ለአንድ ሰራተኛ ማስጠንቀቂያ መፃፍ ብቻውን “የስራ መሪ” የማያስብልና ጉዳዩ በስራ ክርክር ችሎት ላታይ አይችልም የሚባልበት አግባብ የልለ ስለመሆኑ፡አሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 377/96 3/2/ /ሐ/ ስ እና ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 494/98 አንቀጽ 2/1/ /ሐ/ XXVIII
No summary available.
ህዳር 22 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ሙስጠፋ አህመድ አብርሃ መሰለ ጳውሎስ ኦርሺሶ ሰናይት አድነው አመልካች፡- አቶ ብርሃኑ ጌቱ ጠበቃ ተፈሪ ፅጌ ቀረቡ።
ተጠሪ፡- ብሕራዊ ትምባሆ ድርጅት አ/ማ ሰራተኛ ማሕበር የቀረበ የለም ።
መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቀረበው አመልካች የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ አጣርቶ ለመወሰን ነው። ጉዳዩ በመጀመሪያ የታየው በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው። የሥር ከሳሽ የአሁን አመልካች በተጠሪ ድርጅት ውስጥ በአስተዳደር ሙያ ስራ ተቀጥረው በወር 1712.00 /አንድ ሺህ ሰባት መቶ አስራ ሁለት ብር/ እየተከፈላቸው ኤ/አ/16/5/2014 ጀምሮ በካምቲን አስተዳደር ኃላፊ የስራ መደብ ተቀጥረው ሲሰሩ ፈቃድ እንዲወጡ ተደርጎ ከ04/04/16—13/04/16 በፈቃድ ቆይተው ሲመለሱ በብትድ/ሰ/መማ/ካ/04/07/16 በተፃፈ ደብዳቤ ከ14/04/16 ጀምሮ የስራ ውሉ ከህግ ውጭ እንዲቋርጥ በማድረጉ የስራ ስንብት ክፍያ፤የማስጠንቀቂያ ጊዜ ክፍያ፤የካሳ ክፍያ፤የዓመት እረፍት የመሳሰሉት አመልካች እንዲከፍል ተብሎ እንዲወሰንላቸው ክስ አቅርበዋል። ተጠሪም ለቀረበው ክስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና በአማራጭ መልስ በመስጠት ተከራክረዋል። ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም በቀረበው መቃወሚያ መሰረት አመልካች የስሪ መሪ በመሆናቸውን የቀረበው ክስ በስራ ክርክር ችሎት ላታይ አይችልም በማለት ብይን ሰጥቷል።
የአሁን አመልካች የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢያቀርቡም የስር ፍርድ ቤት ብይን ስህተት ያለበት ሆኖ አልተገኘም በማለት በትእዛዝ ሰርዞታል። የሰበር አቤቱታው የቀረበውም ይህንኑ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። አመልካች ሚያዚያ 13 ቀን 2009 ዓ.ም በፃፉት አቤቱታ በስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስሕተት ተፈጽሟል የሚሉባቸውን ምክንያቶችን ዘርዝረው አቅርበዋል። የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ በመደረጉ ተጠሪ መልስ እንዲሰጥበት በታዘዘው መሰረት ሐምል 18 ቀን 2009 ዓ.ም የተፃፈ መልስ አቅርበዋል። አመልካችም አቤቱታቸውን በማጠናከር የመልስ መልስ በማቅረብ ተከራክረዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ሲሆን ይህ ችሎትም አቤቱታ የቀረበበትን ውሳኔ ከግራ ቀኙን ክርክርና ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም የዚህን ችሎት ምላሽ የሚያስፈልገው ነጥብ አመልካች የስራ መሪ ናቸው በማለት የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ሆኖ ተገኝቶአል።
