በትምህርት ደረጃው ከፍተኛ የሆነና በባህሪው ለህብረተሰብ አርአያ ላሆን የሚገቡ ሰዎች ፍፁም ነውረኛ በሆነና ጨካኝነት በተሞላበት ሁኔታ የፈፀሙት ከባድ የወንጀል ድርጊት የወንጀል አፈጻጸሙን ከባድነት እና የወንጀለኛውን አደገኛነት የሚያሳይ በሆነ ጊዜ ወንጀለኛው ላይ የቀረበ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ ያለመኖር ወንጀለኛው ጥሩ ፀባይ ወይም መልካም ፀባይ ያለው ነው የሚል አበባየሁ ሳሙኤል እና የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ዐቃቤ ህግ XXIV ለመውሰድ የማያበቃ ስለመሆኑ፣ -የወ/ህ/ቁ. 184/1/ሀ/ እና ለ ቁ. 539 ቁ. 671/1/0/ የፍ/ጠ/ፍ/ቤት የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ. 2/2006 የኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 15 እና የወ/ህ/ቁ. 117
No summary available.
መስከረም 24 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- ብርሃኑ አመነው በዕውቀት በላይ እንዳሻው አዳነ ሃይሉ ነጋሽ እትመት አሰፋ አመልካች፡- አበባየሁ ሳሙኤል -ጠበቃ ዮሴፍ ኪሮስ ተጠሪ፡- የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ዐቃቤ ህግ -አልቀረበም መዝገቡ የተቀጠረው መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ነው። በመሆኑም መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ይህ የሰበር አቤቱታ ላቀርብ የቻለው አመልካች የምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ በቀን 01/06/2008፣ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ በቀን 17/09/2008 እና የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ/ በቀን 8/02/2009 በሰጠው ትእዛዝ ላይ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመ በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለታቸው ነው።
ጉዳዩ ውንብድናና ከባድ ሰው መግደል ወንጀል የቅጣት ውሳኔ የሚመለከት ነው። በስር ፍርድ ቤት ተጠሪ በአመልካችና ልሎች 5 ሰዎች ላይ ሁለት የተሻሻለ የወንጀል ክሶችን ያቀረበ ሲሆን የመጀመሪያው የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ /ሀ/ እና 671/1/ /ሀ/ የተመለከተውን በመተላለፍ ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ ካልተያዘው አቡሽ ተከተል ጋር በመሆን አመልካች የግል ተበዳይ ሟች ዶ/ር ቢንያም ማሞ መጽሀፍ ለማዘጋጀት ያዘጋጀውን ጽሁፍ ለመውሰድ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በመምከርና 2ኛ ተከሳሽ ገንዘብ ከተከፈለው ጽሁፋን በእጁ እንደሚያስገባለትና አመልካች የሚከፍል መሆኑን ተስማምተው 2ኛ ተከሳሽም ይህንኑ ከ3ኛ-5ኛ እና ካልተያዘው አቡሽ ተከተል ጋር ተመካክረው 5ኛ ተከሳሽ ሜሮን አየለ ከሟች ጋር ተቀራርባ በሚፈልጉት ጊዜ እንድትጠራው ተስማምተው በ20/12/2006 ሟችን ጠርታ እስከ ልላት 6፡00 