አንድ ድርጅት በመክሰር ወይም በልላ ምክንያት ለዘለቄታው መዘጋት ሰራተኞችን የሥራ ውልን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለማቋረጥ የሚያስችል ሲሆን መረጋገጥ ያለበት መሰረታዊው ነጥብ የአሰሪው ድርጅት ለዘለቄታው መዘጋት ስለመሆኑ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 24(4)
No summary available.
ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ሙስጠፋ አህመድ አብርሃ መሰለ ጳውሎስ ኦርሺሶ ሰናይት አድነው አመልካች፡- ዋኢል አብዱጌት አብዱላዚዝ ፕላስቲክ ፋብሪካ - የቀረበ የለም ተጠሪ፡-
መዝገቡ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል።
**
በዚህ መዝገብ የቀረበው ጉዳይ የስራ ክርክርን የሚመለከት ነው። ተጠሪዎች ከልሎች ሶስት ግለሰቦች ጋር በመሆን በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰበታ አዋስ ወረዳ ፍ/ቤት በመሰረቱት ክስ አመልካች ያለአግባብ ከስራ ያሰናበታቸው በመሆኑ የተለያዩ ክፍያዎች እንዲከፍላቸው ጠይቀዋል። አመልካች ለክሱ መልስ ሲሰጥ የተጠሪዎች የስራ ውል የተቋረጠው ድርጅቱ ከውጪ አገር የሚመጣ ጥሬ እቃ በውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ ማቅረብ ባለመቻሉ ፋብሪካው ለዘለቄታው ስራ በማቆሙ ስለሆነ የተጠየቀው ክፍያ ላከፈል እንደማይገባና ለተጠሪዎችም መከፈል የሚገባውን ክፍያ ከፍሎ ያሰናበታቸው በመሆኑ የቀረበው ጥያቄ ውድቅ ላሆን ይገባል ሲል ተከራክሯል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው ፍርድ ቤትም ተገቢ ነው ያለውን ዳኝነት ሰጥቶ የነበረ ሲሆን ጉዳዩ በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን በይግባኝ ከታየ በኋላ የተከሳሽ መከላከያ ማስረጃ ዳግም እንዲሰማ በማለት በመለሰለት አግባብ ማስረጃዎችን ከሰማ በኋላ ጉዳዩን ተጠሪዎች ከስራ የተሰናበቱት ድርጅቱ ከስሮ ለዘለቄታው በመዘጋቱ ምክንያት ስለመሆኑ አመልካች ድርጅት አላስረዳም በማለት ደምድሞ ስንብቱ ህገ ወጥ ነው በማለት አመልካች የተለያዩ ክፍያዎችን ለተጠሪዎች እንዲከፍል በማለት ወስኗል። በዚህ ውሳኔ ላይ አመልካች በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርቦ ግራ ቀኙ እንዲከራከሩ ከተደረገ በኃላ ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ አመልካች ተጠሪዎችን ያሰናበታቸው በመክሰሩ ምክንያት በመሆኑ ስንብቱ በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀፅ 24(4) አግባብ ሕጋዊ ነው በማለት ወስኗል። በዚህ ውሳኔ የአሁኑ ተጠሪዎች ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው ግራ ቀኙ ከተከራከሩ በኋላ ችሎቱ ጉዳዩን መርምሮ አመልካች መክሰሩን በማናቸውም ማስረጃ የሚያረጋግጥ ቢሆን እንኳን በመክሰር ምክንያት ስራውን የሚዘጋ መሆኑን ለተጠሪዎች ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ስንብቱን ማከናወኑ ሕጋዊ ላያደርገው አይችልም በማለት ስንብቱን ህገ ወጥ ነው በማለት የደመደመ ሲሆን ክፍያዎችን በተመለከተ ግን አመልካች ለተጠሪዎች የከፈላቸው የክፍያ አይነቶችና መጠናቸው በስር ፍርድ ቤት ተጣርተው እንዲወሰኑ በማለት በዚህ ረገድ ያለውን ነጥብ ብቻ ለወረዳው ፍርድ ቤት መልሶለታል።
አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረበው ይህንን ውሳኔ ለማስለወጥ ነው። በቅሬታውም አመልካች ድርጅት የተዘጋው በጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረት ስለመሆኑ በማስረጃ ተረጋግጦ እያለና ማስጠንቀቂያም በቃል የሰጠ ሆኖ እያለ ስንብቱ ህገ ወጥ ነው ተብሎ የተወሰነው ያላግባብ ነው በማለት ተከራክሯል። ጉዳዩ ተመርምሮም የተጠሪዎች የስራ ስንብት ህገ ወጥ ነው ተብሎ የመወሰኑን አግባብነት ለመመርመር አቤቱታው ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ የተደረገ ሲሆን ተጠሪዎችም ክርክራቸውን በፁሁፍ አቅርበዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች አንጻር ስንብቱ ህገ ወጥ የተባለበትን አግባብ እንደሚከለተው መርምሮታል።
