በይግባኝ ፍ/ቤቶች አንድ ማስረጃ እንዲቀርብ በማድረግ ውሳኔ ለመስጠት የሚችሉ ቢሆንም የሚሰጠው ውሳኔ የግራ ቀኙን ተከራካሪዎች የይግባኝ መብት የሚያጣብብ ሆኖ ሲገኝ የቀረበው ማስረጃ ተገቢ በሆነ ምክንያት አቶ ተስፋዬ በቀለ እና የፍ/ዐ/ህግ XVI እንዲጣራ እና ውሳኔ እንዲሰጥ ጉዳዩን ወደ ስር ፍ/ቤት ለመመለስ የሚችሉ ስለመሆኑ፣ የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 143 እና 195/2/ለ//2/
No summary available.
መስከረም 23 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡ ብርሃኑ አመነው በዕውቀት በላይ እንዳሻው አዳነ ሃይሉ ነጋሽ እትመት አሰፋ አመልካች፡- አቶ ተስፋዬ በቀለ -ቀረቡ ተጠሪ፡- የፍድራል ዓቃቤሕግ- ቀረቡ መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል።
የአሁን ተጠሪ አመልካች የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 32/1/ሀ እና 676/1 በመተላለፍ በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ማሕበር ሥብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ደብረመድሐኒት መድሐኔዓለም ቤተክርስትያን ሒሳብ ሹም ሆኖ ሲሰራ ከመጋቢት 2004 ዓ.ም እስከ ሕዳር 2005 ዓ.ም ድረስ ሲሰራ ሀላፊነቱን ወደጎን በመተው የሂሳብ አሰራር እና ደንብ ከሚፈቅደው ውጪ ብር 689,688.34 / ሥድሥት መቶ ሰማንያ ዘጠኝ ሺህ ሥድሥት መቶ ሰማንያ ሥምንት ብር ከሰላሣ አራት ሣንቲም / ከሥር 1ኛ ተከሳሽ ጋር በአንድነት በማጉደል ከባድ የእምነት ማጉደል ወንጅል ፈጽሟል በማለት ያቀረበበትን ክስ የተመለከተው የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የተጠሪን ምስክሮች ከሰማ በኋላ አመልካች ላከላከል የሚገባው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 675/1 መሰረት ነው በማለት ብይን ከሰጠ በኋላ የአመልካችን መከላከያ ምስክሮች ሰምቶ አመልካች በወንጀል ሕግ አንቀጽ 675/1/ መሰረት ጥፋተኛ ነው በማለት በአንድ አመት ከሥምንት ወር ቀላል እሥራት እንዲቀጣ ወስኗል።
አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ አቅርቧል። ይግባኙ የቀረበለት ፍ/ቤት ግራቀኙን ካከራከረ በኋላ አመልካች የኦዲት ምርመራው በሚከናወንበት ወቅት በሐገር አቀፍ ምርጫ በምርጫ አስፈጻሚነት ሥራ ላይ የነበሩ መሆኑ፤ የፍትሕ ሚኒስቴርም አመልካች ኦዲቱ በተሰራበት ወቅት በሐገራዊ የምርጫ ማስፈጸም ሥራ ላይ የነበሩ መሆኑን አረጋግጦ አመልካች በተገኙበት የኦዲት ሥራው ተከናውኖ ውጤቱ እንዲገለጽለት ለአዲስአበባ ፖሲስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀል ምርመር ዲቪዝዮን ማዘዙን እና አስፈላጊ የሆኑ ማስረጃዎች ተሰባስበው አመልካች በተገኙበት ድጋሚ ኦዲት ተደርጎ ውጤቱ እንዲገለጽለት ቤተክርስቲያንዋን ማዘዙን፤የኢትዮጲያ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤትም ለአቃቂ ቃላቲ ክፍለከተማ ምርጫ ጽ/ቤት አመልካች ከሕዳር 27/2005 ዓ.