ለአንድ ክርክር መነሻ የሆነ ቤትና ይዞታ በክልል የሚገኝ ሲሆንና የስረ ነገር ስልጣኑ የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቢሆንም ጉዳዩ መታየት ያለበት ንብረቱ በሚገኝበት ክልል የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስለመሆኑ፡-
No summary available.
ቀን 27/03/2010 ዓ/ም ዳኞች፡- ተኽላት ይመሰል ተፈሪ ገብሩ ቀነዓ ቂጣታ ተሾመ ሽፈራው ፀሐይ መንክር አመልካች፡- ወ/ሮ ዘይባ ሳኒ ተጠሪ፡- ወ/ሮ ለይላ ዘይኑ ተወካይ ድቻሳ ጉርሙ ቀረቡ መዝገቡ የተቀጠረው መርምሮ ተገቢውን ለመስራት ነበር። መዝገቡን መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ የቤት ክርክር የሚመለከት ሲሆን የጀመረው በፍድራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአሁኑ ተጠሪ በአመልካች ላይ በኮ/መ/ቁ. 63738 ባቀረቡት ክስ መነሻ ነው። የስር ከሳሽ ያቀረቡት ክስ ይዘትም በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ሰበታ ከተማ አስተዳደር ዓለምገና ቀበል 02 ውስጥ ስፋቱ 395.7 ካሬ ሜትር በሆነው ይዞታ ላይ ቤት ሰርተው ተጠሪ በነበራቸው ጊዜያዊ ችግር በቤቱ እንዲኖሩ ተፈቅዶላቸው የነበረ ቢሆንም ቤቱን ለቀው እንዲያስረክቡ ተጠይቀው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለቀው እንዲያስረክቡ እንዲወሰን መጠየቃቸውን የሚያሳይ ነው።
የአሁኑ አመልካች የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እንዲሁም በፍሬ ጉዳዩ የበኩላቸውን መልስ አቅርቧል። አመልካች ባቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ የማየት የስረ ነገር ስልጣን የለውም የሚል ክርክር ያቀረቡ ሲሆን በፍሬ ጉዳዩም ቤቱ የራሳቸው እንጂ የአሁኑ ተጠሪ አለመሆኑን በመግለጽ ክሱ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።
በዚህ አግባብ ክርክሩ የቀረበለት ፍርድ ቤትም የግራ ቀኙ ክርክርና ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ለክርክሩ ምክንያት የሆነውን ቤት የተጠሪ ነው ከሚል መደምደሚያ የደረሰ ሲሆን በዚህም አመልካች ቤቱን ለቀው ለተጠሪ እንዲያሰረክቡ ፍርድ ሰጥቷል። አመልካች ይህ ውሳኔ በመቃወም ለፍደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቅሬታ ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔና ትዕዛዝ በመቃወም ለማሳረም ነው። አመልካች ባቀረቡት የሰበር አቤቱታም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ከህግ ውጭ ውድቅ ስለ መደረጉ በፍሬ ጉዳዩም ቤቱ የአመልካች እንጂ የተጠሪ አለመሆኑን በፍሬ ነገር ደረጃ በተረጋገጠበት ሁኔታ በስር ፍርድ ቤት ውድቅ መደረጉ በህጉ አግባብ አይደለም በማለት የተከራከሩ ሲሆን በዚህ አግባብ አቤቱታ የቀረበለት አጣሪ ችሎትም አመልካች ቤቱን ለተጠሪ በአደራ መስጠታቸው ባልተጠረጋገጠበት ሁኔታ ቤቱን ለቀው እንዲያስረክቡ የመወሰኑን አግባብነት ተጠሪ ባሉበት ማጣራት ይቻላል ዘንድ ለዚህ ችሎት ያስቀርባል ተብሐል። ተጠሪም የበኩላቸውን መልስ ያቀረቡ ሲሆን የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲፀና አመልክቷል።
የመልስ መልስም ቀርቧል ።
የጉዳዩ አመጠጥ ከላይ የተገለጸው አጭር ይዘት ያለው ሲሆን እኛም ለሰበር አቤቱታ መነሻ የሆነውን ውሳኔ አግባብነት ከላቸው የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ መርምረናል። እንደመረመረነው የዚህ ችሎት ምላሽ የሚያሻው ዓቢይ ነጥብ በፍሬ ጉዳዩ የተሰጠው ፍርድና ትዕዛዝ ተገቢነት ከመመርመራችን በፊት ጉዳዩ በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ታይቶ ፍርድ መሰጠቱ ከስረ ነገር ስልጣን አንጻር በህጉ አግባብ መሆን አለመሆኑን መታየት ያለበት ሆኖ አገኝተነዋል። ከስር ፍርድ ቤት መዝገብ መረዳት የሚቻለው ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤትና ይዞታ የሚገኘው ኦሮሚያ ክልል ፈንፊኔ ልዩ ዞን ሰበታ ከተማ አስተዳደር ቀበል 02 ውስጥ ነው። አመልካችም ነዋሪነታቸው ኦሮሚያ ክልል ስለመሆኑ ያከራከረ ጉዳይ አይደለም። የአሁኑ ተጠሪ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ባቀረቡት መልስ ጉዳዩ የፍድራል ሆኖ በውክልና በኦሮሚያ ክልል ባሉ ፍርድ ቤቶች የሚታይ ቢሆንም ውክልና ሰጪው በጉዳዩ ላይ ስልጣን የለውም ማለት ስላልሆነ ከዚህ አንጻር የቀረበው መቃወሚያ ተቀባይነት የለውም የሚል ክርክር ማቅረባቸውን ተመልክተናል።
