የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር እና የመከላከያ ሰራዊት ፋውንድሽን የተለያየ ህጋዊ ሰውነት ያላቸው ስለመሆኑና የሰራዊት አባላት በፋውንድሽኑ ንብረት ላይ የሚፈጽሟቸው ማንኛውም ወንጀሎች በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ላይ እንደተፈጸሙ ተደርጎ የማይቆጠሩ ስለመሆናቸው፡የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት በመከላከያ ሰራዊት ፋውንድሽን ንብረት ላይ የሚፈጽማቸው ወንጀሎችን የማየት ስልጣን የመደበኛ ፍ/ቤቶች ሆኖ የፍ/ከ/ፍ/ቤትም ጉዳዩን የማስተናገድ የመጀመሪያ ደረጃ የፍርድ ስልጣን የሚኖረው ስለመሆኑ፡የአዋጅ ቁጥር. 434/1997 አንቀጽ 7/1/ እና የአዋጅ ቁጥር. XVII 809/2006 አንቀጽ 28 እና 38 ደንብ ቁ. 179/2002
No summary available.
መስከረም 25 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡ ብርሃኑ አመነው በዕውቀት በላይ እንዳሻው አዳነ ሃይሉ ነጋሽ እትመት አሰፋ አመልካች፡- ሻለቃ አለማየሁ ወንጀሎ ለኰ - ጠበቃ አይረሳም ሸንቁጤ ተጠሪ፡- የፍደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ - አልቀረቡም መዝገቡ የተቀጠረው መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ነው። በመሆኑም መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
ይህ የሰበር አቤቱታ ላቀርብ የቻለው አመልካች የፍደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ጥር 18 ቀን 2008 ዓ.ም በአብላጫ ድምጽ የሰጠውን ብይን የፍደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመ/ በቀን 22/02/2009 ዓ.ም በመሻሩ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት በመሆኑ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለታቸው ነው።
ጉዳዩ የዳኝነት ሥልጣን የሚመለከት ነው፡ ተጠሪ በስር ፍርድ ቤት አመልካች ላይ ባቀረበው ክስ አመልካች የወንጀል ህግ አንቀጽ 676/1/ የተመለከተውን በመተላለፍ በኢ.ፍ.ድ.ሪ የሀገር መከላከያ ሚ/ር የመከላከያ ሰራዊት ፋውንድሽን ውስጥ ከግንቦት 8 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ በአልባሳት ዋና ግምጃ ቤት ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለልላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ በሥራው ምክንያት ከመስሪያ ቤቱ ከተረከባቸው የ15 ዓመት የሽልማት ሜዳላያዎች ውስጥ የሰኔ ወር ግምጃ ቤት ቆጠራ ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም ሲካሄድ 300 ሜዳላያ የአንዱ ዋጋ ብር 2425.49 ጠቅላላ ለራሱ ያደረገ/ የወሰደ/ ያስወሰደ/ የሰወረ በመሆኑ ከባድ እምነት ማጉደል ወንጀል ፈጽሟል የሚል ነው።
አመልካች በተጠሪ የቀረበው ክስ ከደረሰው በኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን አይቶ ለመወሰን ሥልጣን የለውም ፤አመልካች የኢፍ.ዲ.ሪ የመከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ሰራዊት አባል ነኝ በአዋጅ 809/2006 አንቀጽ 38/1//ለ/ መሰረት በሰራዊቱ አባላት መካከል የሚፈፀም የግድያ የድብደባ ወንጀል ወይም የሰራዊቱ አባላት በሚንስትሩ ንብረት ላይ በሚፈጽሟቸው ማናቸውም ወንጀሎች የማየት ሥልጣን የቀዳሚ ወታደራዊ ፍ/ቤት ነው፣ ይህ ከታለፈም ጉድለቱ የተከሰተው ተቀጥሬ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ወስጥ በተደረገ ቆጠራ ነው፤ ምስክሮች ልላ ተጠርጣሪ እንዳለ እያስረዱ ነበር ስለሆነም የሙያ ሥራን በአግባቡ አለመምራት ነው ክሱ ላቀርብብኝ የሚገባው ። የሚል ነው።