ም እስከ የካቲት 11/2005 ዓ.ም በመራጮች እና እጩዎች ምዝገባ እንዲሁም ከመጋቢት 13 ቀን 2005 ዓ.ም እስከ ግንቦት 02 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ በወረዳ 06 ምርጫ ጽ/ቤት አስተባባሪነት ቅዳሜ እና እሁድን የበአል ቀናትን ጨምሮ ሲሰሩ ቆይተው ከግንቦት 12/2005 ጀምሮ ወደ መደበኛ ስራቸው መመለሳቸውን ለአዲስ አበባ ፖላስ ኮሚሽን ከጻፈው ደብዳቤ መገንዘብ ተችሐል፤በኦዲቱ ሥራ ገንዘብ ያዥ፤የሂሳብ ሹም እና የውስጥ ተቆጣጣሪ አስፈላጊዎች መሆናቸው የኦዲት ሪፖርቱ ያስገነዝባል፤አመልካች ሂሳብ ሹም በመሆናቸው ለኦዲት ሥራው አስፈላጊ ቢሆኑም አዲቱ ሲሰራ አልነበሩም፤ሒሳቡን የሰሩት ባለሙያዎች የኦዲት ሥራው አስፈላጊ የሆኑ ገቢ እና ወጪ የሂሳብ ሰነዶች ባልተገኙበት የተከናወነ ስለመሆኑ በሂሳብ ስራው ሂደት ያጋጠሙን ችግሮች ናቸው በማለት ዘርዝረዋል።
በመሆኑም አመልካች የተከሰሱበትን የእምነት ማጉዳል ወንጀል ለማረጋገጥ ዓይነተኛ ማስረጃ ሆኖ የቀረበው የኦዲት ሪፖርት ውጤት የአመልካችን ጥፋት ላያሳይ አይችልም በማለት የሥር ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮ ለክሱ መነሻ የሆነው የኦዲት ሥራ ግራ ቀኙ በተገኙበት እና በሚያቀርቡት ማስረጃ በገለልተኛ ሂሳብ አዋቂ በድጋሚ ተሰርቶ ላቀረብ ይገባል፤የሥር ፍ/ቤት የኦዲት ሥራው ድጋሚ ተመርመረሮ የተገኘው ውጤት ከቀረበለት በኋላ የመሰለውን እንዲወስን በማለት ወስኗል። የሰበር አቤቱታው የቀረበው ይህን ውሳኔ በመቃወም ነው።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የሥር ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ ከሻረ በኋላ አመልካችን በነጻ ማሰናበት ሲገባው ቀደም ሲል ውሳኔውን የሰጠው ፍ/ቤት ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያይ በማለት ጉዳዩን በመመለስ የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ሥሕተት የተፈጸመበት በመሆኑ ላታረም ይገባል የሚል ነው።
የአመልካች የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የቀረበለትን ይግባኝ አስቀርቦ ግራቀኙን ካከራከረ በኋላ የሥር ፍ/ቤት ውሳኔ የሚነቀፍ ሆኖ ስለተገኘ ተሽሯል በማለት ከወሰነ በኋላ ከወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 195/2ለ ውጪ በሆነ ሁኔታ ጉዳዩ ወደ ሥር ፍ/ቤት ተመልሶ የግራቀኙ ማሥረጃ ተሰምቶ እንዲወሰን በማለት ጉዳዩን ወደ ሥር ፍ/ቤት የመለሰበትን አግባብነት ለማጣራት ሲባል ጉዳዩ በዚህ ችሎት እንዲታይ ተደርጓል። ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎም ግራቀኙ በጽሑፍ ተከራክረዋል።
ተጠሪ በሰጠው መልስ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 195/2/ለ/2 ጉዳዩ እንደገና እንዲታይ በግልጽ የሚደነግግ ባይሆንም ከአጠቃላይ የይግባኝ ዓላማ እና ግብ አንጻር ላታይ የሚገባው ከመሆኑም በላይ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የሥር ፍ/ቤት ጉዳዩን አጣርቶ እንዲወስን ትዕዛዝ ከመስጠት የሚያግደው ነገር የለም በማለት የአመልካች አቤቱታ ውድቅ ላደረግ ይገባል በማለት ተከራክሯል።
