ወንጀል መፈጸሙን ለማጣራትና ምርመራ ለማጠናቀቅ ወሳኝ የሆኑ መረጃዎች በህግ ጥበቃ የሚደረግላቸው እና ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ለማግኘት የማይቻል በሆነ ጊዜ ፍ/ቤቶች የሚቀርብላቸውን ጥያቄ በአግባቡ በማጤን ተገቢውን ትእዛዝ መስጠት ያለባቸው ስለመሆኑ የአ.ቁ 592/2000 አንቀጽ 28/4/ /ሰ/ አ.ቁ 720/2004 XXIII አንቀጽ 6
No summary available.
መስከረም 22 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- ብርሃኑ አመነዉ በዕዉቀት በላይ እንዳሻዉ አዳነ ኃይሉ ነጋሽ እትመት አሰፋ አመልካች:- የጉለል ክ/ከተማ ፖላስ መምሪያ - ኢንስፔክተር የትምወርቅ ጋሻው - ቀረቡ ተጠሪ፡- የለም መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ የወንጀል ምርመራ ሂደት የተጠረርጣሪን የባንክ ሂሳብ መረጃ የማግኘት ፈቃድን የሚመለከት ሆኖ የተጀመረዉ በፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ነዉ። አመልካች በተጠርጣሪ አቶ መኮንን በላይ ላይ ለጀመረዉ የቼክ ማጭበርበር ወንጀል ምርመራ ሥራ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተጠርጣሪዉን የባንክ ሂሳብ መረጃ እንዲሰጠዉ እንዲታዘዝለት ለስር ፍ/ቤት ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ ጥያቄዉን መርምሮ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 3(3) መሰረት የፍድራል ጠቅላይ ዐ/ሕግ በወንጀል ምርመራ ወቅት ባንክ ማዘዝ የሚችል ስለሆነና ስልጣኑም የጠቅላይ ዐ/ሕግ በመሆኑ የአመልካች ጥያቄ በዐ/ሕግ በኩል ላስተናገድ ስለሚችል ጥያቄዉን አልተቀበልኩም በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል። ይህን ትዕዛዝ በመቃወም አመልካች ያቀረበዉን ይግባኝ የተመለከተዉ የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ጉዳዩን መርምሮ የአዋጅ ቁጥር 943 አንቀጽ 6(3/ሀ) ለፖላስ የተሰጠ ወንጀል የመመርመር ስልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ የሚል ቃል ያለዉና ለፖላስ ራሱን በቻለ አዋጅ ስልጣኑ ተለይቶ ተሰጥቶ ባለበት ሁኔታ የስር ፍ/ቤት የሰጠዉ ትዕዛዝ ተገቢ አይደለም በማለት ትዕዛዙን በመሻር ሲወስን፤ ፖላስ እንዲሰጠዉ የጠየቀዉን ትዕዛዝ አስፈላጊነት በተመለከተ ፖላስ ስንቅ የልለዉ ቼክ ቀርቦለት፤ ባንኩ የቼኩ ባለቤት ቼኩ ተሰርቆብኛል በማለት ያስታወቀዉ መሆኑን በገለጸበት ሁኔታ ፖላስ ባንክ የሚገኝ ማስረጃ የሚፈልግበት ምክንያት ግልጽ አይደለም በማለት የአመልካችን ጥያቄ ሳይቀበል ቀርቷል። አሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ በዚህ ዉሳኔ ባለመስማማት ለማስለወጥ ነዉ።
