አንድ ሰራተኛ መደበኛ የጡረታ ዕድሜው ደርሶ የመብቱ ተጠቃሚ መሆኑ በተረጋገጠበት አግባብ ለጡረታ መብት ላልተያዘለት ጊዜ የሥራ ስንብት ካሳ ላከፈለኝ እነ አቶ አስቻለው አስማማው (2 ሰዎች ) እና XXVII በማለት የሚያቀርበው ጥያቄ የህግ መሰረት የልለው ስለመሆኑ፡የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 39፤ 43 (4)ፈ አዋጅ ቁጥር 494/98 አንቀጽ 2/2/ሰ/ እና /ሸ/፤ የደቡብ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት
No summary available.
መስከረም 26 ቀን 2010 ዓ/ም ዳኞች፡- ፀጋይ አስማማው አልማው ወል ሙስጠፋ አህመድ አብርሃ መሰለ ሰናይት አድነው አመልካች፡-
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
ጉዳዩ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 “ን” መሰረት አድርጎ የቀረበን የስራ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካቾች በሀዋሳ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተጠሪ ላይ ሕዳር 24 ቀን 2008 ዓ/ም በመሰረቱት ክስ መነሻ ነው። የክሱ ይዘትም ባጭሩ፡- ከተጠሪ ጋር ከ1969 ዓ/ም ጀምሮ የመሰረቱትን የስራ ግኙነት አመልካቾች ከጳጉሜ 01 ቀን 2007 ዓ/ም ጀምሮ በጡረታ በመገለላቸው ምክንያት የተቋረጠ ቢሆንም ለጡረታ መብታቸው የተያዘላቸው የአገልግሎት ዘመን ከሐምል ወር 1988 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 2007 ዓ/ም ድረስ ያለው ብቻ መሆኑን ገልፀው ከ1969 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 1988 ዓ/ም ድረስ በተጠሪ ድርጅት ለአገለገሉበት ጊዜ የስራ ስንብት ካሳ ክፍያ እንዲከፈላቸው ይወሰንላቸው ዘንድ ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።
የአሁኑ ተጠሪ ለክሱ በሰጠው መልስም አመልካቾች ጋር የተደረገው የስራ ውል የተቋረጠው እድሜአቸው ለጡረታ ደርሶ መሆኑንና አመልካቾችም በጡረታ የወጡና የመብቱ ተጠቃሚ የሆኑ ሰራተኞች መሆናቸውን ጠቅሶ ክሱ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል። የስር ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ አመልካቾች በጡረታ የተገለሉና የጡረታ መብት ተጠቃሚ ሁነው እያለ ከ1969 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ሐምል 1988 ዓ/ም ድረስ ለአገለገሉበት ጊዜ የስራ ስንብት ክፍያ እንዲከፈላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ሕጋዊ አይደለም በማለት ክሱን ውድቅ አድርጎታል።
በዚህ ውሳኔ አመልካቾች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ለሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም። እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በበታች ፍርድ ቤቶች በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም በማለት የአመልካቾችን አቤቱታ ሳይቀበለው ቀርቷል:: የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካቾች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- አመልካቾች በተጠሪ ድርጅት ከ1969 ዓ/ም ጀምሮ ለበርካታ አመታት አግልግሎት የሰጡ ስለመሆኑ ተረጋግጦ እያለና ለዘላቂ የጡረታ መብት የተያዘው አገልግሎታቸውም ከሐምል 1988 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 2007 ዓ/ም ድረስ ያለው ጊዜ ብቻ ሁኖ እያለ አመልካቾች ከ1969 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ሀምል 30 ቀን 1988 ዓ/ም ድረስ ለዘላቂ ጡረታ ላልተያዘላቸው ጊዜ ያቀረቡት የስራ ስንብት ክፍያ ውድቅ መደረጉ ያላግባብ ነው የሚል ነው። አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ የተደረገ ሲሆን ተጠሪ ቀርቦም ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም በጉዳዩ ላይ በተሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ለማለት ይቻላል?
