No summary available.
ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች- ተኽላት ይመስል ተፈሪ ገብሩ ቀነአ ቂጣታ ተሾመ ሽፈራው ፀሐይ መንክር አመልካች- ፍፁም ኢንተርናሽናል ኃ/የተ/የግ/ማህበር -ጠበቃ አሸናፊ አርአያ -ቀረቡ ተጠሪ- የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት - ነ/ፈ ፍቅሬ ተስፋዬ - ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
የሰበር አቤቱታው የቀረበው ተጠሪ ጽ/ቤት ለአመልካች በቁጥር 714 በስሙ መዝግቦ የሰጠውን የኢንዱስትሪ ንድፍ ጥበቃ ሰርተፍኬት በአዋጅ ቁጥር 123/1987 አንቀጽ 46(2)(ሀ) የተቀመጠውን የአዲስነት መስፈርት አሟልቶ የተሰጠ ባለመሆኑ ላሰረዝ ይገባል በማለት ያሳለፈውን ውሳኔ እና ይግባኙ የቀረበለት የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔው የሚነቀፍበት የህግ ስህተት የለም በማለት ያሳለፈውን ብይን በመቃወም ነው።
ከመዝገቡ መረዳት እንደሚቻለው በላይነህ ደቻሳ የተባሉ ግለሰብ በጠበቃቸው በኩል ለተጠሪ ጽ/ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ለአሁን አመልካች በማመልከቻ ቁጥር ET/ID/2015/2433 በቀን 19/02/2008 ዓ.ም በቁጥር 714 ተመዝግቦ የተሰጠው ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ሰርተፍኬት የአዋጅ ቁጥር 123/1987 አንቀጽ 46(1)(2) ድንጋጌዎችን ሳያሟላ ያላግባብ የተሰጠው በመሆኑ ሰርተፍኬቱ ላሰረዝ ይገባል በማለት አመልክተዋል። ተጠሪ ጽ/ቤትም አቤቱታውን ተቀብሎ አከራካሪ የሆነው ንድፍ በጽ/ቤቱ በመዝገብ ከመግባቱ በፊት በታይላንድ እና በኢትዮጵያ የሚታወቅ መሆኑን ከቀረቡት ማስረጃዎች ተገንዝቤያለሁ፤ ንድፉ አዲስነት አለው ላባል የሚችል አይደለም በማለት የተሰጠው ሰርተፍኬት እንዲሰረዝ ተወስኗል።
አመልካች የካቲት 13/2009 ዓ.ም በተፃፈ የሰበር አቤቱታ ተፈፀመ የሚሉትን የህግ ስህተት በመዘርዘር ያቀረቡ ሲሆን ይዘቱ ባጭሩ፡-
የኢንዱስትሪ ንድፍ ምዝገባም ሆነ ስረዛን በተመለከተ ተፈጻሚነት ያለው ህግ የፈጠራ፣ የአነስተኛ ፈጠራና ኢንዱስትሪ ንድፍ አዋጅ ቁጥር 123/1987 ሲሆን አዋጁ ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ይሰረዝልኝ አቤቱታ ላቀርብ የሚገባው ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ስለመሆኑ በግልፅ የደነገገ በመሆኑ የተጠሪ ጽ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ይሰረዝልኝ አቤቱታን የማየትም ሆነ የመወሰን ስልጣን ሳይኖረው ጉዳዩን ተቀብሎ በማየት ውሳኔ መስጠቱና የጽ/ቤቱ ዳይሬክተር ውሳኔውን ማፅደቃቸው የህግ መሰረት የልለው ነው እንዲባል፤