ሰዓት አብረው ቆይተው ከ2ኛ-4ኛ ያሉ ተከሳሾችና አቡሽ ተከተል በጉልበት ይዘውት ባንተ ላይ የምንፈጽመውን ለፖላስ ከተናገርክ እንገድልሃለን በማለት የሞት አደጋ የሚያደርሱ መሆኑን በማስጠንቀቅ ሞባይል፣ ጃኬት፣ ጫማ፣ ፍላሽ ሟች መድሐፍ ለማሳተም በእጁ የያዘው ጽሁፍ ሶፍት ኮፒ የወሰዱ በመሆኑ ከባድ የውንብድና ወንጀል ፈጽመዋል የሚል እና 2ኛው ክስ ደግሞ ከ1ኛ -6ኛ ተከሳሾች የወንጀል ህግን አንቀጽ 32/1/ /ሀ// /ለ/ እና 539 /1/ /ሀ/ /ለ/ /ሐ/ በመተላለፍ ከላይ በ1ኛው ክሱ የገለፀውን ከፈፀሙ በኋላ ሟችን ለመግደል አስበው ከአቡሽ ተከተል ጋር በመሆን ሟች ለማሳተም ያዘጋጀውን ጽሁፍ ሶፍት ኮፒ 2ኛ ተከሳሽ ለአመልካች /1ኛ ተከሳሽ/ ከሰጠ በኋላ አመልካች ሟች በህይወት ሳለ በዚህ ጽሁፍ መጠቀም ስለማይቻል ሟችን መግደል አለባችሁ ብሎ ሲገልጽ ገንዘብ እንደሚጨምር ከተስማሙ በኋላ ለ2ኛ ተከሳሽ /ሰላሳ ሺህ/ ለ4ኛ ተከሳሽ /አስራ አምስት ሺህ ብር/ ለ5ኛ ተከሳሽ ብር 5000 /አምስት ሺህ ብር/ 3ኛ ተከሳሽ እና አቡሽ ተከተል የወሰዱት ገንዘብ የማይታወቅ ከወሰዱ በኋላ 5ኛ ተከሳሽ ሟችን ሻሸመኔ ከተማ ቀበል 03 ልዩ ቦታው ሻልት ከተባለ ሆቴል በስልክ ቀጥራው ሲመጣ ልላት ከ2፡00-3፡00 ሰዓት ከ2-4ኛ ያልተያዘው አቡሽ ተከተል ወደ ሆቴል ሲገባ አፍነው መኪናው ውስጥ በመወርወር ከወሰዱት በኋላ ለስድስት ቀን ልላት ልላት ሻሸመኔ ከተማ መልካ ኦዳ አና ለገጐጌቴ በተባለ ቦታ በመውሰድ በፕላስቲክ አፉን በማሸግ እግርና እጁን በማሰር በዘግናኝ ሁኔታ የተያዩ ጉዳቶች ካደረሱበት በኋላ የጐን አጥንት መሰበር፣ የግራ ሳንባ እና ኩላላት መሰንጠቅ በአሰቃቂ ሁኔታ በ30/12/2006 ከገደሉት በኋላ እሬሳውን በመኪና ጭነው አርሲ ነገሬ ወረዳ ዳኮ ሆራ ቀሎ በተባለ ቀበል ውስጥ ልላት 5፡00-8፡00 ሰዓት የጣሉት በመሆኑ በአሰቃቂ ሁኔታ የግድያ ወንጀል ፈጽሟል የሚል ነው።
አመልካች የቀረበበትን የወንጀል ክስ አልፈፀምኩም ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ክዶ የተከራከረ ቢሆንም አምስተኛ ተከሳሽ የነበረችው የወንጀል ድርጊቱን መፈፀሟን አምና በሰጠችው ቃል መሰረት በቀረበው ክስ መሰረት ጥፋተኛ በማለት የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት የቅጣት ውሳኔ የሰጠ ሲሆን በተቀሩት ተከሳሾች ላይ 5 የተጠሪ ምስክሮችን፣ የ5ኛ ተከሳሽ የሰጠችው የእምነት ቃል፣ ሐናን ጌታቸው በቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍ/ቤት የሰጠችው የምስክርነት ቃል፣ ሟች የተጣለበትን ቦታ የሚያሳይ ፎቶግራፍ፣ አንድ የቪዲዮ ሲዲ፣ የሟች ሲም ካርድ ከ5ኛ ተከሳሽ የተወሰደ፤ከዳግማዊ ሚኒላክ ሆስፒታል የተጻፈ የሟች የህክምና ምስክር ወረቀት የቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ እንዲከላከሉ አመልካችን ጨምሮ በሰጠው ብይን መሰረት አመልካች የተከሳሽነት ቃሉንና የመከላከያ ምስክሮች አቅርቦ ያሰማ እና በፖላስ ምርመራ የተጣራ መዝገብ እና 5ኛ ተከሳሽ በፍ/ቤት ቀርባ የሰጠችው ቃል፣ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር የስልክ ልውውጥ ስለማድረጌ ከኢትዮ ቴልኮም ማስረጃ ማቅረብ እና ከአድማስ ገጽ ስነጽሁፍ ማህበር የተጻፈ ማስረጃ አቅርቧል ፍርድ ቤቱም በአመልካች ላይ የቀረበውን ክስ እና