ማንኛውም ሰው አግባብነት ካለው አካል ፍቃድ ባላገኘበት ሁኔታ የተሸከርካሪውን የሞተር፣ የሻንሲ ቁጥር እና መሰለ መረጃዎችን የመቀየር ተግባር የፈጸመ ከሆነ አደራጎቱ የተከለከለና በወንጀል ህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል የገ/ጉ/ባለስልጣን ዓ/ህግ እና 1ኛ አቶ ፋሲል ጥላሁን 2ኛ አቶ ካላድ ሳቢት XXII አንድ ተሽከርካሪ የጉምሩክ ሕግን በመተላለፍ በህገወጥ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ መግባቱ በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠ ከሆነ የጉምሩክ አዋጅ በሚደነግገዉ አግባብ መኪናዉ በመንግስት ከመወረስ ላድን የሚችልበት ሁኔታ ስላለመኖሩ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 104/3/ /ሀ/ ፤ ስለተሽከርካሪዎች መለያ፤መመርመሪያ እና መመዝገቢያ የወጣ አዋጅ ቁጥር 681/2002 አንቀጽ 42/5/ እና 48/2/ /ሐ/
No summary available.
መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም.
ዳኞች፡- ብርሃኑ አመነው በእውቀት በላይ እንዳሻው አዳነ ሃይሉ ነጋሽ እትመት አሰፋ አመልካች፡- የገ/ጉ/ባለስልጣን ዓ/ህግ ተጠሪዎች፡- 1ኛ አቶ ፋሲል ጥላሁን 2ኛ አቶ ካላድ ሳቢት መዝገቡ የተቀጠረው ለምርመራ ነው ስለሆነም ተመርምሮ የሚከተለው ፍርድ ተሰጥቷል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የኮንትሮባንድ ወንጀልን መነሻ ያደረገ ክርክር ሲሆን፣ጉዳዩ ለዚህ ችሎት ላቀርብ የቻለዉ የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ. በ30/3/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲታረምልን በማለት የአሁን አመልካች ያቀረበዉን የሰበር አቤቱታ መርምሮ ለመወሰን ነዉ። የጉዳዩ አመጣጥ ሲታይ በፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአሁን አመልካች ከሳሽ፣ የአሁን 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች ደግሞ 1ኛ ና 2ኛ ተከሳሽ ሆነው ሲከራከሩ የነበር ሲሆን፣ከሳሽ ባቀረበዉ 1ኛ ክስ፡-በአሁኑ ተጠሪዎች ላይ የቀረበ ሲሆን ይዘቱም የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1(ሀ)) እና የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 99ን በመተላለፍ ተከሳሾች እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባቸው ለራሳቸውም ሆነ ለልላ ሰው ያልተገባ ጥቅም ለማስገኘት ምንም ዓይነት የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈፀመበትና በሞድል 270 ተመዝግቦ ወደ መንግስት መጋዘን የገባው የሰልዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 020775 ሐረር ሚኒባስ የሆነ ተሸከርካሪ ቀረጥ ተከፍሎበት የገባ መኪና ለማስመሰል የሻንሲ ቁጥር LH172-1039214 እና ሞተር ቁጥሩ 5L21455255 ከልላ መኪና ተቆርጦ የተለጠፈውን በቀን 10/08/05 ዓ/ም ከቀኑ 8፡00 አከባቢ በፍድራል ፖላስ አካላት ክትትል በሃረር ከተማ ቀበል 14 በመያዙ 1ኛ ተከሳሽ የህገወጥ መኪና ባለቤት እና 2ኛ ተከሳሽ ለህገወጥ መኪናው የ1ኛ ተከሳሽ ወኪል ሆነው ህገወጥ እቃ ይዘው በመገኘታቸው ተከሷል። 