በኦሮሚያ የገጠር መሬት አጠቃቀም ለረጅም ጊዜ በልላ ሰው የተያዘና ጥቅም ላይ ሲውል የነበረን የገጠር መሬት የተያዘው ሕገወጥ ውልን መሰረት በማድረግ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ መሬቱ እንዲለቀቅ የሚቀርብ ክስ በአስራ ሁለት ዓመት ይርጋ የሚታገድ ስለመሆኑ፣ የኦሮሚያ የገጠር መሬት አጠቃቀም እና አስተዳደር ደንብ ቁጥር 151/2005 አንቀጽ 32
No summary available.
ጥር 24 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡ ...1.ዳኜ መላኩ 2. ተኽላት ይመሰል 3. ቀነዓ ቂጣታ 4. ተሾመ ሽፈራዉ 5. ፀሐይ መንክር አመልካች፡- ..... አቶ ለማ ማሙዬ- ቀርበዋል ተጠሪ፡- ...........በአዳማ ከተማ አስተዳደር ቀበል 12 ጽ/ቤት -ነ/ፈጅ አቶ ነቢ ፈይሶ ቀርበዋል ይህ መዝገብ የተቀጠረዉ ለምርመራ ሲሆን ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የመንግስት ቤት ለማስለቀቅ የቀረበ ክስን የሚመለከት ሲሆን ለዚህ ችሎት ላቀርብ የቻለዉ የአሁን አመልካች የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.232835 በ7/2/2009 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበዉን አቤቱታ መርምሮ ለመወሰን ነዉ።
የጉዳዩ መነሻ ሲታይ በአዳማ ወረዳ ፍ/ቤት የአሁን ተጠሪ ከሳሽ፣የአሁን አመልካች ደግሞ ተከሳሽ ሁኖ ሲከራከሩ ነበር። ከሳሽ ባቀረበዉ ክስ ተከሳሽ የቤት ቁጥር 286.04 ከከሳሽ በዉል የተከራየ ቢሆንም በሚስቱ በወ/ሮ ዘነበች ተክል ስም የቤት ቁጥር 202 ሰርቶላት ተጠቃሚ አድርጓት እያለ በቀበል ቤት ዉስጥ መኖር ስለማይገባዉ ተከሳሽ ቤቱን እንዲለቅልን በማለት ከሷል።
በዚህ ክስ ላይ ተከሳሽ ባቀረበዉ መልስ ባለቤቴ ያልተጠናቀቀ ቤት አግኝታ ነበር፣ ቤቱን አልገባንበትም፣ ይህ ቤት በእዳ ምክንያት በፍ/ቤት ዉሳኔ የተወሰደ ስለሆነ የመንግስት ቤት ላለቅ አይገባም በማለት ተከራክሯል።
ከዚህ በኋላ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን በመመርመር በሰጠዉ ዉሳኔ ተከሳሽ በባለቤታቸዉ ስም የሰሩትን ቤት ወደ ልጃቸዉ ያዛወሩ ስለሆነ በዉላቸዉ እና በመመሪያዉ መሰረት የመንግስት ቤት ይዘዉ የሚቀጥሉበት አግባብ ስለልለ ቤቱን ለከሳሽ እንዲለቅ በማለት ወስኗል። የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ይህን ጉዳይ በይግባኝ በማየት በሰጠዉ ዉሳኔ ይግባኝ ባይ በሚስታቸዉ ስም የተሰራዉ ቤት በእዳ ምክንያት በፍ/ቤት ዉሳኔ በአፈጻጸም ከፍላጐታቸዉ ዉጭ ስለተወሰደ፣ ይህን ለልጃቸዉ በዘድ አዛዉረዉ አስወስደዋል የሚባልበት ምክንያት ስለልለ፣ ይህን የመንግስት ቤት ላለቁ አይገባም በማለት የሥር ዉሳኔ በመሻር ወስኗል። የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የከፍተኛ ፍ/ቤት ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል። የሥር ከሳሽ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታ ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረበ ሲሆን ችሎቱም ግራ ቀኛቸዉን በማከራከር በሰጠዉ ዉሳኔ የሥር የከፍተኛ ፍ/ቤት እና የሥር የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ዉሳኔዎችን በመሻር የሥር የወረዳ ፍ/ቤት ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል።
የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ለማስቀየር ነዉ።
የአሁን አመልካች በ18/2/2009 ዓ.ም በተጻፈ አቤቱታ፡ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በሥር ፍ/ቤት ያልተነሳዉን ክርክር የኪራይ ዉል ጊዜ ገደብ ማለቁን በተመለከተ በማንሳት ቤቱን እንዲለቅ መወሰኑ ስህተት ነዉ። አመልካች በባለቤታቸዉ ስም ሰርቷል የተባለዉ ቤት ከአቅም በላይ በሆነና በእዳ ምክንያት በፍ/ቤት ዉሳኔ ከእጃችን መዉጣቱ እየታየ ቤት ነበራቸዉ በሚል ምክንያት የተከራየሁትን ቤት እንዲለቅ የተሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲሻርልኝ በማለት አመልክቷል።
