አንድ ሰው የትራንስፖርት ክፍያ ከፍሎ በመኪና ሲጓዝ በነበረበት ወቅት የአካል ጉዳት ቢደርስበት የንግድ ህጉን መሰረት ያደረገና በውል ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በተጎጂው እና በአጓዡ መካከል ተመስርቷል ማለት ስለሚቻልበት ሁኔታና አጓዡ ለመንገደኛው ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ኃላፊነቱ ላታይ የሚገባው በንግድ ህጉ ስለ አጓዥ እና ተጓዥ በተደነገገው ድንጋጌ መሰረት መሰረት ስለመሆኑ፡- XXXI የንግድ ሕግ ቁጥር 561፣ 595 ፣596 ፣ 597 እና 599
No summary available.
ህዳር 20 ቀን 2010 ዓ/ም ዳኞች፡- አልማው ወል ሙስጠፋ አህመድ አብርሃ መሰለ ጰውሎስ ኦርሺሶ ሰናይት አድነው አመልካች፡- ወ/ሮ ምስራ መሐመድ፤ ቀረቡ ተጠሪዎች፡- 1.አቶ አብደላ፤ አሜ ቀረቡ 2 አቶ ፋሃሚ መሐመድ፣ በልሉበት የታየ ነው መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
የክርክሩ ምክንያት የአካል ጉዳት ካሳን የሚመለከት ነው። የአሁን አመልካች የሥር ከሳሽ በሆኑበት በአሁኑ ተጠሪዎች ላይ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ክፍተኛ ፍርድ ቤት ላይ ባቀረቡት ክስ ንብረትነቱ የ1ኛ ተከሳሽ /የአሁን 1ኛ ተጠሪ/ የሆነ የሰልዳ ኦሮ የሆነ በ2ኛ ተከሳሽ /በአሁን 2ኛ ተጠሪ/ ይሽከረከር የነበረ አይሱዙ መኪና በቀን 22/07/2007 ዓ/ም ከተፈቀደለት በላይ በፍጥነት በማሽከርከር ላይ እያለ ከግድግዳ ጋር በመጋጨት ድንጋይ ተፈናጥሮ የቀኝ አይኔ ላይ ጉዳት ስላደረሰብኝ የጉዳት ካሳ እና የተለያዩ ወጪዎችን ጨምሮ በድምሩ ብር 71,100.00 /ሰባ አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር/ ተከሳሾች የአሁኖቹ ተጠሪዎች/ እንዲከፍሉ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል።
የአሁን 1ኛ ተጠሪ /የሥር 1ኛ ተከሳሽ/ መኪናዬ የጭነት እንጂ የህዝብ አይደለም፣ ከሳሽ /የአሁን አመልካች/ በመኪናዬ አልተሳፈረችም በማለት ከተከራከሩ በኃላ መኪናው የሶስተኛ ወገን የኢንሹራንስ ሽፋን ስላለው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጥሪ ተደርጎለት ቀርቦ መኪናው የሶስተኛ ወገን የኢንሹራንስ ሽፋን የልለው መሆኑን በመግለጹና የሥር 1ኛ ተከሳሽም ማስረጃ ባለማቅረባቸው መድን ከክርክሩ እንዲወጣ የተደረገ ሲሆን የአሁን 2ኛ ተጠሪም /የሥር 2ኛ ተከሳሽም/ ከሳሽን መጫናቸውን አምነው ጉዳት ግን እሳቸው በሚያሽከረክሩት መኪና እንዳልደረሰ ክደው በመከራከር ኃላፊነት የለብንም ብለዋል።
ጉዳዩን የተመለከተው የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃዎችን መርምሮ ለደረሰው ጉዳት ተጠሪዎች /ተከሳሾች/ ኃላፊነት አለባቸው ብሎዋል። የጉዳት ካሳን በተመለከተ ግን አመልካች በማስረጃ አላስረዱም በማለት አልፎባቸዋል።
