አንድ በወንጀል የተከሰሰ ሰው በመግደል ሙከራ ወንጀል ጥፋተኛ ላደረግ የሚገባው የወንጀሉ አፈፃፀም አበራ ዋቅጅራ እና መስከረም 25/2010 XIX ሁኔታ እና በተበዳዩ ላይ ከደረሰው ጉዳት አንፃር እውነትም ወንጀሉን ለመፈፀም ሀሳብ የነበረው እና የተፈለገው ውጤት ያልተገኘው ሀሳቡን ለማሳካት የማያስችል ሁኔታ በመፈጠሩ ምክንያት መሆኑን ለማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ስለመሆኑ የወንጀል ህግ አንቀፅ 555 (1) እና 540፣ 27(1) የቤ/ጉ/ክልል ፍትህ ቢሮ 35. በአንድ የወንጀል የማድረግ ሃሳብ ወይም ቸልተኝነት የተፈጸመዉ የወንጀል ድርጊት በሕግ በተጠበቀ አንድ መብት ላይ በሚሆንበት ጊዜ እና ድርጊቶቹ በሙሉ በአንድ ድንጋጌ ስር መሸፈን ከተቻለ፤ ፈጻሚዉ የሚቀጣዉ ድርጊቶቹ በሚሸፈኑበት በአንድ ድንጋጌ ስር እንጂ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ተደራራቢ ወንጀሎች ስላለመሆኑ፡በወንጀል ሕግ አንቀጽ 61(1)
No summary available.
ቀን-መስከረም 23 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- ዳኜ መላኩ ብርሃኑ አመነዉ በዕዉቀት በላይ ኃይሉ ነጋሽ እትመት አሰፋ አመልካች:- አቶ አበበ ተፈራ አለሙ ተጠሪ፡- የፍድራል ጠቅላይ ዐ/ሕግ መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል።
ጉዳዩ ወንጀል ሲሆን የተጀመረዉ በፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ተጠሪ በአመልካች ላይ በመሰረተዉ ክስ መነሻነት ነዉ። አመልካች ላይ ቀርበዉ የነበሩት ሁለት ክሶች ሲሆኑ የ1ኛ ክስ ይዘት፡- በወንጀል ሕግ አንቀጽ 543(3) ላይ የተመለከተዉን በመተላለፍ የሙያ ግድታዉን በመተላለፍ ሟች አያን ገቦቤን ወደ ተከራየበት ቤት በመዉሰድ በባለሙያ ብቻ የሚሰጠዉ ዲያዜፖም እና ትራማ ዶ የሚባሉትን አደንዛዥ መድሃኒቶችን እራሱ በመርፍ በመዉጋት ብልቷን ከሰፋት በኃላ በተወጋችዉ መድሃኒት የተነሳ የመተንፈስ ችግር ተከስቶ የሞተች በመሆኑ በፈጸመዉ በቸልተኝነት ሰዉ መግደል ወንጀል ተከሷል የሚል ነዉ። የ2ኛ ክስ ይዘት ደግሞ በወንጀል ሕግ ቁጥር 566(1) የተመለከተዉን በመተላለፍ በ1ኛ ክስ ላይ በተገለጸዉ ጊዜና ቦታ የሟች አያን ገቦቤን ብልት የሰፋ በመሆኑ የሴት ልጅ ብልት የመስፋት ወንጀል ተከሷል የሚል ነዉ።
በስር ፍ/ቤት አመልካች የእምነት ክህደት ቃል ሲጠየቅ ድርጊቱን መፈጸሙን አምኖ ጥፋተኝነቱን በማረጋገጥ አፈጻጸሙን በዝርዝር ሲያስረዳ ሚያዚያ 21 ቀን 2007 ዓ.