በጋብቻ በተሳሰሩ ባልና ሚስት መካከል ከአንዱ ጋር የውል ግድታ የገባ ሰው በዋናው ክርክር ሁለቱን አጣምሮ ላከስ የሚችልበት አግባብ የልለ ስለመሆኑ እንዲሁም ተዋዋይ በሆነው ተጋቢ ላይ የተሰጠ ውሳኔ የተጋቢዎች የጋራ እዳ ነው ወይስ የተወሰነበት ተጋቢ የግል እዳ ነው የሚለው ክርክር ላነሳ የሚችለው በአፈጻጸም ወቅት እንጂ ልላኛው ተጋቢ ላከሰስም ሆነ ላፈረድበት ስላለመቻሉ፡- XXXV
No summary available.
ቀን መስከረም 22/2010 ዓ.ም ዳኞች፡- ብርሃኑ አመነው በእውቀት በላይ እንዳሻው አዳነ ኃይሉ ነጋሽ እትመት አሰፋ አመልካቾች፡- 1ኛ. ተኽሉ አስፍሃ 2ኛ. ሃለቃ ደስታ ሃ/ስላሴ 7ኛ. ወ/ሮ ዮዲት ግርማይ 3ኛ. አቶ ገ/ትንሳኤ ጸሃዬ 8ኛ. አቶ ገ/መድህን አባይ 4ኛ. አቶ ልብሰ ማሪያም አሳይ 9ኛ. አቶ ሃይላይ ገ/አምላክ 5ኛ. ወ/ሮ ንግስቲ ገብሩ 10ኛ. አቶ ወ/ገሪማ ገ/መድህን 6ኛ. አቶ ገ/እግዚአብሕር ገ/አረጋዊ 11ኛ. ቄስ እቡይ ገ/እግዚአብሕር ተጠሪዎች፡- 1ኛ. አቶ ስብሃቱ ገ/መስቀል አልቀረቡም 2ኛ. ወ/ሮ ብርሃን ገ/ማሪያም መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ አፈጻጸምን የሚመለከት ሆኖ የተጀመረው በመቀል ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት ሲሆን በዚሁ ፍ/ቤት የአሁን አመልካቾችን ጨምሮ 17 ሰዎች የፍርድ ባለመብቶች፣ የአሁን 1ኛ ተጠሪ የፍርድ ባለእዳ ሲሆኑ 2ኛ ተጠሪ የፍርድ ባለእዳው ባለቤትና የመቃወም አመልካች ነበሩ። የፍርድ ባለመብቶች በተለያዩ መዝገብ በ 1ኛ ተጠሪ ላይ ያስፈረዱትን ፍርድ ለማስፈጸም የባለእዳውን ንብረት ጠቁመው በመቀል ከተማ በቀዳማዊ ወያኔ የሚገኙ 1ኛ/ በምስራቅ ገበያ፣ በሰሜን ታደሰ ኪዳኑ፣ በምእራብ መንገድ፣ በደቡብ ኣጽበሃ የሚዋሰን በ 32 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ቤትና ቦታ፣ 2ኛ/ በምስራቅ ግደይ ገ/መድህን፣ በሰሜን ታደሰ ኪዳኑ፣ በምእራብ ኣርያ መለሰ፣ በደቡብ መንገድ የሚዋሰን በ 311.75 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ቤትና ቦታ በፍርድ ባለእዳው ስም የሚታወቅ መኖሩን ገልጸው ስላቀረቡ ለአፈጻጸሙ እንዲውሉ ተገምተው እንዲቀርቡ በስር ፍ/ቤት ትእዛዝ ተሰጥቷል።
የአሁን 2ኛ ተጠሪ ከፍርድ ባለእዳው ጋር ከ 1967 ዓ.ም ጀምሮ በትዳር የኖሩና ለአፈጻጸም ተገምተው እንዲቀርቡ የተባሉ ንብረቶች በጋራ ያፈሯቸው መሆኑን ገልጸው አመልካቾች ያስፈረዱት በፍርድ ባለእዳው ላይ በመሆኑ ንብረቶቹ የሚሸጡ ከሆነ መብታቸው የሚነካ በመሆኑ በድርሻቸው ላይ የተሰጠው ትእዛዝ እንዲነሳላቸው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 418 መሰረት መቃወሚያ አቅርበዋል። የፍርድ ባለመብቶች ለመቃወሚያው በሰጡት መልስ ተጠሪዎች በትዳር በነበሩበት ወቅት 1ኛ ተጠሪ የገቡት እዳ እንደባልና ሚስት እዳ የሚታሰብ በመሆኑ ከባል ወይም ከሚስት የግል እና የጋራ ንብረት ላጠየቅ እንደሚችል በንግድ ሕግ አንቀጽ 19 ተደንግጎ የሚገኝ በመሆኑና ተቃዋሚ ነጋድ በመሆናቸው እንዲሁም ከደደቢት ብድር ተቋም ተጠሪዎች በጋራ ተበድረው ስለነበር የጋራ እዳቸው ነው። በተጨማሪም 1ኛ ተጠሪ ከስር 7ኛ የአፈጻጸም ከሳሽ የወሰዱት በቼክ የንግድ ፈቃድ ከመመለሱ በፊት ስለሆነ ያቀረቡት ተቃውሞ ውድቅ ተደርጎ አፈጻጸሙ ይቀጥልልን በማለት ተከራከሩ።