ገንዘብ የተከፈለ መሆኑን የሚገልጽ ሰነድ ወይም ደብዳቤ ሰነዱን ባዘጋጀዉ ወይም ደብዳቤዉን በፃፈዉ ሰዉ ላይ ማስረጃ የሚሆን ስለመሆኑ፡ፍ/ሕ /ቁ 2018(1)
No summary available.
የሰበር መዝገብ ጥር 14 ቀን 2005 ዓ/ም ዳኞች፡- ተገኔ ጌታነህ ተሻገር ገ/ሥላሴ አልማው ወል ዓላ መሐመድ ረታ ቶሎሳ አዳነ ንጉሴ ሙስጠፋ አህመድ አመልካች፡- የአቶ ካሣ አበበ ወራሽ አቶ ሰለሞን ካሣ; ከጠበቃ አስናቀ ስፍራ ጋር ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ አያልነሽ ባይለየኝ ጠበቃ ሰለሞን ተሾመ ቀረቡ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለውን ፍርድ ተሰጥቷል።
በዚህ መዝገብ የቀረበው ክርክር በልላ ሰው ሃብት አላግባብ መበልፀግ የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኗ ተጠሪ በፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ባቀረቡት ክስ መነሻ ነው። የክሱ ይዘትም ባጭሩ የስር ተከሣሽ (የአሁኑ ተጠሪ አውራሽ) አቶ ካሣ አበበ ገዳሙ ንብረትነቱ የከሣሽ የሆነ የሰ.ቁ. 3-16729 የሆነ የጭነት ተሽከርካሪ ወስደው ባለመመለሣቸው ቀደም ሲል በመ.ቁ. 03016 በተደረገ ክርክር ተከሣሽ ተሽከርካሪውን እንዲመልሱና እስከ 12/11/92 ዓ.ም ላለው ጊዜ ከተሽከርካሪው ያገኙትን ጥቅም ብር 366,000 ለከሣሽ እንዲከፍሉ መወሰኑን በውሣኔው መሰረት ከሣሽ መኪናውን በ01/10/98 ዓ.ም መረከባቸውን የተከሣሹን ንብረት በአፈፃፀም አሽጠው ብር 497,000 በእጃቸው መግባቱን ከዚህ ገንዘብ ላይ ከልዩ ልዩ ወጭ ጋር ተከሣሽ የሚከፍሉትን ገንዘብ ብር 413,580 ሲቀነስ ብር 83,470 በትርፍነት በእጃቸው የሚገኝ መሆኑንና በቀድሞው ክስ እና ውሣኔ ውስጥ ያልካተተውን የመኪናውን የገቢ ጥቅም በክስ መጠየቅ እንደሚችሉ በቀድሞው ውሣኔ ላይ መብት የተጠበቀላቸው መሆኑን በዝርዝር የሚገልጽ ሆኖ ተሽከርካሪው የሚያስገኘው ወርሀዊ የተጣራ ገቢ ብር 3000 (ሶስት ሺህ) መሆኑ በቀድሞው ክርክር ጊዜ በማስረጃ በተረጋገጠው መሰረት ከ30/10/92 ዓ.ም እስከ 01/10/98 ዓ.ም ድረስ ላለው የ71 ወር ጊዜ ብር 213‚000 (ሁለት መቶ አስራ ሶስት ሺህ) የሚመጣ በመሆኑ በትርፍ በእጃው የሚገኘው የተከሣሽ ገንዘብ ተቀናሽ ተደርጐ ተከሣሽ ብር 129,530 (አንድ መቶ ሃያ ዘጠኝ ሺህ አምስት መቶ ሰላሣ) እንዲከፍሉ ይወሰንልኝ የሚል ነው።
የሥር ተከሣሽ በበኩላቸው ክሱ በፍ.ህ.ቁ. 2143(1) መሰረት በሁለት አመት ይርጋ እንደሚታገድ እና ክስ የማቅረብ መብት የሚመነጨው ከሕግ እንጂ ከፍ/ቤቱ ውሣኔ እንዳልሆነ በመግለጽ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርበው በአማራጭም በፍሬ ነገሩ ተከራክሯል።
