ሁከት ተወግዶ ይዞታ እንዲለቀቅ ክስ ቀርቦ ፍርድ ከተሰጠ በኋላ በድጋሚ ይዞታ ይለቀቅልኝ በሚል ክስ መመስረት ዳኝነት በተሰጠበት ጉዳይ ላይ በድጋሚ የቀረበ በመሆኑ ተቀባይነት የልለው ስለመሆኑ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 5፣ 244(ለ)
No summary available.
ህዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም.
ዳኞች- ተኽላት ይመስል ተፈሪ ገብሩ ቀነአ ቂጣታ ተሾመ ሽፈራው ፀሃይ መንክር አመልካች- የሰቆጣ ከተማ ቤቶች ልማት ጽ/ቤት ዓ/ህ ሙሉ ባዩለኝ ቀረቡ ተጠሪ- ወ/ሮ አድና ምህረቱ ጠ/ነቀዓጥበብ ገ/ሚካኤል ቀረቡ መዝገቡን መርምረን የሚከተለውን ፍርድ ሰጥተናል።
በዚህ መዝገብ የተያዘው ክርክር የተጀመረው የአሁን አመልካች በተጠሪ ላይ በአማራ ብ/ክ/መንግስት በሰቆጣ ወረዳ ፍርድ ቤት ባቀረበው ክስ ነው።
የክሱ ይዘት፡- ተከሳሽ የከሳሽ መ/ቤት የሆነን በሰቆጣ ከተማ 02 ቀበል የሚገኝ ኮንደሚኒየም የጋራ መኖሪያ ቤት ቁጥር B 13 R7 ባለሁለት መኝታ ቤት ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ሳያገኙና ሳይሰጣቸው በራሳቸው ከጥር ወር 2008 ዓ.ም ጀምሮ ንብረታቸውን አስገብተው ቤቱን ይዘው ስለሚገኙ ቤቱን ለቀው እንዲያስረክቡ እንዲወሰን በማለት ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው።
ተጠሪ ለክሱ ባቀረቡት መቃወሚያ በዚሁ ጉዳይ በመ/6 በሁከት ይወገድልኝ ከሶኝ ተከራክረን ፍርድ ቤቱ ሁከት አለመፍጠሬንና በህጋዊ መንገድ በቤቱ መቀመጤንና የሚፈለገውን ክፍያ እየከፈልኩ ለመሆኔ አረጋግጦ የፈጠርኩት ሁከት የልለ ስለመሆኑ ተወስኖልኝ እያለ የመጨረሻ ውሳኔ ባገኘ ጉዳይ ድጋሚ እንደአዲስ ከሳሽ ጭብጡን ሳይቀይር የክሱን ርዕስ ብቻ በመቀየር ይዞታ ይረጋገጥልኝ በሚል ሰበብ ከቤቱ ለማስወጣት ያቀረበው የሃሰት ክስ በመሆኑ በፍ/ብ/ሥሥ/ቁ 5 እና 244(ለ) መሰረት በፍርድ ያለቀ ጉዳይ ነው ተብሎ ክሱ ውድቅ ይደረግልኝ በማለት ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያው ላይ ግራቀኙን ያከራከረ ሲሆን ከሳሽ በመቃወሚያው ላይ ባቀረበው ክርክር በመጀመሪያው ክስ ተከሳሾች ሁለት የነበሩ መሆኑንና በአሁኑ ክስ ግን ተከሳሽ አንድ ሰው ብቻ መሆናቸውን፤ የክርክሩ ፍሬ ነገርም የመጀመሪያው የሁከት ይወገድልኝ ሲሆን የአሁኑ ግን ይዞታ ይለቀቅልኝ የሚል መሆኑን፤ የሚያዙት ጭብጦችም በመጀመሪያው ሁከት አለ የለም የሚል ሲሆን በአሁኑ ደግሞ ተከሳሽ ይዞታውን ይለቃሉ አይለቁም የሚል በመሆኑ የተለያዩ መሆናቸውን በማንሳት ተከራክሯል። ተከሳሽ በበኩላቸው በመጀመሪያው ክስ ሁለት ተከሳሾች ቢኖሩም ከእሳቸው ውጪ ልላዋ ተከሳሽ አለመከራከራቸውንና ውሳኔም እንዳልተሰጠባቸው፤ የክርክሩም ይዘት በጭራሽ ልዩነት የልለውና ዝርዝር ክሱ ተመሳሳይ መሆኑን፤ በመጀመሪያው ክስ ፍርድ ቤቱ አከራክሮ የሰጠው ውሳኔ ሁከት አለ የለም የሚለው ብቻ ሳይሆን የቤት ኪራይ ግንኙነት ስለመኖሩ ጭምር አከራክሮ ውሳኔ የሰጠ መሆኑን በማንሳት መቃወሚያቸውን አጠናክረዋል።
