በተጎጂ ላይ ከደረሰ የሞት አደጋ የተነሳ በራሳቸው ስም ሆነው በመተዳደሪያ ረገድ ለሚደርስባቸው ጉዳት ካሳ ለመጠየቅ የሚችሉት፤ የተጎጂ ባል ወይም ሚስት፤ ወይም ወላጆቹና ልጆቹ ብቻ እንጂ ወንድም ወይም እህት መጠየቅ ስላለመቻላቸው፡የፍ/ብ/ህ/ቁ.2095/1/
No summary available.
መስከረም 25 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- ፀጋይ አስማማው ሙስጠፋ አህመድ አብርሃ መሰለ ጳውሎስ ኦርሺሶ ሰናይት አድነው አመልካች፡- አቶ ፍቃዱ በለጠ - የቀረበ የለም ተጠሪዎች፡-
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበውን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ ሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው። በሥር ፍርድ ቤት የአሁን ተጠሪዎች በአመልካችና 2ኛ ተከሳሽ በነበረው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ላይ ያቀረቡት ክስ የአመልካች ንብረት የሆነው የሴ.ቁ 3-75918 ሲኖትራክ የጭነት መኪና በ03/05/2008 ዓ.ም ከጋምቤላ ወደ ቴፒ አሸዋ ጭኖ በመጓዝ ላይ እያለ በደቡብ ክልል ሸካ ዞን የኪ ወረዳ እርምጫ ቀበል ልዩ ስሙ ጫቲ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ሲደርስ መንገድ ስቶ አቶ ታምሩ ገላቶ መኖሪያ ቤት ላይ በመውጣት የ1ኛ ተጠሪ ልጅ የሆነውን ተሻለ ታምሩ የተባለውን ልላት በተኛበት ገጭቶ የገደለ በመሆኑ ይህ ሟች በግብርናና ንግድ ስራ ተሰማርቶ በሚያገኘው ገቢ ይጦራችን ስለነበረ በመሞቱ ምክንያት የተቋጠረውን ገቢ ለ1ኛ ተጠሪ ብር 50,000.00 (ሃምሳ ሺህ ብር)፤ለ2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ለእያንዳንዳቸው ብር 80,000.00 (ሰማንያ ሺህ ብር) በድምሩ 160,000.00 (አንድ መቶ ስልሳ ሺህ ብር) እንዲሁም ወላጅ አባታቸው አቶ ታምሩ ገላቶም በ40 ዓመት እድሜያቸው በዚህ አደጋ ስለሞቱና ይጦራቸው ስለነበረ 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ትምህርታቸውን እስከሚጨርሱ ብር 108,000.00 ( አንድ መቶ ስምንት ሺህ ብር) እና 118,800.0 (አንድ መቶ አስራ ስምንት ሺህ ስምንት መቶ ብር) ለሁለቱ እንዲከፍሉ፤ 4ኛ ተጠሪ የሟች የአቶ ታምሩ ገላቶ ወላጅ እናት የሆኑት ሟች ልጃቸው ለመጦሪና ለቀለብ ይሰጣቸው የነበረው ስለተቋረጠ ብር 51,000.00 (ሃምሳ አንድ ሺህ ብር) እሱ በመሞቱ የሞራል ካሳ ብር 2,000.00 (ሁለት ሺህ ብር) እና ለቀብር ማስፈፀሚያ ብር 10,000.00 (አስር ሺህ ብር) በድምሩ ብር 499,800.00 (አራት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ሺህ ስምንት መቶ ብር) 2ኛ ተከሳሽ የጉዳት አድራሹ መኪና ባለቤት ከኢንሹራንስ ሽፋን ሰጭ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጋር ሆነው ለተጠሪዎች እንዲከፍሉ ተብሎ እንዲወሰንላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል። ክሱ የቀረበለት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከአመልካችና 2ኛ ተከሳሽ ከነበረው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት መልስ ተቀብሎ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ተከሳሾቹን ለክሱ ኃላፊ በማድረግ ተጠሪዎች በርትዕ ብር 236,000.00 (ሁለት መቶ ሰላሳ ስድስት ሺህ ብር) ላከፈላቸው ይገባል፤ከዚህ ውስጥ 2ኛ ተከሳሽ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ብር 40,000.00 (አርባ ሺህ ብር) ይክፈለው ቀሪ ብር 196,000.00 ( አንድ መቶ ዘጠና ስድስት ሺህ ብር) አመልካች እንዲከፍል ሲል ወስኗል።
