No summary available.
የካቲት 27 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡ ...1.ዳኜ መላኩ 2. ተፈሪ ገብሩ (ዶ/ር) 3. ቀነዓ ቂጣታ 4. ተሾመ ሽፈራዉ 5. ፀሐይ መንክር አመልካች፡- ......ወ/ሮ ጀምላ ጆብር ተወካይ ሸፊቃ ሁሴን ቀርበዋል ተጠሪ፡- ............አቶ ሶፊያ ጅማ የቀረበ የለም።
ይህ መዝገብ የተቀጠረዉ ለምርመራ ሲሆን ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የንብረት ክርክር የሚመለከት ሲሆን ለዚህ ችሎት ላቀርብ የቻለዉ የአሁን አመልካች የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.253490 በ05/04/2009 ዓ.ም የሰጠዉ ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረበችዉን አቤቱታ መርምሮ ለመወሰን ነዉ።
የጉዳዩ መነሻ ሲታይ በምስራቅ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የአሁን አመልካች ከሳሽ፣ የአሁን ተጠሪ ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ ፣በዚህ ችሎት የክርክሩ ተካፋይ ያልሆኑት ሚማ ሚስጠፋ፣ሩማና ጅማ፣አላማ ጅማ፣መሀመድ ጅማ እና ናስር ሁሴን 2ኛ-6ኛ ተከሳሾች ሆነው ሲከራከሩ ነበር። ከሳሽ ባቀረበችዉ ክስ በተከሳሾች አክስት ግቢ ዉስጥ በነበረዉ ክፍት መሬት ላይ ሰርቪስ ቤት እና ከ1-22 የተዘረዘሩትን አትክልቶች ያለማሁት ቢሆንም አሁን ይዞታዉን ለወራሾች እንዲተላለፍ ዉሳኔ ስለተሰጠ ግምቱን እንዲከፍሉኝ በማለት ከሳለች።
በዚህ ክስ ላይ ከ1ኛ-5ኛ ተከሳሾች ባቀረቡት መልስ ይህ ጉዳይ ከዚህ ቀደም የመጨረሻ ዉሳኔ ያገኘ በመሆኑ እና አትክልቱን እርሷ ስላልተከለች የንብረት ግምት እንዲከፈለኝ በማለት ያቀረበችዉ ክስ ተቀባይነት የለዉም በማለት ተከራክሯል። 6ኛ ተከሳሽ በበኩሉ ባቀረበዉ መልስ የከሳሽ ክስ ተገቢ ነዉ በማለት ተከራክሯል።
ከዚህ በኋላ ፍ/ቤቱ የሰዉ ምስክሮችን በመስማት የቀረበዉን የሰነድ ማስረጃ በመመዘን በሰጠዉ ዉሳኔ ተከሳሾች የቤት እና የአትክልት ግምት በአጠቃላይ ለከሳሽ እንዲከፍሉ፣ ሰርቪስ ቤቱ እና አትክልቶቹ የዉርስ ንብረት ሆኖ ተከሳሾች እንዲከፋፈሉ በማለት ወስኗል።
የሥር 1ኛ-5ኛ ተከሳሾች በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን ፍ/ቤቱ ግራ ቀኛቸዉን በማከራከር በሰጠዉ ዉሳኔ ይግባኝ ባዮች ከዚህ ቀደም የአክስታቸዉ ይዞታ 800 ካ.ሜ የሆነዉን በዉርስ ለመከፋፈል በፍ/ቤት ክስ ባቀረቡ ጊዜ መልስ ሰጭ /የሥር ከሳሽ/ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.41 መሰረት ጣልቃ ገብታ ስትከራከር በይዞታዉ ላይ ስለሰራችዉ ቤት ሲሆን በዚህ መሰረት የቤቱ ግምት እንዲከፈላት እና ቤቱ ወደ ዉርስ ተቀላቅሎ እንዲከፋፈሉ የተወሰኑ በመሆኑ፣ መልስ ሰጭ ከዚህ ዉሳኔ በኋላ እንደአዲስ የአትክልቶች ግምት እንዲከፈለኝ በማለት ክስ ያቀረበች በመሆኑ ይህ ደግሞ ዳኝነት በአንድ ቦታ አጠቃላ መጠየቅ ሲገባት ከፋፍላ የጠየቀች በመሆኑ፣ የሥር ፍ/ቤት የሰርቪስ ቤት ግምት ይግባኝ ባዮች እንዲከፍሐት በማለት የሰጠዉ ዉሳኔ ተገቢ ቢሆንም የአትክልቶችን ግምት እንዲከፍሐት የሰጠዉ ዉሳኔ ግን ያለአግባብ ነዉ፣ ይግባኝ ባዮች የአትክልቶችን ግምት ለመልስ ሰጭ መክፈል የለባቸዉም በማለት ወስኗል። የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የቀረበዉን ቅሬታ ዉድቅ በማለት የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል። የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ለማስለወጥ ነዉ።
የአሁን አመልካች በ21/5/2009 ዓ.ም በተጻፈ የሰበር አቤቱታ፡ ከዚህ ቀደም በነበረዉ ክርክር ወራሾች ከዉርስ ንብረት ቀላቅለዉ የጠየቁት አንድ ትልቅ መኖሪያ ቤት ብቻ ነዉ እንጂ የተለያዩ አትክልቶችን ጨምረዉ ባልጠየቁበት አመልካች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.41 መኖሪያ ቤቱን በተመለከተ ተጠሪዎች የጠየቁትን መብት ለመቃወም ወደ ክርክሩ የገባሁት ሆኖ እያለ በክርክሩ ዉስጥ ያልነበረዉን የተለያዩ አትክልቶችን በተመለከተ በዛን ጊዜ መጠየቅ ነበረባት አሁን መጠየቅ አትችልም በማለት የሰጡት ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲሻርልኝ በማለት አመልክታለች።
የሰበር አጣሪ ችሎት ጉዳዩን በማየት ፣የአሁን አመልካች በቀድሞ ክስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.41 መሰረት ጣልቃ ገብተሸ ሲትከራከሪ የአትክልት ግምት አልጠየቅሽም በማለት ክሷ ዉድቅ ሲደረግ በቀድሞ ክስ አትክልቶች በተመለከተ ክርክር ስለመኖሩ አለመኖሩን ለማጣራት ተጠሪ መልስ እንዲሰጥ ባዘዘዉ መሰረት በ4/8/2009 ዓ.ም የተጻፈ መልስ አቅርቧል። የመልሱም ይዘት በአጭሩ፡ የሥር ፍ/ቤቶች በዚህ ጉዳይ የሰጡት ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያልተፈጸመበት ስለሆነ እንዲጸናልኝ ወጪና ኪሳራ እንዲወሰንልኝ በማለት በዝርዝር ተከራክሯል። የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ለማስለወጥ ነዉ።
No topics extracted.
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተመለከተዉ ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኛቸዉን ክርክር አግባብነት ካላቸዉ የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንዲሁም አቤቱታዉ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘዉ ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለዉ መርምሮታል። እንደመረመርነዉ የአሁን ተጠሪ ጨምሮ የሥር ተከሳሾች በጉቶ ጊዳ ወረዳ ፍ/ቤት የአክስታቸዉን የወ/ሮ ሀዋ ኡስማን በ800 ካ.