ጉዳዩ የቀረበለት ፍ/ቤትም ከውሉ ውጭ ኃላፊነት ክስን አስመልክቶ በፍ/ህ/ቁ. 2143(1) የተደነገገው የሁለት አመት የይርጋ ጊዜ አላግባብ መበልፀግ አስመልክቶ በሚቀርብ ክስ ጉዳዩ ተፈፃሚነት እንደልለው ከፍ/ህ/ቁ. 2143(3) ድንጋጌ መገንዘብ የሚቻል በመሆኑ የይርጋ መቃወሚያ ተቀባይነት የለውም በማለት ብይን ከሰጠ በኃላ በቀጣይ ቀጠሮዎችም የፍሬ ጉዳይ ክርክሩን መርምሮ ከ12/11/92 ዓ.ም ጀምሮ ከሣሽ መኪናውን እስከተረከቡበት 01/10/98 ዓ.ም ድረስ ያለው ገቢ በወር በብር 3000 /ሶስት ሺህ/ ተሰልቶ በትርፍነት በከሣሽ እጅ የሚገኘው ገንዘብ ተቀናሽ ከተደረገ በኃላ ቀሪውን ብር 129,530 (አንድ መቶ ሃያ ዘጠኝ ሺህ አምስት መቶ ሰላሣ) ከወለድና ልዩ ልዩ ወጪዎች ጋር ተከሣሽ ለከሣሽ እንዲከፍሉ ውሣኔ ሰጥቷል። የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤትም የአሁኑ አመልካች ያቀረቡለትን ይግባኝ ዘግቶ አሰናብቷል።
አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡትም በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሣኔ እና ትእዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለባቸው በመሆኑ ላሻሩ ይገባል በማለት ሲሆን ግራ ቀኙ የጽሑፍ ክርክር ተለዋውጠዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ባጭሩ ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም ይርጋውንም ሆነ ፍሬ ነገሩን አስመልክቶ በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ወይስ አይደለም የሚል ጭብጥ መሰረት በማድረግ ጉዳዩን መርምረናል።
በዚህም መሰረት የይርጋ ጉዳይን በተመለከተ አመልካች አጥብቀው የሚከራከሩት በፍ.ሕ.ቁ. 2143 (1) ሥር የተደነገገው የሁለት አመት የይርጋ ጊዜ አላግባብ መበልፀግን አስመልክቶ በሚቀርቡ ክሶች ላይ ጭምር ተፈፃሚነት እንደሚኖረው የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ቀደም ሲል በመ.ቁ. 34406 በ07/08/2000 ዓ.ም የትርጉም አስገዳጅነት ያለው ውሣኔ ሰጥቶ እያለ የሥር ፍ/ቤቶች ይህንን ውሣኔ ወደ ጐን በመተው በፍ/ሕ/ቁ.
2143(1) የተመለከተው የሁለት አመት የይርጋ ጊዜ ለክርክር በቀረበው ጉዳይ ተፈጽሚነት የለውም ሲሉ የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ነው በማለት መሆኑ እና ተጠሪው የሚከራከሩት ደግሞ በፍ.ሕ.ቁ. 2143(1) የተመለከተው የይርጋ ዘመን ለጉዳዩ ተፈፃሚነት ላኖረው አይገባም በማለት መሆኑን ተገንዝበናል።
እኛም አላግባብ መበልፀግን አስመልክቶ ለሚቀርቡ ክሶች አግባብነት ላኖረው የሚገባውን የይርጋ ዘመን ለመለየት ያስችለን ዘንድ የግራ ቀኙን ክርክር እና የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ.ቁ. 34406 የሰጠውን ውሣኔ አግባብነት ካላቸው የፍ.ሕጉ ድንጋጌዎች ጋር አገናዝቦ ማየቱን ተገቢ ሆኖ አግኝተነዋል። በዚህም መሰረት የፍ.ሕ.ቁ. 2143 በን.ቁ (1) “ሥር ተበዳዩ ክስ ማቅረብ የሚችለው ካሣ የሚጠይቅበት ጉዳት ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2 አመት ድረስ ነው” በማለት በን.ቁ (2) “ሥር ስለሆነም ጉዳቱ በወንጀል የሚያስቀጣ ሆኖ የይርጋ ዘመኑ ርዝመት የበለጠ እንደሆነ የካሣው ጉዳይ ክስ የይርጋ ዘመን ልክ በዚሁ መሰረት ይሆናል” በማለት እና በን.ቁ.