የአመልካች ጥያቄ በተጠሪ ድርጅት በአስተዳደር ስራ ከመቀጠር በስተቀር አንድ የአስተዳደር ኃላፊ መስራት ያለበትን እንደ ሰራተኛ መቅጠር፤ማሰናበት እድገት መስጠት መቅጣት ስራዎችን ማከናውን የሚያስችል ስልጣን ባልተሰጠበት ሁኔታ ስራ መሪ የሚያስብል ምክንያት ባለመኖሩ አመልካች በአስተዳደር ስራ መደብ በመስራቱ ብቻ የስራ መሪ አያሰኝም፤በስር ፍርድ ቤቶች የስራ መሪ ነህ ለማለት የቻሉት በቀን 4/4/14 ለወ/ሮ እታገኝ እንድሪስ የጻፍኩትን መነሻ እንደሆነ በብይኑ ላይ ገልጾ አስቀምጦታል፣ ነገር ግን የዚህ ዓይነት ልላ የአስተዳደር ስራ እንዲሰራ ተጠሪ ባላስረዳበት በዚህች ድብዳቤ መነሻ ብቻ የስራ መሪ ነህ በማለት የተሰጠ ብይን መሰረታዊ የህግ ስህተት ላታረም ይገባል የሚል ሲሆን በተጠሪ በኩል ደግሞ የአመልካች ቅጥር ደብዳቤ የስራ መሪ መሆኑን ያስረዳል፣ እንዲሁም የአስተዳደር ኃላፊ፣ የክበቡ ዋና መሪ ፣የሰራተኞች አስተዳዳሪ ቀጣሪም፣ አሰናባችም፣ ማስጠንቀቂያ ሰጪም የክበቡ የምግብ ዝግጅትና መሪ፤
በአጠቃላይ ለክበቡ ከአሁን አመልካች በቀር የመጨረሻ ባለስልጣን የለም ፣ መሪውና አስተዳዳሪው አመልካች በመሆኑ የስር ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 494/98 አንቀጽ 2/1/ሐ/ መሰረት ውሳኔ መስጠታቸው ባግባቡ ስለሆነ ላፀና ይገባል በማለት ተከራክረዋል።
በመሰረቱ የሥራ መሪ ማለት በሕግ ወይም እንደ የድርጅቱ የስራ ፀባይ በአሰሪው በተሰጠ የውክልና ስልጣን መሰረት የሥራ አመራር ፖላሲዎችን የማውጣት የማስፈፀም ከነዚሁ በተጨማሪ ወይም እነዚሁኑ ሣይጨምር ሰራተኛን የመቆጣጠር የማዛወር፣ የማገድ፣ ለማሰናበት የመመደብ ወይም የስነ-ስርዓት እርምጃ የመውሰድ ተግባሮችን የሚያከናውንና የሚወስን ግለሰብ ስለመሆኑ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ ቁ.
377/96 3/2/ /ሐ/ ስር እና በማሻሻያ አዋጁ ቁጥር 494/98 አንቀጽ 2/1/ /ሐ/ ሥር ተመልክቷል።
አመልካች በአስተዳደር ሙያ ስራ የተቀጠሩ ስለመሆናቸውና ለወ/ሮ እታገኝ እንድሪስ ማስጠንቃቂያ መፃፋቸውን ሳይክዱ በአዋጁ እንደተመለከተው የስራ መሪ ተግባራትን ስለማከናወናቸው በተጠሪ የቀረበ ማስረጃ የለም፤ለአንድ ሰራተኛ ማስጠንቀቂያ በመጻፉ ብቻ የስራ መሪ አያሰኝም ከማለት ውጭ ክበቡን የሚያስተዳድረው፣ ሰራተኞች የሚቀጥረው፤ የሚያሰናብተው የማን እንደሆነ ፤የስራ ግንኙነታቸው ከማን እንደሆነ ፤እና ስለ ክበቡ አደረጃጀት /መዋቅር/ የገለጹት ነገር የለም። የአስተዳደር ኃላፊ፣ የክበቡ ዋና መሪ፣ የሰራተኞች አስተዳዳሪ ቀጣሪም፣ አሰናባችም፣ ማስጠንቀቂያ ሰጪም፣ የክበቡ የምግብ ዝግጅትና መሪ፣ በአጠቃላይ ለክበቡ ከአሁን አመልካች በቀር የመጨረሻ ባለስልጣን የለም፣ መሪውና አስተዳዳሪው አመልካች መሆናቸው ተገልፆ በተጠሪ ለቀረበው ክርክርም አመልካች ግልፅ የሆነ ማስተባበያ በመልስ መልሳቸው ያላቀረቡ መሆኑንም ተገንዝበናል።
የስር ፍርድ ቤቶች ለአንድ ሰራተኛ ማስጠንቀቂያ በመጻፉ ብቻውን የስራ መሪ ተብሎ ይገመታል በማለት የያዙት ምክንያት ለጉዳዩ በቂ ባይሆንም አመልካች የስራ መሪ ስለሆኑ ጉዳያቸው በስራ ክርክር ችሎት ላታይ አይችልም በማለት የሰጡት ውሳኔ ግን ከላይ ከተመለከቱት ምክንያቶች አንፃር በውጤት ደረጃ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ ስላልተገኘ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ ሰኔ 15 ቀን 2008 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ጥር 16 ቀን 2009 ዓ/ም በትእዛዝ የፀናው ብይን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ፀንቷል።
ለክርክሩ የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻቻሉ ብለናል።