ጋብቻ ሳይፈጸም እንደባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነትን ለማስረዳት የቀረበ ማስረጃ ግንኙነቱን የማሳየት ብቃት ያለው መሆኑ ከተረጋገጠ የግንኙነቱን ያለመኖር በማንሳት የሚከራከረው ልላኛው ወገን በህግ ጥበቃ ላደረግለት የሚገባ ግንኙነት ስላለመኖሩና ንብረቶችም የግል ስለመሆናቸው የማስረዳት ግድታ ያለበት ስለመሆኑ፣ አዋጅ ቁ. 75/1995 117/4/ እና 114 እና 97 አንቀጽ 109፣110፣113 እና 117
No summary available.
መስከረም 23 ቀን 2010 ዓ/ም ዳኞች፡- አልማዉ ወል ሙስጠፋ አህመድ አብርሃ መሰለ ጳውሎስ ኦርሺሶ ሰናይት አድነው አመልካች፡- አቶ ተስፋጊዩርጊስ አዳነ -ጠበቃ ኤልያስ መሐመድ ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ አሰፉ ግርማ -የቀረበ የለም መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ የተጀመረዉ በአማራ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት በጎንደር ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲሆን ተጠሪ ከሳሽ፣ አመልካች ተከሳሽ፣ ወ/ሮ አለም መንግስተአብ ደግሞ ጣልቃ ገብ ነበሩ። ተጠሪ ከአሁኑ አመልካች ጋር እንደባልና ሚስት በመሆን አብረን የኖርን ስለሆነ ንብረት ላያካፍለኝ ይገባል በማለት ክስ ያቀረቡ ሲሆን አመልካች ከተጠሪ ጋር በሕግ ጥበቃ በሚደረግለት ግንኙነት ውስጥ ያልነበሩና በጋራ ያፈሩት ንብረትም የልለ መሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል። የአመልካች ሕጋዊ ሚስት ነኝ ያሉት ግለሰብም ወደ ክርክሩ ጣልቃ እንዲገቡ ጥያቄ አቅርበው ፍርድ ቤቱም ፈቅዶላቸው ጣልቃ ገብተው ተከራክረዋል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ሰምቶ አመልካች ከሁለቱም ሴቶች ጋር እንደባልና ሚስት የኖሩ መሆኑ የተረጋገጠ ቢሆንም የተሻለ ያስረዱና መጀመሪያ ከአመልካች ጋር መኖር የጀመሩት የአሁን ተጠሪ ናቸው በማለት አመልካችና ተጠሪ ንብረቱን እኩል ከተካፈሉ በኃላ የአሁኑ አመልካች ከድርሻቸው ለስር ጣልቃ ገብ እንዲያካፍሐቸው ጣልቃ ገቧ መጠየቅ ይችላሉ በማለት ወስኖአል። በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካችና የስር ጣልቃ ገብ ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለሰሜን ጎንደር መስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ እና በስር ፍርድ ቤት የተሰሙትን የተጠሪ ምስክሮችን በድጋሚ ከሰማ በኋላ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ከአሁኗ ተጠሪ ጋር እንደባልና ሚስት መኖር የጀመሩት ከ1996 ዓ/ም ጀምሮ እንደሆነ ተጠሪ በምስክሮቻቸው ማስረዳታቸውን፣ አመልካች ከስር ጣልቃ ገብ ጋር እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር የጀመሩት ደግሞ ከ1995 ዓ/ም ጀምሮ በማስረጃ ተነግሯል ወደሚል ድምዳሜ ደርሶ የስር ፍርድ ቤት ሁለቱንም ሚስቶች ናቸው በማለት የሰጠው የውሳኔ ክፍል ተገቢ ቢሆንም በንብረት መብት ረገድ ቅድሚያ ደረጃ ላሰጣቸው የሚገባው ግን የአሁኗ ተጠሪ ሳይሆኑ ለስር ጣልቃ ገብ ሁኖ እያለ ይኼው መታለፉ ያላግባብ ነው በማለት በዚህ ረገድ የተሰጠውን የውሳኔ ክፍል በማሻሻል የጣውላ ቤት ድርጅትና 46 ካ/ሜትር የማህበር ቤት የአሁኑ አመልካችና የስር ጣልቃ ገብ የጋራ ሃብት ሁኖ ላከፈል እንደሚገባ፣ ከአሁኑ አመልካች ድርሻ ግማሹን ማለትም ከጠቅላላ ንብረቱ ¼ኛው ለአሁኗ ተጠሪ እንዲያካፍሉ፣ ክፍፍሉም በአይነት ወይም ግምቱን በመክፈል ላከናወን ይገባል በማለት ወስኖአል። በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበው ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን ሲያከራክር ቆይቶ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች በወረዳው ፍርድ ቤት በተሰጠው ውሳኔ ይግባኛቸውን ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አሻሽሎ በወሰነበት አግባብ ድጋሚ ይግባኝ ማቅረባቸው ስነ ስርዓታዊ አይደለም በሚል ምክንያት ወደ ፍሬ ነገሩ ሳይገባ የአመልካች