የባልና ሚስት ንብረት ክፍፍልን በተመለከተ ለአፈፃፀም የቀረበ አከራካሪ የሆነ ቤት ላካፈልም ሆነ ላሸጥ የማይችል ሲሆን ላካፈል የሚችለው በፕሮፖርሽን / በተነጻጻሪ ካርታ / ነው በማለት ባለሙያ አስተያየት በተሰጠበት ሁኔታ በዚሁ አግባብ ክፍፍሉ ሲደረግ የበለጠ ይዞታ የደረሰው ወገን ለልላው ወገን ግምቱን እንዲከፍል በማድረግ መፈፀም የሚገባው እንጂ በፍርዱ በተቀመጠው ልላ አማራጭ መሰረት ክፍፍሉ እንዲፈጸም ማድረግ የማይገባ ስለመሆኑ፡የተሻሻለው የፍድራል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 91(1)እና(2)
No summary available.
የሰበር መዝገብ ሕዳር 28 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- ብርሃኑ አመነው በዕውቀት በላይ እንዳሻው አዳነ ሃይሉ ነጋሽ እትመት አሰፋ አመልካች፡- አቶ እለፋቸው ታምሩ አልቀረቡም ተጠሪ፡- ወ/ሮ እመቤት ተሾመ አልቀረቡም መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የባልና ሚስት ንብረት ክፍፍል አስመልክቶ የቀረበን አፈጻጸም የሚመለከት ነው። በአመልካች እና በተጠሪ መካከል ሲደረግ የነበረውን የባልና ሚስት ንብረት ክፍፍል በተመለከተ የፍድራል ፍ/ቤቶች ፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት አፈጻጸሙን ለመራው የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ የይዞታ አስተዳደር ጽ/ቤት በላከው ምላሽ ቤቱን በዓይነት ለማካፈል የሚችል መሆኑን ገልጾ ክፍፍሉ ሲፈጸም ለግራቀኙ በደረሰው ንብረት የሐብት ማጋደል ስለሚኖርበት ግራቀኙ ልዩነቱን በማካካስ የሚፈጽሙት ነገር ካለ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ መጥሪያ የተላከላቸው ቢሆንም የፍርድ ባለመብት ሃሳባቸውን ይዘው ቀርበው የፍርድ ባለእዳ ሀሳባቸውን ያላቀረቡ በመሆኑ አፈጻጸሙ በምን መንገድ መቀጠል እንዳለበት ፍ/ቤቱ ትእዛዝ እንዲሰጥበት በማለት ጠይቋል። ፍ/ቤቱም ግራቀኙ ሀሳባቸውን እንዲሰጡ ካደረገ በኋላ በዋናው ውሳኔ ላይ የግራቀኙ የጋራ ንብረት ናቸው በማለት ፍርድ ያረፈባቸው ቤቶች ግራቀኙ ከተቻለ በዓይነት እንዲካፈሉት፤በዓይነት መካፈል ካልተቻለ ክፍፍሉን በተመለከተ በውሳኔው ላይ በተቀመጠው አማራጭ መሰረት እንዲካፈሉት በማለት የተሰጠ ውሳኔ ነው፤በፍርድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ቤቶቹ እኩል መካፈል እንደማይችሉ ተገልጿል፤የሐብት ማጋደል ባለበት ሁኔታ ግራቀኙ እንዲካፈሉ ለማድረግ የግራቀኙን ሥምምነት ይጠይቃል፤ግራቀኙ በሰጡት አስተያየት ሥምምነት የልላቸው መሆኑን የገለጹ በመሆኑ የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት በውሳኔው ላይ በቀጣይ በተቀመጡት አማራጮች መሰረት ውሳኔውን እንዲያስፈጽም በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል። አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ያቀረቡ ቢሆንም አቤቱታቸው ተቀባይነት አላገኘም።
የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይህን ውሳኔ በመቃወም ነው።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- የሥር ፍ/ቤት አፈጻጸሙ በፍርዱ በተቀመጡት ልሎች አማራጮች መሰረት እንዲፈጸም በማለት የሰጠው ትዕዛዝ ፍርዱ እንዳይፈጸም እና ዋጋ አልባ እንዲሆን የሚያደርግ ነው፤የሚመለከተው አካል ፍርድ ያረፈባቸው ቤቶች ከዋናው ቤት ተነጥለው መሸጥ እንደማይችሉ፤ይዞታው ለሁለት እኩል ሲካፈል ለግራቀኙ ከ150 ካ.ሜ ያነሰ ቦታ ላደርሳቸው ስለማይችል በዓይነት እኩል ማካፈል እንደማይቻል ያረጋገጠ በመሆኑ በፍርዱ በተቀመጡት ልሎች አማራጮች መሰረት ፍርዱ ላፈጸም አይችልም፤ፍ/ቤቱ ፍርዱን ለማስፈጸም ተስማሚ ነው የሚለውን ትዕዛዝ በመስጠት ፍርዱን ማስፈጸም ስላለበት ጉዳዩን በአግባቡ ካጣራ በኋላ ቤቶቹ የየራሣቸው የሆኑ ሁለት መግቢያ እና መውጫ በሮች ስሐሐቸው ግራቀኙ በፕሮፖርሽን / በተነጻጻሪ ካርታ / ተካፍለው እንዲገለገሉባቸው ከማድረግ ውጪ ፍርዱ የሚፈጸምበት ልላ አማራጭ ስለልለ በፕሮፖርሽን / በተነጻጻሪ ካርታ / ክፍፍሉ እንዲፈጸም በማለት ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ሲሰጥ ከቆየ በኋላ በልላ አማራጭ መሰረት ፍርዱ ይፈጸም በማለት የሰጠው ትዕዛዝ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ሥሕተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም የሚገባው ነው የሚል ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ የበታች ፍ/ቤቶች አከራካሪ የሆነው ቤት ላካፈልም ሆነ ላሸጥ የማይችል ነው፤ላካፈል የሚችለው በተነጻጻሪ ካርታ ነው በማለት ባለሙያ አስተያየት በሰጠበት ሁኔታ በልላ አማራጭ ይፈጸም በማለት የመወሰናቸውን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ በዚህ ችሎት እንዲታይ ተደርጓል። ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎም ግራቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ በአጭሩ ከላይ የተገለጸው ነው። እኛም እንዲጣራ የተያዘውን ነጥብ ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ሕጎች ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው መርምረነዋል።
የተሻሻለው የፍድራል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 91(1)እና(2) እያንዳንዱ ተጋቢ ከጋራ ሐብቱ የተወሰነ ንብረት እንዲደርሰው በማድረግ የጋራ ሐብቱ በዓይነት እንዲከፋፈል ይደረጋል፤እኩል ለማከፋፈል የማይቻል ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ልዩነቱ በገንዘብ እንዲካካስ ይደረጋል በማለት ይደነግጋል። የበታች ፍ/ቤቶች የሐብት ማጋደል ባለበት ሁኔታ ቤቱን በዓይነት ለማካፈል የግራቀኙ ሥምምነት ያስፈልጋል፤ግራቀኙ ስምምነታቸውን ባልሰጡበት ሁኔታ በዓይነት ማካፈል የማይቻል በመሆኑ በውሳኔው በቀጣይ በተቀመጠው የክፍፍል አማራጭ መሰረት ውሳኔው ላፈጸም ይገባል ከሚል መደምደሚያ ላይ የደረሱ ቢሆንም የሚመለከተው አካል ቦታው በዓይነት ሲካፈል እያንዳንዳቸው 150 ካ.ሜ ማግኘት አለባቸው ሁለቱም ሰዎች የየራሣቸው መግቢያ እና መውጫ መንገድ ስላላቸው ሰዎቹ የሚሥማሙ ከሆነ በፕሮፖርሽን / በተነጻጻሪ ካርታ / መገልገል የሚችሉ መሆኑን ገልጿል። ተጠሪ የአመልካች አቤቱታ ተጠሪ መጠለያ እና ቀለብ ለመንፈግ የቀረበ ነው ከማለት በቀር ክፍፍሉ በተነጻጻሪ ካርታ ቢፈጸም የሚያመጣባቸው ጉዳት መኖሩን በመግለጽ ያቀረቡት ክርክር የለም። ጉዳዩ የቀረበለት ፍ/ቤት ቤቶቹ በፕሮፖርሽን / በተነጻጻሪ ካርታ / መከፋፈል እንሚችሉ በሚመለከተው አካል እስከተገለጸ ድረስ በቤተሰብ ሕጉ የባልና ሚስት ንብረት ክፍፍል በተቻለ መጠን ባልና ሚስት ንብረታቸውን በዓይነት የመካፈል መብታቸውን ባስጠበቀ መንገድ ላፈጸም ይገባዋል የሚለውን የክፍፍል መርህ ባስጠበቀ መልኩ በዚሁ ቤቶቹ በፕሮፖርሽን / በተነጻጻሪ ካርታ / እንዲከፋፈሉ በዚሁ አግባብ ክፍፍሉ ሲደረግ የበለጠ ይዞታ የደረሰው ወገን ለልላው ወገን ግምቱን እንዲከፍል በማድረግ ማስፈጸም ሲገባው በፍርዱ በተቀመጠው ልላ አማራጭ መሰረት ክፍፍሉ እንዲፈጸም በማለት መወሰኑ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም ይህንኑ ሳያርም መቅረቱ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ሥሕተት የተፈጸመበት ሆኖ አግኝተነዋል። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ. ሕዳር 12 ቀን 2009 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ፤የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ. ሚያዝያ 18 ቀን 2009 የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 348/1 መሰረት ተሽሯል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ከላይ በፍርድ ሐተታው በተገለጸው መሰረት አፈጻጸሙን እንዲቀጥል ጉዳዩ ተመልሶለታል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪ ግራቀኙ የየራሣቸውን ይቻሉ።
-የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የመ. የሆነው መዝገብ ወደ መጣበት ይመለስ።
-መዝገቡ ተዘግቷል።ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.