ም ማታ ከሟች ጋር አብረን አድረናል። ቀን ሥራዬን አጠናቅቄ ለመዉጣት ስል ሟች ቀደሞ የፍቅር ጓደኛዬ ስለነበረች በመማጸን እጮኛዬ ከዉጭ ይመጣል፤ በባህሉ ብልቴን ተሰፍቶ ካላገኘኝ ለቤተሰቤም ለእኔም ዉርደት ይሆንብኛል፤ አግብቶኝ ዉጭ ሀገር የመሄድ አጋጣሚዉ ያመልጠኛል በማለቷ ለድርጊቱ የሚያስፈልጉ ቁሶችን በመያዝ ወደ ቤት ሄጃለሁ። የአክስቴ ቤት ገብተን ክፍል ተሰጥቶን አድረናል። ከዚያም ጧት ላይ ብልቷን ሰፍቼ ካጠናቀቅኩ በኃላ ሟች ሕይወቷ አልፏል። ስለሆነም ጥፋተኛ ነኝ በማለቱ የስር ፍ/ቤት አመልካች በሰጠዉ የእምነት ቃል መሰረት የወንጀል ሕግ ቁጥር 543(3) እና 566(1) የተመለከቱትን ድንጋጌዎች በመተላለፍ በሁለቱም ክሶች ጥፋተኛ በማድረግ አመልካች በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል። አመልካች በዉሳኔዉ ቅር ተሰኝቶ ያቀረበዉን ይግባኝ የተመለከተዉ ፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የስር ፍ/ቤትን የጥፋተኝነትና የቅጣት ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል። አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት ይህንኑ ዉሳኔ በመቃወም ለማስቀየር ነዉ።
አመልካች ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ ይዘት፡- ድርጊቱን ስፈጽም ሁለት የወንጀል ድርጊቶችን ለመፈጸም አቅጄ የፈጸምኩት የወንጀል ድርጊት አይደለም። ሟችን ብልቷን ስሰፋ የሕመም ስሜት እንዳይሰማት በክሱ ላይ የተገለጹትን መድሃኒቶችን ልሰጣት ችያለሁ። በወ/ሕ/ቁ 61(1) በአንድ መብት ላይ የሚደረግ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ የተቀላቀሉ የወንጀል ድርጊቶች የተደረጉት በአንድ የወንጀል ማድረግ ሀሳብ ወይም ቸልተኝነት ሲሆን እና ድርጊቱም በአንድ ድንጋጌ ስር የሚሸፈኑ ሲሆን አድራጊዉ ተመሳሳይ ባህሪ ባላቸዉ በሁለት ወይም ከሁለት በበለጡ ተደራራቢ የቅጣት ድንጋጌዎች አይቀጣም በማለት ደንግጓል። ስለሆነም በአንድ የወንጀል ማድረግ ቸልተኝነት የተፈጸመ በመሆኑ ድርጊቶቹም በአንድ የወንጀል ድንጋጌ ስር የሚሸፈኑ በመሆኑ የስር ፍ/ቤት ያቀረብኩትን መቃወሚያ ዉድቅ ማድረጉም ሆነ ይግባኝ ሰሚዉ ፍ/ቤት ዉሳኔዉን ማጽናቱ መሰረታዊ የሕግ ስህተት በመሆኑ በአንድ ክስ ተጠቃልሎ ስህተቱ ይታረምልኝ።
የስር ፍ/ቤት የ1ኛ ክስ ደረጃና እርከን ሲያወጣ ደረጃ 2 እርከን 25 ስር ያሳረፈዉ ማደንዘዣ መድሃኒት መስጠት እና ህክምናዉን ለመስጠት ባልተፈቀደ የግል መኖሪያ ቤት በማድረጉ ሁለት የድንጋጌዉ ፍሬ ነገሮች ተሟልተዋል በማለት ነዉ። እነዚህ ፍሬ ነገሮች እንደሁለት የሚወሰዱ ሳይሆን በድንጋጌዉ ስር ግልጽ የሆነ ደንብን በመተላለፍ የሚለዉን ፍሬ ነገር ብቻ የሚያሟሉ በመሆናቸዉ እንደ አንድ የሚወሰዱ ናቸዉ።
ስለሆነም በደረጃ 1 እርከን 21 ስር የሚያርፍ ይሆናል። 2ኛ ክስ በ1ኛ ክስ የሚጠቃለል ከመሆኑም በላይ ደረጃዉን መካከለኛ ማለቱ ተገቢ አይደለም። በስር ፍ/ቤት ካቀረብኳቸዉ 6 ማቅለያ ምክንያቶች ዉስጥ አንዱን ብቻ በመተዉ አምስቱን የወሰደ ቢሆንም 4 እርከን ብቻ መቀነሱ ተገቢ ባለመሆኑ 5 እርከን ተቀንሶ ቅጣቱ ላቀነስልኝ እና ላገደብልኝ ይገባል የሚል ነዉ።