በግራ ቀኙ የቀረቡትን ማስረጃዎች ከመረመረ በኋላ የቀረበበትን ሁለቱንም ክስ አልተከላከለም በማለት ጥፋተኛ ነው በማለት ቅጣትን በተመለከተ የአመልካች የወንጀል ድርጊት አፈጻጸም ሁኔታ የወ/ህ/አንቀጽ 539/1/ የሚፈልገውን ሁሉ በመተላለፍ ከዚህ በፊት ጥሩ ሥነ ምግባር የልላቸው ተከሳሾች ጋር በመሆን ትእዛዝ በመስጠት እና በመፈፀም ተቀራራቢ በሆኑ ጊዜያት ከባድ ዝርፊያ እና ከባድ ግድያ ወንጀል መፈፀሙ ያለፈ የህይወት ታሪኩ መልካም ነው ተብሎ በማቅለያነት ታሳቢ የሚደረግ አይደለም ፤ቤተሰብ አለው በማለት የቀረበው በህጉ በግልጽ ያልተቀመጠና ማስረጃ ያልቀረበበት በመሆኑ ተቀበይነት የለውም በማለት በሞት እንዲቀጣ ወስኗል።
አመልካች በዚህ የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ያቀረበውን ይግባኝ የተመለከተው የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት እና አቤቱታ የቀረበለት የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የስር ፍ/ቤት የሰጠውን የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ አጽንተዋል።
የአመልካች የሰበር አቤቱታም የቀረበው ይህንን በመቃወም መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በማለት ሲሆን ይዘቱም ጥፋተኛ የተባለባቸው ሁለት ድርጊቶች በአንድ የወንጀል ህግ ድንጋጌ የሚጠቃለሉ ናቸው፣ የመከላከያ ምስክሮች በሚገባ ቀርበው ሳይመረመሩ የተሰጠ ውሳኔ ነው ፤የማስረጃ ምዘና መሰረታዊ መርሆዎች አልተከተሉም ቅጣትን በተመለከተም የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶችን በመያዝ ቅጣት ላቀልልኝ ይገባ ነበር የሚል ነው። ፍርድ ቤቱ የአመልካችን አቤቱታ መርምሮ በአመልካች የቀድሞ የወንጀል ሪከርድ በልለበት እና ከቅጣት አወሳሰን መመሪያም የቅጣት ውሳኔ ያልተሰጠ መሆኑን መሰረት በማድረግ ከወ/ህ/አንቀጽ 117 አንጻር ለመመርመር ተጠሪ ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ በታዘዘው መሰረት በሰጠው መልስ የወ/ህ/ አንቀጽ 82/1/ /ሀ/ መሰረት የወንጀል ድርጊቱ በዕውቀት ማነስ ባለማወቅ በየዋህነት ከተፈፀመ የወንጀል ሪከርድ ባልቀረበ ጊዜ በማቅለያነት የሚያዝ እንጂ እንደአመልካች የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመው በዕውቀት ማነስ ሳይሆን የዕውቀት ሥራን ለራስ ለማድረግ ለማሳተም ዕውቅና ለማግኘት በማሰብ እና የተማረ በመሆኑ ቅጣቱ ላቀልለት አይገባም፣ አመልካች ሁለት የወንጀል ድርጊቶችን አከታትሎ የፈፀመ በመሆን ግምት ውስጥ ገብቶ የተሰጠ የቅጣት ውሳኔ በመሆኑ የተፈፀመ መሰረታዊ ስህተት የለም በማለት የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ይጽናልኝ ብሐል። የአመልካች የመልስ መልስ አቅርቧል።
የክርክሩ አመጣጥ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው ምክንያት ከሆነው ውሳኔ እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር ያስቀርባል ሲባል ከተያዘው ጭብጥ አንጻር መርምረነዋል።
ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ የሚቻለው አመልካች የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ /ሀ/ እና 671/1//ሀ/ በግብረአበርነት ከባድ የውንብድና የተመለከተውን በመተላለፍ እና የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ እና 539/1/ /ሀ//ለ//ሐ/ በግብረአበርነት ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ጥፋተኛ ተብሐል። የስር ፍርድ ቤት አመልካች ከባድ የውንብድና ወንጀል ካስፈፀመ በኋላ ከባድ የግድያ ወንጀል እንዲፈጽም ትእዛዝ አስተላልፎ በማስፈፀም የአመልካች ጠበቃ ያቀረበው የወንጀል ሪከርድ የልለበት መሆን ከላይ በተገለፁት ምክንያቶች ያልተቀበለው መሆኑን እና የቤተሰብ አስተዳደሪነት በተመለከተ በማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑና ለፍርድ ቤቱ የተተወ ነው በማለት ውድቅ በማድረግ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ 2/2006 መሰረት ምንም ማቅለያ ሳይዝ በሞት እንዲቀጣ መወሰኑን ነው።
በመሰረቱ የወንጀል ህግ ግብ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል ሲሆን ይህንን የሚያደርገው ስለወንጀሎችና ስለቅጣታቸው በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ማስጠንቀቂያነቱ በቂ ባልሆነበት ጊዜ ወንጀል አድራጊዎቹ ተቀጥተው ልላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡና ለልሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ በማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ እርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው በማድረግ ነው። ህጉ በአንቀጽ 87 ላይ ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎች ህጉ ላደርስበት ያሰበውን ዓላማ ለማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ በህጉ መንፈስ መሰረት መፈፀም እንዳለባቸው በመርህ ደረጃ ይደነግጋል። ይኸው አንቀጽ ቅጣቶችና የጥንቃቄ እርምጃዎቹ ምን ጊዜም ሰብዓዊ ክብርን በሚጠብቅ መንገድ መፈፀም እንደሚኖርባቸው ያስገነዝባል። የወንጀል ህጉ አንቀጽ 88 ሲታይም ፍርድ ቤቱ ቅጣቶችንና የጥንቀቄ እርምጃዎችን የሚወስነው የወንጀል ህጉን ጠቅላላ ክፍል ድንጋጌዎችን እንዲሁም ስለወንጀሎችና ስለቅጣታቸው የሚደነግጉትን የልዩ ክፍሉ ድንጋጌዎች መሰረት በማድረግ መሆኑን፣ ቅጣት ላወሰን የሚገባው የወንጀል አድራጊውን ግላዊ የአደገኛነት መጠን ያለፈ የህይወት ታሪኩን ወንጀል ለማድረግ ያነሳሱትን ምክንያቶችን የአሳቡን ዓላማ የግል ኑሮውን ሁኔታ፣ የትምህርቱን ደረጃ፣ እንዲሁም የወንጀሉን ከባድነትና የአፈፃፀሙን ሁኔታዎች በማመዛዘን መሆኑን፣ የወንጀል ህግ ልዩ ክፍል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ ፍርድ ቤቱ እጅግ ቀላል ከሆነው ቅጣት አንስቶ እስከ ከባዱ ድረስ ያለውን በጥንቃቄ በመመርመር ለእያንዳንዱ ጉዳይ ተገቢ የሆነውን ቅጣት እንደሚወስን ነው። በዚህም አፈጻጸም አወሳሰን ትክክለኛነትና አንድ ወጥነት ለማረጋገጥ የፍደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የቅጣት አወሳሰን መመሪያ የወጣ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው።
