ሰበር ችሎቶች ሥነ ሥርዓታዊ የሆነ የህግ ጥያቄን ብቻ ለማየት ስልጣን እንዳላቸው ግንዛቤ በመውሰድ በአንድ ጉዳይ ላይ የተሰጠ ውሳኔ ስነ-ስርዓታዊ ሕጎችን መሰረት አድርጎ የተሰጠ መሆን ያለመሆኑን መመርመር እነ ሶፍያን ከማሎ(6ሰዎች) እና ወ/ሮ ጀሚላ ቃሲም XIII ከዚህ ውጪ መደበኛ ሕጎችን መሰረት አድርገው በሸሪዓ ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ ላመረምሩ የሚችሉበት አግባብ የልለ ስለመሆኑ፡በኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ህገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ))፣ 80(3(ለ)) እና አዋጅ ቁጥር 53/94 እና አዋጅ ቁጥር 188/1992 አንቀጽ 6
No summary available.
የሰ/መ/ የካቲት 29 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- አልማው ወል ሙስጠፋ አህመድ አብርሃ መሰለ ፈይሳ ወርቁ ጳውሎስ ኦርሺሶ አመልካች፡- አቶ ይስሃቅ ተክለ ፃዲቅ ተጠሪ፡-
ይህ የሰበር ጉዳይ ክርክር ላቀርብ የቻለው አመልካች ታህሳስ 10 ቀን 2009 ዓ/ም ባቀረቡት የሰበር አቤቱታቸው በፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በኮ/መ/ ነሀሴ 30 ቀን 2008 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ላታረም ይገባል በማለት የአቀረቡት አቤቱታ በዚህ ችሎት ታይቶ እንዲወሰን በሰበር አጣሪ ችሎቱ ስለተወሰነ ነው።የሕጉ ጥያቄም በአንድ የፍትሃብሕር ክርክር ላይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ጣልቃ በገባ ተከራካሪ ወገን ላይ በክርክሩ ከሳሽ የሆነው ወገን ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ክርክር ለማንሳት የሚችልበት የሕግ አግባብ መኖር ያለመኖሩን የሚመለከት ነው።፡ ክርክሩ የተጀመረው የአሁኑ አመልካች ሚያዚያ 19 ቀን 2007 ዓ/ም በፃፉት ማመልከቻ ሲሆን የማመልከቻቸው ይዘትም ወላጅ አባታቸው መምሬ ተክለፃዲቅ ወ/ዳዊት እና ወላጅ እናታቸው ወ/ሮ ፀዳለ ታደሰ ተሰማ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ክልል ውሰጥ ቁጥሩ 190 በሆነ ቤት ውስጥ ሲኖሩ ወላጅ አባታቸው ጥር 22 ቀን 1996 ዓ/ም፣ ወላጅ እናታቸው ደግሞ ግንቦት 21 ቀን 1995 ዓ/ም ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ገልፀው የወላጆቻው የውርስ ሃብት በመረጧቸው አጣሪ እንዲጣራላቸው ዳኝነት መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው። አመልካች ልላ ተጠሪ ሰይመው ያልነበሩ ቢሆኑም የአሁኑ ተጠሪዎች ወደ ክርክሩ ጣልቃ ገብተዋል። ውርሱ እንዲጣራ ከተደረገ በኋላም ሪፖርቱ በ28/03/2008 ዓ/ም ለፍርድ ቤቱ ቀርቦ ግራ ቀኙ አስተያየት እንዲሰጡበት የተደረገ ሲሆን በዚህ ጊዜም አመልካች ተጠሪዎች ወራሾች ነን በማለት መቅረባቸው በይርጋ የታገደ ነው የሚል መቃወሚያ አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱም በዚህ መልኩ የቀረበውን የአመልካችን መቃወሚያ መርምሮ አመልካች በራሳቸው አመልካችነት ውርሱ እንዲጣራ ጠይቀው የውርስ አጣሪው በሕጉ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ወራሾችን ከለየ በኋላ ይርጋ ማንሳታቸው የህግ አግባብ የልለው መሆኑን፣ ይርጋውን ማንሳት ይችላሉ ቢባል እንኳን የውርስ አጣሪው ይቋቋም የሚል ጥያቄ ሲቀርብ መሆን አለበት የሚሉ ምክንያቶችን ይዞ የአመልካችን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ አድርጎታል፤ የሟች ወራሾች እነማን እንደሆኑ በመለየት የውርስ አጣሪውን ሪፖርት አሻሽሎ አፅድቆታል።
