No summary available.
መስከረም 24 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- ብርሃኑ አመነው በዕውቀት በላይ እንዳሻው አዳነ ሃይሉ ነጋሽ እትመት አሰፋ አመልካች፡- የፍደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ - ሙሉተስፋ ከበደ ተጠሪ፡- እዮኤል ተስፋዬ የሺጥላ - አልቀረቡም መዝገቡ የተቀጠረው መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ነው። በመሆኑም መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ይህ የሰበር አቤቱታ ላቀርብ የቻለው አመልካች የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ በቀን 22/02/09 የሰጠውን ውሳኔ የፍደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ በቀን 13/06/2009 ዓ.ም በማጽናቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመ በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለታቸው ነው።
ጉዳዩ በዐቃቤ ህግ አማካኝነት የቀረበን ክስ ስለማንሳትና ከክርክር ውጭ ስለመሆን የሚመለከት ነው። አመልካች በስር ፍ/ቤት በተጠሪ ላይ ሁለት የወንጀል ክስ ያቀረበ ሲሆን ይኸውም የወንጀል ህግ ቁጥር 559/2/ እና 575 /2/ /ሀ/ የተመለከተውን ተላልፎ በዋናው መንገድ ለሚጓዝ ተሽከርካሪ ቅድሚያ በመከልከልና ያለጥንቃቄ ሲያሽከረክር የሰልዳ ቁጥር ኮድ 4-06155 ኢ.ት የሆነ መኪና የኋላ ግራ ጐን የገጨና አቅጣጫ እንዲስትና ከድንጋይ ጋር ተጋጭቶ በውስጡ የነበሩት የግል ተበዳይ አብነት ጐሹ በመኪናው አካል ተመትቶ የአንገት የቀኝ እግር እና የአካል ጡንቻዎች ላይ የህመም ስሜት እንዲሰማ ያደረገ እና እርዳታ ሳያደርግ በልላ መኪና ገብቶ ያመለጠ በመሆኑ በቸልተኝነት ቀላል የአካል ጉዳት ያደረሰና በአደጋ ላይ የሚገኝ ሰውን አለመርዳት ወንጀል ፈጽሟል የሚል ነው።
ተጠሪ የቀረበው ክስ ደርሶት እምነት ክህደት ቃል ሲጠየቅ ከግል ተበዳይ ጋር የታረቀ መሆኑን የገለፀ ሲሆን ፍ/ቤቱም ይህንኑ ገልጾ በተጠሪ ላይ የቀረበው ክስ በወንጀል ህግ ሥ/ሥርዓት ቁ 151/2/ መሰረት መዝገቡን ዘግቷል። አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ያቀረቡትን ይግባኝ የተመለከተው የፍደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤትም ይግባኙን ሳይቀበል መዝገቡን ዘግቶቷል። የአመልካች የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ በመቃወም ሲሆን ይዘቱም በተጠሪ ላይ የቀረበው የወንጀል ህግ አንቀጽ 575/2/ /ሀ/ በወንጀል ህግ 212 መሰረት በግል አቤቱታ የማይቀርብና በወንጀል ህግ ሥነ-ሥርዓት ቁጥር 151/2/ መሰረት በእርቅ ላነሳ የማይችል በመሆኑ ፍ/ቤቱ ክሱን ያቋረጠው መሰረታዊ የህግ ስህተት ስለሆነ ይታረምልኝ የሚል ነው።
የአመልካች አቤቱታ ተመርምሮ የወንጀል ህግ አንቀጽ 575/2/ /ሀ/ የቀረበ ክስ በወንጀል ህግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 151/2/ መሰረት በእርቅ በመጨረስ የሚቋረጥ መሆኑን ለመመርመር ተጠሪ ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ታዞ በሰጠው መልሱ በወቅቱ እኔም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኝ እራሴን ለማዳን ወደ ህክምና ተቋም ሄጃለሁ ሆነ ብዬ ሰውን ላለመርዳት አልሄድኩም ብሎ ክሱን በመካድ የተከራከረ ሲሆን ተጠሪም ዕርቁን የማይቃወም መሆኑን እና የሚያቀርቡት ማስረጃ እንደልለ በመግለጽ ፍ/ቤቱ ክሱን አቋርጧል እንጂ የግል አቤቱታ ነው በማለት አይደለም፤ በመሆኑም የስር ፍ/ቤት ውሳኔ ይጽናልኝ ብሐል። አመልካች በሰጠው የመልስ መልስም ሁለቱም ክሱ የተቋረጠው በእርቅ እንጂ አመልካች ማስረጃ ባለማቅረቡ ወይም እንደክሱ ባለማስረዳቱ አይደለም የወንጀል ህግ አንቀጽ 559/3/ የተመለከተውን ተቃውሞ አላነሳንም እንጂ በሁለተኛው ክስ ላይ ተቃውሞ ገልፀናል፡ ስለሆነም ፍ/ቤቱ ክሱን ማቋረጡ ተገቢ አይደለም በማለት የመልስ መልስ ሰጥተዋል፡ የክርክሩ አመጣጥ ከላይ የተመለከተው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔና አግባብነት ካላቸው የህጉ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ በሚከተለው መልኩ መርምረነዋል። እንደመረመርነው በግል አቤቱታ የሚቀርቡ ክሶችንና የሚቀርቡበትን አግባብ የሚመለከት በመሆኑ የአመልካች አቤቱታ ተመርምሮ በዚህ ችሎት እንዲታይ ከቀረበው ጭብጥ አንጻር የወንጀል ህግ አንቀጽ 575/2/ሀ/ በወንጀል ህግ ሥርዓት ቁጥር 151/2/ መሰረት ከተበዳዩ ጋር በዕርቅ በመጨረስ ክሱ የሚቋረጥ ስለመሆኑ አለመሆኑ ምላሽ የሚሰጥ ጭብጥ ሆኖ አግኝተነዋል።
