ተከሳሽ በዋስትና ወረቀት እንዲለቀቅ ጠይቆ የሥር ፍ/ቤት የተከሳሽን የዋስትና መብት ጠብቆ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ይግባኝ መነሻነት ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሥር ፍ/ቤት የተከሳሽን የዋስትና መብት በመጠበቅ የሰጠውን ውሳኔ በመሻር በሰጠው ውሳኔ ላይ ተከሳሽ ይግባኝ ማቅረብ የሚችል ስለመሆኑ፡የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 75/2
No summary available.
የሰበር መዝገብ ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- ብርሃኑ አመነው በዕውቀት በላይ እንዳሻው አዳነ ሃይሉ ነጋሽ እትመት አሰፋ አመልካች፡- አቶ አክላሉ አፈወርቅ ጠበቃ ናትናኤል ተክሉ ቀረቡ ተጠሪ፡- የፍድራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አልቀረበም መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል።
የሰበር አቤቱታው ላቀርብ የቻለው አመልካች ነሐሴ 08 ቀን 2009 ዓ.ም ጽፎ ባቀረበው አቤቱታ የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ. ሐምል 28 ቀን 2009 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ሥሕተት የተፈጸመበት በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለቱ ነው። የአሁን አመልካችን ጨምሮ ልሎች ሥድሥት ተከሳሾችን ክስ የተመለከተው የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የተጠሪን ማሥረጃዎች ከሰማ በኋላ ተከሳሾች በዋስ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ፈቅዷል።
ተጠሪ በዚህ ትዕዛዝ ቅር በመሰኘት ለፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ባቀረበው ይግባኝ መነሻነት ይግባኙ የቀረበለት ፍ/ቤት የሥር ፍ/ቤት ለአመልካች እና ለሥር ተከሳሾች የሰጠውን የዋስትና መብት በመሻር ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ በማለት ወስኗል። አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የይግባኝ አቤቱታ ያቀረበ ቢሆንም ይግባኙ የቀረበለት ፍ/ቤት በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 75/2 በዋስትና ጉዳይ ላይ ከአንድ ጊዜ በላይ ይግባኝ እንደማይኖር የተደነገገ በመሆኑ አመልካች አቤቱታውን ለሰበር ሰሚ ችሎት አቅርቦ ከማሳረም ውጪ ሁለተኛ ይግባኝ ላያቀርብ አይችልም በማለት የአመልካችን አቤቱታ ውድቅ አድርጎታል። የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይህን ውሳኔ በመቃወም ነው።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- አመልካች ከመነሻውም ቢሆን በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የዋስትና መብቴ ያልተከለከለ በመሆኑ የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 75/2 ሁለተኛ ይግባኝ አይፈቅድም በማለት የአመልካችን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ሥሕተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል የሚል ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የአመልካችን የዋስትና መብት የሻረው ተጠሪ ባቀረበው ይግባኝ መነሻነት ሆኖ ሳለ የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በዋስትና ጉዳይ ላይ ሁለት ጊዜ ይግባኝ ማለት አይቻልም በማለት የአመልካችን የይግባኝ አቤቱታ ወድቅ ማድረጉ የሰጠው ውሳኔ ከወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 75/2 እና ከአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 9 አንጻር ለመመርመር ሲባል ጉዳዩ በዚህ ችሎት እንዲታይ ተደርጓል። ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎም ጥቅምት 02 ቀን 2010 ዓ/ም በሰጠው መልስ በሥር ፍ/ቤት የአመልካች የይግባኝ መብት መታለፉ ተገቢ አይደለም በማለት ሥሕተቱ ቢታረም ተቃውሞ የልለው መሆኑን ገልጿል።
የጉዳዩ አመጣጥ በአጭሩ ከላይ የተገለጸው ነው። እኛም እንዲጣራ የተያዘውን ነጥብ ከግራቀኙ ክርክር እና ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ሕጎች ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው መርምረነዋል።የፍድራል ፍ/ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 9/2 የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በይግባኝ ሰሚነት ሥልጣኑ የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ከሰጠው ውሳኔ የተለየ ውሳኔ በሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ የይግባኝ ሥልጣን እንዳለው ይደነግጋል።
የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 75 (1)እና(2) በዋስትና ወረቀት ለመለቀቅ የቀረበውን ማመልከቻ ፍ/ቤቱ ያልተቀበለው እንደሆነ ለይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚቻል እና በዚህ ጉዳይ ላይ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ ይግባኝ የልለው መሆኑን ይደነግጋል። ሆኖም በድንጋጌው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው የዚህ ድንጋጌ ተፈጻሚነት ተከሳሹ በዋስትና ወረቀት እንዲለቀቅ ጠይቆ ባልተፈቀደ ጊዜ እንጂ የሥር ፍ/ቤት የተከሳሽን የዋስትና መብት ጠብቆ ዓቃቤሕግ ባቀረበው ይግባኝ መነሻነት ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሥር ፍ/ቤት የተከሳሽን የዋስትና መብት በመጠበቅ የሰጠውን ውሳኔ በመሻር በሰጠው ውሳኔ ላይ ተከሳሽ ይግባኝ እንዳያቀርብ ተፈጻሚ የሚሆን አይደለም። በወንጀል ሥነ ስርዓት ሕጉ ቁጥር 75 (2) ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ ይግባኝ የለውም በማለት የተደነገገው ድንጋጌ ተከሳሹ በበታች ፍ/ቤት የተፈቀደለት የዋስትና መብት በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በተሻረበት ጊዜም የተከሳሹ ይግባኝ የማቅረብ መብት እንደሚከለክል አድርጎ መተርጎም የዜጎችን ይግባኝ የማቅረብ መሰረታዊ መብት የማጣበብ ውጤት ያለው ነው።
በተያዘው ጉዳይ የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የአመልካችን የዋስትና መብት የሻረው ተጠሪ ባቀረበው ይግባኝ መነሻነት በመሆኑ አመልካች የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በሰጠው ውሳኔ ላይ በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 9/2 መሰረት ለፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ የማቅረብ መብት አለው። የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ጉዳዩን በዚህ አግባብ በማየት መወሰን ሲገባው የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 75/2 ሁለተኛ ይግባኝ አይፈቅድም በማለት የሰጠው ውሳኔ በሕገመንግሥቱ ዕውቅና ያገኘውን የአመልካችን ይግባኝ የማለት መብት ያጣበበ እና መሰረታዊ የሆነ የሕግ ሥሕተት የተፈጸመበት ነው። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ. ሐምል 28 ቀን 2009 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር 195/2/ለ/2 መሰረት ተሽሯል።
ከላይ በፍርድ ሐተታው ላይ በተገለጸው ምክንያት አመልካች የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ. ሰኔ 05 ቀን 2009 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ ላይ ለፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ የማቅረብ መብት አለው ብለናል።
የፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት አመልካች ድጋሚ ይግባኝ የማቅረብ መብት የለውም በማለት የሰጠው ውሳኔ የተሻረ መሆኑን አውቆ አመልካች ያቀረበውን ይግባኝ መርምሮ ተገቢ ነው ያለውን ውሳኔ ይሰጥበት ዘንድ ጉዳዩ ተመልሶለታል።
-መዝገበ ተዘግቷል። ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.