በመሰረቱ የስረ ነገር ስልጣን ጥያቄ በየትኛውም የክርክር ደረጃ የሚነሳ ጉዳይ ስለመሆኑ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ. 9 እና 231 (1) (ለ) እና ይህ ሰበር ሰሚ ችሎት በበርካታ መዝገቦች በሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። አንድ ጉዳይ በፍድራል ፍርድ ቤቶች የስረ ነገር ስልጣን የሚወድቅ መሆኑ አለመሆኑን ለመለየት አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 5 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ማየቱ ተገቢ ይሆናል።
በተያዘው ጉዳይ ለክርክሩ ምክንያት የሆነው የማይንቀሰቀስ ንብረት በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ ከመሆኑ በተጨማሪ አመልካች እና ተጠሪ የኦሮሚያና አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ስለመሆናቸው የተካደ ጉዳይ አይደለም። የፍድራል ፍርድ ቤቶች በይፋ ባልተቋቋባቸው ክልሎች የፍድራል ጉዳይ በውክልና የሚታይ ስለመሆኑ የኢ.ፍ.ድ.ሪ ህገ መንግስት በግልጽ ያስቀመጠ ሲሆን በተያዘው ጉዳይ የስረ ነገር ስልጣኑ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቢሆንም ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤትና ይዞታ በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ በመሆኑ መታየት ያለበት በኦሮሚያ ክልል ንብረቱ የሚገኝበት የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ላይ ስለመሆኑ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 80(4) ያስገነዝበናል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ይሁን የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የስረ ነገር ስልጣን የልላቸው መሆኑን መገንዘብ ሲገባቸው ይህንን በማለፍ ግራ ቀኙን በማከራከር ፍርድና ትዕዛዝ መስጠታቸው በህጉ አግባብ ሆኖ አልተገኘም። በዚህ ሁሉ ምክንያት የስር ፍርድ ቤቶች የስረ ነገር ስልጣን ሳይኖራቸው የሰጡት ፍርድና ትዕዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት በመሆኑ ላሻር የሚገባው ነው ብለናል። በዚህም ተከታዩን ወስነናል።
የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ. 63738 በ29/11/2008 ዓ/ም የሰጠው ፍርድ የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኮ/መ/ቁ. 185671 በ29/06/2009 ዓ/ም የሰጠው ፍርድ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ. 348(1) መሰረት ተሽሯል።
ለክርክሩ መነሻ የሆነውን ቤትና ይዞታ በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ በመሆኑ የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የስረ ነገር ስልጣን የለውም በማለት ወስነናል። ይሁንና የአሁኑ ተጠሪ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ክስ የማቅረብ መብታቸው ይህ ውሳኔ አያግዳቸውም ብለናል።
የዚህ ፍርድ ቤት ክርክር ያሰከተለው ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል።
በዚሀ ፍርድ ቤት በ2/08/2009 ዓ/ም የተሰጠው የዕግድ ትዕዛዝ ተነስቷል።
No topics extracted.