አመልካች የአነሱት የይርጋ ክርክር ውድቅ በመደረጉ ላይ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኛቸውን ወደ ፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ያቀረቡ ሲሆን ከፍተኛ ፍ/ቤቱም ግራ ቀኙን ከአከራከረ በኋላ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን አፅንቶታል። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም፡- ተጠሪዎች አውራሾቻቸው ከሞቱ ከአስር አመታት በኋላ አመልካች ባቀረቡት የውርስ ንብረት ክፍፍል መዝገብ ላይ የሟቾች ወራሾች ነን በማለት የአቀረቡት የክፍፍል ጥያቄ በይርጋ ቀሪ ነው በማለት አመልካች የአቀረቡት መቃወሚያ በበታች ፍርድ ቤቶች ውድቅ የተደረገው ከሕግ ውጪ ነው የሚል ሲሆን አቤቱታቸው በዚህ ችሎት እንዲታይ ተደርጎም ተጠሪዎች ቀርበው ከአመልካች ጋር በፅሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጓአል።
የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ ከላይ የተገለፀው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ የሆነውን ውሳኔ አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን እንደሚከተለው መርምሮታል። እንደመረመረውም የበታች ፍርድ ቤቶች የአመልካችን የይርጋ መቃወሚያ ስነ ስርዓታዊ አይደለም በሚል ምክንያት ውድቅ ማድረጋቸው ሕጋዊ መሰረት አለው? ወይስ የለውም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ላታይ የሚገባ ሆኖ ተገኝቷአል።
ከክርክሩ ሂደት መረዳት የተቻለው አመልካች የሟች አባታቸው አቶ ተክለጻዲቅ ወ/ዳዊት እና የሟች እናታቸው ወ/ሮ ፀዳለ ታደሰ ወራሽ መሆናቸው የተረጋገጠ መሆኑን፣ 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች የሟች ወ/ሮ ጸዳለ ታደሰ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ መሆናቸውን፣ 3ኛ ተጠሪ የሟች አቶ ተክለጻዲዲቅ ወ/ዳዊት የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ መሆናቸውን በአመልካች ያልተካደ ከመሆኑም በላይ የወራሽነት ማስረጃ ቀርቦ መረጋገጡን፣ ተጠሪዎች ያገኙት የወራሽነት ማስረጃ መብትና ጥቅም ባለው ወገን ተቃውሞ ቀርቦበት ያልተሰረዘ መሆኑን ነው። እንዲሁም የበታች ፍርድ ቤቶች የአሁኑ አመልካች የሟቾች የውርስ ሃብት በፍርድ ቤት ትእዛዝ አጣሪ ተሹሞ የውርስ ሃብቱ ተጣርቶ ብቸኛ የሟቾች ወራሽ መሆናቸው ተረጋግጦ የውርስ ሃብቱ በስማቸው እንዲዛወር አመልካች በመሆን ክስ ከማቅረባቸው ውጪ ተጠሪዎች የአመልካችን ክስ በመቃወም በተከሳሽነት ጣልቃ ገብተው ለመከራከር አቤቱታ ከማቅረብ ውጪ የሟቾች ወራሽ መሆናቸው ተረጋግጦ ማስረጃ እንዲሰጣቸውም ሆነ የውርስ ሃብት ድርሻቸው እንዲሰጣቸው ከሳሽ በመሆን ክስ ያለማቅረባቸውን በአቢይ ምክንያትነት ይዘው አመልካች የክስ ማቅረቢያ የጊዜ ገደብ የይርጋ መከራከሪያ በመጥቀስ ያቀረቡት ክርክር ውድቅ ማድረጋቸውን ተመልክተናል።
