የተፋጠነ ሥነ-ሥርዓት የክርክር አመራር የሰዎችን የመከላከልና የመሰማት ሕገ መንግስታዊ መብትን በሚነካ መልኩ መተርጎም እና ሥራ ላይ መዋል የማይገባው ስለመሆኑ፡ፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.284-287
No summary available.
መስከረም 24 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- 1.ዳኜ መላኩ 2. ረታ ቶለሳ 3. ተኽላት ይመሰል 4. ቀነዓ ቂጣታ 5. አብዬ ካሳሁን አመልካች፡- አቶ መሳይ ቦጋለ - ተወካይ ወ/ሮ አይናለም በቀለ ቀርበዋል።
ተጠሪ፡- ወ/ሮ አይናለም አለሙ - ጠበቃ ፋሲል ይነሱ ቀርበዋል።
መዝገቡ ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የብድር ዉልን መነሻ ያደረገ ክርክር ሲሆን፣የአሁን አመልካች የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ.176598 በ14/11/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲሻርልኝ በማለት ያቀረበዉን አቤቱታ መርምሮ ለመወሰን ነዉ።
የጉዳዩ አመጣጥ ሲታይ በፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የአሁን ተጠሪ ከሳሽ፣የአሁን አመልካች ተከሳሽ ሆኖ ተከራክሯል። ከሳሽ ባቀረበችዉ ክስ በከሳሽ እና ተከሳሽ መካከል በ18/1/2003 ዓ.ም በተደረገ የገንዘብ ብድር ዉል ተከሳሽ ብር 400,000 /አራት መቶ ሺህ/ ከከሳሽ ተበድረዉ በዉሉ መሰረት ስላልከፈለ ይህን ገንዘብ ከሕጋዊ ወለድ እንዲሁም ወጪና ኪሳራ ጋር እንዲከፍለኝ በማለት በተፋጠነ ሥነሥርዓት ክስ አቅርቧል።
ይህን ክስ በተመለከተ ተከሳሽ ቀርበዉ የመከላከያ መልስ እንዲያቀርብ እንዲፈቀድለት ማመልከቻ ቢያቀርብም ፍ/ቤቱ ሳይቀበለዉ አልፎታል።
ከዚህ በኋላ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን በመመርመር በሰጠዉ ዉሳኔ ተከሳሽ በብድር ብር 400,000 /አራት መቶ ሺህ/ ከከሳሽ የወሰደ መሆኑን የቀረበዉ የገንዘብ ብድር ዉል ሰነድ የሚያስረዳ በመሆኑ ተከሳሽ በዉሉ መሰረት የመፈጸም ግድታ ያለበት ስለሆነ ከሳሽ ደግሞ በዉሉ መሰረት እንዲፈጸምላቸዉ የመጠየቅ መብት ስላላቸዉ ተከሳሽ ይህን በብድር የወሰደዉን ገንዘብ ለከሳሽ እንዲከፍል ክስ ከቀረበበት ቀን ጀምሮ ከሚታሰብ 9% ወለድ ጋር እንዲከፍል በማለት ወስኗል። የሥር ተከሳሽ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረበ ቢሆንም ፍ/ቤቱ የቀረበዉን ይግባኝ ዉድቅ በማድረግ የሥር ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል። የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ለማስለወጥ ነዉ።
የአሁን አመልካች ሐምል 9 ቀን 2008 ዓ.ም የተጻፈ አራት ገጽ አቤቱታ አቅርቧል።
የአቤቱታዉ ይዘት በአጭሩ፡- የአሁን ተጠሪ ላቀረቡት ክስ አመልካች ማስፈቀጃ በማቅረብ ወደ ክርክር እንድገባ ያቀረብኳቸዉ ምክንያቶች የብድር ዉሉ በይርጋ የሚታገድ ነዉ፣ ዉሉ ፈራሽ ነዉ፣ ብድሩ ሕገ ወጥ የአራጣ ብድር ዉል ስለሆነ ፈራሽ ነዉ፣ የብድር ዉሉ የኮንዶሚኒያም ቤት ሽያጭ ዉል ተቀጽላ እና ጥገኛ /መተማመኛ/ ዉል ነዉ፣ አመልካች በ1997 ዓ.ም የደረሰኝን ባለ ሁለት ክፍል መኝታ ያለዉ የኮንዶሚኒየም ቤት ለተጠሪ በመሸጥ ዉክልና ሰጥቼ ለዚህ መተማመኛ እንዲሆን የብድር ዉል በማስመሰል የተፈረመ እንደሆነ በመግለጽ ያቀረብኩት ሲሆን የሥር ፍ/ቤት ማስፈቀጃዉን ሳይቀበል እና መልስ እና ማስረጃዬን ሳይሰማኝ የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲሻርልኝ በማለት በዝርዝር አመልክቷል።