ወይስ አይቻልም? የሚለው ሁኖ ተገኝቷል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የተቻለው አመልካቾች በጡረታ የወጡ ሰራተኞች መሆናቸውን፣ ከተጠሪ ጋር ያደረጉት የስራ ውልም ከ1969 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 1988 ዓ/ም ድረስ የኮንትራት የስራ ውል በመሆኑ ይኼው ጊዜ ለጡረታ መብት አከባበር እንዲያዝላቸው ስልጣን ለአለው አካል አቅርበው ተቀባይነት ያጡና በስርዓቱም መሰረት በይግባኝ ወይም በሰበር ያልተለወጠ መሆኑን፣ ከሐምል ወር 1988 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 2007 ዓ/ም መጨረሻ ያለው ጊዜ ለጡረታ መብታቸው ተይዞላቸው ከጳጉሜ 01 ቀን 2007 ዓ/ም ጀምሮ ከተጠሪ መስሪያ ቤት በጡረታ በመገለል የጡረታ መብትም ወዲያውኑ ተጠቃሚ የሆኑ መሆናቸውን ነው።
በመሰረቱ ለተወሰነ ጊዜ ወይም ስራ የተደረገ የስራ ውል ከህግ ውጪ መቋረጡ ከሚያስከትላቸው ሕጋዊ ውጤቶች አንዱ የሥራ ስንብት ክፍያ ስለመሆኑ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 43 (4) ከተቀመጠው ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ የምንረዳው ጉዳይ ነው።
በመሆኑም ለተወሰነ ጊዜ ወይም ስራ የተደረገ የስራ ውል በሕግ አግባብ ከተቋረጠ የሥራ ስንብት ክፍያ የሚከፈልበት የሕግ አግባብ የልለ መሆኑን ከሕጉ ቅርጽና ይዘት የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።
በሥር ፍ/ቤቶች በተደረገው ክርክር ያልተካደው ወይም የተረጋገጠው አመልካቾች ከ1969 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 1988 ዓ/ም ድረስ ከተጠሪ ጋር የነበራቸው የሥራ ውል ግንኙነት በኮንትራት ላይ የተመሰረተ መሆኑና ይህ ጊዜ ለጡረታ መብት አከባበር ለአመልካቾች እንዲያዝላቸው ለማህበራዊ ዋስትና ኤጂንሲ አመልካቾች አቅርበው አገልግሎታቸው ለጡረታ አይያዝላቸውም ተብሎ ውሳኔ ማግኘቱንና በበላይ የዳኝነት አካልም ያለመለወጡን ነው። አመልካቾች የሥራ ስንብት ክፍያ ጥያቄውን ያቀረቡት በጡረታ ተገልለው የመብቱ ተጠቃሚነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ስለመሆኑም ያልተካደ ጉዳይ ነው። ተጠሪ የክፍያ ጥያቄውን ከሥር ጀምሮ ሲቃወም የመጣውም አመልካቾች መደበኛ የጡረታ ዕድሜ የደረሱና የጡረታ አበልም የሚከፈላቸው ናቸው፣ ከ1969 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 1988 ዓ/ም ድረስ ያለው ጊዜ ደግሞ የኮንትራት ውል የነበረበት ከመሆኑም በላይ ተጠሪው ሕጋዊ ሰውነቱን ያላገኘበት ጊዜ ነው በማለት ነው።
የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁ. 377/96 "ን" ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁ.494/98 አንቀጽ 2/2/ሰ/ እና /ሸ/ ከተቀመጡት ድንጋጌዎች መገንዘብ እንደሚቻለው በአዋጅ ቁ.377/96 አንቀጽ 39 እንደተደነገገው የሥራ ስንበት ከፍያ የሚከፈለው ሰራተኛው የፕሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ወይም የጡረታ መብት የልለው ከሆነ እንደዚሁም ሥራውን ሲለቅ መደበኛ የጡረታ ዕድሜ ያልደረሰ ሲሆን ነው። በያዝነው ጉዳይ አመልካቾች ሥራቸውን የጡረታ መውጫ እድሜያቸው ደርሶ መብቱም ተከብሮላቸው በሕግ አግባብ የተሰናበቱ መሆኑ በሚገባ ተረጋግጧል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ከአዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀፅ 43 (4) እና ከማሻሻያ አዋጅ ቁ. 494/98 አንቀጽ 2/2/ሰ/ እና /ሸ/ ከተቀመጡት ድንጋጌዎች መገንዘብ እንደሚቻለው አመልካቾች ከ1969 ዓ/ም ጀምሮ እስከ 1988 ዓ/ም የአገለገሉት ጊዜ የኮንትራት ጊዜ ነው ተብሎ ለጡረታ መብት ላያዝላቸው አይገባም በሚል ዳኝነት በተሰጠበትና አመልካቾች የጡረታ መብት ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ መደበኛ የጡረታ ዕድሜም ደርሰው የመብቱ ተጠቃሚ መሆናቸው ጭምር በተረጋገጠበት አግባብ ለጡረታ መብት ላልተያዘላቸው ጊዜ የሥራ ስንብት ካሳ ላከፈለን ይገባል በማለት የሚያቀርቡት ጥያቄ የህግ መሰረት የልለው መሆኑን ነው። በመሆኑም አመልካቾች የስራ ስንብት ክፍያ የሚያገኙበት የሕግ አግባብ የለም ተብሎ በሥር ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሣኔ በሕጉ አተረጓጎም ረገድ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነው ለማለት ስላልተቻለ ተከታዩን ወስነናል።
ው ሣ ኔ
በሐዋሳ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ ታህሳስ 08 ቀን 2008 ዓ/ም ተሰጥቶ በሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ የካቲት 17 ቀን 2008 ዓ/ም፣ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመ/ በ04/12/08 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348/1/ መሰረት ጸንቷል።
አመልካቾች ከ1969 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ሐምል 1988 ላለው ጊዜ የስራ ስንብት ካሳ እንዲከፈላቸው ያቀረቡት ጥያቄ የሕግ መሰረት የለውም ተብሎ በመወሰኑ የተፈፀመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለም ብለናል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
No topics extracted.