ፍሬ ጉዳዩን በተመለከተም ተጠሪ ጽ/ቤት ለውሳኔው መሰረት ያደረገውን ህግ አላግባብ በመተርጎም በአዋጅ ቁጥር 123/1987 አንቀጽ 46(2) መሰረት “የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ህግ የአዲስነት መስፈርት ፍጹማዊ ወይም በየትም ቦታ ከታወቀ ንድፍ የተለየ እንዲሆን ይጠይቃል“ ከማለቱም በተጨማሪ “የቀረበው ንድፍ በኢትዮጵያም ሆነ በልላ ሃገር አምሳያ ላኖረው አይገባም “ በማለት በአዋጁም ሆነ በማንኛውም ደንብም ሆነ መመሪያ ውስጥ ያልተገለፀ የተሳሳተ ትርጉም በመስጠት የአመልካች የኢንዱስትሪ ንድፍ አዲስነት፣ ፍፁማዊነት እና በልላ ሃገር አምሳያ የልለው ላሆን ይገባዋል በማለት የተሳሳተ ትርጉም በመስጠት ይህን ትርጉም ተከትሎ የኢንዱስትሪያዊ ንድፉ ይህን ሳያሟላ የተሰጠ በመሆኑ ላሰረተዝ ይገባዋል በማለት የደረሰበት መደምደሚያ መሰረታዊ ስህተት በመሆኑ እንዲታረም፤
አመልካች የኢንዱስትሪ ንድፍ ሰርተፍኬት የተሰጠኝ ጽ/ቤቱ በአግባቡ አጣርቶ እና መርምሮ ህግን በተከተለ መንገድ ሲሆን ተጠሪ ጽ/ቤት ሰርተፍኬት ለመስጠጥ የመረመረበት መንገድም ሆነ የምርመራው ውጤት ትክክል አይደለም የሚል ክርክር ሲመጣ የምርመራውን ውጤት፣ የምርመራውን ሂደት ሆነ ልሎች ምርመራውን የተመለከቱ አጠቃላይ ማስረጃዎች በራሱ በተጠሪ እጅ እያሉ እና የአመልካችም ክርክር ጽ/ቤቱ አስቀድሞ ምርመራውን በትክክል ማድረጉን የሚገልፅ ሆኖ እያለ የተጠሪ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በእጁ ያለውን ማስረጃ ሳይመረምር (ሳያጣራ) የሰጠው ውሳኔ ስህተት ነው፤
እንዲሁም ተጠሪ ጽ/ቤት በአዋጅ እንዲያስፈጽማቸው ከተሰጡት የፖላሲ አላማዎች በተቃራኒ የሰጠውን ሰርተፍኬት እና እሱን ተከትሎ የሚሰጠውን ጥበቃ በማመን ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አውጥተው ስራ የሚሰሩትን ኢንቨስተሮች መተማመኛ እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ውሳኔ መስጠቱ ከተቋቋመለት አላማ እና ከመሰረታዊ የአዕምሯዊ ንብረት ፖላሲ የሚጣረስና ስህተት በመሆኑ ውሳኔው ተሽሮ የአመልካችን የተመዘገበ የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ጥበቃ እንዲያደርግ ተብሎ እንዲወሰን ጠይቋል።
የሰበር ቅሬታው ተመርምሮ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ እና ተጠሪ መልስ እንዲሰጥበት ተደርጓል። ተጠሪ ሚያዚያ 17/2009 ዓ.ም በተፃፈ መልስ፡-
በተጠሪ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 320/95 ለተጠሪ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት መካከል የምዝገባ ማመልከቻዎችን በመቀበል አስፈላጊውን ምርመራ በማካሄድ ተገቢውን ውሳኔ መስጠት ሲሆን፤ ህጎቹ ያስቀመጧቸውን መስፈርቶች ሳያሟሉ የተመዘገቡ ማመልከቻዎች ላይ አቤቱታ ሲቀርብ ምዝገባውን የመሰረዝ ስልጣን (ፈራሽ የማድረግ) እንዳለው ተጠሪ የሚያስፈጽማቸውን ህጎች አውደ ንባብ (contextual interpretation) መሰረት በማድረግ የሰበር ችሎቱ አስቀድሞ ትርጉም የሰጠ በመሆኑ ተጠሪ የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ሰርተፍኬት ይሰረዝልኝ ጥያቄን ተቀብሎ ያስተናገደው ህጉ በሰጠው ሥልጣን መሰረት ነው፤
