ኑዛዜ ጥብቅ የሆነ፣ የግል ጠባይ ያለው እና በሟች ብቻ የሚፈፀም በመሆኑ ብዙ ሰዎችን አንድ በሆነ ፅሁፍ በጋራ ማናዘዝ የማይቻል እና ኑዛዜውን ፈራሽ የሚያደርግ ስለመሆኑ፡የፍ/ብ/ህ/ቁ 857፣858 እና 880
No summary available.
መስከረም 25 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- ፀጋይ አስማማው አልማው ወል ሙስጠፋ አህመድ አብርሃ መሰለ ጳውሎስ ኦርሺሶ አመልካች፡- አቶ አባተ ሀይሉ -ጠበቃ አዲስ ለገሰ ቀረቡ ተጠሪዎች፡-
አቶ አስረስ ረታ
አቶ ኑርዬ ሰማው
አቶ የሽምቢ ሰማው የቀረበ የለም።
አቶ ሀይሉ ከበደ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በአማራ ብ/ክ/መ/ ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ፍርድ ቤት ነው። በሥር ፍርድ ቤት የአሁን ከ1-3 ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተጠሪዎች አሻሽለው ባቀረቡት ክስ እነዚህ ተጠሪዎች የሟች ዘሙ ሰማው ወንድምና እህት መሆናችን በመዝገብ 88 በህጋዊ መንገድ ወራሽነታችንን አረጋግጠናል። ሟች ዘሙ ሰማው ከመሞቷ በፊት ከ4ኛ ተጠሪ ጋር ባልና ሚስት ነበሩ፤
የንብረት አስተዳደራቸውንም አስመልክቶ በየግላቸው ይዘው ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ በቀን 20/03/2006 ዓ.ም ለአመልካች በ108 ካ/ሜ ቦታ ውስጥ ያለው የግል መኖሪያ ቤቷን በኑዛዜ ካስተላለፈች በኋላ 4ኛ ተጠሪ ጋር ንብረታቸውን የጋራ ለማድረግ ተስማምተው ቆቦ ከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት በቀን 30/05/2006 ዓ.ም ማስረጃ ያወጡ ሲሆን በኑዛዜ ለማንም ያልተሰጠውንና በቆቦ ከተማ 01 ቀበል በክሱ በአዋሳኝ የተገለፀው 253 ካ/ሜ ቦታ በጋራ የሰሩትን አሜሪካን ሞድ ቤት ጓዳና ሳሎን ያለው እና አንድ ሰርቪስ በብሎኬት የተሰራ ግምቱ ብር 500,000.00/አምስት መቶ ሺህ ብር/ የሚያወጣው ድርሻ 126.5 ካ/ሜ ከፍሎ እንዲሰጠን እንዲወሰንልን በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል።
የአሁን 4ኛ ተጠሪም ለአቤቱታው የሰጡት መልስ ክርክር የተነሰበት ንብረት ያረፈበት የመኖሪያ ቤት ከእናቱ እሟሆይ ሙሽራ አባይ በውርስ ያገኘው እና አሜሪካ ሞድ የተባለው ቤትንም ከሟች ጋር ከመጋባቱ በፊት በግሉ የሰራው መሆኑን ገልፆ የተከራከረ ሲሆን የአሁን አመልካች በበኩሉ በክርክር ጣልቃ እንዲገባ ጠይቆ ተፈቅዶለት አከራካሪው ቤት 4ኛ ተጠሪ እና ሟች ዘሙ ሰማው በወረዳ ፍትህ ጽ/ቤት በመቅረብ በ20/03/2006 ዓ.ም ባደረጉት ኑዛዜ ያስተላለፉልኝ በመሆኑ በውርስ ላጠየቁት የማይገባ ፤ኑዛዜውም በህግ በተደነገገው ኑዛዜ በተሰጠበት አይነት ግልፅ ተግባር ያልተሻረ መሆኑን በመግለፅ ያቀረቡት የሟች ንብረት ያለኑዛዜ ወራሽነት ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግ በማለት ተከራክረዋል። የስር ፍርድ ቤትም ኑዛዜው ብዙ ሰዎች በአንድ ላይ ስለአደረጉት እና በተዘዋዋሪ መንገድ ተሽሯል በማለት የፍ/ብ/ህ/ቁ.858 እና 900/1/ በመጥቀስ ለክርክር ምክንያት የሆነው ቦታና ቤት ለተጠሪዎች ይገባል በማለት ወስኗል።
