በነባር ይዞታ ላይ ያረፈ ንብረት በውርስ የሚተላለፍ እንደሆነ ወደ ላዝ ስሪት ማስገባት የማይችል እና ለጉዳዩ የላዝ አዋጅ ቁጥር 721/2004 ተፈጻሚነት የልለው ስለመሆኑ፡-
No summary available.
ጥቅምት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡ ..1. ዳኜ መላኩ 2. ተፈሪ ገብሩ 3. ቀነዓ ቂጣታ 4. ተሾመ ሽፈራዉ 5. ፀሐይ መንክር አመልካች፡- የወ/ሮ ጌጤ ካሳ ወራሾች ወ/ሮ ኤፍሶን ወልድ እና ወ/ሮ አምሳለ ከተማ ወ/ሮ፤ ወ/ሮ ኤፍሶን ወልድ ቀርበዋል።
ተጠሪ፡- .የኮልፍ ቀራኒዮ ክ/ከተማ መሬትና አስተዳደር ጽ/ቤት ዐ/ህግ ሰይፈ ስላሴ ገሪማ ቀርበዋል ይህ መዝገብ የተቀጠረዉ ለምርመራ ሲሆን ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የይዞታ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ለዚህ ችሎት ላቀርብ የቻለዉ የአሁን አመልካች የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ.ቁ.127492 በ16/10/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ መርምሮ ለመወሰን ነዉ።
የጉዳዩ መነሻ ሲታይ በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአሁን አመልካች እና በዚህ ችሎት የክርክሩ ተካፋይ ያልሆኑት ወ/ሮ ጸዳለ ካሳ እና ወ/ሮ ገነት ካሳ የመቃወም ተጠሪዎች፣የአሁን ተጠሪ ደግሞ የመቃወም አመልካች ሆነው ሲከራከሩ ነበር። የአሁን ተጠሪ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.358 መሰረት ባቀረበዉ አቤቱታ የመቃወም ተጠሪዎች የግራ ቀኛቸዉ አባት የሻለቃ ካሳ ሃይሉ በወረዳ 24 ቀበል 09 የቤት ቁጥር 622 ስፋቱ 942 ካ.ሜ ይዞታ በተመለከተ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ/ካርታ ሳይኖራቸዉ ባለይዞታ አይደሉም፣ ይዞታዉ ላስተናገድ የሚገባዉ በነባር ይዞታ ሆኖ ሳለ የመቃወም ተጠሪዎች በግልግል ዳኝነት ባደረጉት ስምምነት ይዞታዉን ሶስት ቦታ ተካፍለዉ በ29/10/1993 ዓ.ም ፍ/ቤቱ ስምምነቱን አጽንቷል። ስለዚህ ይህ ዉሳኔ እንዲሻርልን፣ እስከ 500 ካ.ሜ በነባር ይዞታ እንዲወስዱ እና ቀሪዉን 434 ካ.ሜ ይዞታ ግን በላዝ አዋጅ መሰረት ላወስዱ ይገባል ተብሎ እንዲወሰንልን በማለት አመልክቷል።
የመቃወም ተጠሪዎች ባቀረቡት መልስ በታዘዘዉ መሰረት 1ኛ የመ/ተጠሪ /የአሁን አመልካች/ ለክርክር ምክንያት የሆነዉ ቤትና ቦታ የአባታችን ንብረት ሲሆን በአባታችን ስም ግብር እየገበርን፣ ካርታ ለመዉሰድ ጥያቄ አቅርበን እየተጠባበቅን እንገኛለን።
በአዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 6 /3/ መሰረት አዋጁ በዉርስ በሚተላለፍ ንብረት ላይ ተፈጻሚነት የለዉም፣ስለዚህ የቀረበዉ አቤቱታ ተቀባይነት የለዉም በማለት ተከራክሯል። የሥር 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች መልስ ባለማቅረባቸዉ መብታቸዉ ታልፏል።
ከዚህ በኋላ ፍ/ቤቱ ግራ ቀኛቸዉን በሰጠዉ ዉሳኔ የመ/ተጠሪዎች የንብረት ክፍፍል ስምምነት ያደረጉት በ1993 ዓ.ም ሲሆን ፍ/ቤቱም ይህን ስምምነት ያጸደቀዉ በ1993 ዓ.ም በመሆኑ፣ የላዝ አዋጅ ቁጥር 721/2004 በአንቀጽ 6 መሰረት በዉርስ በሚተላለፍ ይዞታ ወይም ቤት ላይ ተፈጻሚነት ስለልለዉ በፍ/ቤት የግልግል ዳኞች ስምምነትን ያጸደቀዉ ዉሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.360 /2/ መሰረት ጸንቷል በማለት ወስኗል።
የሥር የመቃወም አመልካች በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ ግራ ቀኛቸዉን በማከራከር በሰጠዉ ዉሳኔ የአሁን መልስ ሰጭዎች በስምምነት የተከፋፈሉት የዉርስ ሀብት የተባለዉ ይዞታ የሰነድ አልባ በመሆኑ የሰነድ አልባ ይዞታዎች ስርዓት ላከተል ስለሚገባ ይዞታዉ በስምምነቱ መሰረት ላካፈል የሚችል መሆን አለመሆኑ በባለሙያ ማጣራት አለበት በማለት የሥር ዉሳኔ በመሻር ለሥር ፍ/ቤት መልሶታል። የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ጉዳዩን በይግባኝ በማየት የሥር ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል። የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ ይህን ዉሳኔ በመቃወም ለማሳረም ነዉ።
የአሁን አመልካች ነሐሴ 5 ቀን 2008 ዓ.ም የተጻፈ አምስት ገጽ አቤቱታ አቅርቧል።
የአቤቱታዉ ይዘት በአጭሩ፡--ወላጅ አባታችን ይህን መኖሪያ ቤትና ቦታ በ1952 በዉል ገዝተዉ ቤቶችን ሰርተዉ በ1962 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸዉ አመልካችና የሥር የመ/ተጠሪዎች ወራሽነታችንን አረጋግጠን የቤቱና ቦታዉ ባለሀብት ሆነናል።
ይህን ቤትና ቦታ ለመከፋፈል በእርቅ ስምምነት ለመጨረስ ተስማምተን በዚህ መሰረት ስምምነት አድርገን ፍ/ቤቱም ስምምነቱ ከሕግና ሞራል የማይቃረን መሆኑን በማረጋገጥ ስምምነቱን በማጽደቅ ክርክሩ ተቋጭቷል። በዚህ ጉዳይ የላዝ አዋጅ ቁጥር 721/2004 እና አዋጁን ለማስፈጸም የወጡት መመሪያዎች ተፈጻሚነት የልላቸዉ ሆኖ እያለ የስር ፍ/ቤት በባለሙያ እንዲጣራ የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ የይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ዉሳኔ እንዲሻርልን የሥር ፍ/ቤት ዉሳኔ እንዲጸናልኝ ወጪዎችን ተጠሪ እንዲተካልኝ በማለት አመልክቷል።
