135፣ 185፣196፣ 117 94.88 123-131 እና 186-149 33. በወንጀል የተከሰሰ ሰው የግል ተበዳይን በመከላከያ ምስክርነት ያቀረበና የግል ተበዳይም ድርጊቱ ያለመፈፀሙን በመግለጽ የምስክርነት ቃል የሰጠ ከሆነ ዓ/ህግ የግል ተበዳይ የምስክርነት ቃል በድለላ ወይም በጥቅም የተገኘ መሆኑን ለማረጋገጥ እስካልቻለ ድረስ ተከሳሽ ክሱን አላስተባበለም ላባል የማይገባ ስለመሆኑ፡የወ/መ/ሥ/ሥ/ህግ/ ቁጥር 149 (2)
No summary available.
መስከረም 25 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- ብርሃኑ አመነዉ በዕዉቀት በላይ እንዳሻዉ አዳነ ሃይሉ ነጋሽ እትመት አሰፋ አመልካች፡- አበራ ዋቅጅራ ተጠሪ፡- የቤ/ጉ/ክልል ፍትህ ቢሮ መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል ።
በዚህ መዝገብ የቀረበዉ ጉዳይ የወንጀል ክርክር የሚመለከት ነዉ ።ተጠሪ አመልካች ላይ ያቀረበዉ ክስ ይዘት የወንጀል ህግ አንቀጽ 27/1 እና 539/1/ሀ ተላልፎ በ09/02/07 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ላይ በወንበራ ወረዳ ገሳንገሳ ቀበል አቶ ፍቃዱ አድማሱ መጠጥ ቤት ዉስጥ ምንም ምክንያት ሳይኖረዉ ከተቀመጠበት ተነስቶ የግል ተበዳይ አቶ በየነ ቡባ መቀመጫዉ ላይ በካራ ሁለት ጊዜ የወጋዉ ስለሆነ ከባድ የግድያ ሙከራ ወንጀል ፈጽሟል የሚል ሲሆን አመልካች ክዶ በመከራከሩ የመተከል ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የግራቀኝ ማስረጃ ከመረመረ በኋላ አመልካች የዓቃቤ ህግ ማስረጃ ማስተባበል አልቻለም በማለት በተከሰሰበት አንቀጽ ጥፋተኛነትና 16 ዓመት ከ6ወር ጽኑ እስራት ቅጣት ወስኖበታል አመልካች በዚህ ዉሳኔ ቅር ተሰኝቶ ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ በማቅረቡ ፍ/ቤቱም አከራክሮ ድርጊቱ የተፈጸመዉ በመጠጥ ቤት በተነሳ ድንገተኛ ፀብ መሆኑ በማስረጃ መረጋገጡን መሰረት በማድረግ አንቀጹን ወደ 27/1/ እና 540 በመለወጥ ቅጣቱንም ወደ 10 ዓመት ጽኑ እስራት አሻሽሎ ፍርድ ሰጥቷል ።
አመልካች ለክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ያቀረበ ቢሆንም ተቀባይነት አላገኘም ።