በልላ በኩል ወጪዎችን በተመለከተ ለህክምና፣ ለትራንስፖርት እንደዚሁም ለተለያዩ ነገሮች ከሳሽ /አመልካች/ ታወጣለች ተብሎ የተገመተ ብር 5,519.00 /አምስት ሺህ አምስት መቶ አስራ ዘጠኝ ብር/፣ ክስ ለማዘጋጀት፣ ለኮፒ እና ለትርጉም በክርክሩ ምክንያት ታወጣለች ተብሎ የተገመተ ብር 3,500.00 /ሶስት ሺህ አምስት መቶ ብር/፣ ለሞራል ካሳ ብር 1000.00 /አንድ ሺህ ብር/ በድምሩ ብር 10,019.00 /አሥር ሺህ አሥራ ዘጠኝ ብር/ ተከሳሾች /ተጠሪዎች/ በአንድነትና በነጠላ ለአመልካች ይክፈሉ።
የዳኝነት ክፍያ በተወሰነው ገንዘብ ታሪፍ ልክ ተከሳሾች/ተጠሪዎች/ ለከሳሽ /ለአመልካች/ እንዲከፍሉ ሲል ውሳኔ ሰጥቷል።
የአሁኗ አመልካች በውሳኔው ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምሥራቅ ችሎት አቅርበው ተቀባይነት ያላገኘ ሲሆን ቀጥለውም አቤቱታ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ቢያቀርቡም ተዘግቶባቸዋል።
ይህ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ውሳኔውን ለማስለወጥ ሲሆን አመልካች በሥር ፍርድ ቤቶች ተፈጽመውብኛል ያሉዋቸውን ዝርዝር የቅሬታ ነጥቦችን አቅርበዋል።
የሰበር አቤቱታውን አጣሪው መርምሮ አመልካች ላይ የደረሰውን የአካል ጉዳት አስመልክቶ አግባብነት ያለው ህግ የትኛው ነው? የንግድ ህጉ ነው የሚባል ከሆነም የስልቱ መጠን ከደረሰው ጉዳት አንጻር ከህጉ ቁጥር 598 (2) አኳያ የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር ሲባል መዝገቡ ለሰበር ይቅርብ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ለተጠሪዎች ጥሪ ተደርጎላቸው 1ኛ ተጠሪ ቀርበው ግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ/ም የተጻፈ መልስ ያቀረቡ ሲሆን 2ኛ ተጠሪ መጥሪያ ለመቀበል እምቢተኛ ሆነዋል ተብሎ ቃለ መኻላ ስለቀረበ መልስ የመስጠት መብታቸው ታልፏል። ለ1ኛ ተጠሪ መልስ አመልካች በቀን 05/10/2009 ዓ/ም የተጻፈ የመልስ መልስ ሰጥተዋል።
የነገሩ አመጣጥና የክርክሩ ሂደት በአጭሩ ከላይ የተመለከተውን የሚመስል ሲሆን በሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም? የሚል ጭብጥ ተይዞ ጉዳዩ እንደሚከተለው ተመርምሯል። አመልካች በ1ኛ ተጠሪ መኪና ላይ አልተሳፈሩም በማለት 1ኛ ተጠሪ ክደው ቢከራከሩም በወቅቱ መኪናውን ያሽከረክሩ የነበሩት 2ኛ ተጠሪ አመልካች በመኪናው ላይ ስለመሳፈራቸው አምነው ተከራክረዋል። ከዚህ በተጨማሪ የግራ ቀኙ ምስክሮችም አመልካች በ2ኛ ተጠሪ አማካይነት ይሽከረከር በነበረው በ1ኛ ተጠሪ መኪና ላይ ስለመሳፈራቸው ፣አመልካች በመኪና ላይ እንዳሉ ድንጋይ ዓይኔን መታኝ እያሉ ሲጮኹ እንደነበረ ከአመልካች ጋር አብረው ተሳፍረው ሲጓዙ የነበሩ ምስክሮች መመስከራቸውን ተያይዞ ከቀረበልን የውሳኔ ግልባጭ ተመልክተናል። ከዚህ በተጨማሪ ከድሬ ጮራ ሆስፒታል በቁጥር g/268424 በቀን 19/05/2008 ዓ/ም የተጻፈ የጽሁፍ ማስረጃ የአመልካች የቀኝ ዓይን ብልን ቦታውን ለቋል፣በቋሚነት 48% ጉዳት ደርሶባታል ሲል ይገልጻል።
የምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን መርምሮ በአመልካች ዓይን ላይ ስለደረሰው ጉዳት ተጠሪዎችን ኃላፊ አድርጎዋቸዋል። ለወደፊት የታጣ ገቢ በማለት አመልካች የጠየቁትን ዳኝነት በተመለከተ ግን ከሳሽ ሥራቸው ምን እንደሆነ፣ እንደዚሁም ጤነኛ ሳሉ በወር ሲያገኙ የነበረው ገቢ ምን ያህል እንደሆነ በማስረጃ የተረጋገጠ እና የተገለጸ ነገር የለም። እንደዚሁም ይህ በዓይናቸው ላይ የደረሰው ጉዳት ለወደፊት ሰርተው የሚያገኙትን ገቢ የሚከለክላቸው ስለመሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ ነገር የለም በማለት በዚህ በኩል የተጠየቀውን ዳኝነት ውድቅ በማድረግ አልፎባቸዋል።
ለተለያዩ ወጪዎች እና ሞራል ካሳ በድምሩ ብር 10,019.00 /አሥር ሺህ አሥራ ዘጠኝ ብር/ ተከሳሾች /ተጠሪዎች/ በአንድነትና በነጠላ ለአመልካች እንዲከፍሉ ሲል ውሳኔ ሰጥቷል። የአሁን የአመልካች ቅሬታ መሰረት የሚያደርገውም የጉዳት ካሳ ሳይወሰን በመታለፉ ምክንያት ነው። በዚህ ረገድ የሥር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ ተገቢ መሆን አለመሆኑን ከደረሰው ጉዳት እና አግባብነት ካለው የህግ ድንጋጌዎች አንጻር መመልከት ተገቢ ነው።
በመሰረቱ ከላይ እንደተገለጸው በአመልካች ዓይን ላይ ጉዳት ስለመድረሱ የተረጋገጠ ሲሆን ተጠሪዎችም ለደረሰው ጉዳት ኃላፊ ተደርገዋል። ይህ ኃላፊነት ላታይ የሚገባው ደግሞ በንግድ ህጉ ስለ አጓዥ እና ተጓዥ በተደነገገው ድንጋጌ መሰረት ነው።
ምክንያቱም አመልካች ለመኪናው የትራንስፖርት ክፍያ ከፍለው ሲጓዙ በነበረበት ወቅት ድንጋይ ተፈናጥሮ በዓይናቸው ላይ ጉዳት በማድረሱ ነው። በዚህ መሰረት የንግድ ህጉን መሰረት ያደረገና በውል ላይ የተመሰረተ ግንኙት በግራ ቀኙ መካከል ተመስርቷል ማለት ነው። የንግድ ህግ አንቀጽ 561 የማጓጓዝ ውል ማለት አጓጓዥ ዋጋ በመቀበል ሰውን፣ ጓዝንና እቃዎችን የተወሰነ ስፍራ ለማድረስ ግድታ የገባበት ስምምነት ነው በማለት ይደነግጋል። የንግድ ህጉ አንቀጽ 595 ደግሞ አጓዥ ለመንገደኞች ያለበትን ኃላፊነት ያስቀምጣል። አጓዥ ከኃላፊነት የሚድንባቸው ምክንያቶች በአንቀጽ 596 ላይ የተቀመጡ ሲሆን የአጓዥ ኃላፊነት ከተረጋገጠ በአንቀጽ 599 ላይ የተመለከተው ልዩ ሁኔታ ከልለ በስተቀር የንግድ ህግ አንቀጽ 597 /1/ ላይ የተጎዳው ማንኛውም ዓይነት መንገደኛ ቢሆንም አጓዡ በአላፊነት ለአንድ መንገደኛ የሚከፍለው ገንዘብ መጠን ከ40,000.00 ብር /ከአርባ ሺህ ብር/ ላበልጥ እንደማይችል ይደነግጋል።