ይግባኝ መዝገብ ዘግቶታል። ከዚህም በኋላ አመልካች የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም አጣሪ ችሎቱ በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ የተፈጸመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም በማለት መዝገቡን ዘግቶታል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም:- ከተጠሪ ጋር በሕጉ ጥበቃ የሚደረግለት ግንኙነት ውስጥ የነበሩ ስለመሆኑ በሕጉ አግባብ ሳይረጋገጥና አመልካች ከ1988 ዓ/ም ጀምሮ ከልላ ሴት ጋር በሕጋዊ ግንኙነት ያሉ መሆኑ የሚያሳዩ ማስረጃዎች በአግባቡ ሳይታዩ መታለፋቸውን ዘርዝረው የበታች ፍርድ ቤቶች ከ1996 እስከ 2004 ዓ/ም እንደባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነት ነበር በማለት የሰጡት ውሳኔ እንዲሻር ቅድሚያ ዳኝነት የጠየቁ መሆኑንና በአማራጭ ደግሞ ብር 75,000.00 ተጠሪ እንዲከፍሉ ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም አመልካች ከንብረቱ ¼ኛ እንዲወስዱ የሚያደርግ የክፍፍል ውሳኔ መሰጠቱ በአግባቡ መሆን ያለመሆኑን ለመመርመር ተብሎ ጉዳዩ ለዚህ ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርበውም ግራ ቀኙ በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጎአል።
በአጠቃላይ የክርክሩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተጠቀሰዉ ሲሆን እኛም የግራ ቀኙን ክርክር አቤቱታ ከቀረበበት ዉሳኔ እና አግባብነት ካለዉ የህግ ድንጋጌ አንጻር መርምረናል። እንደመረመርነውም በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ለማለት ይቻላል? ወይስ አይቻልም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሁኖ ተገኝቷል።
አመልካች አጥብቀው የሚከራከሩት ከተጠሪ ጋር በሕግ ጥበቃ የሚደረግለት ግንኙነት የለኝም፣ በስር ፍርድ ቤቶች መታየት የነበረባቸው ውሳኔዎች በማስረጃነት አልታዩም፣ የተጠሪ ምስክሮች ዘመዶቻቸው ሆነው በሐሰት የሰጡት የምስክርነት ቃል የማስረጃነት ዋጋ መሰጠቱ ያላግባብ ነው የሚሉ ነጥቦችን በማንሳት ስለመሆኑ ከሰበር አቤቱታቸው ይዘት ተገንዝበናል። ይሁን እንጂ አመልካች በስር ፍርድ ቤት የማስረጃ አሰማም ላይ ቅሬታ አድሮባቸው ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ባቀረቡት ይግባኝ መነሻ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተጠሪን ምስክሮች እንደገና የሰማ ሲሆን የተጠሪ ምስክሮችም በስር ፍርድ ቤት የሰጡትን የምስክርነት ቃል በመድገም አመልካች እና ተጠሪ እንደባልና ሚስት ሁነው ከ1995 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 2004 ዓ/ም ድረስ አብረው የቆዩ መሆኑን፣ ከ1991 እስከ 1995 ዓ/ም መጀመሪያ ድረስ በፍቅር ጓደኝነት የቆዩ መሆኑን ማስረዳታቸውን፣ ምንም እንኳን የአሁኑ አመልካች የስር ጣልቃ ገብን ሚስቴ ናት በማለትና ንብረቶችን ደግሞ የልላ ሚስቴና የግል ልጅ በሰጠችኝ ብር የተገዙ ናቸው የሚል ክርክር ቢያቀርቡም በስር ፍርድ ቤት የተሰሙት የአመልካች ምስክሮች ግን አመልካችና የስር ጣልቃ ገብ ባልና ሚስት እንደሆኑ፣ ጋብቻ ግን ሲፈጸም አለማወቃቸውን፣ የስር ጣልቃ ገብም አራት ልጆችን ወልደው ከአሁኑ አመልካች ጋር አብረው እንደሚኖሩ ያስረዱ መሆናቸውን፣ እነዚህ የአመልካች ምስክሮች አመልካች ከተጠሪ ጋር ግንኙነት የላቸውም በማለት ያላስረዱና ስለንብረቱም ያስረዱት ነገር ያለመኖሩን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የደመደመ መሆኑን ከውሳኔው ግልባጭ ተገንዝበናል። ይህ የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ድምዳሜ የተያዘው ደግሞ ፍርድ ቤቱ ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ ሲል የተጠሪ ምስክሮችን በድጋሚ በመስማት ፍሬ ነገሩን በሚገባ ከአጣራና በጉዳዩ በሕጉ አግባብ የቀረቡትን የግራ ቀኙን ማስረጃዎች ከመዘነ በኋላ ስለመሆኑ የክርክሩ ሂደት በግልጽ ያሳያል። ይህ የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የፍሬ ነገር ማጣራትና የማስረጃ ድምዳሜ ደግሞ ከስር ፍርድ ቤት ድምዳሜ ጋር ተመሳሳይ ከመሆኑም በላይ በሕጉ አግባብ የተቆጠሩትንና የተሰሙትን ማስረጃዎችን በመመዘን የተያዘ በመሆኑ ይህ ችሎት በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ)) እና አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 10 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ላለወጠው የሚችለው አይደለም። ምክንያቱም ለዚህ ችሎት በሕጉ ተለይቶ የተሰጠው ስልጣን መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ማረምን እንጂ የፍሬ ነገር ማጣራት ስህተት ወይም የማስረጃ ምዘና ስህተትን የሚመለከተውን ጉዳይ አይደለምና። በመሆኑም አመልካች ከተጠሪ ጋር ሕጉ ጥበቃ በሚያደርገው ግንኙነት ውስጥ አልነበርኩም በማለት የሚያቀርቡት ቅሬታ የፍሬ ነገርና የማስረጃ ምዘና ጉዳይ በመሆኑ በዚህ ችሎት ላታይ አይችልም በማለት አልፈነዋል።
ከዚህ አንጻር ጉዳዩን ስንመለከተው ጋብቻ ሳይፈጸም እንደባልና ሚስት አብሮ የመኖርን ግንኙነት ለማስረዳት የሚቀርበው ማስረጃ ግንኙነቱን የማሳየት ብቃት ያለው መሆኑን ፍሬ ነገሩን የማጣራትና ማስረጃን የመመዘን ስልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች ከአረጋገጡ ሕጉ ግንኙነቱን ጥበቃ የሚያደርግለት መሆኑን ከክልሉ የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 79/1995 አንቀጽ 109፣110፣113፣ 117 እና ከልሎች ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ መረዳት ይቻላል። ስለሆነም አመልካች ከተጠሪ ጋር በሕጉ ጥበቃ ላደረግ የሚገባው ግንኙነት ስላለመኖሩ በተጠቃሹ አዋጅ አንቀፅ 117 (4) ድንጋጌ አግባብ የማስረዳት ግድታቸውን ያልተወጡ ስለመሆኑ በበታች ፍርድ ቤቶች የተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ ንብረቶቹ የግላቸው ስለመሆኑም በአዋጁ አንቀፅ 114 እና 97 ድንጋጌዎች መሰረት የማስረዳት ግድታቸውን አልተወጡም። አመልካች በዚህ ሰበር ደረጃ ባቀረቡት ክርክር ድርሻቸው ¼ኛ እንዲሆን በተሰጠው የውሳኔ ክፍል ግልጽ የሆነ ቅሬታ ያላቀረቡና ክፍፍሉም የእኩልነት መርህን ወይም የእያንዳንዱ ተጋቢ በንብረቱ ላይ የነበረውን አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት መኪናውን ነበረበት በማለት ያቀረቡት ክርክር ካለመኖሩም በላይ በሰበር አቤቱታቸው መጨረሻ ላይ የጠየቁት ዋናም ሆነ አማራጭ የዳኝነት ጥያቄ መጠንም በዚህ ረገድ የሚጠቅሰው ግልጽ የሆነ የዳኝነት ጥያቄ የልለ በመሆኑ የሰበር አጣሪው ስለንብረት ክፍፍሉ የያዘውን ጭብጥ ተገቢነት ያልነበረው ሁኖ አግኝተናል።
ሲጠቃለልም በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የተሰጠው የግራ ቀኙ ክርክር በአግባቡ ተሰምቶና ፍሬ ነገሩም በሚገባ ተጣርቶ የግራ ቀኙን የማስረጃ ማቅረብና የማስረዳት ግድታቸውን ባገናዘበ መልኩ ከመሆኑ ውጪ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት የሚቻልበትን አግባብ አላገኘንም። በዚህም መሰረት ተከታዩ ዉሳኔ ተሰጥቷል።
በአማራ ክልል በጎንደር ወረዳ ፍርድ ቤት በመ.ቁ 0228 ጥር 29 ቀን 2006 ዓ/ም ተሰጥቶ በሰሜን ጎንደር መስተዳደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ.ቁጥር 01-16605 በ27/07/2007 ዓ/ም ተሻሽሎ በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር አጣሪ ችሎት በመ.ቁ 03-56035 መጋቢት 01 ቀን 2008ዓ.ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል።
አመልካች ከአሁኗ ተጠሪ ጋር እንደባልና ሚስት መኖር የጀመሩት ጊዜ በ1996 ዓ/ም ጀምሮ እንደሆነ ተጠሪ በምስክሮቻቸው አስረድተዋል፣ ከአሁኑ አመልካች ድርሻ ግማሹን ማለትም ከጠቅላላ ንብረቱ ¼ኛውን ለአሁኗ ተጠሪ እንዲያካፍሉ፣ ክፍፍሉም በአይነት ወይም ግምቱን በመክፈል ላከናወን ይገባል ተብሎ በተሰጠው ውሳኔ የተፈጸመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻቻሉ ብለናል።