በመሰረቱ በክርክሩ ውስጥ ለመግባት የሚችልና ተካፋይ ያልሆነበት ክርክር የሚሰጠው ፍርድ መብቱን የሚነካበት ማናቸውም ወገን አቤቱታውን ለማቅረብ መብት እንደአለው የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 39፣ 40 እና 41 ድንጋጌዎች ያስገነዝባሉ። በእነዚህ ድንጋጌዎች የተዘረጋው የጣልቃ ገብነት ስርዓት በአንድ በመካሄድ ላይ ባለ ክርክር ውስጥ በከሳሽነት ወይም በተከሳሽነት ያልተሰየሙ ሰዎች ለክሱ ምክንያት በሆነው ነገር ላይ መብት ወይም ጥቅም ያላቸው መሆኑን በማስረዳት ፍርድ ቤቱ በከሳሽነት ወይም በተከሳሽነት ገብተው ተካፋይ እንዲሆኑ እንዲፈቀድላቸው ዳኝነት የሚጠይቁበትን አግባብ የሚያሳይ ስርዓት ነው። ድንጋጌዎቹ ጣልቃ ገብ የሆኑት ወገኖች የሚያቀርቡት አቤቱታ ክስ ከቀረበበት ምክንያት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለው መሆን ያለበት ሲሆን በሚሰጠው ፍርድ ወይም ውሳኔ መብታቸው በቀጥታ የሚነካ መሆኑ መረጋገጥ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ክስ በቀረበበት ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ መብት፤ ጥቅማቸውን ወይም ግድታቸው የሚነካባቸው ወገኖች የግድ ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸው የፍትሃብሕር ስነ ስርዓት ሕጉ በቁጥር 40 (2) ስር ያስቀመጠበት አቢይ ምክንያትም አንድን የክስ ምክንያት የሚመለከቱ የክርክር ነጥቦች ሁሉ በማያዳግም ሁኔታ ዳኝነት እንዲያገኙ ለማድረግ ታስቦ ስለመሆኑ ይታመናል። እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ደግሞ የክሱ ማመልከቻ መሻሻል እንደአለበትም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 40(3) ድንጋጌ በግልጽ ያሳያል። እንደዚህ አይነት የክርክር አመራር መከተል ደግሞ የይርጋ ጥያቄውንም ሆነ ልሎች ክርክሮችን በሕጉ አግባብ በመምራት ተገቢውን ዳኝነት መስጠት የሚያስችልና የፍትሃብሕር ስነ ስርዓት ሕጉ መሰረታዊ አላማዎችንም የሚያሳካ ነው ተብሎ ይታሰባል።
ከዚህ አንጻር ሲታይ አንድ ክርክር ታይቶ የፍርድ ውሳኔ ቢያርፍ የሚሰጠው ውሳኔ መብቴን፤ጥቅሜን ወይም ግድታን የሚነካ ነው በማለት ወደ ክርክሩ ለመግባት ጥያቄ የሚያቀርብ ሰው ከሳሽ ወይም ተከሳሽ ለመሆን በቂ የክስ ምክንያት ያለው መሆኑ ከተረጋገጠ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 40(3) አግባብ ክሱ እንዲሻሻል በማድረግ ስርዓቱን ጠብቆ የሚቀርበውን ማናቸውንም ክርክር አግባብነት ካለው መሰረታዊና ስነ ስርዓታዊ ድንጋጌ ጋር በማገናዘብ ተገቢውን ዳኝነት መስጠት የዳኝነት አካሉ ተግባር ነው።
ስለሆነም የጣልቃ ገብነት አቤቱታ አቅራቢዎች በከሳሽነትም ሆነ በተከሳሽነት ሲሰየሙ ይርጋን ለማንሳት የሚችሉበትና የማይችሉበት አግባብ ያለ መሆኑን ከላይ የተመለከቱት ስነ ስርዓታዊ ድንጋጌዎች ያስገነዝባሉ። እነዚህ ድንጋጌዎች የውርስ ንብረቱን ለብቻው ለመውሰድ ጥያቄ ያቀረበ ወገን በልሎች መብት አለን በሚሉ ወገኖች የጣልቃ ገብነት አቤቱታ ቀርቦበት የዳኝነት ጥያቄው ተቀባይነት እንዳያገኝ መፍትሕ ሲጠየቁ ዳኝነት ሰጪው አካል በጣልቃ ገብነት ጊዜ የይርጋ ክርክር ላነሳ የሚችልበት አግባብን መሰረት በማድረግ ተገቢውን ዳኝነት ላሰጥ እንደሚችል የሚያሳዩ እንጂ ይርጋ ሁሉጊዜ መነሳት የአለበት በተከሳሽነት በተሰየሙ ሰዎች ብቻ ነው ወደሚለው ድምዳሜ የሚያደርሱ አይደሉም። እንደየክርክሩ ይዘትና አቀራረብ እንዲሁም የዳኝነት ጥያቄው ውጤት የሚያስከትለውን የመብት አድማስ እየታዬ ከሳሽ የሆነ ወገን ተከሳሽ፣ ተከሳሽ ደግሞ ከሳሽ በሚል ዘንግ ተመድቦ ዳኝነት ላሰጥበት የሚገባው ነው።
ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ አመልካች በተጠሪዎች ላይ ያቀረቡት የይርጋ መቃወሚያ ላስተናገድ የሚችል አይደለም የተባለው ይርጋ መቃወሚያ የሚነሳው በተከሳሽ በመሆኑና ተጠሪዎችም የጠየቁት ዳኝነት የውርስ ሃብት እንዲሰጣቸው የሚል ይዘት የለውም በሚል ከሳሽ በነበሩት ባሁኑ አመልካች የሚነሳበት አግባብ የለም በሚል ነው።
ይሁን እንጂ ተጠሪዎች በጉዳዩ ላይ የሚሰጠው የፍርድ ውሳኔ መብታቸውን፤
ጥቅማቸውን የሚነካ መሆኑን ጠቅሰው ወደ ክርክሩ ለመግባት የሚያስችላቸው የክስ ምክንያት ያላቸው መሆኑ ግራ ቀኙን ያላከራከረና በስር ፍርድ ቤቶችም የተረጋገጠ ጉዳይ ሲሆን ጥያቄያቸውም አመልካች የሟቾችን የውርስ ንብረት ብቻቸውን ለመጠቀም የሚያስችላቸው መብት የለም በማለት በሕጉ አግባብ አግኝተናል በሚሉት የወራሽነት ማስረጃ መሰረት ድርሻቸው እንዲጠበቅላቸው መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው። ይህ የተጠሪዎች ጥያቄ በሕጉ በተመለከተው የጊዜ ገደብ ያልቀረበ መሆኑን አመልካች ገልጸው መከራከራቸው ደግሞ ክርክሩ የውርስ እንደመሆኑ መጠን አመልካችን እንደተከሳሽ ተጠሪዎችን ደግሞ እንደከሳሽ የሚያስቆጥራቸው ነው የሚል ትርጉም ከሚያሰጥ በስተቀር ልላ የተከራካሪ ወገኖች ዘንግን የሚፈጥር አይደለም። በመሆኑም የበታች ፍርድ ቤቶች ከተጠሪዎች የጣልቃ ገብነት አቤቱታ ጠቅላላ ይዘት እና መጨረሻ ላይ በፍርድ ቤቱ እንዲረጋገጥላቸው ከጠየቁት የዳኝነት ጥያቄ አንጻር እንዲሁም የክርክሩ ባህርይም የውርስ ንብረት ድርሻ ጋር ተያይዞ የተነሳ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ተጠሪዎችና አመልካች የተከራካሪነት ቦታ እንደተለዋወጡ በመቁጠር የአመልካችን የይርጋ መቃወሚያ መሰረት አድርጎ በመሰረታዊ ሕጉ የተደገፈ መሆን ያለመሆኑን በመመርመርና አስፈላጊ ከሆነም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 245 (1) አግባብ በማስረጃ አጣርቶ የተጠሪዎች የዳኝነት ጥያቄ በይርጋ የታገደ መሆን ያለመሆኑ ላይ ብይን መስጠት ሲገባቸው አመልካች በከሳሽነት ዘንግ መቅረባቸውን ብቻ መሰረት በማድረግ የይርጋ መቃወሚያቸውን ላያነሱ የሚችሉበት የሕግ አግባብ የለም በማለት የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ አግኝተናል።
አመልካች ይርጋን ማንሳት አይችሉም ተብሎ በፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ የካቲት 28 ቀን 2008 ዓ/ም ተሰጥቶ በፍድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ ነሐሴ 30 ቀን 2008 ዓ/ም የጸናው የውሳኔ ክፍል በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁጥር 348 (1) መሰረት ተሽሯል።፡
አመልካች ተጠሪዎች ጣልቃ ሲገቡ ይርጋ ለማንሳት የሚከለክላቸው ሕግ የለም ብለናል። በዚህም መሰረት የፍድራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመ/ ቀጥሎ በአመልካች የይርጋ ጥያቄ ላይ አስፈላጊ ሲሆን ተገቢውን ማጣራት አድርጎ ተገቢ ዳኝነት እንዲሰጥበት ጉዳዩን በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁጥር 341(1) መሰረት መልሰን ልከንለታል። ይጻፍ።