2ኛ ክስ በ2ኛ ና 3ኛ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1(ሀ)) እና የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91 /2/ በመተላለፍ ተከሳሾች እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባቸው የካቲት 30 ቀን 2005 ዓ/ም ምንም አይነት የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈፀመበትና ከላይ በ1ኛ ክስ ላይ የተመለከተው ተሸከርካሪ በ2ኛ ተከሳሽ ወኪልነት ለ3ኛ ተከሳሽ የሸጠለት በመሆኑ ተከሳሾች የኮንትሮባንድ እቃ የተገበያዩ በመሆናቸው በኮንትሮባንድ ወንጀል ተከሷል፣ 3ኛ ክስ 1ኛ ተከሳሽ የተመለከተ ሲሆን የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 93 (1(መ))ን በመተላለፍ ተከሳሽ በ1ኛ ክስ ለተጠቀሰዉ ተሽከርካሪ በህገወጥ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ ካስገባ በኋላ ተገቢዉን ቀረጥና ታክስ ለመንግስት እንዳይከፈል ለማድረግ በማሰብ በፋጢማ መሃመድ ያሲን ስም ተመዝግቦ በህጋዊ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ የገባውን ተሸከርካሪ የሻንሲ ቁጥር LH172-1039214 በመጠቀም በራሱ ስም ላብሬ አውጥቶ ሲገለገልበት በቀን 10/08/05 ዓ/ም በቁጥጥር ስር በመዋሉ ተከሷል የሚል ነዉ።
ተጠሪዎች በሥር ፍ/ቤት ቀርበው ክሱ ደርሷቸው ተቃውሞ እንደልላቸው ገልፀው፣ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል ደርጊቱን አልፈጸምንም በማለት ክደው ተከራክሯል።
ከዚህ በኋላ ፍ/ቤቱ የዐ/ሕግ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በመመርመር ተከሳሾች በቀረበባቸው ሁሉም ክሶች እንዲከላከሉ ባዘዘዉ መሰረት ተከሳሾች የፅሁፍ ማስረጃና የሰዉ መከላከያ ምስክሮችንም አቅርበው አሰምቷል። በመቀጠል ፍ/ቤቱ የዐ/ሕግ የሰነድ ማስረጃዎች እና የተከሳሽ መከላከያ ማስረጃዎችን በሕጉ አግባብ ከመዘነ በኋለ በሰጠዉ ዉሳኔ በክስ የተመለከተዉ ተሽከርካሪ በሕገ ወጥ መንገድ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ሳይፈጸምበት ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልበት ከዉጭ አገር ወደ አገር ዉስጥ መግባቱ እና ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልበት እንደተከፈለ በማስመሰል ሰነድ የተዘጋጀ መሆኑም አልተረጋገጠም ተከሳሾች በሚገባ ተከላክለዋል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል። አመልካች በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ የቀረበዉን ይግባኝ ዉድቅ በማድረግ የሥር ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል። የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ ይህን ዉሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነዉ።
የአሁን አመልካች በ18/05/2008 ዓ.ም በተጻፈ አራት ገጽ አቤቱታ አቅርቧል።
የአቤቱታው ይዘት ባጭሩ ተጠሪዎች በቀረበባቸው ክስ የሻንሲ ቁጥር LH172-1039214 እና የሞተር ቁጥር 5L21455255 የሆነ ተሸከርካሪ እነዚህ ቁጥሮች ለተሸከርካሪው በፋብሪካ የተሰጡት ቁጥሮች ሳይሆኑ በህጋዊ መንገድ በዲክለራሲዮን ቁጥር C- 1828/2010 በፋጡማ መሃመድ ያሲን ስም ወደ ሃገር ውስጥ የገባው ህጋዊ የሻንሲ ቁጥር LH172-1039214 ሲሆን ለልላ መኪና ተቆርጦ የተመታ መሆኑ ለተያዘው መኪና እንደ ሻንሲ ቁጥር አገልግሐል ። ስለሆነም እነዚህ ተሸከርካሪዎች ሻንሲና ሞተር ቁጥር ወደ ሃሰት ተለውጧል የሰልዳ ቁጥር ከኮድ 3-17811 ኦሮ ወደ ሰልዳ ቁጥር ኮድ 3-02075 ሐረ. ሲቀየር አካላዊ ሻንሲ ቁጥርና ሞተር ቁጥሩ ከሰነዱ ጋር አልተመሳከረም ይህ ስለመሆኑ በቀረበው ማስረጃ ተረጋግጧል። በተጨማሪም የሥር ፍ/ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 104 /3፣ ሀ/ለ/ መኪናዉ እንዲወረስ ዉሳኔ መስጠት ሲገባቸው ይህንን ማለፋቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲሻርልኝ በማለት አመልክቷል። ጉዳዩ ተመርምሮ ለሰበር ችሎት እንዲቀርብ በመወሰኑ ተጠሪዎች ቀርበው