የመቃወሚያ ክርክሩ በዚህ መልኩ የቀረበለት የሥር ፍርድ ቤት ጉዳዩን መርምሮ የመጀመሪያው ክስ ላይ ሁለት ተከሳሾች የነበሩ መሆኑና የአሁኑ ክስ ደግሞ በተጠሪ ላይ ብቻ መሆኑ ጉዳዩ በፍርድ ያለቀ ነው ከሚለው የመከራከሪያ ሃሳብ ጋር ፍፁም ግንኙነት የልለው መሆኑን፤ የሥረ ነገር ክርክሩ እና የተያዘው ጭብጥ ሲታይ የከሳሽ የዳኝነት ጥያቄ በፊተኛው ክስም ሆነ በአሁኑ ክስ የቤቱ ይዞታ እንዲለቀቅለት ስለመሆኑ ሁለቱንም የክስ ዝርዝር ይዘቶች አይቶ መረዳት እንደሚቻል፤ በአጠቃላይ በመጀመሪያው ክስ ከሳሽ በሁከት ይወገድልኝ ሽፋን ክስ ያቀረበ ቢሆንም ተከሳሽ የቤት ኪራይ ግንኙነት ያላቸው መሆኑ በተረጋገጠበት ሁኔታ ሁከት ላባል እንደማይገባና በኪራይ ግንኙነት ምክንያት የያዙት ይዞታ ህጋዊ ውጤት ያለው መሆኑ ተረጋግጦ ፍርድ ተሰጥቶበት ያደረ ጉዳይ በመሆኑ በድጋሚ የቀረበው ክስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 5፣ 244(ለ) እና 245 መሰረት ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ብይን ሰጥቷል።
አመልካች ይህን ብይን በመቃወም ቅሬታውን ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም። የሰበር አቤቱታው ለዚህ ፍርድ ቤት የቀረበው በዚህ ነው።
አመልካች የካቲት 8/2009 ዓ.ም ባቀረበው የሰበር ማመልከቻ በሥር ፍርድ ቤቶች የተላለፈው ብይን እና ትዕዛዝ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ነው እንዲባል እና ተጠሪ በህገወጥ መንገድ የያዙትን ቤት ለአመልካች ላያስረክቡ ይገባል ተብሎ እንዲወሰን ጠይቋል። ተጠሪ መልስ እንዲሰጡበት ተደርጎ ሀምል 11/2009 ዓ.ም በተፃፈ መልስ ቤቱ ውስጥ የገባሁት አመልካች እንደሚለው በህገወጥ መንገድ ሳይሆን እንደማንኛውም የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኛ በከተማ ቤቶች ልማት ጽ/ቤት በነበረው አሰራር መሰረት ቤት እንዲሰጠኝ ወረፋ ከያዝኩ በኋላ መሆኑና በየወሩ የቤቱን ኪራይ እየከፈልኩ መሆኑ አመልካች እራሱ በፍርድ ቤት ያመነውና የማይክደው ከመሆኑ በተጨማሪ በሥር ፍርድ ቤት ተገቢው ማስረጃ ቀርቦ ከዚህ ቀደም ሁከት ይወገድልኝ በማለት ባቀረበው ክስ ውሳኔ ያገኘ በመሆኑ አንድ አይነት ጭብጥ የተያዘበትና አንድ አይነት ክርክር ነው ተብሎ ክሱ ውድቅ መደረጉ በአግባቡ ነው እንዲባል ጠይቀዋል። አመልካቹም የመልስ መልስ አቅርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን በበኩላችን የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ብይን እና አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምረናል።
የፍትሃብሄር ስነ ስርዓት ህጉ ክርክሮች መቋጫ ይኖራቸው ዘንድ ከዘረጋው ሥርዓት አንዱ በአንቀፅ 5 ሥር የተደነገገው የመጨረሻ ፍርድ ያገኙ ጉዳዮችን የተመለከተው ድንጋጌ ነው። በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 5 ስር እንደተደነገገው አንድ ጉዳይ አስቀድሞ በፍርድ ያለቀ ነው ለማለት መረጋገጥ ያለባቸው ሁኔታዎች ቀደም ሲል ቀጥተኛ የፍሬ ነገር ጭብጥ የነበሩ ጉዳዮች በድጋሚ በቀረበው ክስም ላይ በቀጥታ በፍሬ ነገር ጭብጥ ሆነው መቅረባቸው፣ ቀደም ሲል የነበረውን ክርክር አሁን በክርክር ተሣታፊ በሆኑ ወገኖች ወይም ከእነሱ መብት በተላለፈላቸው ወገኖች መሆኑንና እነዚህ ጉዳዮች ቀደም ሲል በተካሄደው ሙግት የመጨረሻ ፍርድ ያረፈባቸው መሆኑን ይመለከታል። ከሕጉ ይዘት መገንዘብ እንደሚቻለው ቀጥተኛ የፍሬ ነገር ጭብጥ የሚለው ሐረግ በመጀመሪያው ክርክር ላይ ከአንደኛው ወገን ተጠይቆ በልላኛው ወገን የተካደ ወይም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የታመነና በዚሁ ላይ የፍርድ ውሣኔ ያረፈበት የክርክር ነጥብ መሆኑን መረዳት ይቻላል። በመሆኑም በድጋሚ በቀረበው ክስ በቀድሞው ክርክር ተሣታፊ በነበሩ ወገኖች ወይም ከእነሱ መብት በተላለፈላቸው ወገኖች የሚካሄድ መሆኑና በሁለተኛው ክስም የተያዘው ፍሬ ነገር ጭብጥ ከመጀመሪያው ጋር ተመሣሣይ ሆኖ የመጨረሻ ፍርድ ያረፈበት መሆኑ ከተረጋገጠ እንዲሁም ጉዳዩ የመጨረሻ ፍርድ አርፎበታል የሚል ተቃውሞ በተከራካሪ ወገን ከተነሣ ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 5፣ 244(2(ለ)) እና 245(2) ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል።
በተያዘው ጉዳይ ከክርክሩ ሂደት መገንዘብ እንደተቻለው አመልካች ሁከት ይወገድልኝ በሚል አከራካሪው ቤት እንዲለቀቅለት አስቀድሞ ባቀረበው ክስ መሰረት በግራቀኙ መካከል ክርክር ተደርጎ አመልካች ከተጠሪ ጋር የቤት ኪራይ ግንኙነት ያለው መሆኑ በተረጋገጠበት ሁኔታ ተጠሪ ሁከት ፈጥረዋል ላባል እንደማይገባና በኪራይ ግንኙነት ምክንያት የያዙት ይዞታ ህጋዊ ውጤት ያለው መሆኑ ተረጋግጦ ፍርድ ተሰጥቶበት ያደረ መሆኑን የሥር ፍርድ ቤት በፍሬ ነገር ደረጃ በማረጋገጥ ወስኗል።
ስለሆነም አመልካች ሁከቱ ተወግዶ ቤቱ እንዲለቀቅለት ክስ አቅርቦ የተጠሪ ይዞታ ህጋዊ መሆኑ ዳኝነት ከተሰጠበት በኋላ ይዞታ ይለቀቅልኝ በማለት ያቀረበው ክስ ዳኝነት በተሰጠበት ጉዳይ ላይ በድጋሚ የቀረበ በመሆኑ ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5 ድንጋጌዎች አንፃር ተቀባይነት ያለው አይደለም። አመልካች በቀደመው ውሳኔ ላይ ቅሬታ ካለው በየደረጃው በይግባኝ እና በሰበር ስርዓት አቤቱታ ከሚያቀርብ በቀር በዚያው ጉዳይ ድጋሚ ዳኝነት መጠየቁ ህጉን የተከተለ አይደለም።
በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤት በድጋሚ የቀረበው ክስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 5፣ 244(ለ) እና 245 መሰረት ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ያሳለፈው ብይንና በየደረጃው ቅሬታ የቀረበላቸው ፍርድ ቤቶች ቅሬታውን አለመቀበላቸው ህጉን መሰረት ያደረገ በመሆኑ የተፈፀመ የህግ ስህተት የለም ብለናል። ተከታዩንም ወስነናል።
ው ሣ ኔ
የሰቆጣ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በፍ/መ/ቁ 01-05940 ሰኔ 6 ቀን 2008 ዓ.ም ያሳለፈው ብይን፤ የዋግኽምራ ብሄረሰብ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍ/መ/ቁ 01- 02548 ሀምል 27 ቀን 2008 ዓ.ም ያሳለፈው ትዕዛዝ፤ እንዲሁም የአ/ብ/ክ/መ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ 03-15514 ታህሳስ 10/2009 ዓ.ም የሰጠው ትዕዛዝ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 348(1) መሰረት ጸንቷል።
አመልካች ሁከት ተወግዶ ይዞታ እንዲለቀቅለት ክስ አቅርቦ ፍርድ ከተሰጠ በኋላ በድጋሚ ይዞታ ይለቀቅልኝ በሚል ክስ የመሰረተበት አግባብ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 5 ድንጋጌ መሰረት ተቀባይነት የለውም መባሉ በአግባቡ ነው ብለናል።
በዚህ ችሎት ስለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ።
No topics extracted.