ተጠሪ በመቃሚያው ላይ በሰጠው መልስ አመልካች የተከሰሰበት ወንጀል በቀጥታ ከውትድርና ሥራቸው ጋር የሚገናኝ ሳይሆን የህዝብና የመንግስት ንብረት አጉድሐል ተብሎ ነው ይህ የሙስና ወንጀል ነው። ስለሆነም ጉዳዩ በልላ ፍርድ ቤት ላታይ የሚችል አይደለም። ልላ ተጠርጣሪ እያለ የቀረበ ነው የተባለው ወደፊት የሚነሳ እንጂ መቃወሚያ የሚሆን አይደለም ብሐል።
ፍርድ ቤቱም መርምሮ በአዋጅ 809/2006 አንቀጽ 38/1//ለ/ በተመለከተው መሰረት የሰራዊቱ አባላት በሚኒስቴሩ ንብረቶች ላይ በሚፈጽሟቸው ማናቸውም ወንጀሎችን ስለሚል እና ከሙስና ወንጀሎች በቀር የሚል ሀረግ ስለልለ፣ የኢ.ፍ.ድ.ሪ የሀገር መከላከያ ሚ/ር የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ከወንጀል ህግ በኋላ የወጣና በቀዳሚነት ተፈጸሚነት ያለው በመሆኑ እና ልዩ ህግ በህጉ ተፈጻሚነት ያለው በመሆኑ፣ እና አመልካች የመከላከያ ሰራዊት አባል ከመሆኑም ባሻገር ፋውንድሽኑ ራሱን በቻለ ደንብ የተቋቋመ ቢሆንም ሰራተኞቹ ወታደሮች መሆናቸው ዓላማውም የሀገር መከላከያ ሚ/ር የመከላከያ ሰራዊት ሥራ በተቀላጠፈ ማስተናገድ ተጠሪነቱም ንብረቱም /ኒሻኑም/ የመከላከያ ሚ/ር በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ሥልጣን የለውም በማለት በአብላጫ ድምጽ ወስኗል። አነስተኛው ድምጽ ፍ/ቤቱ ሥልጣን አለው ብሐል።
ተጠሪ በዚህ ብይን ቅር በመሰኘት ያቀረበውን ይግባኝ የተመለከተው የፍደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የመከላከያ ሰራዊት ፋውንድሽን ራሱን የቻለ ተቋም ነው አይደለም የሚለው በቅድሚያ መርምሮ በደንብ ቁጥር 179/2002 አንቀጽ 2/3/ መሰረት በህጉ የሰውነት አካል የተሰጠው ራሱን የቻለ ተቋም መሆኑን በአንቀጽ 8 እና ተከታዮቹ በቦርድ የሚተዳደር አባላቱን ከሰራዊቱ አባላት በተጨማሪ ልሎች ሰዎችን የሚያሳትፍ ራሱን የቻለ በራሱ በጀት የሚተዳደር ተቋም እና በራሱ መክሰስና መከሰስ የሚችል ነው፣ ተጠሪነቱ ለመከላከያ ሚኒስቴር ይሁን እንጂ በሚንስቴር በጀት የሚተዳደር ባለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 809/2006 አንቀጽ 38/1/ለቀደሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ሳይሆን በመደበኛ ፍርድ ቤት የሚታይ ነው በማለት የስር ፍርድ ቤትን ብይን ሽሯል።
አመልካች በዚህ ፍርድ ቅር በመሰኘት መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በማለት ያቀረበው የሰበር አቤቱታ በአዋጅ ቁጥር 809/2006 አንቀጽ 38/1//ለ/ መሰረት ጉዳዩን የማየት ሥልጣን የቀዳሚ ወታደራዊ ፍ/ቤት ነው፤ አመልካች በመከላከያ ሰራዊት ፋውንድሽን አገልግሎት የምሰጠው በሰራዊት አባልነት በመመደብ በመሆኑ የተቋሙን ህጋዊ ሰውነት እና የአመልካችን ልዩ መብት ያላገናዘበ ስለሆነ መሰረታዊ ስህተት የተፈፀመበት ነው፤ የሚል ሲሆን አመልካች ያቀረበው አቤቱታ ተመርምሮ የስር ፍርድ ቤት አመልካች በአዋጅ ቁጥር 809/2006 አንቀጽ 38/1//ለ/ ጉዳዩን የማየት ሥልጣን ያለው ቀዳሚ ወታደራዊ ፍ/ቤት ነው በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ ውድቅ ያደረገበትን አግባብነት ከደንብ ቁጥር 179/2002 አንቀጽ 3፣6፣7፣13/ለ/ ጋር ለማገናዘብ ተጠሪ መልስ እንዲያቀርብ ታዞ በሰጠው መልሱ አመልካች ተቀጥረው የሚሰሩት በመከላከያ ፋውንድሽን ሲሆን ይህም ራሱን ችሎ የተቋቋመ የህግ ሰውነት ያለው ተቋም ነው፤
