No summary available.
የሰ/መ/ቁ/ - 136024 ጥቅምት 21 ቀን 2010ዓ.ም ዳኞች፡- ዳኜ መላኩ ተፈሪ ገብሩ ቀነዓ ቂጣታ ተሾመ ሽፈራዉ ፀሐይ መንክር አመልካች፡- አቶ ቢልልኝ ጌታነህ - ጠበቃ ፋንታሁን አባተ ቀርበዋል ተጠሪ፡- አቶ ገብራይ ተከስተ - አልቀረቡም **
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የተጀመረዉ በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን፣ የአሁን ተጠሪ በአመልካች ላይ ባቀረበዉ ክስ፤ የወፍጮ ድርጅቱን በዉስጡ ካሉት ሦስት የተለያየ የፈረስ ጉልበት ካላቸዉ ወፍጮዎች እና ሚዛን ጋር በወር ብር 7,000.00 ኪራይ እየከፈለ ከ26/11/2004 እስከ 26/11/2006 ዓ.ም ድረስ እንዲጠቀምበት ለአመልካች ማከራየቱን እና የኪራዩ ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላም አመልካች የወፍጮ ድርጅቱን ከነሙሉ ዕቃዉ አለማስረከቡን እና ቀሪ የኪራይ ገንዘብም ያልከፈለዉ መሆኑን በመግለጽ አመልካች ወፍጮዎቹን፣ የወፍጮ ድርጅቱን እና ሚዛኑን እንዲመልስለት፣ እንዲሁም የዉሉ ጊዜ ካለቀ በኋላ ክሱ እስከቀረበበት ቀን ድረስ ያለዉን የኪራይ ገንዘብ ብር 21,000.00 እና ወፍጮዎቹን እስኪረከባቸዉ ድረስ ያለዉ የድርጅቱ ኪራይ ታስቦ እንዲከፍለዉ ይወሰንለት ዘንድ የጠየቀዉን ዳኝነት መነሻ ያደረገ ነዉ።
አመልካች በበኩሉ ተጠሪ ለክሱ መሰረት ያደረገዉ ዉል በ25/12/04 ዓ.ም በተደረገ ልላ ዉል መተካቱን እና በኋለኛዉ ዉል መሰረትም የዉሉ ጊዜ እስከ 25/12/06 ዓ.ም የሚቆይ በመሆኑ ተጠሪ ድርጅቱን እንዲለቅለት ከፈለገ የሦስት ወር ጊዜ መስጠት ስላለበት የመጠየቂያ ጊዜዉ ያልደረሰ መሆኑን፣ በወር ለመክፈል የተስማማዉ ኪራይም ብር 7,000.00 ሳይሆን ብር 350.00 መሆኑን እና ጊዜዉ ሲደርስ ወፍጮዎቹን ከነሚዛኑ ለተጠሪ እንደሚያስረክብ በመግለጽ ተከራክሯል።
ጉዳዩ በመጀመሪያ የቀረበለት የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም በዚህ መልኩ የቀረበዉን የግራ ቀኝ ክርክር ከሰማ በኋላ፤ በኋላ ላይ ተደርጓል የተባለዉ ዉል በህግ አግባብ የመጀመሪያዉን ዉል የተካ አለመሆኑን በመግለጽ አመልካች ወፍጮዎቹን እንዲመልስ፣ እንዲሁም ከነሐሴ ወር 2006 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 08 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ያለዉን ኪራይ .00 ለተጠሪ እንዲከፍል ሲል ወስኗል። ተጠሪ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበ ሲሆን፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የወፍጮ ድርጅቱ እንዲታሸግ የተደረገዉ በአመልካች ጥፋት ምክንያት መሆኑን በመግለጽ ከታህሳስ 09 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 10 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ ያለዉን የኪራይ ገንዘብ .00 አመልካች ለተጠሪ እንዲከፍል በማለት ወስኗል። አመልካች በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ለፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበዉ ይግባኝም ተቀባይነት አላገኘም።
ይህ የሰበር አቤቱታ የቀረበዉም ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የሰጠዉን ዉሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ሲሆን፣ አመልካች በቀን 28/04/09 ዓ.ም ተዘጋጅቶ በጠበቃዉ አማካይነት በቀረበዉ የሰበር አቤቱታ፤ የወፍጮ ድርጅቱ ከታህሳስ 09 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ አገልግሎት እንዳይሰጥ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታሽጎ እንዲቆይ ተደርጎ እያለ ለእነዚህ ጊዜያት ኪራይ እንዲከፈል በከፍተኛ ፍርድ ቤት ተወስኖ በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በትዕዛዝ የፀናዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆኑን ገልፆ ታርሞ እንዲወሰንለት ጠይቋል።