1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች የሟች ወ/ሮ ጸዳለ ታደሰ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ መሆናቸውን፣ 3ኛ ተጠሪ የሟች አቶ ተክለጻዲዲቅ ወ/ዳዊት የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ መሆናቸውን አስመልክቶ በስር ፍርድ ቤቶች የተያዘው ድምዳሜ በዚህ ውሳኔ አልተነካም።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሳራ በተመለከተ ግራ ቀኙ ወገኖች ይቻቻሉ ብለናል።
ሰ/አ የሰበር መዝገብ ህዳር 19 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፦ አልማው ወል ሙስጠፋ አህመድ አብርሃ መለሰ ጳውሎስ ኦርሺሶ ሰናይት አድነው አመልካች:-
ጉዳዩ ከውርስ ጋር ተያይዞ የቀረበን ክርክርን መሰረት ያደረገ ነው። ይህንን የሰበር አቤቱታ አመልካቾች ያቀረቡት በሱድ ወረዳ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በመ/ በ28/07/2008 ዓ/ም ተሰጥቶ በአርሲ ዞን ከፍተኛ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በመ/ በ3/12/2008 ዓ/ም የጸናውን ውሳኔ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 519/2008 በ28/04/2009 ዓ/ም ሽሮ ተጠሪ 2.1589 ሄክታር የገጠር እርሻ መሬት ለአመልካቾች ላለቁ አይገባም በማለት በመወሰኑና ይኼው የጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም ተብሎ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር አጣሪ ችሎት በመ/ በ21/06/2009 ዓ/ም ትእዛዝ በመሰጠቱ አመልካቾች ቅር በመሰኘት ነው።
የአቤቱታቸው መሰረታዊ ይዘትም፡- የወላጅ አባታቸውን የሟች አቶ ከማሎ ሀምዳ የውርስ ንብረት የሆነውን የገጠር እርሻ መሬትና ባህርዛፍ እንዲካፈሉ ክስ መስርተው የሟቹ ሚስቶች በሆኑት ባሁኗ ተጠሪና የአመልካቾች ወላጅ እናት እጅ ያለው ይዞታ መኖሩ ተረጋግጦ ተጠሪ ያላግባብ የያዙትን ይዞታና ባህርዛፍ እንዲያካፍሉ በወረዳውና በዞኑ የሸሪያ ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ በክልሉ ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት የተሻረው ተጠሪ ተገቢውን ክርክርና ማስረጃ ባላቀረቡት ሁኔታ ከመሆኑም በላይ የአመልካቾችን የውርስ ንብረት እንካፈል ጥያቄ በዝምታ ያለፈ ነው የሚል ነው። አቤቱታው ተመርምሮም በዚህ ችሎት እንዲታይ በመደረጉም ተጠሪ ቀርበው ግራ ቀኙ በጽሑፍ እንዲከራከሩ ተደርጎል።
በመሰረቱ የኢ.ፍ.ዲ.ሪፐብላክ ህገ መንግስት አንቀፅ 34(5) እና በኦሮሚያ ብሕራዊ ክልላዊ መንግት ህገ መንግስት በአንቀጽ 35(5) ስር የግልና የቤተሰብ ሕግን በተመለከተ በተከራካሪዎች ፈቃድ በሀይማኖቶች ወይም በባሕሎች ሕጎች መሰረት መዳኘትን በሕገ መንግስቱ ክልከላ እንዳልተደረገበት በግልጽ ከማስቀመጡም በላይ ዝርዝሩ በሕግ እንደሚወሰን ያሳያል። በሸሪዓ ፍርድ ቤት የመዳኘት መብትም ምንጩ ይኼው የሕገ መንግስቱ ድንጋጌ ሲሆን በአማራ ብሕራዊ ክልላዊ መንግስትም የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 54/1994 መሰረት ተደራጅተዋል። በዚሁ አዋጅም ስልጣናቸው ተለይቶ ተቀምጧል። በአዋጁ የክርክሩን የአመራር ሥርዓት ካልሆነ በስተቀር የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች በሥረ ነገር ሥልጣናቸው ሥር የሆኑ ጉዳዮች የሚቀርብላቸውን አቤቱታና ክርክር የሚወስኑት የሸሪዓ ህግን መሰረት በማድረግ እንደሆነ በአዋጅ ቁጥር 53/94 በአንቀፅ 6(1) ስር በግልፅ የተደነገገ ሲሆን አንድ ሰው ለሸሪዓ ፍርድ ቤት ክስ ወይም አቤቱታ ሲያቀርብ ሥነ ሥርዓታዊ ከሆነው ጭብጥና ጥያቄ ውጭ የሆኑት ጉዳዮች በሸሪዓ ህግ ለመዳኘት ፈቃድ የሰጠ መሆኑም ላረጋገጥ ይገባል።