ይህ አቤቱታ ያስቀርባል በመባሉ ተጠሪ መልስ እንዲያቀርብ በታዘዘዉ መሰረት የአሁን ተጠሪ ህዳር 26 ቀን 2009 ዓ.ም የተጻፈ አራት ገጽ መልስ አቅርቧል። የመልሱም ይዘት በአጭሩ፡--የሥር ከፍተኛ ፍ/ቤት ክርክር ያስነሳዉ ይዞታን በተመለከተ የባለሙያ አስተያየት በመቀበል ዉሳኔ እንዲሰጥበት ወደ ሥር ፍ/ቤት መመለሱ በአግባቡ ስለሆነ እንዲጸናልን ኪሳራ እንዲከፈልን በማለት በዝርዝር ተከራክሯል። አመልካች የመልስ መልስ አቅርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተመለከተዉ ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኛቸዉን ክርክር አግባብነት ካላቸዉ የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንዲሁም ለክርክር ምክንያት የሆነዉ ይዞታ በተመለከተ የክፍፍል ስምምነቱ ላፈጸም የሚችል መሆን አለመሆኑን በባለሙያ ላጣራ ይገባል የመባሉን አግባብነት እንደጭብጥ በመያዝ እንደሚከተለዉ መርምሮታል። እንደመረመርነዉ የአመልካች ወላጅ አባትና አዉራሽ የሆኑት ሻለቃ ካሳ ሃይሉ ለረጅም አመታት ለክርክር ምክንያት የሆነዉን ቤትና ቦታ ይዘዉ ሲኖሩበት እንደነበር እና የባለሀብትነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንደልላቸዉ በሥር ፍ/ቤት የተረጋገጠ ፍሬ ነገር ነዉ። ሻለቃ ካሳ ሃይሉ ይህን ቤትና ቦታ በተመለከተ የይዞታ ምስክር ወረቀት ባይኖራቸዉም ይዞታዉ የዉርስ ሀብት ስለመሆኑ ልሎች ሰነድ ማስረጃዎች መቅረባቸዉን እና ይዞታዉም ሰነድ አልባ እንደሆነ የሥር ዉሳኔ ግልባጭ ያሳያል። ሻለቃ ካሳ መሞታቸዉን ተከትሎ የአሁን አመልካች እና በዚህ ችሎት ባለዉ ክርክር ተካፋይ ያልሆኑት ወራሾች ወራሽነታቸዉን በማረጋገጥ ይህን የዉርስ ሀብት የሆነዉን ቤትና ይዞታ በ1993 ዓ.ም በእርቅ ስምምነት ተከፋፍለዉ ይህን ስምምነታቸዉን ደግሞ ለፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አቅርበዉ ፍ/ቤቱም ስምምነቱን በሕጉ አግባብ በማየት ማጽደቁን የሥር ዉሳኔ የሚያመለክተዉ ጉዳይ ነዉ።
እንግዲህ የአሁን ተጠሪ ባቀረበዉ የፍርድ መቃወም አቤቱታ አመልካችና ልሎች ወራሾች በስምምነት የመንግስትን ይዞታ ስለተከፋፈሉ በነባር ይዞታ አግባብ እና በላዝ አዋጁ መሰረት እንዲፈጸም ዳኝነት መጠየቁን ክርክሩ ያሳያል። አመልካች አጥብቀዉ የሚከራከሩት በዚህ ጉዳይ የላዝ አዋጁ ተፈጻሚነት የለዉም የሚል ነዉ። ስለሆነም በዚህ ጉዳይ መታየት ያለበት የላዝ አዋጅ ቁጥር 721/2004 እና ይህን አዋጅ ተከትለዉ የወጡት መመሪያዎች ተፈጻሚነት አላቸዉ ወይስ የላቸዉም? ይህን አዋጅ መነሻ በማድረግ ይዞታዉ በባለሙያ ላጣራ ይገባል መባሉ ተገቢ ነዉ ወይስ አይደለም?