የአሁን አመልካች የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ለሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱም የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ስህተት ያለበት ሆኖ አልተገኘም በማለት በትእዛዝ ሰርዞታል። በመቀጠል ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኘም።
የሰበር አቤቱታው የቀረበውም ይህንኑ የስር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። አመልካች ህዳር 29 ቀን 2009 ዓ.ም በፃፉት አቤቱታ በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶችን ዘርዝረው አቅርበዋል። የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ በመደረጉ ተጠሪዎች መልስ እንዲሰጡበት በታዘዘው መሰረት ከ1-3 ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተጠሪዎች ሚያዚያ 2 ቀን 2009ዓ.ም፤4ኛ ተጠሪ መጋቢት 28 ቀን 2009 ዓ.ም የተፃፈ መልስ አቅርበዋል። አመልካችም አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክረዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርምረናል። የአመልካች ጥያቄ የስር ፍርድ ቤቶች ኑዛዜው በብዙ ሰዎች የተደረገ ስለሆነ እና በተዘዋዋሪ መንገድ የተሻረ ስለሆነ የሟች ድርሻ ቤትና ቦታ ከ1ኛ-3ኛ ያሉ ተጠሪዎች በውርስ ላተላለፍ የሚገባው ነው በሚል የሰጡት ውሳኔ መስረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ ሙሉ በሙሉ ተሽሮ ክርክር ከተነሰባት ቤትና ቦታ ውስጥ የሟች ድርሻ የሆነው ለአመልካች በኑዛዜ የተላለፈ ነው ተብሎ ላወሰን ይገባል የሚል ሲሆን ከ1ኛ-3ኛ ያሉ ተጠሪዎች ደግሞ ለአሁን አመልካችና ወንድሙ በቀን 20/03/2006 ዓ.ም ኑዛዜ ሲያደርጉ በየግል ንብረታቸው በተለየ ሰነድ መናዘዝ ሲኖርባቸው ነገር ግን ሟች ዘሙ ሰማው የግል ንብረት ላይ 4ኛ ተጠሪ በኑዛዜ ሰነድ ላይ በጋራ ኑዛዜ አድርጎ በመገኘቱ ኑዛዜውን ፈራሽ የሚያደርገው መሆኑ በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔው የተሰጠው በዚህ ረገድ ሆኖ ሳለ አመልካች ግን ከኑዛዜው ውጭ ለአገልግሎት ጽ/ቤት የየግል ንብረታቸውን በስምምነት የጋራ ማድረጋቸው እና ካርታ እና ፕላን ማውጣቸው በዝምታ እንደተሻረ አድርገው ማቅረባቸው ፍፁም ከስር ፍርድ ቤቶች ጭብጥ እና ውሳኔ ጋር የማይገናኝ በመሆኑ የአመልካች አቤቱታ ሙሉ በሙሉ ውድቅ እንዲደረግ በማለት ተከራክረዋል። የ4ኛ ተጠሪ መልስ ለልጆቻቸው የተደረገው ኑዛዜ ላሻር አይገባም በማለት የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተገቢ በመሆኑ በመግለፅ መልስ ሰጥቷል።
ከመዝገቡ መገንዘብ የተቻለው ለክርክር ምክንያት የሆነው ሟች ዘሙ ሰማው ከ4ኛ ተጠሪ ጋር ባልና ሚስት የነበሩ መሆናቸው፤የንብረት አስተዳደራቸውን በተመለከተ በየግላቸው ይዘው ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ ሟች የግል ንብረቷን አስመልክቶ በቀን 20/03/2006 ዓ.ም ለአመልካች በ108 ካ/ሜ ውስጥ ያላትን የግል መኖሪያ ቤቷን ከ4ኛ ተጠሪ ጋር በኑዛዜ ከአስተላለፈች በኋላ ከ4ኛ ተጠሪ /የስር ተከሳሽ/ ንብረታቸውን አስመልክቶ የጋራ ማድረግ እንዳለባቸው ተስማምተው በቆቦ ከተማ አገልግሎት ጽ/ቤት በኩል በቀን 30/05/2006 ዓ.ም ማስረጃ ያስወጡ መሆናቸው ፍሬ ጉዳዩን የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን የተሰጣቸው የስር ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት ጉዳይ ነው።