በፅሁፍ ተከራክረዋል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተመለከተዉ ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኛቸዉን ክርክር ለሰበር አቤቱታ መነሻ ከሆነዉ ዉሳኔ እና አግባብነት ካላቸዉ የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንዲሁም አቤቱታዉ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘዉ ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለዉ መርምሮታል። እንደመረመርነው አመልካች የወንጀሉን ድርጊት ተጠሪዎች ፈጽመዋል በሚል ያቀረበው ክስ ዋናው ድርጊት 1ኛ ተጠሪ ለ2ኛ ተጠሪ የሰጠው ውክልናን መሰረት በማድረግ እያወቁ ወይም ማወቅ እየተገባቸው በክሱ የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት በመተባበር የፈፀሙ መሆኑን በማስረጃ ተረጋግጧል በማለት ነው።
በመሰረቱ አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለው ወንጀሉን የሚያቋቁሙት ሕጋዊ፣ ግዛፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ብቻ መሆኑን የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23/2/ በግልጽ ደንግጓል። እንግዲህ አንድን ድርጊት ወንጀል ነው ብሎ ለመወሰን ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች ተጣምረው መገኘት የግድ ይላል። ሕጋዊ ፍሬ ነገሮች የሚባሉት ደግሞ ለጉዳዩ አግባብነት አለው ተብሎ የተጠቀሰውን ድንጋጌ ለማቋቋም ሙሉ በሙሉ ማሟላት ያለባቸውን ነጥቦች የሚመለከት ሲሆን ግዙፋዊና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች የሚባሉት ደግሞ እንደየቅደም ተከተላቸው ከድርጊት ማድረግ ወይም አለማድረግና ከሐሳብ ክፍል ጋር በሕጉ አንቀጽ 24፣57 እና 58 ድንጋጌዎች ስር የተመለከቱትን ሁኔታዎች የሚመለከቱ መሆኑ ይታመናል።
ወደያዝነው ጉዳይ ስንመለስ አመልካች በቀረበው ክስ ላይ የተገለፀው ለክርክሩ ምክንያት የሆነው ተሸከርካሪ በህጋዊ መንገድ በዲክለራሲዮን ቁጥር C-1828/2010 በፋጡማ መሃመድ ያሲን ስም ወደ ሃገር ውስጥ የገባው ህጋዊ የሻንሲ ቁጥር LH172-1039214 ሲሆን ይህ አሁን በቁጥጥር ስር ከዋለው መኪና ተቆርጦ የተመታ ነው በማለት ክስ ያቀረበ ሲሆን በስር ፍርድ ቤት የቀረበው የባለሞያ ማስረጃ እንደተገለፀው በሰልዳ ቁጥር 3-02075 ሐረ የሆነ ሚኒባስ ተሸከርካሪ ላይ የተገኘው መረጃ በተሸከርካሪው ጋቢና በር ስር (በተሳፋሪ በኩል ) የተገኘው የቻንሲ ቁጥር ሆን ተብሎ ለማጭበርበር ተቆርጦ በልላ የተቀየረ መሆኑ በግልፅ ማረጋገጡ ተለጥፎ የተገኘው የቻንሲ ቁጥር LH172-1039214 መሆኑ እንዲሁም በተሸከርካሪው ሞተር ላይ የተገኘው የሞተር ቁጥር መጀመሪያ በነበረው ቁጥር ላይ በድጋሚ የተመታ መሆኑ በሞተር ላይ የተገኘው ቁጥር 5L-21455255 ስለ ተሸከርካሪው መረጃ የሚሰጥ ፕልት (ስለ መኪናው ቀለም ፤ሞድል፣የምርት ዘመን ፣የሞተር ጉልበት ) በልላ መቀየሩን በቀረበው ማስረጃ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ይህ የመኪና ሞተር እና የሻንሺ ቁጥር አስመስሎ የተመታ እና መረጃ የሚሰጥ ፕልትም የተቀየረ ሲሆን አሁን በአካል የተመረመረው ተሽከርካሪ ግን ከላይ የተገለፀው ከልላ መኪና የተመታ መሆኑ በባለሙያ በመመርመር ተረጋግጧል የሚል በመሆኑ ተጠቃሹ አካል ከጻፋቸው ደብዳቤዎች ይዘት የመኪናው ሞተር እና ሻንሲ ቁጥር ተመሳስሎ የተሰራ እና የተመታ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሐል። ስለሆነም እነዚህ የሻንሲ ቁጥር መለወጥ እና የሞተር ቁጥር መምታት፤ አድራጎቶች ተጠሪዎች ሆነ ብለው ወይም ማወቅ እየተገባቸው ድርጊቱን የፈጸሙትና ውጤቱንም የራሳቸው ያደረጉ መሆኑንን የሚያስገነዝብ ሆኖ አግኝተነዋል።