የሚሉት ነጥቦች ናቸዉ።
በዚህ መሰረት የአሁን አመልካች እና ልሎች ወራሾች የወላጅ አባታቸዉ ሻለቃ ካሳ ሃይሉ ወራሾች መሆናቸዉን፣ ይህን ቤትና ይዞታ በእርቅ ስምምነት በ1993 ዓ.ም ተካፍለዉ ስምምቱም በዛኑ ዓመት በፍ/ቤት የጸደቀ መሆኑን እና ይዞታዉም በነባር ይዞታ አግባብ የሚታይ እንደመሆኑ መጠን የከተማ ቦታን በላዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 6 /3/ መሰረት ተፈፃሚነት ያለዉ ሆኖ አይገኝም። በዚህ አዋጅ አንቀጽ 5 /1/ ሥር እንደተመለከተዉ ማንኛዉም ሰዉ የከተማ መሬትን በአዋጁ ከተደነገገዉ የላዝ ሥርዓት ዉጪ መያዝ እንደማይችል ደንግጎታል። እንዲሁም ነባር ይዞታዎች ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 6 መሰረት ወደ ላዝ ስሪት የሚቀየሩበትን ሁኔታዎች በዝርዝር ደንግጎ እናገኛለን። ይሁን እንጂ በዚህ አዋጅ ቁጥር 6 /3/ ሥር እንደተመለከተዉ በነባር ይዞታ ላይ ያረፈዉ ንብረት ባለቤትነት በዉርስ አግባብ የሚተላለፍ እንደሆነ በአዋጁ የተመለከተዉ የላዝ ስሪት ተፈጻሚነት እንደማይኖረዉ በግልጽ ያመለክታል። ከዚህ መገንዘብ የሚቻለዉ በነባር ይዞታ ላይ ያረፈዉ ንብረት በዉርስ የሚተላለፍ እንደሆነ ወደ ላዝ ሥሪት ማስገባቱ ከአዋጁ ዓላማ ጋር የማይሄድና አዋጁ ተፈጻሚነት ላኖረዉ እንደማይገባዉ ነዉ። ይህን አዋጅ ለማስፈጸም አዋጁን ተከትለዉ የወጡት መመሪያዎች ደግሞ ከአዋጁ ላቃረኑ ይችላሉ ተብሎም ስለማይገመት፣ በነባር ይዞታ ላይ ያረፈዉ ንብረት ባለቤትነት በዉርስ አግባብ ሲተላለፍ መመሪያዎቹም ተፈጻሚነት ላኖራቸዉ አይችልም።
በዚህ ጉዳይ የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ወራሾች ያቀረቡትን የእርቅ ስምምነት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.277 /1/ በሚደነግገዉ አግባብ ሕግንና ሞራልን የማይቃወም መሆኑን በማረጋገጥ በማጽደቅ ከመዝገቡ እንዲያያዝ ያደርጋል ተብሎ ይገመታል። የአሁን ተጠሪ ባቀረበዉ ክርክር በዚህ ድንጋጌ አግባብ አለመፈጸሙን የሚያረጋግጥ ነገር ስለማቅረቡ መዝገቡ አያመለክትም። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 721/2004 ተፈጻሚነት የልለዉ ሆኖ ሳለ የሥር ፍ/ቤቶች ነባር ይዞታዎች ወደ ላዝ ስሪት የሚገቡበትን ሂደት በመጥቀስ ይዞታዉ በስምምነት ላካፈል የሚችል መሆን አለመሆኑን በባለሙያ ላጣራ ይገባል በማለት የሰጡት ዉሳኔ የአዋጁን ዓላማና የተፈጻሚነት ወሰን ያላገናዘብ ሆኖ አግኝተነዋል።
ሲጠቃለል የሥር ከፍተኛ ፍ/ቤት እና የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ለአሁን አመልካች እና ለልሎች ወራሾች የተላለፈዉ በነባር ይዞታ ላይ ያረፈዉ የዉርስ ንብረት በተመለከተ የአዋጅ ቁጥር 721/2004 ተፈጻሚነት የልለዉ ሆኖ ሳለ በዚህ አዋጅ መሰረት የዉርስ ሀብቱ ያረፈበት ይዞታ በስምምነት የሚካፈል መሆን አለመሆኑን ባለሙያ እንዲያጣራ በማለት የሰጡት ዉሳኔና ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመባቸዉ ስለሆነ የሚከተለዉ ተወስኗል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ.165672 በ5/7/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ እና ይህን ዉሳኔ በማጽናት የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.127492 በ16/10/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመባቸዉ ስለሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348 /1/ መሰረት ተሽሯል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ.ቁ.37664 በ3/2/2007 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያልተፈጸመበት ስለሆነ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348 /1/ መሰረት ጸንቷል።
የዚህ ዉሳኔ ግልባጭ ለሥር ፍ/ቤቶች ይድረስ።
ግራ ቀኛቸዉ በዚህ ችሎት የደረሰባቸዉን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸዉን ይቻሉ።
No topics extracted.