የአሁን አመልካች ይህንን የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱም የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ስህተት ያለበት ሆኖ አልተገኘም በማለት በትእዛዝ ሰርዞቶታል። የሰበር አቤቱታው የቀረበውም ይህንኑ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። አመልካች ህዳር 15 ቀን 2009 ዓ.ም በፃፉት አቤቱታ በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶች ዘርዝረው አቅርበዋል። የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ በመደረጉ ተጠሪዎቸ መልስ እንዲሰጡበት በታዘዘው መሰረት ጥር 2 ቀን 2009 ዓ.ም የተፃፈ መልስ አቅርበዋል። አመልካችም አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክረዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን እኛም አቤቱታ የቀረበበት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን አለመሆኑን ለክርክሩ ከተያዘው ጭብጥ አንፃር መርምረናል። እንደመረመርነውም የአመልካች ጥያቄ የጉዳት ካሳ መጠን የስር ፍርድ ቤቶች በርትዕ መወሰናቸው እንዲሁም የአሁን 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ወንድማቸው ተሻለ ታምሩ ላይ በአመልካች መኪና በደረሰው የሞት ጉዳት ምክንያት የተቋረጠውን የመጦሪያ ቀለብ የመጠየቅ መብት ሳይኖራቸው አመልካች የጉዳት ካሳ እንዲከፍል የተሰጠ ውሳኔ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2ዐ95/1/ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ የሚጥስ በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ ላታረም ይገባል የሚል ሲሆን በተጠሪዎች በኩል ደግሞ በጉዳቱ ምክንያት የተቋረጠባቸው ከፍተኛ የሆነ የመጦሪያና የቀለብ ገቢ በርትዕ አመልካች እንዲከፍል መወሰኑ ህግን መሰረት ያደረገ ስለሆነ የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ ላፀና ይገባል በማለት ተከራክረዋል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው 1ኛ ተጠሪ ልጃቸው ተሻለ ታመሩ ፤2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች አባታቸው ታምሩ ገላቶ እና ወንድማቸው ተሻለ ታምሩ በአመልካች መኪና ጉዳት ደርሶባቸው ህይወታቸው በማለፉ ምክንያት መጦሪያና የቀለብ ገቢ እንዲከፈላቸው የጠየቁ መሆናቸው፤የ4ኛ ተጠሪ ጥያቄ ደግሞ የሟች አቶ ታምሩ ገላቶ ወላጅ እናት በመሆናቸው ካሳ የጠየቁ መሆኑን ነው። አመልካች ለጉዳቱ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በተመለከተ አከራካሪ አይደለም እንዲሁም ሟቾች በህይወት እያሉ በእርሻ ስራ፤በንብ ማነብና በንግድ ተሰማርተው ቤተሰቦቻቸው ያስተዳድሩ የነበሩ መሆናቸውና የተቋረጠ ቀለብና መጦሪያ መኖሩን ፍሬ ጉዳዩን የማጣራትና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን የተሰጣቸው የስር ፍርድ ቤቶች ያረጋገጡት ጉዳይ ነው። ስለሆነም አመልካች ተጠሪዎች ለደረሰባቸው ጉዳት ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ከተረጋገጠ የጉዳት ካሳ የመክፈል ግድታ ጥያቄ ውስጥ ላገባ የሚችል አይደለም። በመሆኑም የካሳ መጠን ለመወሰን አስቸጋሪ ሁኔታ መኖሩን ፍርድ ቤቱ ከተገነዘበ በፍ/ብ/ህ/ቁ.2102 ድንጋጌ መሰረት በርትዕ መወሰን እንደሚቻል በግልፅ ተመልክቷል። ስለዚህ አመልካች የካሳ መጠን አወሳሰን በተመለከተ ያቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት የለውም። በልላ በኩል አመልካች አጥብቀው የሚከራከሩበት ነጥብ 