በተያዘው ጉዳይ በአመልካች ዓይን ላይ ለደረሰው ጉዳት ተጠሪዎች ኃላፊ መሆናቸው እስከተረጋገጠ ድረስ በንግድ ህጉ አንቀጽ 561 መሰረት በተመሰረተው በውል ግድታ፣ በአንቀጽ 595 መሰረት በአጓዥነት ግድታ መሰረት በአንቀጽ 597 /1/ ላይ የተደነገገውን ገንዘብ መጠን የመክፈል ግድታ ይኖርባቸዋል። የምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግን አመልካች ሥራቸው ምን እንደሆነ፣ ጤነኛ ሳሉ በወር ሲያገኙ የነበረው ገቢ ምን ያህል እንደሆነ በማስረጃ የተረጋገጠ እና የተገለጸ ነገር የለም። እንደዚሁም ይህ በዓይናቸው ላይ የደረሰው ጉዳት ለወደፊት ሰርተው የሚያገኙትን ገቢ የሚከለክላቸው ስለመሆኑ በማስረጃ የተረጋገጠ ነገር የለም በማለት የደረሰው ድምዳሜ ከላይ የተመለከቱትን የንግድ ህጉን ድንጋጌዎች ያገናዘበ ባለመሆኑ ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም ።
ቀጥሎ ያሉት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ይህንን ሳያርሙ ማለፋቸው ሲታይ የሚነቀፍ ሆኖ ተገኝቷል።
ሲጠቃለልም የሥር ፍርድ ቤቶች ከላይ የተመለከቱትን መሰረታዊ ነገሮችን በአግባቡ ሳያጤኑ በአመልካች ዓይን ላይ ለደረሰው ጉዳት ከሳ ላከፈል አይገባም በማለት የሰጡት ውሳኔ በከፊል መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አግኝተነዋል። በመሆኑም የሚከተለው ውሳኔ ተወስኗል።
የምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ.50296 በቀን 01/07/2008 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ፣ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 243965 በቀን 23/9/2008 ዓ/ም እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመ/ቁ.248800 በቀን 29/2/2009 ዓ/ም የሰጡት ትዕዛዝ በፍትሓብሕር ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 348 /1/ መሰረት ተሻሽሐል።
በአመልካች ዓይን ላይ ለደረሰው ጉዳት ተጠሪዎች ኃላፊነት አለባቸው ተብሎ የተወሰነው የውሳኔ ክፍል ፀንቷል።
ለልዩ ልዩ ወጪዎች እና ለሞራል ካሳ በድምሩ ብር 10,019.00 /አሥር ሺህ አሥራ ዘጠኝ ብር/ ተጠሪዎች በአንድነትና በነጠላ ለአመልካች እንዲከፍሉ ተብሎ የተወሰነው የውሳኔ ክፍል ፀንቷል።
በንግድ ህግ አንቀጽ 561፣ 595 እና 597 /1/ መሰረት 40,000.00 /አርባ ሺህ/ ብር ተጠሪዎች በአንድነትና በነጠላ ለአመልካች ላከፍሉ ይገባል ተብሎ ተሻሽሎ ተወስኗል።
ዳኝነት በተወሰነው ታርፍ ልክ ተጠሪዎች ይክፈሉ ብለናል።
የዚህን ችሎት ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
የውሳኔው ግልባጭ ለሥር ፍርድ ቤቶች ይድረሳቸው።
መዝገቡ ውሳኔ ስላገኘ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.