ተጠሪ የአዋጁን የአዲስነት መመዘኛ በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም ምዝገባው እንዲሰረዝ አድርጓል በሚል የቀረበውን ቅሬታ በተመለከተም አዋጁ ለጥበቃ ብቁነት ያስቀመጠው የአዲስነት ጠባይ ፍፁማዊ ወይም ሁሉን አቀፍ (absolute or qualified universal novelty) የተባለው ሲሆን ንድፉ አዲስ መሆኑ የሚረጋገጠው በኢትዮጵያ ወይም በቀረው የአለም ክፍል አምሳያ ከልለው ነው፤ ፍፁማዊ መመዘኛ የተባለውም ፍለጋው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይወሰን በሁሉም የአለም ክፍል መሆኑን ለማመልከት ነው፤ ስለሆነም የኢንዱስትሪ ንድፉ አዲስ ነው የሚባለው በኢትዮጵያ ወይም በውጪ ከታወቁ ተመሳሳይ ንድፎች የተለየ እና ከምዝገባ ቀን ወይም እንደ አግባቡ ከቀዳሚ ቀን በፊት ባለው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ያልተገለፀ ሲሆን በመሆኑ የአመልካች ቅሬታ በህጉ በግልጽ የተመለከተውን በማዛባት የቀረበ ነው፤
ለአመልካች የኢንዱስትሪ ንድፍ ሰርተፍኬት የተሰጠው ጽ/ቤቱ በአግባቡ አጣርቶ እና መርምሮ ሲሆን ተጠሪ በእጁ ያለውን ማስረጃ ሳይመረምር (ሳያጣራ) የሰጠው የመሰረዝ ውሳኔ ስህተት ነው በሚል የቀረበውን ቅሬታ በተመለከተም ተጠሪ ማመልከቻውን ለምዝገባ ለመቀበል ያካሄደው ምርመራ በአዋጁ አንቀጽ 48(1) የተመለከቱት መመዘኛዎች መሟላታቸውን ለማረጋገጥ በመሆኑ፤ በፎርማላቲ ምርመራ ላይ ብቻ የተመሰረተ የምዝገባ ሥርዓት በንድፉ አዲስነት ላይ የሚደረግን ፍለጋ (search) እና የማሰረዳት ሸክም በገበያ ውስጥ ጥቅም አለን ወደሚሉ ሰዎች የማዛወር ውጤት ያለው በመሆኑ በምዝገባው ተገቢነት ላይ የሚነሳን ተቃዉሞ ለመፍታት ጽ/ቤቱ ምርመራ ያደርጋል፤ የአመልካች ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ምዝገባም አዲስነት የለውም ተብሎ እንዲሰረዝ የተወሰነው በዚሁ አግባብ ነው፤
ተጠሪ የሰጠው የኢንዱስትሪ ንድፍ ሰርተፍኬት እንዲሰረዝ አቤቱታ ሲቀርብ የራሱን አሰራር መከላከል እየተገባው እንዲሰረዝ ማድረጉ የተቋቋመበትን ዓላማ ይቃረናል መባሉም ስህተት ነው፤ አመልካች የንድፉ ፈጠራ የራሱ ቢሆን ኖሮ ንድፉ ከመመዝገቡ በፊት ታይላንድ ሀገር የሚገኘው ፓይኒር ኢንተርናሽል ኮርፖሬሽ አምርቶታል ተብሎ ለቀረበው አቤቱታ በቂ ማስተባበያ ማቅረብ በቻለ ነበር፤
አመልካች የቀረበበትን አቤቱታ በበቂ ሁኔታ ሳያስተባብል ስላስመዘገበ ብቻ ባለመብት የሚሆንበት አሰራር ፍትሃዊ አይሆንም፤ ስለሆነም የአመልካች የኢንዱስትሪ ንድፍ አዲስ አይደለም ተብሎ ምዝገባው እንዲሰረዝ የተሰጠው ውሳኔ እና የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔውን ማጽናቱ በአግባቡ ነው እንዲባል ተከራክሯል። አመልካችም ክርክሩን በማጠናከር ግንቦት 18/2009 ዓ.ም የተፃፈ የመልስ መልስ አቅርቧል።
ከፍ ሲል ባጭሩ የገለጽነው የጉዳዩን አመጣጥ እና ግራ ቀኙ በሰበር ያደረጉትን ክርክር ሲሆን በበኩላችን የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል። እንደመረመርነውም የችሎቱን ምላሽ የሚጠይቁት አብይ ነጥቦች ፡- 1ኛ) ተጠሪ ጽ/ቤት የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ሰርተፍኬት ይሰረዝልኝ አቤቱታን ተቀብሎ የማየትም ሆነ የመወሰን ስልጣን አለው ወይስ የለውም?
2ኛ) ስልጣን አለው ቢባል የፈጠራ፣ የአነስተኛ ፈጠራና የኢንዱስትሪ ንድፍ አዋጅ ቁጥር 123/1987 የአዲስነት መስፈርትን አስመልክቶ የደነገገው አላግባብ ተተርጎሞ ውሳኔ ተሰጥቷል? ወይስ አልተሰጠም?
3ኛ) ለአመልካች ተሰጥቶ የነበረው ሰርተፍኬት እንዲሰረዝ የተወሰነው በህጉ አግባብ ተጣርቶ ነው ወይስ አይደለም? የሚሉት ናቸው። በዚሁ ቅድመ ተከተል ተመልክናቸዋል።
ቀዳሚውን ነጥብ በተመለከተ አመልካች በቅሬታው በአዋጅ ቁጥር 123/1987 ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ሰርተፍኬት ይሰረዝልኝ አቤቱታ ላቀርብ የሚገባው ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ስለመሆኑ በግልፅ የደነገገ በመሆኑ የተጠሪ ጽ/ቤት የይሰረዝልኝ አቤቱታን የማየትም ሆነ የመወሰን ስልጣን ሳይኖረው ጉዳዩን ተቀብሎ በማየት ውሳኔ መስጠቱ የህግ መሰረት የልለው በመሆኑ ስልጣን ሳይኖረው የሰጠው ውሳኔ እንዲሻር የጠየቀ ሲሆን ተጠሪ በበኩሉ የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ሰርተፍኬት ይሰረዝልኝ ጥያቄውን ተቀብሎ ያስተናገደው ህጉ በሰጠው ሥልጣን መሰረት ስለመሆኑ ተከራክሯል። የፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሰ/መ/ በሰጠው ትርጉም የፈጠራ፣ የአነስተኛ ፈጠራና ኢንዱስትሪ ንድፍ አዋጅ ቁጥር 123/1987’ን ጨምሮ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤትን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 320/1995 እና ጽ/ቤቱ የሚያስፈጽማቸውን ልሎች አዋጆች ዝርዝር ይዘት በመመርመር አቤቱታ የሚቀርብበትን እና በይግባኝ የሚስተናገድበትን ሥርዓት በተመለከተ ትርጉም ሰጥቷል።
በዚህም መሰረት ተጠሪ መስሪያ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ (የይሰረዝልኝ አቤቱታን ጨምሮ) ቅሬታ ያለው ወገን የሚኖረው መብት በይግባኝ ሥርዓት የማስከበር እንጂ ቀጥታ ክስ ለፍርድ ቤት የሚቀርብ አለመሆኑን፤ ይግባኙ መቅረብ ያለበትም ለፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሆኑን ወስኗል። ይኸው ውሳኔ በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(1) መሰረት ለተያዘው ጉዳይም በተመሳሳይ ተፈጻሚ ነው። ስለሆነም አመልካች ተጠሪው ጽ/ቤት የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ሰርተፍኬት ይሰረዝልኝ አቤቱታን ተቀብሎ የማየትም ሆነ የመወሰን ስልጣን የለውም በማለት ያቀረበው ቅሬታ ከፍ ሲል የተጠቀሱትን አስገዳጅ የሰበር ውሳኔዎች መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ አልተቀበልነውም። ተጠሪ ጽ/ቤት የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ሰርተፍኬት ይሰረዝልኝ አቤቱታን መርምሮ ለመወሰን ስልጣን አለው ብለናል።
ሁለተኛው ነጥብ በአዋጅ ቁጥር 123/1987 የአዲስነት መስፈርትን አስመልክቶ የተደነገገው አላግባብ ተተርጎሞ ውሳኔ ተሰጥቷል በሚል የቀረበውን ቅሬታ የተመለከተ ነው። አመልካች በቅሬታው “የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ህግ የአዲስነት መስፈርት ፍጹማዊ ወይም በየትም ቦታ ከታወቀ ንድፍ የተለየ እንዲሆን ይጠይቃል“ እንዲሁም “ንድፉ በኢትዮጵያም ሆነ በልላ ሃገር አምሳያ ላኖረው አይገባም “ ተብሎ በተጠሪ ጽ/ቤት በኩል በህጉ ያልተገለፀ የተሳሳተ ትርጉም ተሰጥቶ ይህን ትርጉም ተከትሎ የኢንዱስትሪያዊ ንድፉ ይህን ሳያሟላ የተሰጠ በመሆኑ ላሰረተዝ ይገባዋል በማለት የደረሰበት መደምደሚያ መሰረታዊ ስህተት በመሆኑ እንዲታረም ጠይቋል። ተጠሪ በበኩሉ አዋጁ ለጥበቃ ብቁነት ያስቀመጠው የአዲስነት ጠባይ ፍፁማዊ ወይም ሁሉን አቀፍ መሆኑንና ንድፉ አዲስ መሆኑ የሚረጋገጠው በኢትዮጵያ ወይም በቀረው የአለም ክፍል አምሳያ ከልለው ስለመሆኑ በህጉ የተደነገገ መሆኑን በማንሳት ተከራክሯል።
በአዋጅ ቁጥር 123/1987 አንቀጽ 46(1) ድንጋጌ መሰረት አዲስነት እና ተግባራዊ ተፈፃሚነት ያለው ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ በአዋጁ መሰረት ጥበቃ እንደሚደረግለት ተመልክቷል። በአዋጁ አንቀጽ 46(2)(ሀ) እንደተደነገገውም አንድ ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ አዲስ ነው የሚባለው … ”የንድፉ ዋና ዋና ባህሪያት በኢትዮጵያ ወይም በውጪ ከታወቁ ተመሳሳይ ንድፎች የተለየ እና ከምዝገባ ቀን ወይም እንዳግባቡ ከቀዳሚ ቀን በፊት ባለው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ያልተገለፀ ሲሆን ነው:: በንድፎቹ መካከል ያሉ የተለዩ ገፅታዎች ልዩነት በጥቃቅን ዝርዝሮች ከሆነ ተመሳሳይ ናቸው ተብለው ይወሰዳሉ“። የዚሁ ድንጋጌ እንግላዝኛ ቅጅም “industrial design shall be considered new when the sum total of its essential features is different from that of another design known either in Ethiopia or abroad and has not been disclosed for more than one year before the date of filing of the application for registration or, where appropriate, before the priority date. Designs shall be deemed to be identical if their specific features differ only in immaterial details” በማለት ይደነግጋል።
ስለሆነም ተጠሪ ንድፉ አዲስ መሆኑ የሚረጋገጠው በኢትዮጵያ ወይም በቀረው የአለም ክፍል አምሳያ ከልለው ስለመሆኑ በህጉ የተደነገገ መሆኑን በማንሳት ያቀረበው ክርክር የሚነቀፍ ባይሆንም አንድ ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ አዲስ ነው የሚባለው የንድፉን ዋና ዋና ባህሪያት መሰረት በማድረግ ስለመሆኑ ከፍ ሲል ከተመለከትነው የህጉ ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል። የንድፉን ዋና ዋና ባህሪያት ለይቶ ተመሳሳይነት አላቸው ወይም የላቸውም በማለት መወሰን የሚቻለው ደግሞ የእያንዳንዱን ዲዛይን ዋና ዋና ባህሪያት በቅድሚያ በመለየት ከልላው ጋር በማነፃፀር ነው።
ስለሆነም አመልካች የኢንዱስትሪ ንድፍ አዲስነት፣ ፍፁማዊነት እና በልላ ሃገር አምሳያ የልለው ላሆን ይገባዋል በማለት የተሳሳተ ትርጉም ተሰጥቷል በማለት ያቀረበው ክርክር ከፍሲል የተመለከተውን የህጉን ድንጋጌ መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ ተቀባይነት ባይኖረውም የአከራካሪው ንድፍ ዋና ዋና ባህሪያት ተለይተው የተሰጠ ውሳኔ ስለመሆኑ መዝገቡ ስለማያሳይ ውሳኔው በዚህ ረገድ ላታረም ይገባል ብለናል።