የሰበር አጣሪ ችሎት ጉዳዩን በመመርመር፣በዚህ ጉዳይ አመልካች በተፋጠነ ሥነ ሥርዓት ለቀረበበት ክስ መከላከያ ለማቅረብ ያቀረበዉ ማስፈቀጃ በሥር ፍ/ቤት ዉድቅ የመደረጉን አግባብነት፣ለመመርመር ሲባል አቤቱታዉ ያስቀርባል በማለት ተጠሪ መልስ እንዲያቀርብ በታዘዘዉ መሰረት መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም የተጻፈ ሁለት ገጽ መልስ አቅርቧል። የመልሱም ይዘት በአጭሩ፡--አመልካች ለቀረበባቸዉ ክስ ላያስተባብልላቸዉ የሚችል ማስፈቀጃ በሥር ፍ/ቤት ባላቀረቡበት በሀሰት አቅርቤያለሁ በማለት ለዚህ ችሎት ያቀረቡት ማመልከቻ ዉድቅ በማድረግ የሥር ፍ/ቤቶች ዉሳኔ በማጽናት በቂ ኪሳራ እንዲወሰንልኝ በማለት በዝርዝር ተከራክሯል። የአሁን አመልካች የሰበር አቤቱታዉን በማጠናከር የመልስ መልስ አቅርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተመለከተዉ ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኛቸዉን ክርክር ለሰበር አቤቱታዉ መነሻ ከሆነዉ ዉሳኔ እና አግባብነት ካላቸዉ የሕግ ድንጋገዎች ጋር በማገናዘብ እንዲሁም አቤቱታዉ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘዉ ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለዉ መርምሮታል። እንደመረመርነዉ የአሁን ተጠሪ ባቀረቡት ክስ አመልካች በ18/1/2003 ዓ.ም በተደረገ የገንዘብ ብድር ዉል መሰረት ብር 400,000 ተበድረዉ ስላልከፈሉ ገንዘቡን ከሕጋዊ ወለድ ጋር እንዲከፍላቸዉ እንዲወሰንላቸዉ በተፈጠነ ሥነ ሥርዓት ክስ ማቅረባቸዉ ተመልክተናል። የአሁን አመልካች በበኩሉ ለዚህ ክስ የመከላከያ መልስ ማቅረብ እንዲችል እንዲፈቀድለት የማስፈቀጃ ማመልከቻ ያቀረበ ቢሆንም ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን የሥር ዉሳኔ ያሳያል። የሥር ፍ/ቤት አመልካች ያቀረበዉን የማስፈቀጃ ማመልከቻ ዉድቅ በማድረግ አመልካች በቀረበዉ ክስ መሰረት በብድር ዉሉ መሰረት የወሰደዉን ገንዘብ ከሕጋዊ ወለድ ጋር እንዲከፍል የወሰነ መሆኑን የሥር ዉሳኔ ግልባጭ ያመለክታል። ከዚህ አንጻር ምላሽ ማግኘት ያለበት ጉዳይ ተጠሪ ያቀረቡት ክስ በተፋጠነ ሥነ ሥርዓት መሰረት የቀረበ ነዉ በሚል ምክንያት የአመልካች ማስፈቀጃ ተቀባይነት ማጣቱ የሕጉን ዓላማ ያገናዘበ ነዉ ወይስ አይደለም? የሚለዉ ነዉ።
እንደሚታወቀዉ የፍትሐ ብሕር ክርክር የሚመራበት ሂደት በፍትሐ ብሕር ሥነሥርዓት ሕግ ላይ ተመልክቷል። የሥነሥርዓት ሕጉ የክርክሮችን ባህር ከግንዛቤ በማስገባት የክስና የመልስ አቀራረብ ሂደቱን በሚያመላክት የተቀረጸ መሆኑን ማየት ይቻላል። በዚህ መሰረት የፍትሓ ብሕር ሥነሥርዓት ሕግ በአምስተኛ መጽሐፍ ልዩ ስነሥርዓት ምዕራፍ 1 በአጭር ሁኔታ በሚወሰኑ ክርክሮች ላይ ስለሚፈጸም ሥነ ሥርዓት ከአንቀጽ 284--292 ተደንግጎ እናገኛለን። በዚህ ሥርዓት የሚቀርብ ክርክር የሕግ አዉጭዉን ሃሳብ የሚያሳካ ነዉ ተብሎ ይገመታል። ነገር ግን የእነዚህን ድንጋጌዎች መስፈርት የማያሟሉ ክሶች በዚህ ሥርዓት የሚቀርቡ ከሆነ እና በተከሳሽ በኩል የሚቀርበዉን የመከራከርና የመከላከል መብቱን የሚያሳጡ ከሆነ በሕገ መንግስቱ የተመለከተዉን የመሰማት መብት የሚነፍግ ይሆናል። በአጭር ሁኔታ የሚወሰኑ ክርክሮች መመራት ያለባቸዉ በዚህ ምዕራፍ በተደነገገዉ አግባብ ላሆን ይገባል።