(3) ስር ደግሞ “ተበዳዩ የራሱ የሆኑትን ነገሮች የሚጠይቅበትና ያለአግባብ ስለመበልፀግ በተነገሩት ድንጋጌዎች መሰረት የሚከራከርበት መብቱ የተጠበቀ ነው” በማለት ድንግጐ ይገኛል። የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ.ቁ. 34406 የሰጠው ውሣኔ ደግሞ “……. ያለአግባብ ስለመበልፀግ የሚናገረው ምእራፍ የካሣ ጥያቄ የሚቀርብበትን የጊዜ ገደብ አይናገርም” ነገር ግን አለአግባብ ስለመበልፀግና ከውል ውጭ ስለሚደርስ ኃላፊነት የሚናገሩት ድንጋጌዎች በአንድ አንቀጽ ውስጥ ተካተው መገኘታቸው እንዲሁም ያለአግባብ መበልፀግም ከውል ውጪ የሚደርስ ኃላፊነት በመሆኑ ከውል ውጭ በሚደርስ ኃላፊነት ስር የተመለከተው የይርጋ ዘመን በተመሣሣይ አላግባብ መበልፀግን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት ላኖረው ይገባል…” የሚል ነው።
በሰበር ችሎቱ ውሣኔ ውስጥ አንደተገለፀው ከውል ውጭ ስለሚደርስ ኃለፊነት እና አላግባብ ስለመበልፀግ የሚናገሩት ድንጋጌዎች የሚገኙት በአንድ አንቀጽ ስር ነው።
ይሁን እንጂ በፍ.ብሕር ሕጋችን ውስጥ የተለያየ የይርጋ ዘመንን የሚያቋቁሙ ድንጋጌዎች በአንድ አንቀጽ ውስጥ ተካትተው የሚገኙባቸው አጋጣሚዎች በመኖራቸው ድንጋጌዎቹ የሚገኙት በአንድ አንቀጽ ስር የመሆኑ ጉዳይ ብቻውን ተፈፀሚነት ላደርግባቸው የሚገባው የይርጋ ዘመን ተመሣሣይ መሆን አለበት ወደሚል ድምዳሜ መድረስ የሚያስችል አይሆንም።
ከውል ውጪ የሚደርስ ኃለፊነት እና አላግባብ መበልፀግን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በአንድ አንቀጽ ውስጥ እንዲካተቱ የተደረገው የሚጋሯቸዋው ተመሣሣይ ባህሪያት ስላሐቸው እንደሆነ ይታመናል። ይርጋን በተመለከተ ግን የፍ.ሕ.ቁ. 2143(3) ጉዳዩን በተለየ ሁኔታ እና በግልጽ የደነገገ በመሆኑ በፍ.ሕ.ቁ. 2143(1) የተመለከተው የሁለት አመት የይርጋ ዘመን አላግባብ መበልፀግ አስመልክቶ በሚቀርቡ ክሶች ጉዳይ ተፈፃሚነት እንዳማይኖረው ተገንዝበናል።
ይህ ከሆነ ደግሞ አላግባብ ስለመበልፀግ የሚቀርቡ ክስችን አስመልክቶ በፍ.ሕጉ የተመለከተ የይርጋ ዘመን አለ ወይስ የለም ካለ ምን ያህል ወይም ስንት ነው የሚል ጥያቄ መነሣቱ የማይቀር ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ በቅድሚያ መታየት የሚገባቸው አላግባብ በመበልፀግን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ሲሆኑ ከእነርሱ መካከል ይርጋን የሚመለከት ድንጋጌ የለም። ክርክር የቀረበበትን ጉዳይ የሚገዛው የሕግ ክፍል ይርጋን አስመልክቶ በተለይ የሚያስቀምጠው የጊዜ ገደብ በልለ ጊዜ በፍ.ሕ.ቁ. 1677(1) የተመለከተውን መርህ በመከተል ተፈፃሚ ላደረግ የሚገባው በፍ.ሕ.ቁ. 1845 የተመለከተው የአስር አመት የይርጋ ዘመን ስለመሆኑ የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ቀደም ሲል በመ.ቁ. 31748 በ28/06/2000 ዓ.ም የትርጉም አስገዳጅነት ያለው ውሣኔ ሰጥቷል።