ከዚህ ጋር የተያያዘው ልላው ነጥብ ለአመልካች ተሰጥቶ የነበረው ሰርተፍኬት እንዲሰረዝ የተወሰነው በህጉ አግባብ ተጣርቶ ነው ወይስ አይደለም? የሚለው ነው። ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው የንድፉን አዲስነት ለመወሰን የአከራካሪው ንድፍ ዋና ዋና ባህሪያት ተለይተው ላታወቁ ይገባል። የአንድ ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ዋና ዋና ባህሪያት በኢትዮጵያ ወይም በውጪ ከታወቁ ተመሳሳይ ንድፎች የተለየ መሆኑ የሚረጋግጠው ደግሞ በዘርፉ ያለውን የዳበረ እውቀት እና ልምድ መሰረት ዝርዝር ማጣራት በማድረግ ነው። ስለሆነም ክርክር ባስነሳው ንድፍ ዋና ዋና ባህሪያት ላይ እውቀቱ ያላቸው ባለሙያዎች የሚሰጡት ምስክርነት ለጉዳዩ ተቀባይነት ይኖረዋል። በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት ለአመልካች ሰርተፍኬት ሰጥቶት የነበረው በኢትዮጵያ ገበያ በኢንተርኔት በተደረገ ተመሳሳይ ንድፍ ፍለጋ ሪፖርት መሰረት ንድፉ አዲስ ነው ተብሎ ሲሆን ሰርተፍኬቱ የተሰረዘውም ሰርተፍኬቱ የተገኘበትን የምርመራ ሪፖርት ትክክለኛነት አመልካች (በላይነህ ደቻሳ) ሞግቶታል የአሁኑ አመልካችም ይህን ማስተባበል አልቻለም በሚል ነው። ተጠሪ ጽ/ቤት በዚህ መልኩ ሰርተፍኬት የሚሰጥና የሚሰርዝ ከሆነ አሰራሩ ህጉን የተከተለ ካለመሆኑም በላይ ተቋሙ በአዋጅ የተቋቋመለትን አላማ ዳር የማያደርስ በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም።
በአጠቃላይ ተጠሪ ጽ/ቤት በህጉ እንደተመለከተው የአከራካሪውን ንድፍ አዲስነት ለመወሰን የኢንዱስትሪያዊ ንድፉ ዋና ዋና ባህሪያት በመለየት በኢትዮጵያ ወይም በውጪ ከታወቁ ተመሳሳይ ንድፎች የተለየ ወይም ተመሳሳይነት ያለው ስለመሆኑ በዘርፉ ያለውን የዳበረ እውቀት እና ልምድ መሰረት በማድረግ ዝርዝር ማጣራት በማድረግ መወሰን ሲገባው በዚህ መልኩ ሳያጣራ እና ሳያረጋግጥ ውሳኔ ላይ መድረሱ ጉዳዩ የሚገዛበትን ህግ መሰረት ያደረገ ባለመሆኑ ውሳኔው የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነው ብለናል። ተከታዩንም ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት በቁጥር ኢ/አ/ን ይ/ሰ/ኮ መ/ቁ 02/2008 ሚያዚያ 18/2008 ዓ.ም ለአመልካች በቁጥር 714 በስሙ ተመዝግቦ የተሰጠው ሰርተፍኬት በአዋጅ ቁጥር 123/1987 አንቀጽ 46(2)(ሀ) የተመለከተውን የአዲስነት መስፈርት አሟልቶ የተሰጠ ባለመሆኑ ላሰረዝ ይገባል በማለት የሰጠው ውሳኔ ፤ እንዲሁም የፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ ያሳለፈው ብይን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 348(1) መሰረት ተሽሯል።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ጉዳዩን በህጉ አግባብ በማጣራት የአከራካሪውን ንድፍ አዲስነት ለመወሰን የኢንዱስትሪያዊ ንድፉ ዋና ዋና ባህሪያት በመለየት በኢትዮጵያ ወይም በውጪ ከታወቁ ተመሳሳይ ንድፎች የተለየ ወይም ተመሳሳይነት ያለው ስለመሆኑ በዘርፉ ያለውን የዳበረ እውቀት እና ልምድ መሰረት በማድረግ ዝርዝር ማጣራት አድርጎ ውሳኔ እንዲሰጥ ጉዳዩን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 343(1) መሰረት መልሰናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል።
ቅ/ሀ የማይነበብ የአራት ዳኞች ፊርማ አለበት።
No topics extracted.