መዝገቡ ተመርምሮም የወፍጮ ቤት ድርጅቱ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታሽጎ በነበረበት ወቅት ያለዉን ኪራይ አመልካች እንዲከፍል የመወሰኑን አግባብነት ግራ ቀኝ በተገኙበት ለማጣራት ሲባል ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ በመደረጉ፣ ተጠሪ ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ጥሪ ተደርጎለታል። በዚህም መሰረት ተጠሪ በቀን 20/06/09 ዓ.ም በጠበቃዉ አማካይነት ተዘጋጅቶ በቀረበ መልስ፤ ወፍጮ ቤቱ ላታሸግ የቻለዉ በአመልካች እምቢተኝነት ምክንያት በመሆኑ ድርጅቱ ታሽጎ ለቆየባቸዉ ጊዜያት ጭምር አመልካች ኪራዩን እንዲከፍል የተሰጠዉ ዉሳኔ በአግባቡ መሆኑን በመጥቀስ የስር ፍርድ ቤት ዉሳኔ ላሻር አይገባዉም በማለት ተከራክሯል። አመልካች በዚህ ላይ ያቀረበዉ የመልስ መልስም ቀርቦ ከመዝገቡ ጋር ተያይዟል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የግራ ቀኝ ክርክር ይዘት በአጭሩ ከላይ የተመለከተዉን የሚመስል ሲሆን፣ ይህ ችሎትም ለሰበር አቤቱታዉ ምክንያት የሆነዉን ዉሳኔ መዝገቡን ለማስቀረብ ከተያዘ ጭብጥ፣ ከግራ ቀኝ ክርክር እና ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸዉ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መዝገቡን እንደሚከተለዉ መርምሮታል። እንደመረመረዉም ለክርክሩ መነሻ የሆነዉ የወፍጮ ድርጅት ከታህሳስ 09 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ አገልግሎት ሳይሰጥ ታሽጎ የቆየ መሆኑ ተረጋግጧል። ታሽጎ እንዲቆይ የተደረገዉም ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በግራ ቀኝ መካከል ሲደረግ በነበረዉ ክርክር ምክንያት ጉዳዩን የያዘዉ ፍርድ ቤት ታህሳስ 08 ቀን 2007 በሰጠዉ የዕግድ ትዕዛዝ ምክንያት በመሆኑም ላይ ግራ ቀኝ አልተካካዱም። በልላ በኩል በግራ ቀኝ መካከል በተደረገ ዉል መሰረት አመልካች የወፍጮ ድርጅቱን ኪራይ ለመክፈል የሚገደደዉ እንዲሁም ተጠሪ ኪራዩን ከአመልካች የመጠየቅ መብት የሚኖረዉ ድርጅቱ የወፍጮ አገልግሎት ሲሰጥ ብቻ መሆኑ ይታወቃል። በርግጥ የዉሉ ጊዜ ካበቃ በኋላም ቢሆን ተጠሪ ድርጅቱን እስከሚረከብበት ጊዜ ድረስ ያለዉን ኪራይ አመልካች ለመክፈል ይገደዳል። ይህም የሚሆነዉ ድርጅቱ የወፍጮ አገልግሎቱን የሚሰጥ ሲሆን ወይም አገልግሎቱ እንዳይሰጥ የተደረገዉ በአመልካች ጥፋት ምክንያት መሆኑ ሲረጋገጥ ነዉ።
No topics extracted.
የወፍጮ ደርጅቱ ከፍ ሲል በተመለከቱት ጊዜያት አገልግሎት እንዳይሰጥ የተደረገዉ በአመልካች ጥፋት ምክንያት ሳይሆን በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነዉ። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ላሰጥ የቻለዉም ድርጅቱ እንዲታሸግ እና አገልግሎት እንዳይሰጥ ታግዶ እንዲቆይ ተጠሪ በመጠየቁ ነዉ። ስለሆነም ተጠሪ በአንድ በኩል ወፍጮዉ ተገቢዉን አገልግሎት እንዳይሰጥ እና ታሽጎ እንዲቆይ አስደርጎ እና በዚህም ምክንያት አመልካች ከወፍጮዉ ገቢ ባላገኘበት ሁኔታ፣ በልላ በኩል ታሽጎ ለቆየበት ጊዜ ኪራይ እንዲከፈለዉ የጠየቀዉ ዳኝነት ተቀባይነት ያለዉ አይደለም። ከዚህ አንፃር ሲታይ፣ የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወፍጮዉ ታሽጎ ለቆየበት ጊዜ ያለዉን ኪራይ አመልካች እንዲከፍል የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም ተከታዩ ተወስኗል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/174062 በቀን 15/02/09 ዓ.ም በዋለዉ ችሎት የሰጠዉ ዉሳኔ እንዲሁም የፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ/ በቀን 20/04/09 የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ሥ/ሥ/ ህጉ አንቀጽ 348(1) መሰረት ተሽሯል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ቁ/122163 በቀን 07/01/08 ዓ.ም በዋለዉ ችሎት የሰጠዉ ዉሳኔ ፀንቷል።
በዚህ ችሎት በተደረገ ክርክር ምክንያት የወጣዉን ወጪ እና ኪሳራ ግራ ቀኝ የየራሳቸዉን ይቻሉ።
ዕግድ ተነስቷል፤ ይፃፍ።