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች በወንድማቸው ሞት ምክንያት ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ ለመጠየቅ በፍ/ብ/ህ/ቁ.2095/1/ መሰረት መብት ሳይኖራቸው እንዲከፈላቸው የተሰጠ ውሳኔ ላታረም ይገባል የሚል ነው። በተጎጂው ላይ ከደረሰው የሞት አደጋ የተነሳ በራሳቸው ስም ሆነው በመተዳደሪያ ረገድ ለሚደርስባቸው ጉዳት ካሳ ለመጠየቅ የሚችሉት የተጎጂው ባል ወይም ሚስት፤ወይም ወላጆቹና ልጆቹ እንደሆኑ የፍ/ብ/ህ/ቁ.2095/1/ ይደነግጋል። ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች የጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው መሰረት ያደረጉት አባታቸው አቶ ታምሩ ገላቶ እና ወንድማቸው አቶ ተሻለ ታምሩ በአመልካች መኪና ጉዳት ደርሶባቸው በመሞታቸው ምክንያት ለተቋረጠባቸው መጦሪያና ቀለብ ገቢ እንዲከፈላቸው ነው። ወንድማቸው በመሞቱ ጉዳት ካሳ ለመጠየቅ የሚያስችል መብት ሳይኖራቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት የልለው ሁኖ እያለ በአባታቸውና ወንድማቸው ሞት ምክንያት የተቋረጠባቸው መጦሪያና ቀለብ ገቢ አመልካች እንዲከፍል የተሰጠ ውሳኔ ላታረም የሚገባው ሆኖ አግኝተነዋል።
ሲጠቃለል የስር ፍርድ ቤቶች ተጠሪዎች የተቋረጠባቸው መጦሪያና ቀለብ ገቢ መኖሩን በማረጋገጥ የጉዳት ካሳ መጠን በርትዕ መሰረት በማድረግ መወሰናቸው በአግባቡ ሆኖ ነገር ግን 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች በወንድማቸው ሞት ምክንያት የጉዳት ካሳ የመጠየቅ መብት ሳይኖራቸው ይህን ሳይለይ የተሰጠ ውሳኔ በከፊል መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ሆኖ ስለተገኘ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
በሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ መስከረም 20 ቀን 2009 ዓ/ም ተሰጥቶ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ ጥቅምት 22 ቀን 2009ዓ/ም በትእዛዝ የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ተሻሻለዋል።
2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች በአባታቸው ላይ በደረሰው የሞት አደጋ ካልሆነ በስተቀር በወንድማቸው ላይ ከደረሰው የሞት አደጋ የተነሳ በራሳቸው ስም ሆነው በመተዳደሪያ ረገድ ለሚደርስባቸው ጉዳት ካሳ ለመጠየቅ አይችሉም ብለናል።
ስለሆነም 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ሟቾች አባታቸውና ወንድማቸው በመሞታቸው ምክንያት የተቋረጠባቸውን የቀለብና የመጦሪያ እንዲሁም የትምህርትና የህክምና ወጪ በርትዕ እያንዳንዳቸው ብር 80,000.00/ሰማንያ ሺህ ብር/ እንዲከፈላቸው የተሰጠ ውሳኔ ክፍል በማሻሻል 2ኛ እና 3ኛ ተጠሪዎች ላከፈላቸው የሚገባው ለእያንዳንዳቸው ብር 40,000/አርባ ሺህ ብር/ በማለት ወስነናል።
ተጠሪዎች ላከፈላቸው ከሚገባ የሞት ጉዳት ካሳ፤የሞራል ካሳ እና ለቀብር ማስፈፀሚያ በድምሩ ብር 156,000.00 /አንድ መቶ ሃምሳ ስድስት ሺህ ብር/ ውስጥ 2ኛ ተከሳሽ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ብር 40,000.00 /አርባ ሺህ ብር/ እንዲከፍል ቀሪው ብር 116,000.00 (አንድ መቶ አስራ ስድስት ሺህ ብር) አመልካች ለተጠሪዎች እንዲከፍል ወስኗል።
ከዚህ ፍርድ ቤት ህዳር 20 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቴፒ ምድብ ችሎት በመ/ቁ.12143 የተጀመረው አፈፃፀም ታግዶ እንዲቆይ ተሰጥቶ የነበረው የእግድ ትእዛዝ ተነስቷል። ይፃፍ።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.