አንድ ኩባንያ በደረሰበት ችግር ምክንያት ከገበያ እንዳይወጣ እና ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል ተሰጥቶት የነበረው የኪሣራ ማሸጋገር መብት፤ በቀጥታ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የተለወጠ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ኩባንያው አስቀድሞ ከነበረበት ኪሣራ ወጥቶ በተጨባጭ ያደገ መሆኑ የሚገመት ከሆነ በዚያው የግብር ዘመንም ሆነ ቀደም ባሉት የግብር ዓመታት የደረሰበትን ኪሣራ በሚመለከት አስቀድሞ ተሰጥቶት የነበረው ኪሣራ የማካካስ መብት የሚቋረጥ ስለመሆኑ፡-አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 28(1)(2) 131900 የኢትዮጲያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን እና የኢትዮጲያ ቅመማቅመም ፋብሪካ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር ጥቅምት 22/2010 ዓ.ም 73. አንድ ግብር ከፋይ ለንግድ ስራው ዋስትና ለመስጠትና እንቅስቃሴውን ለማስቀጠል የተደረጉ ወጪዎች ተቀናሽ እንዲደረግለት ለንግድ ስራው ያወጣውን ወጪ ማስረዳት የሚችለው በሚያቀርበው በስሙ ወጪ በሆነ ህጋዊና ተቀባይነት ያለው ደረሰኝ ስለመሆኑ፤- XLI የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀፅ 20 የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀፅ 22(2) ፤ደረሰኝ አያያዝና አጠቃቀም መመሪያ ቁጥር 28/2001 አንቀፅ 4(1)
No summary available.
መ/ ጥቅምት 22 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- ዳኜ መላኩ እንዳሻው አዳነ እትመት አሰፋ ሸምሱ ሲርጋጋ ዋዝሞ ዋሲራ አመልካች፡- የኢትዮጲያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ነ/ፈጅ ኃይለመለኮት አበበ ተጠሪ፡- የኢትዮጲያ ቅመማቅመም ፋብሪካ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር
ተጠሪ በአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 28 መሰረት በተሰጠው የኪሣራ ማሸጋገር መብት መሰረት የኪሣራ ማካካሻ ከተደረገ በኋላ ቀሪው የትርፍ ግብር ብር 847,134.47 /ሥምንት መቶ አርባ ሰባት ሺህ አንድ መቶ ሰላሣ አራት ብር ከአርባ ሰባት ሳንቲም/ ለግብር አስገቢው መስሪያ ቤት ገቢ ከተደረገ በኋላ ተጠሪ የስም እና የካፒታል ለውጥ አድርጓል ከሚል መነሻነት አመልካች መሥሪያ ቤት የኪሳራ ማካካሻ አልቀበልም ማለቱ ተገቢ ስላልሆነ ላሻር ይገባል በማለት ያቀረበውን ቅሬታ የተመለከተው የፍድራል ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ የተጠሪ ስም እና የካፒታል መጠን የተቀየረው ሐምል 02 ቀን 2004 ዓ.ም በመሆኑ እና አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 28/1 መሰረት በአንድ የግብር ዘመን ግብር የሚከፈልበት ገቢ በሚወሰንበት ጊዜ በዚያው የግብር ዘመን ውስጥ በሚቀጥሉት የግብር ዘመናት ከተገኘው ግብር የሚከፈልበት ገቢ ላይ የሚካካስ ይሆናል በማለት የደነገገ በመሆኑ ተጠሪ ኪሳራው ላካካስለት ይገባል በማለት ወስኗል።
አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ አቅርቧል። ይግባኙ የቀረበለት ፍ/ቤት ግራቀኙን ካከራከረ በኋላ የተጠሪ የስም እና የካፒታል ለውጥ የተደረገው የ2004 ዓ.ም የግብር ዘመን በተዘጋ በሁለተኛው ቀን ሐምል 02 ቀን 2004 ዓ.ም ነው፤እንደ ተጠሪ ዓይነቱ ድርጅት የካፒታል መጠን ከ25% በላይ ለማሣደግ ውስብስብ ሂደቶችን የሚጠይቅ ሆኖ ሳለ ተጠሪ የበጀት ዘመኑ ከተዘጋ ከአንድ ቀን በኋላ የካፒታል ለውጡን ያደረገ መሆኑ እና ድርጅቱ ቀደም ባሉት ዘመናት ለደረሰበት ኪሣራ ማካካሻ ሲደረግለት የነበረ መሆኑ ሲታይ ተጠሪ ግብርን ለማስቀረት የኪሳራ ማካካሻ ለማግኘት ከቅን ልቦና ውጪ አስቦ የፈጸመው መሆኑን የሚያሳይ ነው፤በመሆኑም ተጠሪ ግብርን ለማስቀረት ከቅን ልቦና ውጪ በመንቀሳቀስ የበጀት ዓመቱ ከተዘጋ ከአንድ ቀን በኋላ ለውጡን ያደረጉ ቢሆኑ ለውጡ የተደረገው በ2004 ዓ.ም እንደሆነ ስለሚቆጠር በአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 28/2 መሰረት ቀደም ሲል ለነበሩት ዓመታት የተሰጠው የኪሣራ ማካካሻ መብት የተቋረጥ ነው በማለት የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤው የሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል።
ተጠሪ በበኩሉ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ አቅርቧል። የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ቸሎት ግራቀኙን ካከራከረ በኋላ የተጠሪ ሥም እና ካፒታል የተለወጠው ሐምል 02 ቀን 2004 ዓ.ም በ2005 ዓ.ም በጀት ዘመን በመሆኑ፤የኪሣራ ማካካሻ በማድረግ ሂሳቡን የዘጋው ከ2001 እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ በመሆኑ እና የኪሳራ ማካካሻ ካደረገ በኋላ ያገኘው ትርፍ ለአመልካች የከፈለ በመሆኑ ከ2005 ዓ.ም በፊት ላለው ዕዳ ላጠየቅ አይችልም በማለት ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመሻር የግብር ይግባኝ ሰሚው ጉባኤ የሰጠውን ውሳኔ አጽንቷል። የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይህን ውሳኔ በመቃወም ነው።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- የኢትዮጲያ ቅመማቅመም ፋብሪካ ከመንግሥት ወደ ግል ባለቤትነት በሽያጭ ሲዘዋወር በአቶ አካሉ ገለታ በብር 18,600,000 /አሥራ ሥምንት ሚልየን ሥድሥት መቶ ሺህ ብር/ ተገዝቶ በዚሁ ሥሙ እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ ቆይቶ ሰኔ 26 ቀን 2004 ዓ.ም በተፈረመ እና ሐምል 02 ቀን 2004 ዓ.ም በውልና ማስረጃ በጸደቀ ጽሑፍ እና መተዳደሪያ ደንብ ቀደም ሲል ፋብሪካው የተገዛበት ገንዘብ እና በወ/ሮ መሰለች ኪዳኔ በተዋጣ ብር 15,600,000 / አሥራ አምሥት ሚልየን ሥድስት መቶ ሺህ ብር / በድምሩ ብር 34,200,000 / ሰላሳ አራት ሚልዮን ሁለት መቶ ሺህ ብር / በሆነ ካፒታል የኢትዮጲያ ቅመማቅመም ፋብሪካ ሀላፊነቱ የግል ማሕበር በሚል የተቋቋመ በመሆኑ ቀደም ሲል የነበረውን ፋብሪካ የካፒታል ባለቤትነት ድምጽ የመሥጠት መብት በዋጋ ወይም በቁጥር ከ25% በላይ ለውጦታል። የ2004 ዓ.ም የግብር ዘመን ግብር የሚከፈለው ከሐምል 01 ቀን 2004 ዓ.ም እሥከ ጥቅምት 30 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ በመሆኑ ተጠሪ የ2002 ዓ.ም የ2004 ዓ.ም የግብር ዘመን ሲከፍል ኪሳራውን ያሸጋገረበት ጊዜ ተጠሪ በካፒታል ከ25% በላይ በተለወጠበት ጊዜ ነው። አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 28/2 የካፒታል ባለቤትነት ወይም ድምጽ የመሥጠት መብት ከ25% በላይ ከተለወጠ ድርጅቱ በዚያው የግብር ዘመንም ሆነ ቀደም ባሉት የግብር ዓመታት የደረሰበትን ኪሣራ በሚመለከት የኪሣራ ማሸጋገር መብቱ እንደሚቋረጥ በግልጽ የደነገገ ሆኖ ሳለ የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተጠሪ ሥም እና ካፒታል የተለወጠው ከ2001 እሥከ 2004 ዓ.