በመሆኑም የሸሪዓ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ ዳኝነት ከመስጠቱ በፊት በአዋጅ ቁጥር 53/1994 አግባብ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የተሰጠው መሆኑን በቅድሚያ ላያረጋግጥ የሚገባ መሆኑን ከአዋጁ አንቀጽ 6 ድንጋጌና ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 9 እና 231 (1(ለ)) ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። ይህ ችሎትም ሆነ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በኢ.ፍ.ዲ.ሪ.ፐብላክ ህገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ))፣ 80(3(ለ)) እና አዋጅ ቁጥር 53/94 እና አዋጅ ቁጥር 188/1992 አንቀጽ 6 ጣምራ ንባብ መሰረት ስነ ስርዓታዊ የሆነ የህግ ጥያቄን ብቻ ለማየት ስልጣን እንዳላቸው ግንዛቤ በመውሰድ በጉዳዩ ላይ የተሰጠው ውሳኔ ስነ ስርዓታዊ ሕጎችን መሰረት አድርጎ የተሰጠ መሆን ያለመሆኑን መመርመር እንጂ ከዚህ ውጪ መደበኛ ሕጎችን መሰረት አድርገው በሸሪዓ ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ ላመረምሩ የሚችሉበት አግባብ የለም።
እኛም የቀረበውን የሰበር አቤቱታ ግራ ቀኙ በስር ፍርድ ቤት ካቀረቡት ክርክር እና ማስረጃ እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 53/94 ከተዘረጋው ስርዓት አንጻር የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሆነ የሥነ ስርዓት ህግ ስህተት የተፈጸመበት መሆን ያለመሆኑን መርምረነዋል።
ወደተያዘው ጉዳይ ስንመለስም የክልሉ ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ተጠሪ 2.1589 ካ/ሜትር ይዘው እንዲቀሩ ውሳኔ የሰጠው አመልካቾች በወላጅ እናታቸው በኩል ተጠሪ ይዞታውንና ባህርዛፉን እንዲለቁላቸው የመሰረቱትን ክስ የበታች የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ተቀብለው ተጠሪ ይዞታውን እንዲለቁ መወሰናቸው ተገቢውን የፍሬ ነገር ማጣራትና የሸሪዓ ሕግ መሰረት ያደረገ መሆን ያለመሆኑን በመመርመር ስለመሆኑ ከውሳኔው ግልባጭ መረዳት ችለናል።
አመልካቾች በሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ለመዳኘት ፍቃደኛ ሳይሆኑ የተሰጠ ውሳኔ ስለመሆኑ ገልጸው ያቀረቡት ቅሬታ የልለ ሲሆን አጥብቀው የሚከራከሩት ተጠሪ የያዙትን ይዞታ እንድንካፈል አልተወሰነም በሚል ነው። ይህም የሚያሳየው አመልካቾች ተጠሪ የያዙትን ይዞታ በሟች ከማሎ ሀምዳ ወራሽነታቸው ከተጠሪ ጋር ልንካፈል ይገባል በሚል የሚከራከሩ መሆኑን ነው። ይሁን እንጂ የክልሉ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ፍሬ ነገሩን በራሱ አጣርቶ የአመልካቾች ወላጅ እናት የሆኑት ወ/ሮ ሃዲያ አብድሮ 6.77 ሄክታር ይዘው ያሉ መሆኑን፣ ይህን ይዞታ ይዘውም የአሁኑ አመልካቾችን ወክለው ተጠሪ የያዙትን 2.1589 ሄክታር ጭምር ለመውሰድ ዳኝነት መጠየቃቸው በጉዳዩ ከተረጋገጡት ፍሬ ነገሮችና ከሸሪዓ ሕግ አንጻር ተገቢ ያለመሆኑን በመገንዘብ ተጠሪ የያዙትን ይዞታ ላለቁ አይገባም በማለት ዳኝነት መስጠቱን የውሳኔ ግልባጭ የሚያሳይ በመሆኑና ይህም ውሳኔ ከሸሪዓ ሕግ አንጻር ታይቶ ከመሰጠቱም በተጨማሪ የአመልካቾች ወላጅ እናትም ከተጠሪ ይዞታ የበለጠ ይዞታ ይዘው እንደሚገኙና አመልካቾችም ከወላጅ እናታቸው ስር ያሉ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆኑን ተገንዝበናል።