ይህ ችሎት አቤቱታዉ ያስቀርባል በማለት ተጠሪ መልስ እንዲሰጥ ባዘዘዉ መሰረት ተጠሪ በ27/6/2009 ዓ.ም በተጻፈ መልስ፡ የሥር የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎትና የአዳማ ወረዳ ፍ/ቤት የሰጡት ዉሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የለዉም ተብሎ እንዲጸናልን፣ የአመልካች አቤቱታ ዉድቅ ተድርጎልን ኪሳራ እንዲወሰንልን በማለት በዝርዝር ተከራክሯል። የአሁን አመልካች የመልስ መልስ አቅርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተመለከተዉ ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኛቸዉን ክርክር አግባብነት ካላቸዉ የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መርምሮታል። እንደመረመርነዉ በዚህ ጉዳይ ምላሽ ማግኘት የሚገባዉ ነጥብ የአሁን አመልካች ለክርክር ምክንያት የሆነዉን የመንግስት ቤት እንዲለቁ የተሰጠዉ ዉሳኔ በሕጉ አግባብ ነዉ ወይስ አይደለም? የሚለዉን እንደጭብጥ በመያዝ እንደሚከተለዉ ተመርምሯል። ከሥር ፍ/ቤቶች ዉሳኔዎች ግልባጭ መገንዘብ እንደሚቻለዉ የአሁን አመልካች የመንግስት ቤት ከተጠሪ በኪራይ ዉል ተከራይተዉ ሲኖሩ እንደነበር፣ አመልካች በባለቤታቸዉ ስም በአዳማ ከተማ ዉስጥ የመኖሪያ ቤት መስራታቸዉ እና ይህን በባለቤታቸዉ ስም የተሰራዉን ቤት ያበደርኳቸዉን ገንዘብ አልከፈሉኝም በሚል በእዳ ምክንያት ልጃቸዉ በፍ/ቤት ከሷቸዉ ዉሳኔ ተሰጥቶ በአፈጻጸም ተወስዶብናል በማለት የፍ/ቤት ዉሳኔ ማቅረባቸዉን ያመለክታሉ።
ነገር ግን በአመልካች እና በተጠሪ መካከል በተደረገዉ የቤት ኪራይ ዉል አንቀጽ 8 (6) እና በመመሪያ ቁጥር 10/2006 አንቀጽ 15.2 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት አንድ የመንግስት ቤት ተከራይ የራሱ ቤት ካገኘ የመንግስት ቤትን በተከራይነት ይዞ መቀጠል እንደማይችልና የመንግስት ቤት መልቀቅ እንዳለበት ተመልክቷል። ከዚህ አንጻር የግራ ቀኛቸዉ ክርክር ሲታይ የአሁን አመልካች በባለቤታቸዉ ስም የሰሩትን ቤት የልጃችን እዳ አለበት በማለት እርስ በእርሳቸዉ ተካሰዉ እና እዳም እንዳለ አምነዉ ዉሳኔ እንዲሰጥ በማድረግ የምንከፍል ገንዘብ የለንም በማለት ቤቱን ለልጃቸዉ ማስረከባቸዉ ሲታይ፣ በባለቤታቸዉ ስም የሰሩትን ቤት እና የመንግስት ቤት ይዘዉ ለመቀጠል በማሰብ የተደረገ ነዉ ከሚባል በስተቀር የሚታመን ተግባር እንዳልሆነ የሥር ፍ/ቤቶች የረጋገጡት ጉዳይ ነዉ። ስለሆነም የአሁን አመልካች በባለቤታቸዉ ስም የሰሩትን ቤት በዚህ አግባብ ወደ ልጃቸዉ ስም አዛዉረዉ የመንግስት ቤትን ይዘዉ የሚቀጥሉበት አግባብ የለም። የሥር የክልሉ የሰበር ሰሚ ችሎት የመንግስት ቤት የኪራይ ዉል ዓላማ ካለመገንዘብ የተነሳ የኪራይ ዉሉ ለተወሰነ ጊዜ የተደረገ እና ያልታደሰ በመሆኑ ዉሉ ተቋርጧል በማለት የያዘዉ አቋም ተገቢ ባይሆንም በዉጤት ደረጃ አመልካች የመንግስት ቤት በኪራይ ይዘዉ መቀጠል እንደልለባቸዉ አቋም በመያዝ የሥር የወረዳ ፍ/ቤት ዉሳኔ በማጽናት ዉሳኔ መስጠቱ በአግባቡ ነዉ ብለናል።
ሲጠቃለል የሥር የወረዳ ፍ/ቤት እና የሥር የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የአሁን አመልካች በኪራይ ዉል መነሻነት ሲኖሩበት የነበረዉን የመንግስት ቤት ለቀዉ ለተጠሪ እንዲያስረክቡ የሰጡት ዉሳኔ በሕግ አግባብ ነዉ ከሚባል በስተቀር መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመባቸዉ ነዉ ለማለት ስላልተቻለ የሚከተለዉ ተወስኗል።
የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.232835 በ7/2/2009 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ በዉጤት ደረጃ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያልተፈጸመበት ስለሆነ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348 (1) መሰረት ጸንቷል።
የዚህ ዉሳኔ ግልባጭ ለሥር ፍ/ቤቶች ይድረስ።
ግራ ቀኛቸዉ በዚህ ችሎት የደረሰባቸዉን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸዉን ይቻሉ።
No topics extracted.