በመሰረቱ ኑዛዜ ጥብቅ የሆነ የግል ጠባይ ያለው መሆኑን በፍ/ብ/ህ/ቁ.857 ስር ተደንግጓል፤የሟች ጥብቅ የሆነ እራሱ የሚፈፀመው ስራ በመሆኑ በፍ/ብ/ህ/ቁ.858 ስር ብዙ ሰዎች አንድ በሆነ ጽሁፍ ማናዘዝ የማይቻል መሆኑን ተመልክቷል። ይህንንም ከፍ/ብ/ህ/ቁ.880 እና ተከታዮቹ ጭምር ተንፀባርቋል፤ አሁን በተያዘው ጉዳይ ሟች ዘሙ ሰማው እና 4ኛ ተጠሪ ለአመልካችና ለወንድሙ በአንድ የኑዛዜ ጽሁፍ ላይ በጋራ ተናዘዋል፤ይህ ደግሞ ከላይ እንደተመለከትነው ኑዛዜ ጥብቅ የሆነ ሟች ብቻውን እራሱ የሚፈፅመው በመሆኑ በጋራ መናዘዝ በፍ/ብ/ህ/ቁ.858 የተደነገገ በመሆኑ ኑዛዜው ፈራሽ ነው። ስለሆነም የስር ፍርድ ቤቶችም ኑዛዜው በቀን 20/03/2006 ዓ.ም የተደረገው ኑዛዜ ህጋዊነትን አስመልክቶ በሟች ዘሙ ሰማው የግል ንብረት ላይ 4ኛ ተጠሪ የሆነው በግል ንብረቷ ላይ በአንድ የኑዛዜ ሰነድ ላይ ተናዘዘው መገኘታቸው እና ከፍ/ብ/ህ/ቁ.858፤857 እና 880 እና ተከታዩ ድንጋጌዎች አንፃር በመመርመር ሟች ዘሙ ሰማው እና 4ኛ ተጠሪ ለአመልካች እና ለወንድሙ በአንድ የኑዛዜ ፅሁፍ የግል ንብረቷን በአንድ ላይ ተናዘው በመገኘታቸው የስር ፍርድ ቤቶች ኑዛዜውን ፈራሽ ነው በማለት ውሳኔ መስጠታቸው የሚነቀፍበት ህጋዊ ምክንያት የልለበት በመሆኑ አመልካች ክርክር ከተነሰባት ቤትና ቦታ ውስጥ የሟች ድርሻ የሆነው ለአመልካች በኑዛዜ የተላለፈ ነው ተብሎ ላወሰን ይገባል በማለት ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት የለውም።
ሲጠቃለል ስር ፍርድ ቤቶች በዚህ ጉዳይ የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ ሆነ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ስላልተገኘ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
በራያ ቆቦ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/1 መጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ/ም እና በሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ሚያዚያ 17 ቀን 2008 ዓ/ም ተሰጥቶ በአማራ ብ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 03-14318 ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ/ም በውሳኔ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል።
ከዚህ ፍርድ ቤት መጋቢት 8 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በራያ ቆቦ ወረዳ ፍርድ ቤት በመ/ቁ.0127811 የተጀመረው አፈፃፀም ታግዶ እንዲቆይ ተሰጥቶ የነበረው የእግድ ትእዛዝ ተነስቷል። ይፃፍ።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.