አመልካች ድርጅት ከውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ በተከሰተው የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረትና በኪሳራ ምክንያት ለዘለቄታው ስለመዘጋቱ አመልካች ጠቅሶ የሚከራከር ቢሆን ተጠሪዎች ይህ የአመልካች ክርክር በሕጋዊ ማስረጃ ያልተደገፈ መሆኑን ገልፀው የሚከራከሩ መሆኑን ከክርክሩ ሂደት ተገንዝበናል። አመልካች ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ የተዘጋው በጥሬ ዕቃ አቅርቦትና በኪሳራ ስለመሆኑ ማስረዳት የሚቻለው በሰነድ ማስረጃ መሆን ያለመሆኑን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ግልፅና በሕግ የተደገፈ ምክንያት ሳይጠቅስ ስንብቱን ሕገ ወጥ ነው ወደሚለው ድምዳሜ የደረሰው አመልካች ለተጠሪዎች ማስጠንቀቂያ መስጠት ሕጋዊ ግድታ እያለበት ይህንኑ ግድታ ያለመወጣቱ ስንብቱን ህገ ወጥ ያደረገዋል በሚል ምክንያት ስለመሆኑ ከውሳኔው ይዘት ተገንዝበናል። ሆኖም የመክሰር ወይም የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማጋጠሙ ከውጭ አገር የሚገባ የፋብሪካ ጥሬ ዕቃ እጥረት መኖር በማናቸውም የማስረጃ አይነት ላረጋገጡ የሚችሉ ናቸው ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ የማይቻል ሲሆን በዚህ ረገድ ለሚቀርቡ ክርክሮች መቅረብ ያለባቸው ማስረጃዎች በሕጉ አግባብ ስልጣን በተሰጣቸው አካላት የሚሰጡና ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸው መሆን ያለባቸው መሆኑን ከማስረጃ አቀራረብና አመዛዘን መርሆዎች እንዲሁም ስለመክሰርም ሆነ ስለ ውጭ ምንዛሬ አግባብነት ባላቸው በልሎች ሕጎች የተዘረጉትን ስርዓቶች በመመርመር የምንረዳው ጉዳይ ነው። ስለሆነም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በዚህ ረገድ ያሰፈረው የምክንያት ክፍልና አመልካች በዚህ ረገድ ያቀረበው የሰበር ክርክር ሕጋዊ መሰረት የልለው ሆኖ አግኝተናል።
ለጉዳዩ አግባብነት ያለው ድንጋጌ ማስጠንቀቅያ የሚያስፈልገው መሆን ያለመሆኑን ከአዋጁ አንቀጽ 28(2(ሀ)) ድንጋጌ ከአለው አንድነትና ልዩነት አንፃር ተመልክተናል።
በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 28/2/ሀ/ ሰራተኞች የተሰማሩባቸውን ስራዎች በከፊልም ሆነ በሙሉ በቀጥታና ለዘለቄታው የሚያስቆም የሰራተኛ ቅነሳ የሚያስከትል ሁኔታ በአሰሪው ወይም አሰሪውን በሚመለከቱ ምክንያቶች ሲከሰት የስራ ውሉ በማስጠንቀቂያ ላቋረጥ እንደሚችል ይገልፃል። ድንጋጌው ምክንያቶች ከአሰሪው ጋር የተያያዙ መሆናቸውንና የድርጅቱ ስራ በከፊል ብቻ ሳይሆን በሙሉ ለዘለቄታው ሲቆም ማስጠንቀቂያ ላሰጥ እንደሚገባው የሚያስገነዘብ መሆኑን የድንጋጌውን ይዘትና መንፈስ ከአዋጁ አንቀፅ 24(4) ድንጋጌ አቀራረጽ፣ ይዘትና መንፈስ ጋር አዳምረን በምንመለከትበት ጊዜ የምንረዳው ጉዳይ ነው። አንድ ድርጅት በመክሰር ወይም በልላ ምክንያት ለዘለቄታው መዘጋት የሥራ ውልን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለማቋረጥ የሚያስችል ሲሆን ለዚህም መረጋገጥ ያለበት መሰረታዊው ነጥብ የአሰሪው ድርጅት ለዘለቄታው መዘጋት ነው። ከላይ እንደተገለፀው አመልካች ድርጅት በአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 24(4) ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ መሰረት ለዘለቄታው መዘጋቱ አልተረጋገጠም። በልላ በኩል አመልካች ለተጠሪዎች የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ያለመስጠቱን አምኖ ማስጠንቀቂያው በቃል መሰጠቱ ስንብቱን ሕጋዊ ያደርጋል በማለት ያቀረበው ክርክር ከአዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 34 ድንጋጌ ይዘትና መንፈስ አንፃር ተቀባይነት የሚሰጠው አይደለም። በመሆኑም አመልካች ድርጅቱ በዘለቄታው ስለመዘጋቱ ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን ማስረጃ ከሚመለከተው የአስተዳደር አካል ባላቀረበበት ሁኔታ እርምጃው ሕጋዊ ነው በማለት ከአዋጅ ቁጥር 24(4) ድንጋጌ አንጻር የሚያቀርበው ክርክር የድንጋጌውን ይዘትና መንፈስ ያላገናዘበ ሆኖ ስለአገኘን የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ ከውጤት አኳያ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት ነው ለማለት አልተቻለም። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
በኦሮሚያ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ ሚያዚያ 30 ቀን 2009 ዓ/ም የተሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348(1) መሰረት ጸንቷል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
ሰኔ 20 ቀን2009 ዓ/ም የተሰጠው የእግድ ትዕዛዝ ተነስቶአል። ይጻፍ
No topics extracted.