ስለሆነም የጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት በሕግ ተለይቶ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ተጠሪ ይዞታውን የሚለቁበት አግባብ መኖር ያለመኖሩን በማስረጃ አጣርቶና ጉዳዩን በሐይማኖት ስርዓት መዝኖ ይዞታውን ተጠሪ ላለቁ የሚችሉበት ሐይማኖታዊ ምክንያት የልለ መሆኑን ድምዳሜ ላይ ደርሷል። ይሕው ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤቱ ፍሬ ነገርን በማጣራት እና ማስረጃ በመመዘን ስልጣኑ የደረሰበት መደምደሚያ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት በድጋሚ የሚመዘንበት አግባብ የልለ መሆኑን በኢ.ፍድ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 80/3/ሀ/ እና በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀፅ 10፣ እንዲሁም በክልሉ የሸሪዓ ፍ/ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 53/94 ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው።
ከእነዚህ የሕግ ማዕቀፎች አንጸር ስናየው ደግሞ ሸሪዓ ፍ/ቤቶች ክርክሩ ሲመሩ በስነ ስርዓት ሕግ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ፈጽመዋል ለማለት የሚያስችል ምክንያት አላገኘንም። ከዚህ አንፃር ሲታይ አመልካቾች የክፍፍል ጥያቄአችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ ሆኗል በማለት ያቀረቡት ክርክር የጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት ፍሬ ነገሩን አጣርቶና በሐይማኖቱ ስርዓት አግባብ ውድቅ ያደረገውን ያላገናዘበ እና የአመልካቾች ቅሬታ መሰረታዊ ይዘቱ በሐይማኖት ስርዓት ላይ ተመርስቶ የተሰጠውን ውሳኔ በመደበኛው ሕግ እንዲታይ የሚጠይቅ በመሆኑ አልተቀበልነውም።
በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የክልሉ ጠቅላይ ሸሪዓ ፍርድ ቤት የአመልካቾችን ክርክር ውድቅ በማድረግ በሰጠው ውሳኔና ይህንኑ ውሳኔ ባፀናው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር አጣሪ ችሎት ትዕዛዝ ላይ የተፈጸመ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህትት አላገኘንም።
በመሆኑም የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥተናል።
በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ሸሪአ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 519/2008 በ28/4/2009 ዓ/ም ተሰጥቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ አጣሪ ችሎት በመዝገብ በ21/06/2009 ዓ/ም የጸናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348/1/ መሰረት ጸንቷል።
በዚህ ችሎት ለተደረገው ክርክር የወጣውን ወጪና ኪሣራ የየራሣቸውን ይቻሉ ብለናል።