አመልካች ያቀረበዉ የሰበር አቤቱታ ይዘት፡- በፍድራል ፖላስ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 720/04 መሰረት ወንጀል የመመርመር ስልጣን ለፖላስ የተሰጠ ሲሆን እንደሚደርሰን ጥቆማ እና የወንጀሉ ክብደት በብሕራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 እና በአዋጅ ቁጥር 592/2000 መሰረት የግለሰቦች የባንክ መረጃ በፍ/ቤት ትዕዛዝ እንደሚገኝ ተመልክቷል። የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በፍ/ቤት ትዕዛዝ ማስረጃ የማግኘት ያለን መሆኑን ቢያረጋግጥም የወንጀል ምርመራዉ ተጠርጣሪዉ ለባንኩ ጠፍቶብኛል ብሎ ካስታወቀዉ ቼክ ጋር የተያያዘ በመሆኑ እየታወቀ የማስረጃዉ አስፈላጊነት ግልጽ አይደለም በማለት አቤቱታችን ዉድቅ ማድረጉ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነዉ። ስለሆነም የተጀመረዉን ምርመራ ማጠናቀቅ እንዲቻል ቼኩ በወጣበትና ለባንክ ለክፍያ በቀረበበት ጊዜ በተጠርጣረዉ የባንክ ሂሳብ በቂ ስንቅ ወይም ገንዘብ መኖር አለመኖሩ እንዲረጋገጥ እንዲታዘዝልን፤ በተጠርጣሪዉ ፊርማ ላይ የፎረንሲክ ምርመራ ማድረግ በማስፈለጉ ከዚህን ቀደም ተጠርጣሪዉ የፈረመባቸዉ ከ5 እስከ 7 የሚሆኑ ቼኮች እንዲሰጡ እንዲታዝ እና ተጠርጣሪዉ ፊርማ የልለዉ ቼክ ጠፍቶብኛል ብሎ ያመለከተበት ደብዳቤ እንዲሰጠን ትዕዛዝ ይሰጥልን የሚል ነዉ።
አመልካች ያቀረበዉ አቤቱታ ተመርምሮ ጉዳዩ የሚያዝበት ገንዘብ ሳይኖር ቼክ ማዉጣት ወንጀል ተፈጽሟል በሚል በግል ተበዳይ በኩል አቤቱታ ቀርቦ ፖላስ ለምርመራ ይጠቁምኛል ያላቸዉን ሰነዶች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሰጠዉ ማዘዣ ከፍ/ቤት ተጠይቆ የሥር ፍ/ቤት ማስረጃዉ የሚፈለግበት አግባብ ግልጽ አይደለም በሚል የአመልካች ማዘዣ ጥያቄ ዉድቅ ያደረገበትን አግባብ ከአዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀጽ 22(2-ሰ)፣ ከአዋጅ ቁጥር 592/2000 አንቀጽ 28(4-ሰ)፣ ከአዋጅ ቁጥር 720/04 አንቀጽ 6 እና አግባብነት ካላቸዉ የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ ድንጋጌዎች መሰረት ለማጣራት ሲባል ለሰበር ያስቀርባል የተባለ ነዉ።
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተገለጸዉን የሚመስል ሲሆን የአመልካችን አቤቱታ ከስር ፍ/ቤቶች ዉሳኔ እና አግባብነት ካላቸዉ የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መርምረናል።
አቤቱታዉ ለሰበር ያስቀርባል ሲባል ከተያዘዉ ጭብጥ አንጻር መርምረን እንደተረዳነዉ አመልካች በፍድራል ፖላስ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 720/2004 አንቀጽ 6 ወንጀልን የመርመር ስልጣን የተሰጠዉ መሆኑና ለምርመራ የሚያስፈልገዉን የግለሰብ የባንክ ሂሳብ እንቅስቃሴ መረጃ ማግኘት የሚችለዉ ስለባንክ ስራ በወጣዉ አዋጅ ቁጥር 592/2000 አንቀጽ 28(4/ሰ) መሰረት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሆኑ በግልጽ የተመለከተ በመሆኑ ፖላስ ለምርመራዉ አስፈላጊ የሆነ የተጠርጣሪ የባንክ መረጃ ሲኖር ጥያቄዉን ለፍ/ቤት አቅርቦ አስፈላጊነቱ ሲታመን ፍ/ቤት ለባንክ መረጃ እንዲሰጥ ትዕዛዝ መስጠት እንደሚችል የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የደረሰበት ድምዳሜ ተገቢ ነዉ።
በልላ በኩል የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አመልካች የተጠርጣሪዉን የባንክ መረጃዉን የሚመለከተዉ ባንክ እንዲሰጠዉ የፍ/ቤት ትዕዛዝ እንዲሰጥበት ያቀረበዉ ምክንያት በቂ አይደለም በማለት ጥያቄዉን ዉድቅ ማድረጉ በአግባቡ ነዉ? ወይስ አይደለም?