የአመልካች አቤቱታ ተመርምሮ የአመልካች ሃሳብ በሰጣት የማደንዘዣ መድሃኒት ስትደነዝዝ ብልቷን መስፋት ከሆነ ድርጊቱ ሞት ያስከተለ ቢሆንም በድርጊት እና ሃሳብ አንጻር በሁለቱም የሕግ አንቀጾች ጥፋተኛ ተብሎ የተቀጣበት አግባብነት ለማጣራት ሲባል ጉዳዩ ለሰበር ያስቀርባል የተባለ ሲሆን የግራ ቀኙን መልስ እና የመልስ መልስ በጽሁፍ በማቀባበል ክርክር ተደርጓል።
ተጠሪ ያቀረበዉ መልስ ይዘት፡- በወንጀል ሕግ አንቀጽ 60(ለ) መሰረት በአንድ ድርጊት በአንድ ጊዜ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ የሕግ ድንጋጌዎችን ያደረገ እንደሆነ ክሱ በተደራራቢነት መቅረብ እንዳለበት ሕጉ ይደነግጋል። በተያዘዉ ጉዳይ አመልካች በአንድ ድርጊት በአንድ ጊዜ ሁለት ድንጋጌዎችን ወይም በአንድ ድርጊት ልዩ ልዩ ግዙፋዊ ዉጤት የሚያስከትሉ ወንጀሎችን ያደረገ በመሆኑ በ1ኛ ክስ የወ/ሕ/አንቀጽ 543/3/ በቸልተኝነት ሰዉ መግደል ወንጀል እና በ2ኛ ክስ የወ/ሕ/አንቀጽ 566/1/ የሴትን ብልት መስፋት ወንጀል መከሰሱም ሆነ ጥፋተኛ ተብሎ መወሰኑ አግባብና ሕግን መሰረት ያደረገ ነዉ። በስር ፍ/ቤት የተሰጠዉ የ10 ዓመት ጽኑ እስራት የተሻሻለዉን ቅጣት የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 02/2006 መሰረት ያደረገ በመሆኑ ላጸና ይገባል የሚል ነዉ። አመልካች አቤቱታዉን በሚያጠናክር መልኩ የመልስ መልስ አቅርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥ እና የክርክሩ ይዘት ከላይ የተገለጸዉን የሚመስል ሲሆን የአመልካችን አቤቱታ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘዉ ጭብጥ አንጻር ከስር ፍ/ቤቶች ዉሳኔ እና አግባብነት ካላቸዉ የሕግ ድንጋጌዎች አኳያ መርምረናል። በዚህም መሰረት ከስር ፍ/ቤት ዉሳኔ ግልባጭ መርምረን እንደተረዳነዉ አመልካች የሟችን ብልት ለመስፋት የማደንዘዣ መድሃኒት በመስጠት በመስፋት ላይ እያለ በመድሃኒቱ የተነሳ መተንፈስ ተስኗት ሕይወቷ ማለፉ በአመልካች በራሱ የእምነት ቃል የተረጋገጠ በመሆኑ አከራካሪ አይደለም። ግራቀኙን ያከራከረዉ እና ጉዳዩ ለሰበር ያስቀርባል ሲባል በጭብጥነት የተያዘዉ አመልካች በወ/ሕ/አንቀጽ 543(3) የተመለከተዉን በመተላለፍ በቸልተኛነት ሰዉ መግደል ወንጀል ጥፋተኛ በተባለበት ሁኔታ በ2ኛ ክስ የወ/ሕ/አንቀጽ 566(1) የተመለከተዉን በመተላለፍ የሴት ልጅ ብልት በመስፋት ወንጀል ጥፋተኛ መባሉ በአግባቡ ነዉ ወይስ አይደለም? የሚለዉ ነዉ።