የወንጀል ህግ ግብ ስለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የሀገሪቱን መንግስት የህዝቦችን የነዋሪዎቹን ሰላም ደህንነት ሥርዓት መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ነው።
መንግስት በህዝብ ስም ሆኖ ለዜጐች ተወክሎ የወንጀል ጉዳይን እንዲከታተልና ከሶ እንዲያስቀጣ ኃላፊነት ላወድቅበት የቻለውም በዚሁ ምክንያት ነው። ሆኖም የጠቅላላውን ህዝብ ሰላምና ፀጥታ የሚያደፈርሱ ከተጐጂው ሰው ጥቅም በላይ አልፈው የልሎችን ጥቅም የማይነኩ አሉ። በእርግጥ በጠቅላላው ተበዳይ ቢስማማም ባይስማማም የወንጀል ክስን መከታተል የመንግስት ኃላፊነት ቢሆንም በእነደዚህ ባሉ ነገሮች የተጐዳው ሰው ጉዳዩን ክሶ በፍርድ እንዲታይለት ፈቃደኛ መሆኑ በእርግጥ ካላሳየ በቀር መንግስት ይህንን ግዳጁን አያከናውንም።
የወንጀል ህጉ ክስ በቀረበ ጊዜ ብቻ የሚያስቀጡ ወንጀሎች የሚገልጽ የተጠናቀቀ ዝርዝር አይገልጽም ።የወንጀል ህግ አንቀጽ 212 ቢሆንም በጠቅላላው መልክ ነው በወንጀል ህጉ ልዩ ክፍል ውስጥም የሚገኙ ድንጋጌዎች “ማናቸውም … የግል አቤቱታ በቀረበ ጊዜ …. ይቀጣል” ሲል ያዛሉ። እነዚህን አንቀጾች በመተላለፍ ወንጀል በተፈፀመ ጊዜ በግል አቤቱታ እንዲያቀርብ ከተፈቀደለት ሰው በቀር በልላ በማንም ሰው የክስ ጉዳይ ላንቀሳቀስ አይችልም። የግል ከሳሹ የክሱን ማመልከቻ ካዘጋጀ በኋላ የክሱ ጉዳይ በወ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 150-153 በተገለፀው መሰረት ይመራል።
በያዝነው ጉዳይ በአመልካች በስር ፍርድ ቤት የቀረቡት ክሶች 1ኛ የወንጀል ህግ አንቀጽ 559/2/ እና 2ኛ የወንጀል ህግ አንቀጽ 575/2/ /ሀ/ በግል ተበዳይ ወይም ሕጋዊ ወኪሉ አማኻኝነት የሚቀርቡ ወይም እንዲቀርቡ የታዘዙ ክሶች አይደሉም። ክሱም በስር ፍርድ ቤት የቀረበው በአመልካች /በመንግስት/ በዐቃቤ ህግ ነው። ክሱን የሚመራው በወ/ህ/ሥ/ሥ /ቁ 132-135 ፣ 185፣196፣117፣ 94-98፣ 123-131 እና 136-149 በተመለከቱት መሰረት ይሆናል።
ስለሆነም የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአመልካች የቀረበውን የወንጀል ክስ የግል ተበዳይ ክሱን ትቷል በማለት በወ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ 151/3/ መሰረት በግል አቤት ባይ የቀረበ ክስ በሚመራበት ሥነ ሥርዓት የወንጀል ክሱን ያቋረጠው የወንጀል ህግን ግብ እና በዓቃቤ ህግ ስለሚቀርቡ የወንጀል ክስ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ክስ አመራር ያልተከተለ በመሆኑ እና የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤትም ይህንን ሳያርም ማጽናቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነው። በመሆኑም ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
1/ የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ በቀን 22/02/09 የሰጠው ውሳኔ እና የፍደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ/ በቀን 13/06/2009 ዓ.ም የሰጠው ትእዛዝ በወ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ 195/2/ /ሀ/ መሰረት ተሽሯል።
2/ የፍደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በአመልካች የቀረበውን ክስ ተጠሪን አስቀርቦ የወንጀል ክሱን በመስማት ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥ በወ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 195/2/ /መ/ መሰረት መልሰን ልከንለታል።
No topics extracted.