ስለተሽከርካሪዎች መለያ፤መመርመሪያ እና መመዝገቢያ የወጣው አዋጅ ቁጥር 681/2002 ቁጥር 7/1 (ለ) እና (ሐ) የተሸከርካሪን ዝርዝር መግለጫ ለመመዝገብ እና የባለንብረት መታወቂያ ለመስጠት የሞተር ቁጥሩ እና የሻንሲ ቁጥር ላመዘገብ እንደሚገባ ተደንግጓል። የአዋጁ ቁጥር 42/5 እና 48/2/ሐ ማንኛውም ሰው አግባብነት ያለው አካል ሳይፈቅድ የተሽከርካሪውን የሞተር ቁጥር የሻንሲ ቁጥር እና መሰል መረጃዎች መቀየር እንደማይቻል እና በወንጀል እንደሚያስጠይቅ ይደነግጋል።
በሥር ፍ/ቤት በተደረገው ክርክር የተሽከርካሪው ሞተር ቁጥር እና ሻንሲ ቁጥር የተመታ እና ተመሣሥሎ የተሰራ መሆኑ የተረጋገጠ ፍሬነገር ከመሆኑም በላይ ተጠሪ የመኪናው ሞተር ቁጥር እና ሻንሲ ቁጥር የተመታው አግባብነት ያለው አካል ፈቅዶላቸው መሆኑን መኪናው በጨረታ ሲገዙትም አሁን ባለበት ሁኔታ የሚመለከተው አካል አውቆት ስለመሆኑ በመግለጽ ያቀረቡት ክርክር የለም።
በአጠቃላይ የስር ፍርድ ቤት ተጠሪዎች ፈጽመዋቸዋል በማለት በማስረጃ ያረጋገጣቸው ፍሬ ነገሮች ሁለቱም ተጠሪዎች የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1(ሀ)) እና የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 99ን በመተላለፍ እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባቸው ለራሳቸውም ሆነ ለልላ ሰው ያልተገባ ጥቅም ለማስገኘት ምንም ዓይነት የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈፀመበትና በሞድል 270 ተመዝግቦ ወደ መንግስት መጋዘን የገባው የሰልዳ ቁጥሩ ኮድ 3-020775 ሐረር ሚኒባስ የሆነ ተሸከርካሪ ቀረጥ ተከፍሎበት የገባ መኪና ለማስመሰል የሻንሲ ቁጥር LH172-1039214 እና ሞተር ቁጥሩ 5L21455255 ከልላ መኪና ተቆርጦ የተለጠፈውን በቀን 10/08/05 ዓ/ም ከቀኑ 8፡00 አካባቢ ሲገለገሉ በፍድራል ፖላስ አካላት ክትትል በሃረር ከተማ ቀበል 14 በመያዙ 1ኛ ተከሳሽ የህገወጥ መኪና ባለቤት እና 2ኛ ተከሳሽ ለህገወጥ መኪናው የ1ኛ ተከሳሽ ወኪል ሆነው ህገወጥ እቃ ይዘው በመገኘታቸው በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የኮንትሮባንድ ወንጀል የፈፀሙ መሆኑን የተረጋገጠበት በመሆኑ ጥፋተኛ ናቸው ብለናል። ሁለተኛው ክስም በተመለከተ ፣ 2ኛ ተጠሪ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91 /2/ በመተላለፍ እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ምንም አይነት የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈፀመበትና ከላይ በ1ኛ ክስ ላይ የተመለከተው ተሸከርካሪ ሚያዝያ ወር 2005 ዓ.ም የሰልዳ ቁጥር ኮድ 3-17811 ተሽከርካሪ እንዲያስተዳድር የተሰጠውን ውክልና መሰረት በማድረግ ለ3ኛ ተከሳሽ የሸጠለት በመሆኑ ተከሳሾች የኮንትሮባንድ እቃ የተገበያዩ መሆኑ በኮንትሮባንድ ወንጀል መፈፀሙ ተረጋግጧል ፣ እንዲሁም 1ኛ ተጠሪ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 93 (1(መ))ን በመተላለፍ ተከሳሽ በ1ኛ ክስ ለተጠቀሰዉ ተሽከርካሪ በህገወጥ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ ካስገባ በኋላ ተገቢዉን ቀረጥና ታክስ ለመንግስት እንዳይከፈል ለማድረግ በማሰብ በፋጢማ መሃመድ ያሲን ስም ተመዝግቦ በህጋዊ መንገድ ወደ ሃገር ውስጥ የገባውን ተሸከርካሪ የሻንሲ ቁጥር LH172-1039214 በመጠቀም በራሱ ስም ላብሬ አውጥቶ ሲገለገልበት በቀን 10/08/05 ዓ/ም በቁጥጥር ስር በመዋሉ በቀረበው ማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ ጥፋተኛ ነው ብለናል።