ለዚህ ሰበር ችሎት አቤቱታ የቀረበዉ በዚህ ላይ ሲሆን የሰበር አቤቱታዉ ተመርምሮ የግል ተበዳይ ላይ ደረሰ ከተባለዉ ጉዳት አንጻር አመልካች በወ/ህግ አንቀጽ 27/1/እና 540 ስር ጥፋተኛ መባሉ ተገቢ መሆን አለመሆኑን ለመመርመር እንዲቻል ተጠሪ መልስ እንዲሰጥ ተደርጓል ።ለተጠሪ የፍ/ቤት መጥሪያ በፖስታ ቤት በኩል የተላከለት ቢሆንም መልስ አልሰጠም ። የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ ባጭሩ የተገለጸ ሲሆን እኛም ለሰበር ያስቀርባል ከተባለበት ጭብጥ አኳያ ከህጉ ጋር በማገናዘብ መርምረናል ።
ከመዝገቡ መርምረን እንደተገነዘብነዉ ድርጊቱ የተፈጸመዉ በመጠጥ ቤት በተነሳ ድንገተኛ ፀብ ሲሆን ዐቃቤህግ አመልካች በካራ የተበዳይ መቀመጫ ላይ ሁለት ቦታ ወግቶታል ሲል አመልካች ደግሞ በፀቡ ምክንያት ተያይዘዉ ሲወድቁ ተበዳይ አረቄ መጠጫ መለኪያ ሲባሪ ላይ ወድቆ የተወጋ እንጂ አመልካች ስለት ነገር በእጁ እንዳልነበር በመከላከያ ምስክር አስረድቻለሁ በማለት ቢከራከርም የስር ፍ/ቤቶች አልተቀበሉም ስለሆነም አመልካች የግል ተበዳይን በስለት ነገር መቀመጫዉ ላይ ሁለት ጊዜ ወግቶ ጉዳት ማድረሱ ማስረጃ የመመርመርና ፍሬነገር የማጣራት ስልጣን በህግ የተሰጣቸዉ የስር ፍ/ቤቶች አረጋግጠዋል ።በዚህ ችሎት እልባት የሚሻዉ ነጥብ የአመልካች ድርጊት የወ/ህጉን አንቀጽ 540 ያቋቁማል መባሉ ተገቢ መሆን አለመሆኑ ላይ ነዉ ።
በወ/ህግ አንቀጽ 540 ስር አንድ ሰዉ ተራ የሆነ የሰዉ ግድያ ፈጽሟል ተብሎ የሚቀጣዉ የድርጊቱ አፈጻጸም በወ/ህጉ አንቀጽ 539 ወይም 541 ስር የተመለከተዉን ፍሬነገር የማያሟላ ሆኖ ሲገኝ ነዉ ። ስለዚህም የተፈጸመዉ ድርጊት የወ/ህጉን አንቀጽ 539 ሳይሆን 540 ያቋቁማል በማለት ይግባኝ ሰሚዉ ፍርድ ቤት የደረሰበት ድምዳሜ ተገቢነት ላመረመር የቀረበ ነዉ ።ድርጊቱ የተፈጸመዉ ሰዉን መግደል ሀሳብ ኖሮት ነገር ግን ዉጤት ሳያገኝ ቢቀርም በመደቡ ጥፋተኛ ተብሎ እንደሚቀጣ የወ/ህጉ አንቀጽ 27/1/እና/3/ ድንጋጌ ይዘት ያስገነዝባል ።በተያዘዉ ጉዳይ አመልካች የፈጸመዉ ድርጊት ተበዳይን መግደል ሀሳብ ኖሮት በሙከራ የቀረ ነዉን የሚለዉን ስንመረምር የግል ተበዳይ የተወጋዉ መቀመጫዉ ላይ መሆኑና የጉዳቱ መጠንም 2 በ2 ሳ.ሜ እና 2 በ5ሳ.ሜ እንደሆነ በማስረጃ በስር ፍ/ቤት ተረጋግጧል ።
በመሰረቱ የወንጀል አድራጊዉ የሀሳብ ክፍል የሚታወቀዉ ከወንጀሉ አፈጻጸም ጠቅላላ ሁኔታዎች እንደሆነ ልብ ይለዋል ።አመልካች ስለት ነገር ተጠቅሟል እስከተባለ ድረስ የግል ተበዳይን መግደል አስቦ ቢሆን ኖሮ ስስ ብልቶቹ ላይ እንዳይወጋዉ ያላስቻለዉ ነገር ስለመኖሩ አልተረጋገጠም ። አመልካች በመጠጥ ቤት በተነሳ ፀብ መነሻ ከግል ተበዳይ ጋር ተያይዘዉ በወደቁበት ሁኔታ የግል ተበዳይ መቀመጫ ላይ መዉጋቱና የደረሰዉም የአካል ጉዳት መሆኑ ሲታይ አመልካች ተበዳይን የመግደል ሀሳብ ነበረዉ የሚለዉን የሀሳብ ክፍል ግምት ወይም ድምዳሜ ለመድረስ የሚያስችል ሆኖ አላገኘንም ።