No summary available.
መ/ቁ/141677 ህዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡ ብርሃኑ አመነዉ በዕዉቀት በላይ እንዳሻዉ አዳነ ሃይሉ ነጋሽ እትመት አሰፋ አመልካች፡ ያዕቆብ አብዱ - ተጠሪ፡ የደቡብ ክልል አቃቤ ህግ መዝገቡ ለምርመራ የተቀጠረ በመሆኑ ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል ።
የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ አመልካች የወ/ህግ አንቀጽ 27/1/ እና 540 ተላልፎ ተራ የሆነ ሰዉ ግድያ ሙከራ ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የሸካ ዞን ከፍተኛ ፍ/ ቤት የሰጠዉ ፍርድ የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት እና ሰበር ችሎት በማጽናታቸዉ ዉሳኔዉ ላይ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል እንዲታረም ስላመለከተ ነዉ ።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ አመልካች በወ/ህግ 541 ተከሶ እያለ በወ/ህግ 540 ጥፋተኛ መባሉና እና ድርጊቱ በሙከራ ቀርቶ እያለ በወ/ህጉ አንቀጽ 27/3/ መሰረት ቅጣት ያልቀለለበት አግባብ ለመመርመር እንዲቻል ዓቃቤ ህግ መልስ እንዲሰጥ ታዟል። የፍ/ቤቱ መጥሪያ ለዓቃቤ ህግ በፖስታ ቤት በኩል የተላከለት ቢሆንም ቀርቦ መልስ አልሰጠም ። በዚሁ መልስ የመስጠት መብቱ ታልፎ መዝገቡ ተመርምሯል ።
በሰበር አጣሪ ችሎት የተያዘዉ አንደኛ ጭብጥ አመልካች በወ/ህግ አንቀጽ 541 ተከሶ እያለ በአንቀጽ 540 ጥፋተኛ የመባሉን አግባብነት ለመመርመር ሲሆን በእኛ በኩል መዝገቡን መርምረን እንደተረዳነዉ ዐቃቤ ህግ መጀመሪያ ክስ ያቀረበዉ በአንቀጽ 541 ቢሆንም በክርክር ሂደት ክሱን በማሻሻል በወ/ህግ አንቀጽ 27/1/ 540 ስር የለወጠ ስለመሆኑ ስር ፍ/ቤት ዉሳኔ ይዘት ያስረዳል ።ፍ/ቤቱም ተሻሽሎ በቀረበዉ አንቀጽ መሰረት የጥፋተኝነት ዉሳኔ ሰጥቷል ። ስለሆነም አንቀጹን ወደ 540 የለወጠዉ ፍርድ ቤቱ ሳይሆን ከሳሽ ዓቃቤ ህግ ስለሆነ ሰበር አጣሪ ችሎት የስር ፍ/ቤት በራሱ አነሳሽነት ከአንቀጽ 541 ወደ 540 ማለትም ከቀላል ወደ ከባዱ አንቀጽ የለወጠ መስሎት በዚህ ነጥብ ላይ ጭብጥ መያዙ ፍርዱን ባለማገናዘብ እንደሆነ ማየት ችለናል ። በልላ በኩል አመልካች አጥብቆ የሚከራከረዉ ክሱ ከተሻሻለ በኋላ በከበደዉ አንቀጽ ስር የመከራከር መብቱ ባልተጠበቀበት ሁኔታ የጥፋተኝነት ፍርድ መሰጠቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት ነዉ በማለት ነዉ ። ስለዚህም ክስ ከተሻሻለ በኋላ ፍ/ቤቱ የተከተለዉ የክርክር አመራር ስርዓት አግባብነት ከህጉ ጋር በማገናዘብ መርምረናል ።
በመሰረቱ የወንጀል ክስ ላሻሻል የሚችልባቸዉ ምክንያቶች በወ/መ/ስ/ስ/ህግ አንቀጽ118 እና 119 ስር የተመለከቱ ሲሆን የክሱ መሻሻል የሚያስከትለዉ ዉጤት በዚሁ ድንጋጌ አንቀጽ 120 እና 121 ላይ ተመልክቷል ።ከእነዚህ ድንጋጌዎች ይዘት መገንዘብ እንደሚቻለዉ ክስ ተሻሽሎ ከቀረበ በኋላ ለተከሳሹ ተነቦለት የክሱ መሰማት የሚቀጥል መሆኑን እና ምስክሮችም በዚህ አግባብ እንደገና እንዲሰሙ መደረግ የሚችልበት ሁኔታ ስለመኖሩ ነዉ ።በተያዘዉ ጉዳይ ዓቃቤ ህግ የወ/ህግ አንቀጽ 27/1/ እና 541 ጠቅሶ ክስ አቅርቦ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ቃል ከተሰማ በኃላ ዓቃቤ ህግ ክሱን በማሻሻል ወደ አንቀጽ 27/1/ እና 540 ለዉጦ ያቀረበ ሲሆን ጉዳዩን የያዘዉ ፍ/ቤት የተከሳሽን የመሰማት መብት ሳይጠብቅ ቀደም ሲል በተሰማዉ ክርክርና የዓቃቤ ህግ ማስረጃ መሰረት ተከሳሽ /አመልካች / ተሻሽሎ በቀረበበት ክስ ድንጋጌ እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል ።አመልካች ቀደም ሲል የተከሰሰዉ በቀላል ግድያ ሙከራ ወንጀል ሲሆን ተሻሽሎ የቀረበዉ ክስ ደግሞ ተራ የሰዉ ግድያ ሙከራ ወንጀል በመሆኑ ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ የሚጣልበት ቅጣት ከባድ ከመሆኑ አንጻር የተከሳሹ መሰረታዊ መብት ላይ የሚኖረዉ አሉታዊ ተጽእኖ ጋር ተመዛዝኖ በስነስርዓት ህጉ የተጠበቀለት የመሰማት መብት በጥብቅ ተግባራዊ ላደረግ እንደሚገባ መረዳት አዳጋች አይደለም። ከዚህ መሰረታዊ መብት አንጻር የፍርድ ቤቱ የክርክር አመራር በወ/መ/ስ/ስ/ህግ ቁ/119/2/ ፤120 እና 121 ድንጋጌዎች በአግባቡ ያላገናዘበ እንደሆነ መረዳት ተችሐል ። ስለሆነም ክሱ ተሻሽሎ ለዚያዉም ወደ ከባድ አንቀጽ ተለዉጦ ቀርቦ እያለ ክሱ እንደገና እንዲሰማ መደረግ እንዳለበት የተደነገገዉን ስርዓት ሳይጠብቅ ክርክሩን በመምራት የስር ፍ/ቤት የሰጠዉ የጥፋተኝነትም ሆነ የቅጣት ዉሳኔ ላይ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ አግኝተናል ። የበላይ ፍ/ቤቶች ይህንኑ ተገንዝበዉ ሳያርሙ ማጽናታቸዉ ግልጽ ግድፈት ስለሆነ ለታረም ይገባል ብለናል።
ሁለተኛዉ ጭብጥ ድርጊቱ በሙከራ ደረጃ የቀረ ከመሆኑ አኳያ በወ/ህጉ አንቀጽ 27/3/ መሰረት ቅጣት እንዲቀልለት አለመደረጉን አግባብነት ለመመርመር ነዉ። ነገር ግን ክርክሩ በአንደኛዉ ጭብጥ እልባት ያገኘ ስለሆነ መመርመር አስፈላጊ ባለመሆኑ ታልፏል በዚሁ አግባብ ተከታዩን ዉሳኔ ሰጥተናል ።
1ኛ /የሸካ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ቁ/ 5224 በ16/02/09 ዓ.ም አመልካች የወ/ህግ እንቀጽ 27/1/ እና 540 ስር የተመለከተዉን ተላልፎ ተራ የሆነ የሰዉ ግድያ ሙከራ ወንጀል ፈጽሟል በማለት በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የሰጠዉ ዉሳኔ እና ይህንኑ በማጽናት የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/04047 የሰጠዉ ትእዛዝ እና ሰበር ችሎቱ በመ/ቁ/04781 የሰጠዉ ትእዛዝ በወ/መ/ስ/ስ/ህግ ቁ 195/2/ለ/2 / መሰረት ተሽሯል ።
2ኛ/ዓቃቤ ህግ አሻሽሎ ባቀረበዉ ክስ ላይ የአመልካችን እምነት ክህደት ቃል ከመቀበል ጀምሮ በወ/መ/ ስ/ስ ህግ አንቀጽ 119/2/ ፤120 እና 121 በተደነገገዉ አግባብ ክርክሩን በማየት ተገቢዉን ፍርድ እንዲሰጥ ብለን መዝገቡን በወ/መ/ስ/ስ/ህግ ቁ/ 195/2/ሀ መሰረት ለሸካ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት መልሰናል ።ይጻፍ ።
No topics extracted.