በመሰረቱ በወ/ሕ/አንቀጽ 61(1) በሕግ በተጠበቀ በአንድ መብት ላይ የሚደረጉ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ የተቀላቀሉ የወንጀል ድርጊቶች የተደረጉት በአንድ የወንጀል ማድረግ አሳብ ወይም ቸልተኝነት ሲሆን እና ድርጊቶቹ በሙሉ በአንድ ድንጋጌ ስር የሚሸፈኑ ሲሆን አድራጊዉ ተመሳሳይ ባህሪ ባላቸዉ በሁለት ወይም ከሁለት በበለጡ ተደራራቢ የቅጣት ድንጋጌዎች አይቀጣም በማለት ተደንግጓል። ከዚህ ንዑስ አንቀጽ ድንጋጌ የምንገዘበዉ በአንድ የወንጀል የማድረግ ሃሳብ ወይም ቸልተኝነት የተፈጸመዉ የወንጀል ድርጊት በሕግ በተጠበቀ አንድ መብት ላይ በሚሆንበት ጊዜ እና ድርጊቶቹ በሙሉ በአንድ ድንጋጌ ስር መሸፈን እስከቻሉ ድረስ ፈጻሚዉ የሚቀጣዉ ድርጊቶቹ በሚሸፈኑበት በአንድ ድንጋጌ ስር እንጂ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ተደራራቢ ወንጀሎች አለመሆኑን ነዉ።
በተያዘዉ ጉዳይ አመልካች በአንድ ወንጀል በማድረግ ሃሳብ የፈጸመዉ ወይም በሟች ላይ የፈጸመዉ የሴት ብልት መስፋት የወንጀል ድርጊት ለሟች ሞት ምክንያት ሆኗል።
የሟች ሕይወት ባያልፍ ኖሮ አመልካች የወ/ሕ/አንቀጽ 566(1) የተመለከተዉን በመተላለፍ በሴት ብልት በመስፋት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ በተቀጣ ነበር። ሆኖም ድርጊቱ በሟች አካል ላይ ስቃይና ጉዳት ከማድረስ አልፎ ለሟች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሆኗል። የሟች ሕይወት ማለፍ ትልቁ ወንጀል በመሆኑ በዉስጡ በሟች አካል ላይ የሚደርሰዉን ስቃይና ጉዳት አጠቃልሎ የሚይዝ በመሆኑ አመልካች የወ/ሕ/አንቀጽ 543(3) ተላልፎ በሟች ላይ በቸልተኝነት ግድያ ፈጽሟል ተብሎ ክስ ቀርቦበት እስከተቀጣ ድረስ በትንሹ ወንጀል የወ/ሕ/አንቀጽ 566(1) የተመለከተዉን ተላልፏል ተብሎ በተደራራቢ ወንጀል የሚቀጣበት የሕግ አግባብ አይኖርም። የዚህ ማጠናከሪያዉ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ስር የሴት ብልት መስፋቱ የጤና ችግር ወይም የአካል ጉዳት አስከትሎ እንደሆነ ቅጣቱ ከ5 ዓመት እስከ 10 ዓመት ጽኑ እስራት ላደርስ እንደሚችል ሲደነገግ ነገር ግን የደረሰዉ ጉዳት ወይም ዉጤት ከዚህ በላይ የሚያስቀጣ ከሆነ ተፈጻሚ የሚደረገዉ ትልቁን ወይም ከባዱን ቅጣት የያዘዉ መሆኑን ያስገነዝበናል እንጂ በተደራራቢ ወንጀል በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ተደራራቢ ወንጀሎች ይቀጣል አይልም። በዚሁ መሰረት በ1ኛ ክስ የተጠቀሰዉ የወ/ሕ/አንቀጽ 543(3) ከ5 ዓመት እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ በመሆኑ ትልቁን ቅጣት የያዘና በሟች ላይ የተፈጸመዉን ድርጊትና ዉጤት በሙሉ የሚሸፈንበት ከመሆኑም በላይ አመልካች የተከሰሰበትና የተከራከረበት ጭምር በመሆኑ ጥፋተኛ መባል የሚገባዉ የወ/ሕ/አንቀጽ 543(3) ብቻ መሆን ሲገባዉ በ2ኛ ክስ የወ/ሕ/አንቀጽ 566(1) የተመለከተዉን ተላልፏል ተብሎ በተደራራቢ ወንጀል መቀጣቱ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑ በስር ፍ/ቤት በአመልካች ላይ የተላለፈዉን የጥፋተኝነት ዉሳኔ ተሻሽሎ የወ/ሕ/አንቀጽ 543(3) የተመለከተዉን በመተላለፍ በቸልተኝነት ሰዉ መግደል ወንጀል ብቻ ጥፋተኛ ላባል ይገባል።
