No summary available.
ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- ፀጋይ አስማማው አልማው ወል አብርሃመሰለ ጳውሎስ ኦርሺሶ ሰናይት አድነው አመልካቾች፡- 1.አቶ ክንፈ ሐጎስ 2. ቄስ ወረደ ሐጎስ ከጠበቃቸው ሃይለ ገብረማርያም ጋር 3. ወ/ሮ ለተብርሃን ገ/ሂወት ቀረቧል።
ተጠሪ፡- ወ/ሮ ዛፉ ሐጎስ - ቀረቡ።
መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካቾች የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልን በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በትግራይ ብ/ክ/መ/ በመቐለ ከተማ በዓይደር ክፍለ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው። በሥር ፍርድ ቤት የአሁን አመልካቾች ከሳሾች ተጠሪ ደግሞ ተከሳሽ ነበሩ። የክሱ ይዘትም አመልካቾች ለተጠሪ ተቃዋሚ ሆነው ባቀረቡበት የውርስ ማጣራት መቃወሚያቸው ውድቅ በማድረግ ያቀረቡት ውርስ ማጣራት ፀድቆ የወንድማቸው የወራሽነት ማስረጃ የተሰጣቸው መሆኑ በመግለፅ ወንድማቸው አቶ ዮሴፍ ሐጎስ በህይወት እያለ በመቐለ ከተማ ዓይደር ክፍለ ከተማ ቀበል ሰርፀ የሚገኝ መኖሪያ ቤት ስፋቱ 250 ካ/ሜ ግምቱ ብር 300,000.00 /ሶስት መቶ ሺህ ብር/ የሆነው ከተጠሪ ትዳር ከመመስረታቸው በፊት የተፈራ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ የወራሾች ስለሆነ ተጠሪ ከዚህ ቤትና ቦታ እንዲወጡና ልላ የውርስ ዕቃ ድርሻ እንዲያስረክቡን በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል።
የአሁን ተጠሪ ለክሱ የሰጡት መልስ ከ1989 ዓ.ም እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ እንደ ባልና ሚስት ሆነን አንድ ላይ እየኖርን ቆይተን በህዳር 1996 ዓ.ም እስከ እለተ ሞታቸው 2005 ዓ.ም ከአቶ ዮሴፍ ሐጎስ ጋር በጋብቻ ስለነበርን በኤርትራ የሚኖሩ ክብሮም ዮሴፍና ዘካሪያስ ዮሴፍ የተባሉ የሟች ልጆች በሟች የሚታወቁ የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እንዲያካፍሉኝ ለመቐለ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ አቅርቤ፤ፍርድ ቤቱም አጣርቶ ለክርክር ምክንያት የሆነው ቤትና ቦታ ሆነ ልላ የሟች ሀብት ግማሹ ለተጠሪ ግማሹ ደግሞ ለሟች ወራሾች እንዲሆን ወስኗል። የሟች ልጆች እያሉ አመልካቾች ወራሾች ላሆኑ ስለማይችሉ ለመክሰስ መብት የልላቸውና ጉዳዩ በፍርድ ያለቀ ነው በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን በፍሬ ነገሩ የሰጡት መልስ ደግሞ ለክርክር መነሻ የሆነው ቤትና ቦታ የባልና ሚስት የጋራ ንብረት እንጂ የሟች የግል ንብረት አይደለም፤ በሽምግልናም የጋራ ንብረት መሆኑ ተረጋግጧል። ስለዚህ የቀረበው ክስ ውድቅ በማድረግ ወጪና ኪሳራ እንዲከፍሉ ተብሎ እንዲወሰንላቸው የመከላከያ መልሳቸው አቅርበዋል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ የተመለከተው ፍርድ ቤቱም በመጀመሪያ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለኝም በማለት ዘግቶት እንደነበረ ነገር ግን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣንህ ነው በማለት በነጥብ ከተመለሰ በኋላ መቃወሚያዎቹ በብይን ውድቅ በማድረግ የግራ ቀኙ ክርክር ከሰማና ማስረጃ ከመዘነ በኋላ ለክርክር ምክንያት የሆነው ቤትና ቦታ በከፍተኛ መቐለ ከተማ ፍርድ ቤት ግማሹ የሟች አቶ ዮሴፍ ልጆች ቀሪው ግማሽ ደግሞ ለተጠሪ እንዲሆን ተወስኖ በዚሁ ውሳኔ መሰረት በስማቸው የተመዘገበ በመሆኑና የከፍተኛ ፍርድ ውሳኔ እስካልተሻረ ድረስ አመልካቾች ሟች ልጆች የለውም በማለት ያቀረቡት ክርክርና የጠየቁት ዳኝነት አይገባቸውም ሲል ወስኗል።