አመልካችም የሰበር አቤቱታውን በማጠናከር የመልስ መልስ ሰጥቷል።
የጉዳዩ አመጣጥ በአጭሩ ከላይ የተገለጸው ነው። እኛም እንዲጣራ የተያዘውን ጭብጥ ከግራቀኙ ክርክር እና ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ሕጎች ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው መርምረነዋል።
የፍ/ቤቶች ዋነኛ ሚና እውነትን አፈላልጎ ፍትሐዊ ውሳኔ መስጠት እንደሆነ ከወንጀል ህጉ እና ከወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ይዘት መገንዘብ ይቻላል። እውነትን ለማፈላለግ እና እውነቱ ላይ ለመድረስም ፍ/ቤቶች በሕገመንግሥቱ የተሰጣቸውን ሕገመንግሥታዊ ተልዕኮ በአግባቡ በመወጣት ክርክሩን መምራት ይጠበቅባቸዋል። በወንጀል ጉዳይ የተከሰሰ ሰው ጥፋተኛ ሆኖ ላቀጣ የሚችለው ወይም ጥፋተኛ አይደለም ተብሎ በነጻ ላለቀቅ የሚችለው ጥፋተኛ ላያደርገው ወይም ነጻ ላያስለቅቀው የሚችል ተገቢ የሆነ ማሥረጃ ሲቀርብበት ነው።
በተያዘው ጉዳይ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የኦዲት ሪፖርቱ ግራቀኙ በተገኙበት ድጋሚ ተሰርቶ ውጤቱ ከቀረበ በኋላ ላወሰን ይገባል ከሚል መደምደሚያ ላይ ላደርስ የቻለው አመልካች የኦዲት ምርመራው በሚከናወንበት ወቅት በሐገር አቀፍ ምርጫ በምርጫ አስፈጻሚነት ሥራ ላይ የነበሩ በመሆናቸው ነው፤አመልካች ሂሳብ ሹም በመሆናቸው ለኦዲት ሥራው አስፈላጊ ናቸው፤አመልካች ባልተገኙበት የተከናወነው የኦዲት ሥራ የአመልካችን ጥፋት ላያሳይ አይችልም በማለት እንደሆነ ከይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውሳኔ መገንዘብ ይቻላል።ዓቃቤሕግ ያቀረበውን ክስ ለማስረዳት የሚያስችለውን በቂ ማሥረጃ ካላቀረበ ፍ/ቤቱ ተከሳሽን በነጻ ላያሰናብተው የሚገባ ቢሆንም በአመልካች በኩል የቀረበው የኦዲት ሪፖርት በአመልካች ላይ ክስ ለመመስረት የሚያስችል በቂ ማሥረጃ ነው። ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በሥር ፍ/ቤት የቀረበው የኦዲት ሪፖርት አመልካችን ጥፋተኛ ለማስባል በቂ አይደለም ከሚል መደምደሚያ ላይ የደረሰው የኦዲት ሪፖርቱ አመልካች ባልተገኙበት የተሰራ እና አመልካች ሒሳብ ሹም በመሆናቸው ምክንያት ለኦዲት ሥራው አስፈላጊ መሆናቸውን አምኖ ግራቀኙ በተገኙበት እና ግራቀኙ በሚያቀርቡት ማስረጃ የኦዲት ሥራው በገለልተኛ የሒሳብ ባለሙያ ተሰርቶ በሚቀርበው ውጤት መሰረት ላወሰን ይገባል በማለት ነው። ይህ መደምደሚያም አመልካች ባልተገኙበት በተሰራው የኦዲት ሪፖርት መሰረት አመልካች ጥፋተኛ እንዳይባሉ በልላ በኩል ተጠሪ ክስ ለማስረዳት ያቀረበው የኦዲት ሪፖርት አመልካች ባልተገኙበት የተሰራ ነው ስለተባለ ብቻ አመልካችን ከወዲሁ በነጻ እንዳይለቀቁ የሚያደርግ እና እውነትን አፈላልጎ ትክክለኛ ውሳኔ ለመስጠት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። አከራካሪው ጉዳይ እና የዚህ ችሎት ምላሽ የሚያሻው ዋነኛ ነጥብ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት አመልካችን ጥፋተኛ ለማስባል ዓይነተኛ ማስረጃ ሆኖ የቀረበው የኦዲት ሪፖርት አመልካች ባልተገኙበት የተሰራ ስለሆነ አመልካች ባልተገኙበት የተሰራው የኦዲት ሪፖርት አመልካችን ጥፋተኛ ላያስብል አይችልም ከሚል መደምደሚያ ላይ ከደረሰ በኋላ ጉዳዩን ወደ ሥር ፍ/ቤት መመለስ ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ነው።