ም ድረስ ባሉት የግብር ዘመናት ግብር ከፍሎ አጠናቆ ከዘጋ በኋላ ነው በማለት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ሥሕተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል የሚል ነው።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ የተጠሪ የኪሣራ ማሸጋገር መብት የተቋረጠ መሆን አለመሆኑ ከአዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 28 (1) እና (2) ድንጋጌ አንጻር ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ በዚህ ችሎት አንዲታይ ተደርጓል። ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎም ግራቀኙ በጽሑፍ አንዲከራከሩ ተደርጓል።
ተጠሪ በሰጠው መልስ አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 28/2 ሕጉ ባስቀመጠው መሥፈርት እና መጠን በግብር ዘመኑ ውስጥ ለውጥ ቢደረግ በግብር ዘመኑም ሆነ ቀደም ባሉት ዓመታት የደረሰበትን ኪሣራ በሚመለከት ኪሣራ የማሸጋገር መብቱ ይቋረጣል የሚለው ድንጋጌ ለውጡ የተደረገው በግብር ዘመኑ ውስጥ መሆን እንዳለበት በግልጽ አስቀምጧል። በኢትዮጲያ ሕግ የግብር ዘመን የሚባለው ከሐምል 01 ቀን እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ ነው። በሕግም ሆነ በአፈጻጸም አንደሚታየው የግብር መክፈያ ወቅት የግብር ዘመኑ አልቆ የቀጣዩ የግብር ዘመን መጀመሪያ ወር ላይ በመሆኑ በ2004 የግብር ዘመን ለተሰራ ሥራ ግብርን አስታውቆ የሚከፈለው በ2005 ዓ.ም የግብር ዘመን መጀመሪያ ወራት ላይ ነው። በመሆኑም በአዋጁ አንቀጽ 28/2 መሰረት የኪሣራ ማሸጋገር መብት ላቋረጥ የሚችለው የ2005 ዓ.ም የግብር ዘመን ለመክፈል ስንቀርብ እንጂ የ2004 ዓ.ም ግብር ለመክፈል ስንቀርብ አይደለም በማለት የአመልካች አቤቱታ ውድቅ ላደረግ ይገባል በማለት ተከራክሯል።
የጉዳዩ አመጣጥ በአጭሩ ከላይ የተገለጸው ነው። እኛም እንዲጣራ የተያዘውን ነጥብ ከግራቀኙ ክርክር እና ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ሕጎች ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው መርምረነዋል።
የኢትዮጲያ ቅመማቅመም ፋብሪካ የካፒታል መጠኑን ከ25% በላይ በማሳደግ የኢትዮጲያ ቅመማቅመም ፋብሪካ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሚል የተቀየረ መሆኑን ግራ ቀኙን አላከራከረም። በየደረጃው ያሉ ፍ/ቤቶች የተለያዩ ውሳኔዎችን ላሰጡ የቻሉት የተጠሪ የካፒታል መጠኑ ከ25% በላይ ያደገው በ2004 ዓ.ም ወይም በ2005 ዓ.ም የበጀት ዓመት ነው ከሚል መነሻነት ቢሆንም ምላሽ የሚያስፈልገው ዋነኛ ጭብጥ በአዋጁ አንቀጽ 28 ላይ የተሰጠው ኪሳራን የማሸጋገር መብት በመብቱ ተጠቃሚ የሆነው ኩባንያ አስቀድሞ ከነበረበት ኪሣራ በመውጣት የካፒታል ባለቤትነት መብቱ ወይም ድምጽ የመስጠት መብቱ ከ25% በላይ ባደገ ጊዜ ቀሪ ላደረግ ይገባል? ወይስ አይገባም? የሚለው ነው።
በመሰረቱ በአዋጁ የተሰጠው የኪሣራ ማሸጋገር መብት ኩባንያዎች ኪሣራ ውስጥ በገቡ ጊዜ ከገቡበት ኪሣራ እንዲወጡ ለማበረታታት እና በገበያው ተወዳዳሪ በመሆን ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ ስለመሆኑ ከኪሣራ ማሸጋገር መብት ዓላማ እና ከግብር አዋጁ አጠቃላይ ይዘት መገንዘብ ይቻላል። ኩባንያው በኪሣራ ማሸጋገር መብት ተጠቃሚ ከሆነ በኋላ ከነበረበት ኪሣራ በመውጣት የካፒታል ባለቤትነት መብቱ ወይም ድምጽ የመስጠት መብቱ ከ25% በላይ ያደገ ለመሆኑ በተጨባጭ ከተረጋገጠ አስቀድሞ አግኝቶት የነበረው የኪሣራ ማሸጋገር መብት ቀሪ ላሆን ይገባል? ወይስ አይገባም?