የሚለዉን ጭብጥ በተመለከተ አመልካች ስንቅ ሳይኖር ቼክ የማዉጣት ወንጀል በተጠረጠረዉ አቶ መኮንን በላይ በጀመረዉ ምርመራ ምክንያት ምንም እንኳ ቼኩ ለባንክ ቀርቦ ክፍያ ሳይፈጸም ተመላሽ የተደረገ መሆኑ አከራካሪ ባይሆንም ተጠርጣሪዉ አስቀድሞ ቼኩ የተሰረቀ በመሆኑ ክፍያ እንዳይፈጸምበት ለባንኩ ማስታወቁን ባንኩ በመግለጹ ቼኩ የተሰረቀ ነዉ ወይስ በተጠርጣሪዉ ተፈርሞ የተሰጠ ነዉ የሚለዉን እዉነታ ለማጣራትና ምርመራዉን ለማጠናቀቅ የተጠርጣሪን የባንክ ሂሳብ እንቅስቃሴ፣ ቀድሞ የፈረማቸዉን የፊርማ ናሙናዎች ማግኘቱ ወሳኝነት ይኖረዋል። እነዚህ መረጃዎች ያለፍ/ቤት ትዕዛዝና ለተፈቀደላቸዉ ሰዎች ካልሆነ በቀር ለማንም ሰዉ ተላልፎ የማይሰጡ በሕግ ጥበቃ የሚደረግላቸዉ መረጃዎች በመሆናቸዉ ፖላስ በፍ/ቤት ትዕዛዝ መረጃዎችን ካላገኘ በስተቀር በተጠርጣሪዉ ላይ የጀመረዉን ምርመራ ላያጠናቅቅ አይችልም። በመሆኑም የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አመልካች የተጠርጣሪዉን የባንክ መረጃ የሚፈልግበት አግባብ ግልጽ አይደለም በማለት የአመልካችን ጥያቄ ሳይቀበል መቅረቱ የወንጀል ምርመራዉን ልዩ ባህሪ፣ በአዋጅ ቁጥር 720/04 አንቀጽ 6 ለአመልካች የተሰጠዉን ወንጀል የመመርመር ስልጣንና በአዋጅ ቁጥር 592/00 አንቀጽ 28(4/ሰ) መሰረት የተጠርጣሪዉ የባንክ ሂሳብ መረጃ የሚገኝበትን አግባብ ያገናዘበ ባለመሆኑ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነዉ።
ልላዉ ይህ ሰበር ችሎት ለባንክ ትዕዛዝ ይስጥልን የሚለዉን የአመልካች ጥያቄን በተመለከተ በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 80(3/ሀ) እና በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 10 መሰረት ለዚህ ችሎት የተሰጠዉ ስልጣን የመጨረሻ በሆነ ዉሳኔ ላይ የተፈጸመን መሰረታዊ የሕግ ስህተት ማረም በመሆኑ በቀጥታ ለባንክ ትዕዛዝ በመስጠትና መረጃዉ መሰጠቱን በመከታተል የሚያስፈጽምበት አግባብ ባለመኖሩ የተፈጸመዉን የሕግ ስህተት በማረም ትዕዛዙ በስር ፍ/ቤት በኩል እንዲሰጥና አፈጻጸሙን አስመልክቶ ክትትል እንዲደረግበት ለስር ፍ/ቤት ጉዳዩን መመለሱ ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም የሚከተለዉ ዉሳኔ ተሰጥቷል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በወ/መ/ የካቲት 03 ቀን 2009 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ በከፊል መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት በመሆኑ ተሻሽሐል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ የሰጠዉን ትዕዛዝ መሻሩ በአግባቡ ነዉ ተብሎ ተወስኗል።
አመልካች በተጠርጣሪዉ ላይ የጀመረውን ምርመራ ለማጠናቀቅ ቼኩ በወጣበት የባንክ ሂሳብ ጋር የተያያዙና በአመልካች የተጠየቁ መረጃዎችን ማግኘት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ አመልካች መረጃዎችን ማግኘት እንዲችል በስር ፍ/ቤት ተገቢዉ ትዕዛዝ ላሰጥበት ይገባል ተብሎ ተወስኗል።
የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት መዝገቡን በማንቀሳቀስ አመልካች በተጠርጣሪ ላይ እያካሄደ ላለዉ በቂ ስንቅ ሳይኖር ቼክ የማዉጣት ወንጀል ምርመራ የጠየቃቸዉን መረጃዎች ማግኘት እንዲችል ትዕዛዝ ለሚመለከተዉ ባንክ እንዲሰጥበት ጉዳዩ ይመለስለት ተብሎ ተወስኗል። ይጻፍ።
መዝገቡ ዉሳኔ ያገኘ ስለሆነ ተዘግቷል። ይመለስ።
No topics extracted.