ቅጣትን በተመለከተ በተሻሻለዉ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 02/2006 መሰረት አመልካች ጥፋተኛ የተባለበት የወ/ሕ/አንቀጽ 543(3) ደረጃ የወጣለት በመሆኑና የወንጀል ማቋቋሚያ ዉስጥ ግልጽ ደንብና መመሪያ በመተላለፍ የተፈጸመ በመሆኑ የተሟላዉ አንድ የአንቀጹ ማቋቋሚያ ፍሬ ነገር ነዉ። በዚሁ መሰረት ደረጃ አንድ በእስራት ቅጣት እርከን 21 በገንዘብ መቀጮ እርከን 6 ላይ ያርፋል። በስር ፍ/ቤት የገንዘብ መቀጮ ያልተወሰነና ቅሬታ ያልቀረበበት በመሆኑ አልፈነዋል። የእስራት ቅጣቱን በተመለከተ በስር ፍ/ቤት የተያዙለትን አራት የቅጣት ማቅለያዎችን እንዳለ ወስደን አራት እርከን ሲቀነስለት እርከን 17 ላይ ያርፋል። እርከን 17 ፍቅድ ስልጣኑ ከ3 ዓመት ከ3 ወር እስከ 3 ዓመት ከ11 ወር የሚያስቀጣ በመሆኑ አመልካች ለፈጸመዉ አድራጎት ይመጥናል ባልነዉ በ3 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት ላቀጣ ይገባል።
ሲጠቃለል በአመልካች ላይ የተሰጠዉ የጥፋተኝነትና ቅጣት ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ በመገኘቱ የሚከተለዉ ዉሳኔ ተሰጥቷል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ ሐምል 15 ቀን 2007 ዓ.ም ተሰጥቶ በፍድራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በወ/ይ/መ/ ጥቅምት 23 ቀን 2009 ዓ.ም በተሰጠ ዉሳኔ የጸናዉ የጥፋተኝነት እና የቅጣት ዉሳኔ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 195(2/ለ/2) መሰረት ተሻሽሐል።
በስር ፍ/ቤት አመልካች የወ/ሕ/ አንቀጽ 543(3) እና 566(1) የተመለከተዉን ተላልፏል ተብሎ የተሰጠዉ የጥፋተኝነት ዉሳኔ እና የ10 ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት ተሻሽሎ አመልካች የወ/ሕ/አንቀጽ 543(3) የተመለከተዉን በመተላለፍ ጥፋተኛ ነዉ ተብሎ በ3 (ሦስት) ዓመት ከ6(ስድስት) ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል።
በዚህ ዉሳኔ መሰረት እንዲያስፈጽም የዉሳኔዉ ግልባጭ አመልካች ለሚገኝበት ማረሚያ ቤት ይተላለፍ። እንዲሁም ለስር ፍ/ቤቶች ይላክ።
መዝገቡ ዉሳኔ ያገኘ ስለሆነ ተዘግቷል። ይመለስ።
የማይነበብ አምስት ዳኞች ፊርማ አለበት።
No topics extracted.