ሜ ይዞታ ዉስጥ የሚገኘዉን ንብረት እና ይዞታ ለመከፋፈል ዳኝነት ጠይቀዉ የነበሩ ሲሆን፣ የአሁን አመልካች በበኩሐ በዚህ ይዞታ ዉስጥ የሰራችዉን መኖሪያ ቤት በተመለከተ መብቷን ለማስከበር በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.41 መሰረት ወደ ክርክሩ ጣልቃ ገብታ እንደተከራከረች የሥር ዉሳኔ ግልባጭ ያሳያል። ይህ ጉዳይ ለምስራቅ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት በይግባኝ ቀርቦ ፍ/ቤቱ ወራሾች የቤቱን ግምት ለአመልካች ከፍሐት ቤቱን ወደ ዉርስ ንብረት ተቀላቅሎ እንዲከፋፈሉ በማለት ወስኗል። የአሁን አመልካች ባቀረበችዉ ክርክር በቀደመዉ ክርክር የሥር ተከሳሾች ስለ ቤት እንጂ ስለአትክልት ዳኝነት ስላልጠየቁ ወደ ክርክሩ ጣልቃ ሲገባ ስለአትክልት የማነሳበት ሁኔታ የለም የሚል ነዉ። የአሁን ተጠሪ በበኩሉ አመልካች ጣልቃ ለመግባት አቤቱታ ሲታቀርብ አትክልቶች አለኝ ብላ የጠየቀችዉ ነገር የለም፣ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አመልካች በ800 ካ.ሜ ይዞታ ዉስጥ የሚገኘዉን የዉርስ ንብረትና ይዞታዉን እንዲትለቅ ዉሳኔ የሰጠ ስለሆነ ለመጠየቅ መብት የላትም የሚል ነዉ። ከዚህ ዉጭ የአሁን ተጠሪ ለክርክር ምክንያት የሆኑትን ንብረቶች ለመከፋፈል በክሳቸዉ ዝርዝር ስለማቅረባቸዉ የገለጸዉ ነገር የለም። የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የአሁን አመልካች በቀደመዉ ክርክር ጣልቃ ገብታ ስትከራከር አትክልቶችን መጠየቅ ነበረባት ከማለት ዉጭ የሥር ተከሳሾች አትክልቶችን ለመከፋፈል ዝርዝር ማቅረባቸዉን በዉሳኔዉ ያመለከታዉ ነገር የለም። ይህን በሥር ፍ/ቤት የተረጋገጠዉን ፍሬ ነገር በሕግ አግባብ ማየቱ ተገቢ ነዉ።
በዚህ መሰረት የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.41 እንደሚደነግገዉ ባንድ ክስ ልሎች ተከራካሪ ወገኖች መካከል ያለዉ ክርክር ያገባኛል ወይም መብቴን ይነካል የሚለዉ ሶስተኛ ወገን ፍርድ ወይም ዉሳኔ ከመሰጠቱ በፊት ጣልቃ ገብ ሆኖ ለመከራከር እንደሚችል ያመለክታል። ከዚህ ድንጋጌ ይዘትና ዓላማ መገንዘብ እንደሚቻለዉ አንድ ሶስተኛ ወገን በልሎች ተከራካሪ ወገኖች መካከል በሚደረገዉ ክርክር ያገባኛል ወይም መብቴን ይነካል በማለት ወደ ክርክሩ መግባት የሚችለዉ ተከራካሪ ወገኖቹ በግልጽ ዳኝነት ጠይቀዉ የሚከራከሩበት ንብረት፣ ጥቅም፣ ወይም መብት ላይ ነዉ። ባንድ ክስ በልሎች ተከራካሪ ወገኖች መካከል በሚደረገዉ ክርክር በግልጽ ዳኝነት ያልተጠየቀበትን ንብረት፣ ጥቅም፣ ወይም መብት በተመለከተ በዚህ ድንጋጌ መሰረት ጣልቃ ገብቶ መብት ማስከበር የሚቻልበት ሁኔታ የለም።
በዚህ አግባብ አሁን ወደ ተያዘዉ ጉዳይ ስንመለስ የሥር ከሳሾች የአክስታቸዉን 800 ካ.ሜ የሆነዉን ይዞታና ንብረት ለመከፋፈል ዳኝነት መጠየቃቸዉን እንጂ አሁን ለክርክር ምክንያት የሆኑትን የተለያዩ አትክልቶችን ለመከፋፈል በግልጽ ዳኝነት መጠየቃቸዉን የሚያመለክት ነገር የለም። የሥር ተከሳሾች በቀድሞዉ ክስ እነዚህ አትክልቶች ለመከፋፈል በግልጽ ዳኝነት ካልጠየቁ ደግሞ አመልካች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.41 መሰረት ጣልቃ ገብተው ሲትከራከር መብቷን ለማስከበር የሚጠይቀዉ ነገር አይኖርም። አመልካች ጣልቃ ገብ እንጂ ከሳሽ እስካልሆነች በቀድሞ ክርክር እነዚህን አትክልቶች በተመለከተ በግልጽ ዳኝነት እስካልተጠየቀ ድረስ መብቷን ለማስከበር የምትጠይቀዉ ነገር የለም። የአሁን ተጠሪ ባቀረበዉ ክርክር አመልካች በ800 ካ.ሜ ዉስጥ የሚገኘዉን ንብረትና ይዞታ ላይ መብት የላትም ተብሎ ተወስኗል ይባል እንጂ ክርክሩ የይዞታ ሳይሆን የአትክልት በመሆኑ አመልካች በአትክልቶች ላይ መብት የላትም ተብሎ በግልጽ ዉሳኔ እስካልተሰጠ ድረስ በአትክልቶች ላይ ዉሳኔ ተሰጥቷል ላባል አይችልም። በደፈናዉ ንብረት ተብሎ ዉሳኔ ተሰጥቶም ከሆነ በትርጉም አትክልቶችን ያጠቃልላል ተብሎ በመተርጎም አመልካች መብት የላትም ለማለት አይቻልም። በመሆኑም የአሁን አመልካች ጣልቃ ገብ ነበረች እንጂ ቀጥታ ክስ ያላቀረበች በመሆንዋ እና ለክርክር ምክንያት በሆኑት አትክልቶች በተመለከተ በግልጽ ዳኝነት ባልተጠየቀበት ከዚህ ቀደም በነበረዉ ክርክር መብቷን አጠቃልላ መጠየቅ ነበረባት አሁን እንደአዲስ ከፋፍላ መጠየቅ የለባትም በማለት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.216 እና 218 መሰረት ክሷ ተቀባይነት የለዉም ማለት ከፍ ሲል የተመለከተዉን የሕግ ድንጋጌ የሚቃረን ነዉ።
ሲጠቃለል የሥር የክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት የአሁን አመልካች በቀደመዉ ክርክር ጣልቃ ገብ እንጂ ቀጥታ ክስ ያቀረበች ወገን ባልሆነችበት እና ለክርክር ምክንያት በሆኑት አትክልቶች በተመለከተ በቀደመዉ ክርክር ግልጽ ዳኝነት ባልተጠየቀበት አመልካችዋ ከዚህ በፊት መብቷን አጠቃላይ መጠየቅ ነበረባት አሁን ከፋፍላ ያቀረበችዉ ተቀባይነት የለዉም በማለት ክሷን ዉድቅ በማድረግ የሰጠዉ ዉሳኔ እና የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎትም ይህን ዉሳኔ ማረም ሲገባዉ በማጽናት የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ የሚከተለዉ ተወስኗል።
የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት በመ.ቁ.207855 በ15/3/2009 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ እና ይህን ዉሳኔ በማጽናት የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.253490 በ5/4/2009 ዓ.ም የሰጠዉ ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348 /1/ መሰረት ተሻሽሐል።
የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተዘጋዉን መዝገብ በማንቀሳቀስ በፍርድ ሐተታዉ እንደተመለከተዉ ለክርክር ምክንያት የሆኑትን የተለያዩ አትክልቶችን በተመለከተ ግራ ቀኛቸዉን በማከራከር ተገቢ ነዉ ያለዉን ዉሳኔ እንዲሰጥበት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.341 መሰረት ተመልሶለታል።
የሥር ፍ/ቤቶች የቤት ግምት ለአመልካች ተከፍሎ ቤቱ ወደ ዉርስ ንብረት ተቀላቅሎ ወራሾች እንዲከፋፈሉት በማለት የሰጡት የዉሳኔ ክፍል ጸንቷል።
የዚህ ዉሳኔ ግልባጭ ለሥር ፍ/ቤቶች ይድረስ።
ግራ ቀኛቸዉ በዚህ ችሎት የደረሰባቸዉን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸዉን ይቻሉ።
በ29/6/2009 ዓ.ም የተሰጠዉ የእግድ ትዕዛዝ በዚህ ዉሳኔ ተነስቷል። ይጻፍ።