በቅጣት መመሪያ ውስጥ የተቀመጠው የቅጣት አወሳሰን ሥርዓትም ስለቅጣት አወሳሰን በህጉ የተመለከቱት ድንጋጌዎች ሲታዩ የሚያስገነዝቡን ዓቢይ ነጥብ ቅጣቶችን በመጣልና እርምጃዎችን በመውሰድ ረገድ ዳኞች አመዛዝነው የመወሰን ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው መሆኑን ነው።ዳኞች አጥፊውን በተመለከተ ከግምት ውስጥ ላያስገቧቸው የሚገባቸው በርካታ የአጥፊ ሁኔታዎች ቢኖሩም የቅጣት አወሳሰናቸው መሰረት የወንጀል አድራጊውን ግላዊ የአደገኛነት መጠን /degree of individual guilt/ ስለመሆኑ የአንቀጽ 88/2/ ድንጋጌ ይዘትና አቀራረፅ ያስረዳል።
በያዝነው ጉዳይ አመልካች ጥፋተኛ የተባሉት በሁለት ግዘፍነት ባላቸው ተደራራቢ ወንጀሎች ሲሆኑ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1//ሀ/ እና 671/1/ /ሀ/ እና /ለ/ የተመለከተውን በመተላለፍ ከባድ የውንብድና ወንጀል በመፈፀም ሲሆን ከአምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1//ሀ/ 539 /ሀ/ /ለ/ /ሐ/ የተመለከተውን ተላልፎ ከባድ የሰው መግደል ወንጀል በመፈፀም ደግሞ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጡ ወንጀሎች ናቸው። ሁለቱም የወንጀል ድርጊቶች በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 መሰረት ደረጃ እና እርከን የወጣላቸው ናቸው፤ የመጀመሪያውን ክስ በተመለከተ አመልካች በ2ኛው ክስ የተመለከተውን የውንብድና ወንጀል ከፈፀመ በኋላ በዚሁ የወንጀል ድርጊት ምክንያት ከሟች ዶ/ር ቢኒያም ማሞ የወሰደው ጽሁፍ ለማሳተም የግሉን ስብዕና ለማሳደግ ጥቅም ለማግኘት የሟች መገደል አስፈላጊ ነው በሚል አስነዋሪ የአፍቅሮተ ንዋይ ስሜት ከ2ኛ-5ኛ ተከሳሾች የነበሩትን የውንብድና ቡድን በመጠቀም ከሟች የዕውቀት ብርሃን የተገኘውን ጥበብ /ጽሁፍ/ በውንብድና ተግባር የወሰደውን የአዕምሮ የፈጠራ ውጤት እንዳይገለጽ ለማድረግ የፈፀመው መሆኑ የወንጀሉ ደረጃ 2 እርከን 39 ላይ የሚያርፍ ሲሆን ሁለተኛው ክስ በተመለከተ የወንጀል ድርጊቱ ከባድነት እና አፈጻጸሙ ከላይ የተመለከተው በመሆኑና በመጀመሪያ ክስ ዕድሜ ልክ ወይም ሞት የሚያስቀጣ በመሆኑ ሁለተኛው ክስ ላይ የተመለከተው አጠቃሎ የሚይዝ ስለመሆኑ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 184/1/ /ሀ/ /ለ/ በተመለከተው መሰረት መነሻ ቅጣት እርከን 39 ላይ የሚያርፍ ነው።
ተጠሪ በአመልካች ላይ ያቀረበው የቅጣት ማክበጃ ምክንያት የለም ሆኖም አመልካች ላይ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ የልለው መሆኑን በቅጣት ማቅለያነት ቀርቦ ፍርድ ቤቱ አመልካች ተቀራራቢ በሆነ ጊዜ ውስጥ ከባድ የዝርፊያ ወንጀል እና ከባድ ግድያ እንዲፈጽም በማድረግ ጥሩ ፀባይ ያለው ነው ብሎ ለመገመት የሚያስችል አይደለም ብሎ አመልካችን በሞት እንዲቀጣ ወስኗል።