በልላ በኩል አላግባብ መበልፀግን አስመልክቶ በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት ያለው የሁለት አመት የይርጋ ጊዜ ስለመሆኑ የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ውሣኔ ሰጥቶ የነበረ መሆኑን ቀደም ሲል ተገልጽአል። የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፍድራል ወይም የክልል ፍ/ቤት ላይ አስገዳጅነት እንደሚኖረው፤ ሆኖም የሰበር ችሎቱ በልላ ጊዜ በተመሣሣይ ጭብጥ የተለየ ትርጉም ላሰጥ እንደሚችል የፍድራል ፍ/ቤቶች አዋጅን እንደገና ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) ስር ተደንግጓል።
እኛም ይህንኑ ድንጋጌ መሰረት በማድረግ በዚህ መዝገብ የተያዘውን ክርክር ጨምሮ አላግባብ በመልፀግን አስመልክቶ በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት ላኖረው የሚገባው የአስር አመት የይርጋ ዘመን መሆኑን ተገንዝበናል።
በመሆኑም ከላይ በዝርዝር በተገለፁት ምክንያቶች በፍ.ሕ.ቁ. 2143(1) የተመለከተው የይርጋ ዘመን አላግባብ መልፀግን አስመልክቶ በሚቀርቡ ክሶች ላይ ተፈፃሚነት የለውም በማለት የሥር ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ አልተገኘም።
በፍሬ ጉዳይ ረገድ የቀረበውን ክርክር በተመለከተ አመልካች የተጠሪ ንብረት በሆነ ተሽከርካሪ ገቢ አላግባብ የበለፀጉ መሆኑ እና የተሽከርካሪው የወር የተጣራ ገቢ በቀድሚው ክርክር ጊዜ ተረጋግጦ ውሣኔ አርፎበታል። ተሽከርካሪው በመሐል በልላ ግለሰብ እጅ ገብቶ ነበረ በማለት አመልካች ያቀረቡትን ክርክር በተመለከተ የሥር ፍ/ቤት በውሣኔው ላይ እንደገለፀው ግለሰቡን በክስ መጠየቅ የሚችሉ ከመሆኑ ውጪ ጉዳዩ በተጠሪ መብት ላይ ለውጥ ማስከተል የሚችል አይደለም።
በዚህም ሁኔታ በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሣኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ስላልተገኘ የሚከተለውን ውሣኔ ተሰጥቷል።
ው ሣ ኔ
በፍ.ሕ.ቁ. 2143(1) በተመለከተው የይርጋ ዘመን አላግባብ መበልፀግን አስመልክቶ በሚቀርቡ ክሶች ላይ ተፈፃሚነት የለውም በማለት የፍ/የመ/ደ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 184727 በ24/10/03 የሰጠው ብይን እና ፍሬ ነገሩን አስመልክቶ በዚህ በመ.ቁ. 184727 በ17/04/04 የሰጠው ውሣኔ እንዲሁም የፍ/ከ/ፍ/ቤት በመ.ቁ. 118043 በ27/07/04 ዓ.ም የሰጠው ውሣኔ በፍ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ. 348/1 መሰረት ፀንቷል።
አላግባብ መበልፀግን አስመልክቶ በሚቀርቡ ጉዳዩች ላይ ተፈፃሚነት ስለሚኖረው የይርጋ ዘመን የፍ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመቁ. 34406 ሰጥቶት የነበረው የሕግ ትርጉም በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(1) መሰረት በመለወጥ አላግባብ መበልፀግን አስመልክቶ በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት ያለው የይርጋ ዘመን አስር አመት ነው በማለት ወስነናል።
በሰበር ደረጃ ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሣራ ግራ ቀኙ የየራሣቸውን ይቻሉ።
ውሣኔ ያገኘ ስለሆነ መዝገቡ ተዘግቷል።
No topics extracted.