሰረት ተሻሽሐል።
የምዕራብ ጎጃም አስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ግንቦት 30 ቀን 2004 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሐል።
አመልካች 440 ካ/ሜትር ቤትና ቦታ ለተጠሪ ላያስረክቡ ይገባል የተባለው የውሳኔ ክፍል ተሽሯል። አመልካች ብር 62,000 /ስልሳ ሁለት ሺህ ብር/ የቤት ኪራይ ለተጠሪ ላከፍሉ አይገባም፣ 220 ካ/ሜትር ቦታ ላለቁ ይገባል ተብሎ የተሰጠው የውሳኔ ክፍል ፀንቷል።
ለክርክሩ የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
ተጠሪ በውርስ አግባብ አለኝ የሚሉትን መብት ከመጠየቅ ይህ ውሳኔ አያግዳቸውም ብለናል።
በዚህ ችሎት መጋቢት 08 ቀን 2006 ዓ.ም ተሰጥቶ የነበረው የአፈፃፀም ዕግድ ተነስቷል።
ይፃፍ። መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ ብለናል።
No specific laws extracted.
No topics extracted.