No summary available.
ቀን መስከረም 26/2009 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወላ ተፈሪ ገብሩ አብርሃ መሰለ አብዬ ካሳሁን እትመት አሰፋ አመልካቾች፡-
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የውርስ ሐብት ክርክርን የሚመለከት ነው። ክርክሩ የተጀመረው በመኢሶ ወረዳ ፍ/ቤት ነው። በስር ፍ/ቤት ተጠሪዎች አመልካቾች፤ የአሁን አመልካቾች ደግሞ እንደየቅደም ተከተላቸው 5ኛ እና 3ኛ ተጠሪ በመሆን ተከራክረዋል። አመልካቾች በስር ፍ/ቤት ያቀረቡት ክስ ይዘት የሟች አባታቸው አቶ ደበበ ግዛው የውርስ ሐብት እንዲጣራ ዳኝነት የጠየቁ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።
የአሁን 1ኛ አመልካች ለቀረበባቸው ክስ በሰጡት መልስ ከሟች ጋር በ 1973 ዓ.ም ጋብቻ ፈጽመው አብረው የኖሩ እና ንብረት ያፈሩ መሆኑን በመግለጽ ከሟች ጋር በጋብቻ አብረው በነበሩበት ጊዜ ያፈሯቸው ንብረቶች እንዲጣሩላቸው ጠይቀዋል። የአሁን 2ኛ አመልካችም በሰጡት መልስ ሟች አቶ ደበበ ግዛው አባታቸው መሆናቸውን በመግለጽ የግል ንብረታቸው የሆነው መኖሪያ ቤት፤ የእህል ወፍጮ ቤት እና በአንድ ግቢ ውስጥ የሚገኝ መጋዘን ከውርስ ሐብት ጋር እንዳይቀላቀል በማለት ተከራክረዋል። ጉዳዩን በመጀመሪያ የተመለከተው ፍ/ቤት ውርስ አጣሪ በመሾም ውርሱ እንዲጣራ አድርጓል።
በውርስ አጣሪ የቀረበለትን ሪፖርት ከመረመረም በኋላ የውርስ ሐብት ናቸው በማለት በተለያዩ ንብረቶች ላይ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ለዚህ የሰበር አቤቱታ ምክንያት የሆነውን ንብረት በተመለከተ፡- በመኢሶ ከተማ ውስጥ የሚገኝ መኖሪያ ቤት ወፍጮ ቤት እና መጋዘን በ 2ኛ አመልካች ስም የተዘዋወረ ቢሆንም 2ኛ አመልካች ገቢ የላላት መሆኑ እና እንዳልሰራችው ፣ ሟች ይህን ንብረት የሰራው መሆኑን ፍ/ቤቱ የተገነዘበ በመሆኑ እነኝህ ንብረቶች የውርስ ሐብት ናቸው። ሟች በሕይወት እያለ የጣለት ብር 54,000 /ሃምሳ አራት ሺህ/ የእቁብ ገንዘብ 1ኛ አመልካች የወሰዱት እና ገንዘቡም የውርስ ሐብት በመሆኑ እንዲመልሱ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል።
ግራቀኙ በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘታቸው ይግባኝ ለምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት አቅርበዋል። ይግባኙ የቀረበለት ፍ/ቤት ግራቀኙ ያቀረቡትን ይግባኝ አጣምሮ ከመረመረ በኋላ 1ኛ አመልካች የሟች ባለቤት በመሆናቸው እና ንብረቱም በጋብቻ ጊዜ የተፈራ በመሆኑ የ 1ኛ አመልካች ድርሻ ከወጣ በኋላ ቀሪው ድርሻ የወራሾች ነው፤ በ 2ኛ አመልካች ስም ተመዝግቦ የሚገኘው በመኢሶ ከተማ ውስጥ የሚገኝ መኖሪያ ቤት ወፍጮ ቤት እና መጋዘን የ 2ኛ አመልካች ስለመሆኑ በቂ እና አሳማኝ ማስረጃ ስለላላቸው እነዚህ ንብረቶች የሟች አቶ ደበበ ግዛው እና የ 1ኛ አመልካች የጋራ ሐብት ናቸው፤ ከዕቁቡ ገንዘብ ብር 54,000 /ሐምሳ አራት ሺህ/ ላይ ግማሹ የ 1ኛ አመልካች ድርሻ፤ ቀሪው የውርስ ሐብት ነው በማለት የስር ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ በማሻሻል ውሳኔ ሰጥቷል።
አመልካቾች በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በተሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችልት ቅሬታ ያቀረቡ ቢሆንም አቤቱታቸው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 337 መሰረት በትእዛዝ ተሰርዟል። በመቀጠልም አመልካቾች ለክልለ ሰበር ሰሚ ችልት ያቀረቡት አቤቱታ በበታች ፍ/ቤቶች የተፈጸመ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለም በማለት በትእዛዝ ውድቅ ተደርጓል። የሰበር አቤቱታው የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ ለማስለወጥ ነው።
የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ሟች በአካባቢው ማህበረሰብ ከነበራቸው ታዋቂነት እና ማህበራዊ ደረጃ የእቁብ ገንዘቡ ለሟች የቀብር ስነ-ስርዓት የወጣ ሆኖ ሳለ ግማሹ የውርስ ሃብት ነው መባለ እና ሟች ከሞተ በኋላ የተከፈለው የእቁብ ገንዘብ እንደ ውርስ እዳ አለመያዙ ተገቢ አይደለም። መኖሪያ ቤቱን ወፍጮ ቤቱን እና መጋዘኑን በተመለከተ የተሰጠው ውሳኔ ሕጉ ስጦታ ወደ ውርስ የሚመለስበትን ስርዓት አስመልክቶ ያስቀመጠውን ድንጋጌ ያላገናዘበ በመሆኑ ውሳኔው መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው የሚል ነው። የሰበር አቤቱታው ተመርምሮ 2ኛ አመልካች ሟች አባታቸው በሕይወት በነበሩ ጊዜ ያገኙትን በውርሱ ውስጥ ይቀላቅለ የመባላቸውን አግባብነት ከፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1065 እና 1076/2 ድንጋጌ አኳያ ለመመርመር ሲባል አቤቱታ በዚህ ችልት እንዲታይ ተደርጓል። ለተጠሪዎችም ጥሪ ተደርጎ ግራቀኙ በጽሐፍ እንዲከራክሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለ መልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችልትም የግራቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መርምሮታል። እንደመረመረውም የዚህን ችልት ምላሽ የሚያስፈልገው አብይ ነጥብ የበታች ፍ/ቤቶች ሟች በሕይወት እያለ ለ 2ኛ አመልካች የተላለፈው መኖሪያ ቤት፣ ወፍጮ ቤት እና መጋዘን የውርስ ሐብት ነው በማለት ከውርስ ሐብት ጋር በመቀላቀል መወሰናቸው በአግባቡ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነው።
በመኢሶ ከተማ የሚገኘው መኖሪያ ቤት፣ ወፍጮ ቤት እና መጋዘን ሟች በልጃቸው በ 2ኛ አመልካች ስም ያዘዋወሩት እና ያስመዘገቡት መሆኑ ፍሬ ነገርን የማጣራት እና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ባላቸው የበታች ፍ/ቤቶች ተረጋግጧል። ስለሆነም የበታች ፍ/ቤቶች 2ኛ አመልካች ንብረቱን ወደ ውርስ ሐብት እንዲያስገቡ የሰጡት ተገቢ ነው። አከራካሪው ጉዳዩ 2ኛ አመልካች ንብረቱን ወደ ውርሱ የሚያስገቡበት ስርዓት እንድት ሉፈጸም ይገባል? የሚለው ነው። የጋራ ወራሾች ንብረት የሚመልሱበት ስርዓት በፍ/ብ/ሕ/ቁ.
1065-1078 ባለት ድንጋጌዎች ተደንግጓል። ሟች ከመሞቱ በፊት በሟች ፈቃድ ንብረት የተላለፈለት ወራሽ የተላለፈለትን ንብረት ወደ ውርስ ሐብት የሚመልሰው ንብቱን በዓይነት ሳይሆን የንብረቱን ዋጋ ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1065 እና 1074/1 ድንጋጌ ጣምራ ንባብ ያስገነዝባል። ይህ የሰበር ሰሚ ችልትም በተመሳሳይ ጉዳይ በመ.ቁ. 80920 በአዋጅ 454/97 አንቀጽ 2/1 መሰረት በየትኛውም ደረጃ ለሚገኙ ፍ/ቤቶች አስገዳጅ የሆነ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል። የበታች ፍ/ቤቶች በተዘረጋው የሕግ ስርዓት መሰረት 2ኛ አመልካች ንብረቱን ወደ ውርሱ የሚያስገቡበትን ስርዓት በውሳኔው ላይ መግለጽ ሲኖርባቸው ይህን ሳያደርጉ የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አግኝተነዋል። በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
348/1/ መሰረት ተሻሽሎል።
2ኛ አመልካች በመኢሶ ከተማ የሚገኘውን መኖሪያ ቤት፤ ወፍጮ ቤት እና መጋዘን በአይነት የመመለስ ግድታ የላለባቸው በመሆኑ የንብረቱን ግምት ይመልሱ ብለናል።
የንብረቱ ግምት በመኢሶ ወረዳ ፍ/ቤት በመ.ቁ. 06725 በተያዘው የአፈጻጸም ክርክር ታይቶ ይወሰን ብለናል።
በዚህ መዝገብ የተሰጠው የአፈጻጸም እግድ ተነስቷል።
የዚህ ውሳኔ ግልባጭ የስር ፍ/ቤቶች እንዲያውቁት ይድረሳቸው።
በዚህ ችልት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪ እና ኪሳራ ግራቀኙ የየራሳቸውን ይቻለ።
No topics extracted.