የበታች ፍ/ቤቶች ጉዳዩን በዚህ አግባብ በመገንዘብ መወሰን ሲገባቸው ይህንን ማለፋቸው መሰረታዊ የህግ ስህተት ነው ።ልላው መታየት ያለበት በዐ/ሕግ ክስ የተጠቀሰዉ ተሽከርካሪ የጉምሩክ ሕግን የመተላለፍ ድርጊት የተፈጸመበት ስለመሆኑ በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠ እስከሆነ ድረስ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 104/3/ /ሀ/ በሚደነግገዉ አግባብ መኪናዉ በመንግስት ከመወረስ ላድን የሚችልበት ሁኔታ የለም። የተያዘ መኪና ቀረጥና ታክስ ተከፍሎ መኪናዉ ለባለቤቱ ወይም ለተያዘበት ሰዉ ላመለስ የሚችለዉ መኪናዉ የጉምሩክ ሕግን የመተላለፍ ድርጊት የተፈጸመበት ስለመሆኑ አጥጋቢ ማስረጃ ያልቀረበ እንደሆነ ነዉ። አሁን አከራካሪ የሆነው መኪና የጉምሩክ ሕግን የመተላለፍ ድርጊት የተፈጸመበት ስለመሆኑ በበቂና አጥጋቢ ማስረጃ እስከተረጋገጠ ድረስ መኪናዉ እንዲወረስ ከሚደረግ በስተቀር ቀረጥና ታክስ ተከፍሎ ለባለቤቱ ወይም ለተያዘበት ሰዉ የሚመለስበት አግባብ የለም። ስለሆነም ለክርክር የሆነዉ ተሸከርካሪ የጉምሩክ ሕግን የመተላለፍ ድርጊት የተፈጸመበት መሆኑን እስከተረጋገጠ ድረስ መኪናዉ ላወረስ ይገባል።
ሲጠቃለል የስር ፍርድ ቤቶች ለክርክር ምክንያት የሆነዉ ተሽከርካሪ የተጭበርበረ ስለመሆኑ በባለሞያ የቀረበው ማስረጃ ሳይመለከቱ ተሸከርካሪው ሕጋዊ መሆኑ ተከላክለዋል በማለት ተጠሪዎች ነፃ እንዲለቀቁ የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ሥሕተት የተፈጸመበት ሆኖ አግኝተነዋል። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
1 .የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ/ በቀን 28/04/2007 ዓ.ም.እና የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ በቀን 30/03/2008 ዓ.ም. የሰጠው ውሳኔ በወ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ 195/2/ /ሀ/ መሰረት ተሽሯል።
2 .1ኛ ተጠሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1(ሀ)) / ከጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 99ን እና የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 93 (1(መ))ን በመተላለፍ ፣እንዲሁም 2ኛ ተጠሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1(ሀ)) / ከጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 99ን እና የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91 /2/ የተመለከተውን በመተላለፋ ጥፋተኛ ናቸው ብለናል።
3 .የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈጸመበትን ከላይ የተገለጸውን በኤግዚቢትነት የተያዘው ተሸከርካሪ ሰልዳ ቁጥር ኮድ 3-02075 ሐረ. በሚል የሚታወቀው ተጠሪዎች ጥፋተኛ የተባሉ በመሆኑ ከአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 104/1/ መሰረት ለመንግስት እንዲወረስ ታዟል። አመልካች ተከታትሎ ያስፈጸም።
4/ የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙ የቅጣት ሀሳብ ከተቀበለና ከአከራከረ በኋላ ከሕጉ እና ከቅጣት አወሳሰን መመሪያ አንጻር በመመርመር በተጠሪዎች ላይ የቅጣት ውሳኔ እንዲሰጥ በወ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ 195/2/ /ሀ/ መሰረት መልሰን ልከንለታል።
ት እ ዛ ዝ 1/ የፍድራል ፖላስ ተጠሪዎች፡- 1ኛ አቶ ፋሲል ጥላሁን እና 2ኛ አቶ ካላድ ሳቢት ከተገኙበት ቦታ ይዞ ለፍደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ ችሎት እንዲያቀርበው ታዟል።ይጻፍ ።
2/ የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ድሬዳዋ ምድብ ችሎት መ/ በመጣበት አካኋን በፍ/ቤቱ ሬጅስትራር አማካኝነት ተመላሽ ይሁን ።
No topics extracted.