የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዥያ በማናቸዉም አይነት ሰነድ ላይ የተመሰረተ ሲሆን ከተጻፈበት ቀን አንስቶ የማይንቀሳቀሰዉ ንብረት በሚገኝበት ሀገር ባለዉ በማይንቀሳቀስ ርስት መዝገብ ካልተፃፈ በቀር ማንኛውንም አይነት ውጤት የማያስገኝ ስለመሆኑና ዕዳው እንዲከፈል በተወሰነበት ጊዜ ሳይከፈል የቀረ እንደሆነ ገንዘብ ጠያቂው የመያዣ መብት ያገኘበትን የማይንቀሳቀስ ንብረት ይወስዳል የሚል ስምምነት ሁሉ ተቀባይነት የማይኖረዉ ስለመሆኑ፡ፍ/ሕ/ቁ 3052 እና 3060 XLIV
No summary available.
ጥቅምት 22 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡ 1.ዳኜ መላኩ 2. ተፈሪ ገብሩ 3. ቀነዓ ቂጣታ 4. ተሾመ ሽፈራዉ 5. ፀሐይ መንክር አመልካች፡- .....ምስኪ ኢንዱስትሪዎች ኃ/የተ/የግ/ማህበር-ጠበቃ አቶ አለሙ ገበየሁ ቀርበዋል ተጠሪ፡- ..........ቤካስ ኬሚካልስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር -ነ/ፈጅ አቶ አድነው ደቻሳ ቀርበዋል ይህ መዝገብ የተቀጠረዉ ለምርመራ ሲሆን ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል።
ይህ የሰበር ጉዳይ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር የሚመለከት ሲሆን ለችሎቱ ላቀርብ የቻለዉ የአሁን አመልካች የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ.ቁ.120677 በ28/7/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበዉን አቤቱታ መርምሮ ለመወሰን ነዉ።
የጉዳዩ መነሻ ሲታይ በንግድ ዉድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የዳኝነት ችሎት የአሁን ተጠሪ ከሳሽ፣ አመልካች ደግሞ ተከሳሽ ሲሆን፣ተጠሪ ባቀረበዉ ክስ ተጠሪ የፈሳሽና ክሬም ዲተርጀንቶችንና ሳሙናዎችን በማምረት ለ18 ዓመታት ሲሸጥ የቆየ ሲሆን፤ተጠሪ ከሚያመርተዉና ብራይት ቤክስ ከሚለዉ ምርት ጋር ተመሳሳይ በሆነ ቢጫ ቀለም ባለዉ ጀሪካንና ቤስት ብራይት ብሎ አምርቶ ለገበያ እያቀረበ ስለሆነ ይህ ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 8 መሰረት ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር በመፈጸም የተጠሪን ጥቅም በመጉዳቱ፣አመልካች በፈጸመዉ ድርጊት የገንዘብ ቅጣት እንዲወሰንበት፣አመልካች ብራይት ቤካስ ጋር ከሚመሳሰለዉ ቤስት ብራይት በቢጫ ቀለም ጀሪካን ምስል መጠቀሙ ሕገ ወጥ ነዉ እንዲባልልን ፣አመልካች በማምረት በገበያ ላይ የተሰራጩት ምርቶች እንዲሰበሰቡ እና በዚህ ክርክር የወጣዉ ወጪና ኪሳራ እንዲጠበቅልን በማለት ከሷል።
የአሁን አመልካች ባቀረበዉ መልስ ተጠሪ የብራይት ቤካስ እና የቢጫ ጀሪካን ንግድ ምልክት ባለቤት ነኝ ማለቱ ሕጋዊ አይደለም፣ብራይት የሚለዉ ቃል ገላጭና የጋራ መጠቀሚያ እንጂ በአንድ ግለሰብ በብቸኝነት በንግድ ምልክትነት ላመዘገብ የሚገባ አይደለም፤ በጀሪካን ላይ ያለዉ የቢጫ ቀለም የንግድ ምልክት ባለቤት ነኝ በማለት ያቀረበዉ ክርክር ተቀባይነት የለዉም ፤ለተጠሪ የተሰጠዉ የጀሪካን ቀለም ዓይነት ቢጫና አረንጓድ እንጂ በሙሉ ቢጫ ቀለም አይደለም፣ ተጠሪ የንግድ ምልክት መብት አለዉ ቢባል እንኳን የአመልካችና የተጠሪ የንግድ ምልክቶች ፍጹም የተለያዩ ናቸዉ፣ሁለቱም የንግድ ምልክቶች የተለያዩ ስለሆኑ ሸማቾቹን የሚያደናግር አይደለም በማለት ተከራክሯል።