የሚለው ነጥብ ምላሽ ላያገኝ የሚገባው መሰረታዊ ነጥብ ነው። ለዚህ መሰረታዊ ነጥብ ምላሽ ለመሥጠት በአዋጁ የኪሣራ ማሸጋገር መብት አስመልክቶ የተቀመጠውን ድንጋጌ መመልከት አስፈላጊ ነው።
አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 28/1 በአንድ የግብር ዘመን ግብር የሚከፈልበት ገቢ በሚወሰንበት ጊዜ በዚያው የግብር ዘመን ውስጥ የታየው ኪሣራ በሚቀጥሉት ሦስት የግብር ዘመናት ከተገኘው ግብር የሚፈጸመው በመጀመሪያ ያጋጠመውን ኪሣራ በኋላ ካጋጠመው ኪሳራ አስቀድሞ በማካካስ ነው በማለት ይደነግጋል። የዚሁ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 2 ድንጋጌም በአንድ የግብር ዘመን ውስጥ የአንድ ኩባንያ የካፒታል ባለቤትነት ወይም ድምጽ የመሥጠት መብት በዋጋ ወይም በቁጥር ከ25% በላይ በቀጥታ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የተለወጠ እንደሆነ ኩባንያው በዚያው የግብር ዘመንም ሆነ ቀደም ባሉ የግብር ዓመታት የደረሰበትን ኪሣራ በሚመለከት የንኡስ አንቀጽ አንድ ድንጋጌ ተፈጻሚነት ያቋርጣል በማለት ይደነግጋል። ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘት መገንዘብ የሚቻለው ኩባንያው በደረሰበት ችግር ምክንያት ከገበያ እንዳይወጣ እና ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል ተሰጥቶት የነበረው የኪሣራ ማሸጋገር መብት የካፒታል ባለቤትነት ወይም ድምጽ የመሥጠት መብት በዋጋ ወይም በቁጥር ከ25% በላይ በቀጥታ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የተለወጠ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ኩባንያው አስቀድሞ ከነበረበት ኪሣራ ወጥቶ በተጨባጭ ያደገ መሆኑ የሚገመት በመሆኑ በዚያው የግብር ዘመንም ሆነ ቀደም ባሉት የግብር ዓመታት የደረሰበትን ኪሣራ በሚመለከት አስቀድሞ ተሰጥቶት የነበረው ኪሣራ የማካካስ መብት የሚቋረጥ መሆኑን ነው። በመሆኑም ተጠሪ ለውጡ የተደረገው በ2004 ዓ.ም የግብር ዘመን ስላልሆነ አስቀድሞ ያገኘሁት ኪሳራ የማካካስ መብት ላቋረጥ አይገባም በማለት የሚያቀርበው ክርክር የኪሳራ መብት ዓላማን ያላገናዘበ ነው። በመሆኑም ይግባኝ ሰሚው ጠቅላይ ፍ/ቤት ጉዳዩን በዚህ አግባብ በማየት መወሰን ሲገባው ለውጡ የተደረገው በ2005 ዓ.ም የግብር ዓመት ሰለሆነ የተጠሪ የኪሳራ ማካካሻ መብት ላቋረጥ አይገባም በማለት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ሥህተት የተፈጸመበት ሆኖ አግኝተነዋል። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ. ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 348/1 መሰረት ተሽሯል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ. ጥር 12 ቀን 2008 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 348/1 መሰረት ጸንቷል።
ግራቀኙ በዚህ ፍ/ቤት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪ የየራሣቸውን ይቻሉ።