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የመቀል ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት የግራቀኙን ክርክር መርምሮ የንግድ ፈቃድ ከመመለሱ በፊት ቼክ ቆርጫለሁ የሚለው ብቻውን እዳውን የጋራ እዳ ስለማያደርገው እዳው ለትዳር ጥቅም መዋሉ በማስረጃ የተደገፈ ነገር ባለመኖሩ 2ኛ ተጠሪ በቤትና ቦታዎቹ ላይ ያላቸው ግማሽ ድርሻ በዓይነት ወይም በገንዘብ ግምት ይገባቸዋል በማለት ትእዛዝ ሰጥቷል። አመልካቾች የአፈጻጸም ትእዛዙን በመቃወም ይግባኝ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቢያቀርቡም ግራቀኙን ካከራከረ በኋላ መርምሮ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 418 መሰረት ያደረገ ተቃውሞ ሲቀርብ በአፈጻጸም በተያዘ ወይም በተከበረ ንብረት መብት አለኝ የሚል ተቃውሞ አለው ወይስ የለውም ተብሎ የሚታዘዝበት እንጂ እዳ የጋራ ነው የግል ተብሎ በማጣራት የሚወሰንበት ስላልሆነ ንብረቶቹን ተጠሪዎች በጋብቻ ውስጥ በጋራ ያፈሯቸው መሆኑ ባልተካደበት እና በ 2ኛ ተጠሪ ላይ ባልተፈረደበት ሁኔታ ድርሻቸው ለአፈጻጸሙ የሚያዝበት አግባብ የለም በማለት በውጤት ደረጃ የስር ፍ/ቤትን ትእዛዝ አጽንቶታል።
በመቀጠል ለክልሉ ሰበር ችሎት አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኘም።
አመልካቾች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት ይህን ውሳኔ በመቃወም ለማስቀየር ነው።
አመልካቾች ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ ይዘት በአጭሩ፡- ለአፈጻጸም ክርክሩ መሰረት የሆነው እዳ ቼክን መሰረት ያደረገ ሲሆን 1ኛ ተጠሪ ነጋድነታቸው ተረጋግጦ ቼክ ተሰጥቷቸው በንግድ ስራ ተሰማርተው የቆዩ ነጋድ ናቸው። በዚህ ሁኔታ ተጋቢዎች በትዳር እያሉ የመጣ እዳ የባልና ሚስት የጋራ እዳ ለመሆኑ በንግድ ሕግ አንቀጽ 19 ተመልክቷል። 2ኛ ተጠሪ ራሳቸው ነጋድ በመሆናቸው እዳው የሚመለከታቸው በመሆኑ እንዳለ ሆኖ በጋራ ጥቅም ላይ አለመዋሉም የማስረዳቱ ሸክም የራሳቸው ሆኖ እያለ ይህንን አላስረዱም። ይህ ብቻ ሳይሆን በትግራይ ክልል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 90/2/ መሰረት 2ኛ ተጠሪ ባለቤታቸው እዳ የገቡ ለመሆናቸው ቀደም ብለው ያወቁ እንደነበርና ለባለገንዘቦችም ቤቶችን ትወስዳላችሁ ሲሉ እንደቆዩ እየታወቀ ይህንን ባወቁ በ 6 ወር ጊዜ ውስጥ ግድታው ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀው አላስፈረሱም። ስለሆነም 1ኛ ተጠሪ ነጋድ እንደነበሩና ያለ ንግድ ፈቃድ ቼክ ከባንክ እንደማይሰጥ እየታወቀ ንግድ ቢሮውም ሆነ ባንኮቹ ሳይጠየቁ፣ እንደዚሁም 2ኛ ተጠሪ እዳውን ለጋራ ጥቅም አለመዋሉን ሳያስረዱና ተቃውሞ አቅርበው ባላስፈረሱበት ሁኔታ በስር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ይሻርልን የሚል ነው።
የአመልካቾች አቤቱታ ተመርምሮ ቼክ የተሰጠው ተጠሪዎች ባልና ሚስት መሆናቸው ተረጋግጦ ሳለ እንዲሁም 2ኛ ተጠሪም በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ መሆኑ በታወቀበት ሁኔታ እዳው የጋራ አይደለም የተባለበትን አግባብነት ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ያስቀርባል የተባለ ሲሆን 1ኛ ተጠሪ መልስ ባለማቅረቡ መብቱ ታልፎ 2ኛ ተጠሪ እና አመልካቾች መልስ እና የመልስ መልስ በጽሁፍ እንዲቀባበሉ በማድረግ ክርክር ተደርጓል።