ከዚህ በኋላ የዳኝነት ችሎቱ ጉዳዩን በመመርመር የሰጠዉ ዉሳኔ አመልካች የግራቀኛቸዉ የምርት ማሸጊያ ጀሪካን ዲዛይኖች እና የቀለም ዉህድ ሸማቾችን የሚያደናግርና ተጽዕኖ የሚፈጥር፣የማይለያዩ እና ተመሳሳይነታቸዉ የሚጎላ በመሆኑ በንግድ ዉድድርና ሸማቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር አንቀጽ 8 /2፣ሀ/ ሥር ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር ነዉ፤አመልካች ሸማቾችን የሚያደናግር እና ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር መፈጸሙ ስለተረጋገጠ በአዋጁ አንቀጽ 32 መሰረት አስተዳደራዊ እርምጃ እና አስተዳደራዊ ቅጣት መወሰን ተገቢ ነዉ። አመልካች ይህን ምርት ለገበያ ማቅረብ እንዲያቆም፣ አመልካች በፈጸመዉ ያልተገባ የንግድ ዉድድር በአዋጁ አንቀጽ 42 /3/ መሰረት ምርቱን አምርቶ ወደ ገበያ ካቀረበበት ጊዜ ጀምሮ በሰራባቸዉ አጠቃላይ ጊዜያት ዉስጥ ከሽያጭ ገቢ 5% እንዲቀጣ በማለት በአብላጫ ድምጽ ወስኗል።
የአሁን አመልካች በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል የንግድ ዉድድር የሸማቾች ጥያቄ ይግባኝ ሰሚ አስተዳደራዊ ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ ግራቀኛቸዉን በማከራከር በሰጠዉ ዉሳኔ አመልካች በተጠሪ ላይ የፈጸመዉ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር አለ ለማለት የሚያስችል ነገር ስለልለ የሥር ዉሳኔ ተሽሯል በማለት ወስኗል።
የአሁን ተጠሪ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ ግራ ቀኛቸዉን በማከራከር በሰጠዉ ዉሳኔ አመልካች ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ጥበቃ የተደረገለት ቤስት በረኪና ሲሆን ተጠሪ ደግሞ ብራይት ቤካስ የሚል ነዉ፣ አመልካች ግን ይህን የንግድ ምልክት በመተዉ ቤስት ብራይት በማለት ከተጠሪ ጋር ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር ዉስጥ በመግባት ሸማቹን ሕዝብ የማደናገር ተግባር መፈጸሙ የተረጋገጠ ስለሆነ የይግባኝ ሰሚ አስተዳደራዊ ፍ/ቤት ዉሳኔ በመሻር የፍድራል የንግድ ዉድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የዳኝነት ችሎት የሰጠዉን ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል። የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ ይህን ዉሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነዉ።
የአሁን አመልካች ግንቦት 15 ቀን 2008 ዓ.ም የተጻፈ ስምንት ገጽ አቤቱታ አቅርቧል።
የአቤቱታዉ ይዘት በአጭሩ፡--የአሁን አመልካች በተጠሪ ላይ የፈጸመዉ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር ድርጊት በልለበት እና በዚህ ረገድ ዐ/ሕግ ክስ ባላቀረበበት በቅጣት መልክ ከሽያጭ ገቢዉ 5% እንዲቀጣ የተሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ዉሳኔ ተሽሮ የፍድራል የንግድ ዉድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠዉ ዉሳኔ እንዲጸናልን በማለት በዝርዝር አመልክቷል።
የሰበር አጣሪ ችሎት ጉዳዩን በማየት ፣የሥር ፍ/ቤት የካሳ መጠን ሳይጣራ 5% ካሳ ይከፈል ያለበት አግባብነት፣ ለመመርመር ሲባል አቤቱታዉ ያስቀርባል በማለት ተጠሪ መልስ እንዲያቀርብ በታዘዘዉ መሰረት ታህሳስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም የተጻፈ ስምንት ገጽ መልስ አቅርቧል። የመልሱም ይዘት በአጭሩ፡--የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያልተፈጸመበት ስለሆነ እንዲጸናልን ወጪና ኪሳራ የመጠየቅ መብት እንዲጠበቅልን በማለት በዝርዝር ተከራክሯል። የአሁን አመልካች የሰበር አቤቱታዉን በማጠናከር የመልስ መልስ አቅርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተመለከተዉ ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኛቸዉን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነዉ ዉሳኔ እና አግባብነት ካላቸዉ የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንዲሁም አቤቱታዉ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘዉ ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለዉ መርምሮታል። እንደመረመርነዉ የአሁን አመልካች ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽ/ቤት ጥበቃ የተሰጠዉ የንግድ ምልክት ‹‹ቤስት በረኪና›› እንደሆነ፣ ለተጠሪ የተሰጠዉ የንግድ ምልክት ደግሞ ‹‹ብራይት ቤካስ›› የሚል እንደሆነ የሥር ዉሳኔ ያሳያል። የአሁን ተጠሪ ስልጣን ባለዉ አካል ይህን ‹‹ብራይት ቤካስ›› /BRIGHT BEKAS/ የሚለዉ የንግድ ምልክት ጥበቃ የተሰጠዉ ሲሆን አመልካች ግን ስልጣን ባለዉ ሳያስመዘግብ ወይም ስልጣን ባለዉ ዘንድ ባላስመዘገበ ‹‹ቤስት ብራይት›› /BEST BRIGHT/ የሚል ምልክት በመጠቀም ምርቶቹን ለገበያ ማቅረቡ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር መፈጸሙን እና ሸማቹን ማህበረሰብ የሚያደናግር እንደሆነ በሥር የዳኝነት አካላት የቀረበዉ የሰነድ ማስረጃ እንደሚያረጋግጥ የሥር ዉሳኔ ያመለክታል።
በልላ በኩል የአሁን አመልካች ምርቶቹን በማሸግ ለገበያ የሚያቀርብባቸዉ የጀሪካን ዲዛይኖች እና የቀለም ዉህድ በቀላሉ የማይለያይ እና ተመሳሳይነታቸዉ የሚጎላ በመሆናቸዉ ሸማቾችን የሚያደናግርና ተጽዕኖ የሚፈጥር ይህ ደግሞ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር መፈጸሙን የሚያረጋግጥ እንደሆነ በሥር የዳኝነት አካል የተረጋገጠ ፍሬ ነገር ነዉ። ስለሆነም ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች የአሁን አመልካች የንግድ ዉድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 8 በመተላለፍ በተጠሪ ላይ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር ተግባር መፈጸሙን የሥር የዳኝነት አካላት በማረጋገጥ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 32 መሰረት ተገቢ እርምጃ ላወሰንበት እንደሚገባ አረጋግጧል።
ይህ ችሎት ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ 10 መሰረት መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመባቸዉን የመጨረሻ ዉሳኔዎችን ከማረም ባለፈ ፍሬ ነገር የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ስለልለዉ፣ በዚህ ምክንያት የሥር የዳኝነት አካላት ያረጋገጡትን ፍሬ ነገር መቀበል አስፈላጊ ነዉ። በመሆኑም የአሁን አመልካች ሸማቾችን የሚያደናግር እና ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር ተግባር በተጠሪ ላይ መፈጸሙን በሥር የዳኝነት አካላት የተረጋገጠዉን ይህ ችሎትም ተቀብሎታል። ስለዚህ ይህ ችሎት በዚህ ረገድ አመልካች ያቀረበዉን ቅሬታ አልተቀበለዉም።
ልላዉ መታየት ያለበት ጉዳይ የሥር የዳኝነት አካላት የአሁን አመልካች የአዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 8 /2፣ ሀ/ በመተላለፍ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር መፈጸሙን ያረጋገጡ ቢሆንም አስተዳደራዊ ቅጣት መወሰናቸዉ ተገቢ ነዉ ወይስ አይደለም?