በመሰረቱ ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ በተደነገገው ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን ላያጣ እንደማይገባ የኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 15 ስር በኃይለ ቃል የደነገገው ጉዳይ ነው፡ በመሆኑም በሕጉ አግባብ ከባድ ወንጀል መፈጽሙ በተረጋገጠበት ሰው ላይ የሞት ቅጣት ማስተላለፍ የሚፈቀድ መሆኑን ሕገ መንግስቱ አስቀምጧል። በልላ በኩል የሞት ቅጣት ላተላለፍ የሚገባበት አግባብ የወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 117 ስር ተደንግጎ እናገኛለን። በዚህ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር አንደ ድንጋጌ መሰረት የሞት ቅጣት የሚወሰነው ወንጀሉ ፍጻሜ ያገኘ ሆኖ እጅግ በጣም ከባድ በመሆኑና ወንጀለኛውም በተለይ አደገኛ በመሆኑ ለወንጀሉ ቅጣት እንዲሆን በሕጉ በግልጽ ተደንግጎ በተገኘ ጊዜ እንዲሁም ወንጀለኛው ቅጣትን የሚያቀልለት ምክንያት በታጣ ጊዜ እድሜው ቢያንስ አስራ ስምንት አመት የሞላው ሆኖ ሲገኝ መሆኑ ተመልክቷል።
አመልካች ጥፋተኛ የተባለባቸው የወንጀል ድርጊቶች የተፈፀሙት የአሁን አመልካች የሆነው የስር 1ኛ ተከሳሽ የሟችን ዶ/ር ቢኒያም ማሞን መጽሃፍ ለማዘጋጀት ያዘጋጀውን ጽሁፍ በከባድ የውንብድና ቡድን ተግባር ለመውሰድ እና የዚህን ጹሁፍ ባለቤት ለመሆን የእውቀቱን አመንጪ መግደል ለልላኛው ወንጀል ከለላ እንዲሆን ታስቦ የተፈፀመ በመሆኑ በዚህ አይነት ሁኔታ በወንጀል ህግ አክብዶ መወሰን ያለበት ስለመሆኑ ይደነግጋል።
በልላ በኩልም አመልካች የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመበት ሟች ሆነ አመልካች የሀገሪቱ ሀብት እና በዩኒቨርስቲ መምህራን የሚቀርፁ ባለሙያዎች ሆነው በመልካም ባህሪያቸው ለህብረተሰቡ አርአያ ተደርገው የሚወሰዱ ሆነው ፍፁም ወራዳ በሆነ ተግባር መፈፀሙ የአመልካችን አደገኛ ባህሪይ የሚያመለክት ሲሆን በአመልካች የቀረበው የቀደመ የወንጀል ሪከርድ አለመኖር በስር ፍርድ ቤት ተቀባይነት ያላገኘ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት መሆኑን ከውሳኔ ይዘት እና ከወንጀል ህግ አንቀፅ 117 አንጻር የወንጀል ድርጊቶቹ አፈጻጸም ከባድነት በተለይም የአመልካችን አደገኛነት መሰረት ያደረገ መሆኑን ተገንዝበናል።
በአጠቃላይ በአመልካች ላይ የተወሰነው የሞት ቅጣት የወንጀል ሕጉን መሰረታዊ ግብና ዓላማ እንዲሁም የቅጣት አወሳሰን መርሆዎችን ከአመልካች የወንጀል ድርጊት አፈጻጸም ጋር የተገናዘበ በመሆኑ መሰረታዊ የህግ ሥህተት የተፈፀመበት ነው ለማለት አልተቻለም። ስለሆነም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
1/ በምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ በቀን 01/06/2008፣ የሰጠው የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ በቀን 17/09/2008 እና የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ/ በቀን 08/02/2009 የሰጠው ትእዛዝ በወንጀል ህግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 195/2/ /ለ/ /2/ መሰረት ፀንቷል።
2/ አመልካች በሞት እንዲቀጡ ተብሎ መወሰኑ በአግባቡ ነው ብለናል። የሞት ቅጣቱ ተፈጻሚነት የሚኖረው በወንጀል ህግ አንቀጽ 117/2/ መሰረት በሀገሪቱ ርዕሰ ብሕር ከፀና በኋላ ይሆናል ብለናል።