የ 2ኛ ተጠሪ የሰበር መልስ ይዘት፡- አመልካቾች በቼክ ምክንያት ክስ ያቀረቡትና ያስፈረዱት በ 1ኛ ተጠሪ ላይ ሲሆን ሁሉም ቼኮች ደግሞ በ 1ኛ ተጠሪ ስም ከባንክ የወጡ ቼኮች እንጂ በ 2ኛ ተጠሪ ስም የተመዘገቡ ቼኮች አይደሉም። በንግድ ሕግ አንቀጽ 19 መሰረት ተበዳሪው ነጋድ መሆን እንደሚገባው እና ነጋድ ያልሆነ ባል ወይም ሚስት የሚበደረው ብድር ግን በዚህ የሕግ ድንጋጌ የማይሸፈን በመሆኑ ነጋድ ያልሆነው ባል የወሰደው ብድር ነጋድ ለሆነችው ሚስት ይመለከታታል ማለት አይደለም። 1ኛ ተጠሪ ከንግድ ውጭ ብቻቸውን የቆረጡት ቼክ 2ኛ ተጠሪ አያውቁትም የሚል እንደመሆኑ መጠን እና 1ኛ ተጠሪ ቼኩን ሲቆርጡ 2ኛ ተጠሪ ሚስት ከመሆናቸው ውጭ ስለቼኮቹ የሚያውቁት ነገር የለም። 1ኛ ተጠሪ ከንግድ እንቅስቃሴ ውጭ በስማቸው የያዙት ቼክ በ 2ኛ ተጠሪ የንግድ ልውውጥ የተቆረጡ ቼኮች ናቸው የሚባልበት ሕጋዊ ምክንያት ባለመኖሩ፤ እንዲሁም ቼኮቹ በንግድ ልውውጥ ምክንያት የተሰጡ መሆኑ ባልተረጋገጠበት በ 2ኛ ተጠሪ ድርሻ ለአፈጻጸሙ ላውል ስለማይገባ አመልካች አቤቱታ ውድቅ ይደረግ የሚል ነው። አመልካቾች አቤቱታቸውን በሚያጠናክር መልኩ የመልስ መልስ አቅርበዋል።
የግራቀኙ ክርክር ባጭሩ ከላይ የተመለከተውን የሚመስል ሲሆን እኛም አቤቱታ ከቀረበበት ውሳኔ እና አግባብነት ካለው የሕግ ድንጋጌ ጋር በማገናዘብ መዝገቡን መርምረናል።
መርምረን እንደተረዳነው 1ኛ ተጠሪ በሰጣቸው ቼኮች መነሻነት የአሁን አመልካቾች በ 1ኛ ተጠሪ ላይ ክስ መስርተው በተለያየ መዝገብ አስፈርደዋል። አመልካቾች ለአፈጻጸሙ እንዲውሉ የጠየቋቸው ክርክር ያስነሱ ንብረቶች በ 1ኛ ተጠሪ ስም የሚገኙ ቢሆንም ከ 2ኛ ተጠሪ ጋር በትዳር ውስጥ በነበሩበት ወቅት ያፈሯቸው የጋራ ንብረቶች በመሆናቸው አከራካሪ አይደለም። የስር ፍ/ቤት እዳው የተጠሪዎች የጋራ እዳ አይደለም በማለት ውሳኔ የሰጠው ምንም እንኳ እዳው ከቼክ መስጠት ጋር የተያያዘ ቢሆንም ቼኮቹ በ 1ኛ ተጠሪ የተሰጡት 2ኛ ተጠሪ የንግድ ፈቃዳቸውን ከመለሱ በኋላ በመሆኑ የጋራ እዳ ነው ተብሎ ላወሰድ አይችልም የሚል መደምደሚያ ላይ በመድረስ ነው።
ሆኖም የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ያጸናው እዳው የጋራ እዳ አይደለም በማለት ሳይሆን ክስ ቀርቦ የተወሰነበት 1ኛ ተጠሪ ላይ ብቻ በመሆኑና 2ኛ ተጠሪ ባልተከሰሱበትና ባለእዳ ናቸው ተብሎ ሳይፈረድባቸው በአፈጻጸም ላገደዱና ድርሻቸው ለአፈጻጸም ላውል አይገባም በማለት ነው።
በመሰረቱ በጋብቻ በተሳሰሩ ባልና ሚስት መካከል ከአንዱ ጋር የውል ግድታ የገባ ሰው በዋናው ክርክር ሁለቱን አጣምሮ ላከስ የሚችልበት አግባብ የለም። ተዋዋይ በሆነው ተጋቢ ላይ የተሰጠው ውሳኔ የተጋቢዎች የጋራ እዳ ነው ወይስ የተወሰነበት ተጋቢ የግል እዳ ነው የሚለው ክርክር ላነሳ የሚችለው በአፈጻጸም ወቅት እንጂ ልላኛው ተጋቢ ላከሰስም ሆነ ላፈረድበት አይችልም። ይህ ለመሆኑም ከዚህን ቀደም የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በ
በማናቸውም ፍ/ቤት ላይ አስገዳጅነት ያለው ትርጉም ሰጥቶበታል። ስለሆነም 2ኛ ተጠሪ ክርክር ባስነሱ ንብረቶች ላይ ያላቸው ድርሻ ለአፈጻጸም ይውላል ወይስ አይውልም ለማለት በቅድሚያ በአፈጻጸም መዝገቡ እየተፈጸመ ያለው እዳ የጋራ እዳ ነው ወይስ የ 1ኛ ተጠሪ የግል እዳ ነው? የሚለው ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል። በመሆኑም የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት እዳው የጋራ ነው ወይስ የግል የሚለው ክርክር በአፈጻጸም ወቅት ላነሳ አይችልም በማለት 2ኛ ተጠሪ ሳይፈረድባቸው ድርሻቸው ለአፈጻጸም አይውልም ሲል የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው።