ሰራተኞችም የፋውንድሽኑ አንጂ የመከላከያ ሚኒስቴር አይደለም፣ ወታደራዊ ፍ/ቤቶች የተቋቋሙት ወታራዊ ይዘት ያላቸው ነው ፡ አመልካች የፈፀሙት ሲቪል ጉዳይ ነው ስለሆነም ጉዳዩ ወታራዊ ይዘት ያለው ባለመሆኑ ስልጣኑ የመደበኛ ፍርድ ቤት ነው ብሐል። አልካችም የመልስ መልስ አቅርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተመለከተው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ የሆነውን ውሳኔ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ሲቀርብ ከተያዘወ ጭብጥ አንጻር በሚከተለው መልኩ መርምረነዋል።
የክርክሩ ሂደት የሚያስገነዝበው አመልካች የመከላከያ ሰራዊት አባል እና የመከላከያ ሰራዊት ፋውንድሽን የአልባሳት ዋና ግምጃ ቤት ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ በነበረበት ወቅት በሥራው ምክንያት ፈጽሞታል ተብሎ የቀረበበትን የከባድ የእምነት ማጉደል ሙስና ወንጀል ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤት የመዳኘነት ሥልጣን መኖር አለመኖርን የሚመለከት ነው።
በኢ.ፍ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 79 የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው የሚለውን በዚሁ ህገ መንግስት አንቀጽ 37 የፍርድ ቤቶችን የዳኝነት ሥልጣን ወሰን ከሚያመለክተው ጋር አገናዝበን ማየት እንደሚቻለው ማንኛውም ጉዳይ ያለ ገደብ በመደበኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ላታይ የማይችል መሆኑን ነው። በህገ-መንግሥቱ አንቀጽ 37 የተቀመጠው የሥልጣን ክፍፍል ወሰን እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም ጉዳይ በፍርድ ላያልቅ የሚችል እና ጉዳዩንም አይቶ ለመወሰን ከመደበኛ ፍርድ ቤት ውጭ ለልላ የዳኝነት ሰጪ አካል ያልተሰጠ መሆኑ ከተረጋገጠ ይህንኑ በፍርዱ ላያልቅ የሚችለውን ጉዳይ ለማየትና ለመወሰን ብቸኛ ሥልጣን ያላቸው መደበኛ ፍርድ ቤቶች መሆናቸውን ነው። ስለሆነም መደበኛ ፍርድ ቤቶች የቀረበላቸው ጉዳይ በፍርድ ላያልቅ የሚችል መሆኑ ላይ ብቻ ሳይወሰኑ በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 37 መሰረት ይኸው ጉዳይ ከመደበኛ ፍርድ ቤት ውጭ ለልላ በህግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል ቀርቦ የሚታይ መሆን አለመሆኑን በቀጥታ የመመርመር ግድታ አለባቸው።
አሁን በያዝነው ጉዳይ ክሱ በመደበኛነት የቀረበለት የፍደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአመልካች በወ/ህ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ130/2/ መሰረት በቀረበለት የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያ ይህንን ጉዳይ አይቶ ለመወሰን በአዋጅ ቁጥር 809/2006 አንቀጽ 38/1/ለ/ መሰረት ለቀዳሚ ወታራዊ ፍርድ ቤት የተሰጠ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን አይቶ ለመወሰን ሥልጣን የለውም የሚል መቅረቡን እና በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶች የተለያየ ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ነው። ስለሆነም በአመልካች ላይ በስር ፍርድ ቤት የቀረበው ክስ በአዋጅ ቁጥር 809/2006 አንቀጽ 38/1/ለ/ መሰረት ተሰጥቷል አልተሰጠም የሚለውን መርምረናል፣ የአዋጁ አንቀጽ 38 የቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ሥልጣንን የሚዘረዝር ሲሆን በንዑስ አንቀጽ 1/ለ/ በሰራዊቱ አባላት መካከል በሚፈፀም የግድያ ወይም የድብደባ ወንጀል ወይም የሰራዊቱ አባላት በሚኒስቴሩ ንብረት ላይ በሚፈጽማቸው ማናቸውም ወንጀሎች የዳኝነት ሥልጣን ያለው መሆኑን ይደነግጋል በዚሁ ድንጋጌ መሰረት በስር ፍ/ቤት የክርክርም ምክንያት የሆነው የሰራዊቱ አባላት በሚኒስትር ንብረት ላይ የሚፈጽሟቸው ማናቸውም ወንጀሎች የሚለውን መሰረት በማድረግ ነው።