የሚለዉ ነጥብ ነዉ። የፍድራል የንግድ ዉድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የዳኝነት ችሎት የአሁን አመልካች ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር መፈጸሙ ተረጋግጧል በማለት በአዋጁ አንቀጽ 42 /3/ መሰረት ምርቱን አምርቶ ለገበያ ካቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ከሽያጭ ገቢዉ 5% እንዲቀጣ መወሰኑን የሥር ዉሳኔ ግልባጭ ያሳያል። የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎትም ጉዳዩን በይግባኝ በማየት ግራ ቀኛቸዉን በማከራከር በሰጠዉ ዉሳኔ ይህን የሥር የዳኝነት አካል የዉሳኔ ክፍል ሳያርም ማጽናቱን የሥር ዉሳኔ ያመለክታል። በዚህ ረገድ የንግድ ዉድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 37 መሰረት ክስ የማቅረብ ስልጣን ያለዉ አካል ማየቱ አስፈላጊ ነዉ። በዚህ ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት በባለስልጣኑ የዳኝነት ችሎት አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድና አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲጣል ክስ ላያቀርብ የሚችለዉ የባለስልጣኑ ዓቃቤ ሕግ መሆኑን ያስገነዝባል። በመሆኑም በዚህ ጉዳይ የአስተዳደራዊ ቅጣትን ለማስቀጣት ክስ ማቅረብ ያለበት ዐቃቤ ሕግ ነዉ እንጂ የአሁን ተጠሪ ዳኝነት የሚጠይቅበት እና በዚህም ጥያቄ መነሻነት በአመልካች ላይ አስተዳደራዊ ቅጣት የሚወሰንበት አግባብ የለም። ስለሆነም በዚህ ጉዳይ የባለስልጣኑ ዐ/ሕግ ያቀረበዉ ክስ በልለበት አመልካች ለፈጸመዉ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ዉድድር ተግባር አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲወሰንበት በሕግ ስልጣን የተሰጠዉ ተገቢ የሆነ አካል ክስ ባላቀረበበት ከላይ የተጠቀሱት የዳኝነት አካላት የተጠሪን ጥያቄ ተቀበለዉ አስተዳደራዊ ቅጣት መወሰናቸዉ ከአዋጁ ዓላማ ዉጭ ስለሆነ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ የሚከተለዉ ተወስኗል።
የፍድራል የንግድ ዉድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የዳኝነት ችሎት በመ.ቁ.00041 በ7/1/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ እና የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.120677 በ28/7/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348 /1/ መሰረት ተሻሽሐል።
የፍድራል የንግድ ዉድድር የሸማቾች ጥያቄ ይግባኝ ሰሚ አስተዳደራዊ ፍ/ቤት በመ.ቁ.00007 በ17/3/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348 /1/ መሰረት ተሽሯል።
የፍድራል የንግድ ዉድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የዳኝነት ችሎት እና የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አመልካች ከሽያጭ ገቢዉ 5% አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲቀጣ የሰጡት የዉሳኔ ክፍል ተሽሯል። ነገር ግን እነዚህ የዳኝነት አካላት የወሰኑት ልላዉ የዉሳኔ ክፍል ጸንቷል።
የዚህ ዉሳኔ ግልባጭ ለሥር ፍ/ቤቶች ይድረስ።
ግራ ቀኛቸዉ በዚህ ችሎት የደረሰባቸዉን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸዉ ይቻሉ።
በ2/9/2009 ዓ.ም የተሰጠዉ የአፈጻጸም እግድ በዚህ ዉሳኔ ተነስቷል።
ይጻፍ።