በልላ በኩል የሰበር አቤቱታው ያስቀርባል ሲባል ወደተያዘው ጭብጥ ስንመለስ በ 1ኛ ተጠሪ ላይ የተወሰነው የገንዘብ እዳ የጋራ እዳ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን በተመለከተ የዞኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት የግራቀኙን ክርክርና ማስረጃ መርምሮ የጋራ እዳ አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ የ 2ኛ ተጠሪ ድርሻ ለአፈጻጸሙ ላውል አይገባም በማለት ውሳኔ የሰጠ ቢሆንም በዚህ ድምዳሜ ላይ ይግባኝ የቀረበለት የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አከራካሪ በሆነው የፍሬ ነገር ጭብጥ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ አልሰጠበትም። ይህ ሰበር ችሎት በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 80/3/ሀ/ እና በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 10/2/ መሰረት የመጨረሻ ውሳኔ በተሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ የተፈጸመ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ማረም በመሆኑ እዳው የተጠሪዎች የጋራ እዳ ነው ወይስ የ 1ኛ ተጠሪ የግል እዳ የሚለውን የፍሬ ነገር ጭብጥ ማስረጃ መዝኖ የሚያረጋግጥበት የሕግ አግባብ ካለመኖሩም በላይ የአመልካቾችን የይግባኝ መብት የሚያጣብብ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩን ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት መመለሱ ተገቢ ይሆናል።
ሲጠቃለል የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እዳው የጋራ ነው ወይስ የግል የሚለው ክርክር በአፈጻጸም ወቅት ላነሳ አይችልም፤ 2ኛ ተጠሪ ሳይፈረድባቸው ድርሻቸው ለአፈጻጸም አይውልም ሲል የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ተሽሮ እዳው የተጠሪዎች የጋራ እዳ ነው? ወይስ አይደለም?
እንዲሁም በአፈጻጸም ክርክር ባስነሱ ንብረቶች ላይ 2ኛ ተጠሪ ያላቸው ድርሻ ለአፈጻጸሙ ላውል የሚገባው መሆን አለመሆኑን አስመልክቶ ግራቀኙ ያቀረቧቸውን ክርክሮችና ማስረጃዎች በመመዘን የመሰለውን ውሳኔ እንዲሰጥበት ለይግባኝ ሰሚው ችሎት መመለሱ ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
ሐምል 01 ቀን 2008 ዓ.ም በተሰጠ ትእዛዝ የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 348/1/ መሰረት ተሽሯል።
ከላይ በፍርድ ሃተታው በተገለጸው አግባብ አመልካቾች በ 2ኛ ተጠሪ ላይ ያስወሰኑት የገንዘብ እዳ የተጠሪዎች የጋራ እዳ ነው ወይስ የ 1ኛ ተጠሪ የግል እዳ? በሚለው ጭብጥ ላይ ግራቀኙ ያቀረቡትን ክርክርና ማስረጃ በመመርመር ክርክር ባስነሱ ንብረቶች ላይ 2ኛ ተጠሪ ያላቸው ድርሻ ለአፈጻጸሙ መዋል መቻል አለመቻሉን አስመልክቶ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት የመሰለውን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 343/1/ መሰረት ይመለስለት ተብሐል።
የሰበር ክርክሩ ያስከተለውን ወጪና ኪሳራ ግራቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
No topics extracted.