ይልቁንም አመልካች ሆነ ብሎ ስለት ነገር ተጠቀሞ የግል ተበዳይ ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ያደረሰ ስለመሆኑ የተረጋገጠ ፍሬነገር በመሆኑ በወ/ህጉ አንቀጽ 555/1/ የሚያሟላ ድርጊት ሆኖ አግኝተናል ። በዚህ አግባብ የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት በአንቀጽ 27/1/እና 540 ስር ያሰተላለፈዉን የጥፋተኛነት ዉሳኔ በወ/መ/ህ/ስ/ስ/ቁ 113/2/ መሰረት ለዉጠን አመልካች የግል ተበዳይ ላይ ላደረሰዉ ከባድ አካል ጉዳት በወ/ህጉ አንቀጽ 555/1/ስር ጥፋተኛ ነዉ ብለናል ።ቅጣትን በተመለከተ አመልካች ጥፋተኛ የተባለበት ደንጋጌ በፍድራል ጠ/ፍ/ቤት በወጣዉ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁ /2/2006 ደረጃና እርከን የወጣለት ስለሆነ በዚሁ መሰረት በድርጊቱ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱ ስለተረጋገጠ ደረጃ1 እርከን 16 ላይ ይመደባል ። በስር ፍ/ቤት የተረጋገጠ ቅጣት ማክበጃ ምክንያት ስለመኖሩ በፍርዱ አልተመለከተም ። በአመልካች በኩል ተቀባይነት ያገኘዉ 4 የቅጣት ማቅለያ ምክንያት ስለመኖሩ በስር ፍ/ቤት ዉሳኔ ተገልጸዋል። በዚህ ምክንያት 4 እርከን ሲቀነስ እርከን 12 ላይ ያርፋል ። እርከን 12 ላይ የተመለከተዉ የእስራት ቅጣት ፈቅደ ስልጣን ከ2 አመት እስከ 2 ዓመት ከ6ወር ሲሆን አመልካች በዚህ ጉዳይ ከዚህ ቀደም የታሰረዉ ታሳቢ ተደርጎ የእርከኑ ጣሪያ 2 አመት ከ6ወር እስራት እንዲቀጣ ፈርደናል ። በዚሁ መሰረት ተከታዩ ተወስኗል ።
1ኛ/ የቤ/ጉ/ክ/መ/ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/06525 በ22/10/07 ዓ.ም የሰጠዉ የጥፋተኛነትና የቅጣት ዉሳኔ እንዲሁም የክልሉ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ/06674 በ19/02/08 ዓ.ም የሰጠዉ ትዕዛዝ በወ/መ/ህ/ስ/ስ/ቁ 195/2/ለ/2 መሰረት ተሻሽሎ ተወስኗል ።
2ኛ/ አመልካች ለፈጸመዉ ድርጊት በወ/ህግ አንቀጽ 555/1/ስር ጥፋተኛ ነዉ ብለናል።ቅጣቱም በዚህ ጉዳይ የታሰረዉ ታስቦለት በሁለት አመት ከስድስት ወር /2፡6/ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስነናል ።
3ኛ/ መተከል ዞን ማረሚያ ቤት በዚህ ፍ/ቤት ተሻሽሎ በተወሰነዉ መሰረት እንዲያስፈጽም ዉሳኔ ግልባጭ ይተላለፍለት ብለናል ። ለአመልካቹም ዉሳኔ ግልባጭ በማ/ቤት በኩል ይድረሰዉ ።ይጻፍ ።
No topics extracted.