የወ/መ//ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 143 ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ማንኛውንም ማስረጃ መጥራት እንደሚችል ይደነግጋል። ይህ ድንጋጌ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በሥር ፍ/ቤት በአግባቡ ያልተጣሩ ነጥቦች ሲገኙ እና ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ሲባል መጣራት ያላባቸው ሆነው ሲገኙ ተገቢ የሆነውን ትዕዛዝ በመስጠት ጉዳዩ እንዲጣራ ማድረግ የሚችልበትን ሥርዓት የሚደነግግ ነው።
የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 195/2/ለ/2 ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ጥፋተኛ ነው በተባለበት ውሳኔ እና በቅጣቱ ይግባኝ በተባለ ጊዜ ጥፋተኛ ነው የተባለበትን ውሳኔ እና ቅጣቱን ሰርዞ ተከሳሹን በነጻ ለመልቀቅ ወይም ፍርዱን ለውጦ ወይም ሳይለውጥ ቅጣቱን ያጸናል፤ይጨምራል ወይም ይቀንሳል በማለት ይደነግጋል።ይህ ድንጋጌ ፍርድን መለወጥ፤ቅጣትን ማጽናት፤ መጨመር፤መቀነስ እንዲሁም ፍርድን ሰርዞ ተከሳሹን በነጻ እስከመልቀቅ ድረስ ለይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ሥልጣን የሰጠ ድንጋጌ እስከሆነ ድረስ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በተከሳሽ ላይ የቀረበው ማሥረጃ ተገቢ በሆነ ምክንየት ድጋሚ ላጣራ ይገባል ብሎ ሲያምንበት በድጋሚ ተጣርቶ እንዲወሰን በማለት ጉዳዩን ወደ ሥር ፍ/ቤት እንዳይመለስ የሚያደርገው ነው ተብሎ ላተረጎም አይገባም። በእርግጥ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት በወ/መ//ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 143 በተሰጠው ሥልጣን መሰረት የኦዲት ሪፖርቱ ግራቀኙ በተገኙበት በገለልተኛ የሒሳብ ባለሙያ ተሰርቶ እንዲቀርብለት ካደረገ በኋላ ራሡ ለመወሰን የሚችል ቢሆንም ጉዳዩ በይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ቢወሰን የግራቀኙ የይግባኝ መብት የሚጣብብ በመሆኑ ጉዳዩን ለሥር ፍ/ቤት በመመለስ በሰጠው ውሳኔ ላይ የተፈጸመ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ሥሕተት አላገኘንበትም። በዚህም ምክንያት ተከታዩን ወስነናል።
የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ. መጋቢት 12 ቀን 2008 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ በወ/መ//ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 195/2/ለ/2 መሰረት ጸንቷል።
No topics extracted.