አመልካች የመከላከያ ሰራዊት አባል ሲሆን የእምነት ማጉደል ወንጀል ፈጽሞበታል የተባለው በመከላከያ ሰራዊት ፋውንድሽን በመሆኑ በመከላከያ ሚኒስቴር ንብረት ላይ ተፈጽሟል ለማለት የሁለቱን አካላት አንድነትና ልዩነት ካቋቋማቸው ድንጋጌዎች ተመልክተናል።
የኢ.ፍ.ድ.ሪ አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁ.316/2008 አንቀጽ 9/1/ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የተቋቋመ እና ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የሆነ የመንግስት አስፈጻሚ አካል ሲሆን በአዋጅ ቁጥር 809/2006 አንቀጽ 38/1//ለ/ላይ … በሚኒስቴሩ ንብረት ላይ በሚፈፀሙ ማናቸውም ወንጀል ሲል በዚህ የሀገር መከላከያ ሚኒስትር ንብረት ላይ የሚፈፀም ማናቸውም ወንጀሎችን ነው። በልላ በኩል የመከላከያ ሰራዊት ፋውንድሽን በመንግስት በጀት ላሟሉ የማይችሉት የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ፍላጐት የሚያረኩና የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽሉ አገልግሎቶች በማቅረብ የተለያዩ ድጋፎችን የማድረግ ዓላማ ይዞ በደንብ ቁጥር 179/2002 የተቋቋመ የህግ ሰውነት ያለው አካል ነው። ከዓላማው አንጻር ተጠሪነቱ ለሀገር መከላከያ የሚኒስቴር መሆኑ፣ በአባልነትም ከተሰናበቱ የሰራዊቱ አባላትና ልሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መኖር ፋውንድሽኑን ንብረት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሚኒስቴሩ ንብረት ላይ የተፈጸመ አያደርገውም። ይህም የሚያስገነዝበው የተለያዩ ህጋዊ ሰውነት ያላቸው አካላት መሆናቸው ነው። ስለሆነም የሰራዊቱ አባላት በፋውንድሽኑ ንብረት ላይ የሚፈጽማቸው ማናቸውም ወንጀሎች በሚኒስቴር ላይ እንደተፈፀመ ወንጀሎች የሚገመቱ አለመሆናቸውን ነው።
በልላ በኩልም ወታደራዊ የፍትህ አካላት በአዋጅ ቁጥር 809/2006 አንቀጽ 28 መቋቋም መሰረታዊ ዓላማ ከሥራው ልዩ ባህሪ አንጻር ወታደራዊ የሆነ የወንጀል ድርጊቶችን በተለይም በቁጥር 38 የተመለከቱትን የመከላከል ፤የመመርመር ፤የመክሰስ፤
ውሳኔ የመስጠትና የማስፈፀም ነው። ስለሆነም በአመልካች ላይ በስር ፍርድ ቤት የቀረበው ክስ የሰራዊቱ አባል በሚኒስትሩ ንብረት ላይ የተፈፀመ ተብሎ የሚወሰዱ አይደለም። ጉዳዩ የቀረበለት የፍደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደግሞ ድርጊቱ ተፈጽሟል በተባለበት ጊዜ በሥራ ላይ በነበረው የተሻሻለው የፀረ-ሙስና የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ህግ አዋጅ ቁጥር 434/1997 አንቀጽ 7/1/ መሰረት ጉዳዩን የማየት የመጀመሪያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን አለው።
በአጠቃላይ የፍደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በስር ፍ/ቤት በአመልካች ላይ ተጠሪ ያቀረበውን ከባድ እምነት ማጉደል ወንጀል ክስ የማየት የዳኝነት ሥልጣን የፍደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው በማለት የስር ፍ/ቤት በአብላጫ ድምጽ የሰጠውን ውሳኔ በመሻር የሰጠው ፍርድ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ባለመሆኑ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥተናል።
1/ የፍደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ ጥር 18 ቀን 2008 ዓ.ም በአብላጫ ድምጽ የሰጠውን ብይን በመሻር የፍደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ/ በቀን 22/02/2009 ዓ.ም የሰው ፍርድ በወ/ህ/ሥ/ሥ/ቁ 195/2/ /ለ/ /2/ መሰረት ፀንቷል።