የአሁን አመልካቾች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለመቐለ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱም አመልካቾች የሟች ወራሾች መሆናቸው የሚያረጋግጥ የፍርድ ቤት ውሳኔ ቅጂ ስላቀረቡ ተጠሪ በዚሁ የውርስ ማጣራት መቃወሚያ አቅርበው ውድቅ መደረጉ፤በመቐለ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ ክብሮም ዮሴፍ እና ዘካሪያስ ዮሴፍ ራሳቸው ወይም በወኪላቸው ዳኝነት ጠይቀው ወይም ተከራክረው ሳይሆን ተጠሪ ራሳቸው በይዞታቸው ለሚገኘው ንብረት እነዚህ የሟች ልጆች ባለእኩል ናቸው በሚል በእነርሱ ላይ ክስ መስርተው በልሉበት የተሰጠ ውሳኔ ስለሆነ አመልካቾች ነን ብለው ቢያረጋግጡም በቀጥታ ወራሾች አለን ብለው የቀረበ ተቃውሞ ስለልለ ክብሮምና ዘካሪያስ ቀጥታ ወራሾች መሆናቸው ያቀረቡት የውርስ ማስረጃ ሆነ ክርክር ስለልለ ህጋዊ ወራሾች ናቸው ለማለት ስለማይቻል፤አመልካቾች ግን የፍርድ ቤት የውርስ ማስረጃ ስላቀረቡ ወራሾች የማይሆኑበት ህጋዊ ምክንያት የለም በሚል ምክንያት የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር ለክርክር ምክንያት የሆነው ቤትና ቦታ ግማሹ አመልካቾች በወራሽነታቸው፤ ግማሹ ደግሞ ለተጠሪ እንዲሆን ይገባል ሲል ወስኗል።
የአሁን ተጠሪ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙ ክርክር ከሰማ በኋላ የሟች 1ኛ ደረጃ ወራሾች የሆኑ የሟች ልጆች መኖራቸው የፍርድ ቤት ውሳኔና አፈፃፀም ትእዛዝ ተረጋግጦ እያለ ፤ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔና ትእዛዝ ደግሞ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ባልተቀየረበት 1ኛ ደረጃ ወራሾች እንደልሉ ታስቦ የሟች ሀብት ድርሻ ለ2ኛ ደረጃ ለሆኑ ወራሾች እንዲሆን የተሰጠ ውሳኔ ህጋዊነት ስልለው ላሻር ይገባል በማለት የወረዳ ፍርድ ቤት ውሳኔ አፅንቶታል። የአሁን አመልካቾች ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኘም።
No topics extracted.
የሰበር አቤቱታው የቀረበውም ይህንኑ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። አመልካቾች ሰኔ 10 ቀን 2008 ዓ.ም በፃፉት አቤቱታ በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶችን ዘርዝረው አቅርበዋል። የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ በመደረጉ ተጠሪ መልስ እንዲሰጡበት በታዘዘው መሰረት ሚያዚያ 9 ቀን 2009 ዓ.ም የተፃፈ መልስ አቅርበዋል። አመልካቾችም አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክረዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርምረናል። እንደመርመርነውም የአመልካቾች ጥያቄ በአመልካቾችና በተጠሪ መካካል ሲካሄድ የቆየው የውርስ ማጣራት ሂደት የፍ/ብ/ህ/ቁ.826 በሚያዘው መሰረት የውርስ ማጣራቱ ሂደት ሟች ይኖሩበት በነበረው ስፍራ ስልጣኑ በሚፈቅድለት የዓይደር ወረዳ ፍርድ ቤት እንጂ በከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲታይ ተደርጎ ውሳኔ ያገኝ መባሉ፤ተጠሪ ወራሽ ናቸው ለተባሉት እናት አይደሉም ሞግዚትነትም ሆነ የውክልና ስልጣን የላቸውም በማለትያቀረብነው መቃወሚያ ግምት ውስጥ ሳይገባ ወራሽነቱ እንዲፀድቅ መደረጉ፤የዚህ ውርስ ተጠቃሚዎች ናቸው የተባሉት ከነአካቴው ያልተወለዱና በአካልም የልሉ ሆን ተብሎ ተጠሪ ንብረቱን ያለ ጠያቂ ለብቻ ለማስቀረት በተንኮል የፈጠሩት ዘድ ሆኖ እያለና ተጠሪም የልጆቹ መወለድና በሕይወት መኖር በተጨባጭ ባላረጋገጡበት እንዲያውም ወራሾች ናቸው የተባሉት በአካል ቀርበው ውርስ ባልጠየቁበት የፀደቀ በመሆኑ እና ሟች ወንድማችን ያለ አመልካቾች ልላ ወራሽ የልለው መሆኑ በስር ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝና ሰበር ችሎቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ ላታረም ይገባል የሚል ሲሆን በተጠሪ በኩል ደግሞ የሟች ልጆች እያሉ ወንድሞች ወራሾች ላሆኑ ስለማይገባ የስር ፍርድ ቤቶች የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የልለበት ስለሆነ ላፀና ይገባል በማለት ተከራክረዋል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የአሁን ተጠሪ ሟች ልጆች ላይ ባቀረቡት ክስ ጉዳዩን በልሉበት ታይቶ ልጆች የሟች አባታቸው ወራሽ ናቸው በማለት ውሳኔ መሰጠቱ ግልፅ ነው። በልላ በኩል የአሁን አመልካቾች የወንድማቸው ሟች አቶ ዮሴፍ ሐጎስ ወራሾች መሆናቸው በፍርድ ቤት ተረጋግጧል። እዚህ ላታይ የሚገባው ነጥብ የወራሽነት ሰርተፊኬት በፍርድ ቤት ከተሰጠ በኋላ እውነተኛ የሟች ወራሽ ነኝ በማለት መቃወሚያ ላቀርብብት የሚችል ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነጥብ ነው። በፍ/ህ/ቁ 996 (1) ወራሽ የሆነ ሰው ለሟቹ ወራሽ መሆኑንና ከውርሱ ላይ የሚያገኘውን ድርሻ የሚያመላክት የወራሽነት የምስክር ወረቀት እንዲሰጠው ለፍርድ ቤት ማመልከት የሚችል ሲሆን የተሰጠው የወራሽነት ምስክር ወረቀትም በፍ/ህ/ቁ/998(1) በተመለከተው ሁኔታ ላሰረዝ ይችላል። በልላ በኩል በፍ/ህ/ቁ/999 በተደነገገው መሰረት አንድ ሰው ዋጋ ያለው የወራሽነት ማስረጃ ሳይኖረው ውርሱን ወይም ከውርሱ አንዱን ክፍል በእጁ ያደረገ እንደሆነ እውነተኛው ወራሽ ወራሽነቱ እንዲታወቅለትና የተወሰዱበት የውርስ ንብረቶች እንዲመለሱለት የወራሽነት ጥያቄ ክስ ማቅረብ እንደሚችል ተመልክቷል።
የውርስ ሰርተፊኬት አንድ ሰው የራሱን ወራሽነት ለማስረዳት የሚወስደው ማስረጃ እንጂ ልሎች ወራሾች አለመኖራቸውን የሚሳይ ሰነድ አይደለም። በግራ ቀኙ የሟች ወራሾች መሆናቸው በማረጋገጥ ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ ከማስረጃነት በዘለለ የፍ/ብ/ስ/ስ/ህግ በሚያዘው መሰረት ከልሎች ሰዎች ክርክር ተደርጎበት ውሳኔ ያገኘና በፍርድ ያለቀ መቃወሚያ የማይቀርብበት ተደርጎ ላወሰድ አይገባም። ስለሆነም ትክክለኛ የሟች ወራሽ ማነው? የሚለውን ጭብጥ ተገቢውን ማጣራት ከተደረገበት በኋላ ነው እውነተኛ ወራሽ መለየት የሚቻለው። ስለዚህ ወራሾች የተባሉትን ግራ ቀኙ ባሉበት የሟች እውነተኛ ወራሽ ማን ነው? የሚለውን ጭብጥ ማጣራት ሳይደረግበት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሁኖ ስለተገኘ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የትግራይ ብ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ ጥር 18 ቀን 2008 ዓ/ም የመቐለ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 17334 ሰኔ 24 ቀን 2007 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ በመሻር የዓይደር ክፍለ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 4884 የካቲት 30 ቀን 2007 ዓ.ም የተሰጠ ውሳኔ በማፅናት የሰጠው ውሳኔ በትግራይ ብ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበርሰሚ ችሎት በመ/ ሚያዝያ 4 ቀን 2008 ዓ/ም በዋለው ችሎት በትእዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሽሐል።
የስር ፍርደ ቤቶች የአሁን ተጠሪ ግማሽ ድርሻ እንዲያገኙ የሰጡት ውሳኔ ክፍል በማፅናት፤የሟች አቶ ዮሴፍ ሐጎስ ድርሻ አመልካቾች ላወርሱ አይገባም፤የልጆቹ ድርሻ ነው በማለት የተሰጠ ውሳኔ ክፍል በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.348/1/ መሰረት ተሽሮአል።
የዓይደር ክፍለ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የሟች ድርሻ ለመውረስ ትክክለኛ ወራሽ ማስረጃ የያዘ ማንነው ወይም የሟች እውነተኛ ወራሽ ማን ነው?
የሚለውን ጭብጥ በመያዝ፤የሟች ልጆች የተባሉት ስነስርዓት ህጉ መሰረት ጥሪ ተደርጎላቸው ባሉበት ተገቢው ማጣራት አድርጎ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ.343/1/ መሰረት መልሰናል። ይፃፍ።