አንድ የንግድ ቤት በኪራይ የተሰጠው በትዳር ግንኙነት ወይም በጋብቻ ውስጥ መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ የንግድ ፈቃድ የተሰጠው ከትዳር ግንኙነት በፊት መሆኑ ብቻ የንግድ ሱቅ ከጋብቻ በፊት የተገኘ የግል ንብረት ነው ለማለት የማያስችል ህንጻ እስጢፋኖስ ሀይሉ እና ወ/ሮ ሽቱ ቦንገን XXXVI
No summary available.
መስከረም 26 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ሙስጠፋ አህመድ አብርሃ መሰለ ጳውሎስ ኦርሺሶ ሰናይት አድነው አመልካች፡- ህፃን እስጢፋኖስ ኃይሉ ሞግዚት ወ/ሮ ብርቱኳን ተረፈ -ቀረቡ ተጠሪ፡- ወ/ሮ ሽቱ ቦንገን-ጠበቃ ነገደ ለማ -ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው። በሥር ፍርድ ቤት የአሁን አመልካች በ21/11/2006 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሟች አቶ ኃይል ተረፈ ውርስ እንዲጣራ አመልክተው ተጠሪ ባሉበት ወርሱ እንዲጣራ በማድረግ ግራ ቀኙ ሪፖርቱን አስመልክተው አስተያየት ከሰጡ በኋላ የስር ፍርድ ቤት ሪፖርቱን መዝግቦታል። የአሁን ተጠሪ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዋል። ይግባኝ የቀረበለት ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በጉለል ክ/ከተማ ወረዳ 01 ክልል ውስጥ የሚገኘውና ቁጥሩ 101 የሆነው የንግድ ኮንቴነር ሱቅና ከሱቁ የተገኘው የኪራይ ገንዘብ የሟችና የተጠሪ የጋራ ሀብት ስለሆነ ተጠሪ ግማሽ ድርሻ አላት በማለት የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ በማሻሻል ውሳኔ ሰጥቷል። የአሁን አመልካች የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ለፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱም የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ስህተት ያለበት ሆኖ አልተገኘም በማለት በትእዛዝ ሰርዞታል።
የሰበር አቤቱታው የቀረበውም ይህንኑ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። አመልካች ጥር 18 ቀን 2009 ዓ.ም በፃፉት አቤቱታ በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶችን ዘርዝረው አቅርበዋል። የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ በመደረጉ ተጠሪ መልስ እንዲሰጡበት በታዘዘው መሰረት የካቲት 24 ቀን 2009 ዓ.ም የተፃፈ መልስ አቅርበዋል። አመልካችም አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክረዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርምረናል። እንደመረመርነውም በጉለል ክ/ከተማ ወረዳ 01 ክልል ውስጥ የሚገኘውና ቁጥሩ 101 የሆነው የንግድ ኮንቴነር ሱቅ ላይ ተጠሪ ግማሽ ድርሻ አላት ተብሎ የተሰጠውን ውሳኔ በአግባቡ መሆን ያለመሆኑ በጭብጥነት ላታይ የሚገባው ሆኖ አግኝተናል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው የአሁን ተጠሪና ሟች ባልና ሚስት እንደነበሩና ጋብቻቸውም የተፈፀመው በ2001 ዓ.ም እንደሆነ፤ሟች አቶ ኃይል ተረፈ የንግድ ፍቃድ የተሰጣቸው ከጥር 5 ቀን 1998 ዓ.ም አንስቶ እንደሆነ፤ ለክርክር ምክንያት የሆነው ኮንቴነሩን/የንግድ ቤቱን/ በኪራይ ያገኙት ግን ጥር 18 ቀን 2002 ዓ.ም መሆኑን የጉለል ክ/ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት የንግድ ምዝገባ ፍቃድ እና ግብይት ዋና ስራ ሂደት በ28/06/2008 ዓ.ም ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በላከው ደብዳቤ አረጋግጧል። ስለሆነም ለክርክር ምክንያት ሆነው የኮንቴነር ሱቁ በጋብቻ ውስጥ መንግስት በአነስተኛ እና ጥቃቅን ተቋም አደራጅቶ የሰጣቸው መሆኑን ፍሬ ጉዳዩን የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን የተሰጣቸው የስር ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት ጉዳይ ነው። በመሆኑም አመልካች ኮንቴነር ሱቁ /ንግድ ቤቱ/ ከጋብቻ በፊት የተገኘ የሟች የግል ንብረት በመሆኑ ኮንቴነር ሱቁና የኪራይ ገንዘብ ግማሹ የተጠሪ ድርሻ መባሉ አግባብ አይደለም በማለት ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት የለውም። ሲጠቃለል የስር ፍርድ ቤቶች የኮንቴነር ሱቁ እና ከሱቁ ኪራይ የተገኘው ገንዘብ የተጠሪና የሟች የጋራ ሀብት በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ ስላልተገኘ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ ሰኔ 22 ቀን 2007 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ሐምል 25 ቀን 2008 ዓ/ም በውሳኔ የተሻሻለው እና በፍድራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ በመ/ ታህሳስ 28 ቀን 2009 ዓ/ም በትእዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል።
ከዚህ ፍርድ ቤት ጥር 29 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በፍድራል ፍርድ ቤቶች የፍርድ አፈፃፀም ዳይሬክቶሬት በመ/ቁ. 28805 የተጀመረው አፈፃፀም ታግዶ እንዲቆይ ተሰጥቶ የነበረው የእግድ ትእዛዝ ተነስቷል። ይፃፍ።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.