ስለሆነም በአጭር ሁኔታ የሚወሰኑ ክርክሮች ወይም በተፋጠነ ሥነሥርዓት የሚቀርብ ክስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.284 የተመለከተዉን ቅድመ ሁኔታዎችን ያሟላ መሆን እንዳለበት ግልጽ ነዉ። በዚህ ድንጋጌ ሥር እንደተመለከተዉ ከሳሽ ከተከሳሽ ላይ የሚጠይቀዉ ሂሳብ ወይም ጥሬ ገንዘብ ከነወለዱ ወይም ያለወለድ ወይም ልኩ ተወስኖ የታወቀ ሲሆን ክሱም የተመሰረተዉ ከዚህ ቀጥሎ የተመለከቱት ምከንያቶች ላይ በሆነ ጊዜ ፡- /ሀ/ በዉል መሰረት በግልጽ በተደረገ ዉል ወይም በሐዋላ ወረቀት ወይም በገንዘብ አለብኝ ሰነድ ወይም በቼክ ወይም ተራ የሆነ የባለዕዳነትን በሚገልጽ ዉል በማለት ይደነግጋል። በዚህ ድንጋጌ አግባብ የሚቀርብ ክስ የተፋጠነ ሥነሥርዓት የሚል አርዕስት ተሰጥቶና በቃለ መሓለ ተደግፎ መቅረብ እንዳለበት ይገልጻል። የዚህን ድንጋጌ መስፈርት የሚያሟላ ክስ ላቀርብ የሚገባዉ በዚህ በአጭር ሁኔታ በሚወሰኑ ክርክሮች ወይም በተፋጠነ ሥነሥርዓት እንደሆነ የሚያከራክር አይሆንም።
በዚህ ድንጋጌ አግባብ የሚቀርብ ክስ ደግሞ የተከሳሽ የመከራከርና የመከላከል መብት ሙሉ ለሙሉ ለመንፈግ ታስቦ የተቀረጸ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.285 ይዘትና ዓላማ እንደሚያመለክተዉ ተከሳሽ ቀርቦ መከላከያ እንዲያቀርብ እንዲፈቀድለት ለፍ/ቤት ማመልከት እንደሚችል ነዉ። በዚህ መልክ የመከላከያ መልስ እንዲያቀርብ እንዲፈቀድለት ማመልከቻ ያላቀረበ እንደሆነ ግን ከሳሽ የጠየቀዉን ገንዘብ ከነወለዱ እንዲከፍል እንደሚወሰንበት ያስገነዝባል። ተከሳሽ ቀርቦ እንዲከላከል እንዲፈቀድለት የሚያመለክተዉ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.286 ሥር በተመለከተዉ አግባብ ላሆን እንደሚገባዉ ነዉ። ተከሳሽ ቀርቦ ለመከላከል እንዲፈቀድለት የሚያቀርበዉ ማመልከቻ በቃለ መሓለ ተደግፎ መቅረብ እንዳለበት ነዉ።
ፍ/ቤቱ የቀረበዉን መሓላ ቃሉን ተቀብሎ ላመረምር እንደሚችልና የቀረበዉ የመሐላ ቃልና ማመልከቻዉ ለከሳሽ እንዲደርሰዉ ማድረግ እንደሚገባዉ ይደነግጋል። ፍ/ቤቱ የቀረበዉን ለመከላከል ማስፈቀጃ ማመልከቻ እና መሐላ ቃል የተቀበለዉ እንደሆነ ተከሳሽ ሙሉ ክርክሩን እንዲያቀርብ የሚደረግ ሲሆን፣ ፍ/ቤቱ የቀረበዉን ማስፈቀጃ ያልተቀበለ እንደሆነ ግን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.287 መሰረት ወዲያዉኑ ለከሳሽ ፍርድ መስጠት እንደሚገባዉ ማየት ይቻላል። ይህ የተፋጠነ ሥነሥርዓት የክርክር አመራር የሰዎችን የመከላከል የመሰማት የመደመጥ ሕገ መንግስታዊ መብትን በሚደፈጥጥ መልኩ መተርጎም እና ሥራ ላይ መዋል እንደማይገባዉ የሚያከራከር አይደለም።
በዚህ አግባብ አሁን ወደ ተያዘዉ ጉዳይ ስንመለስ የአሁን አመልካች ባቀረበዉ ክርክር የብድር ዉሉ የተደረገዉ በማስመሰል ነዉ፣ በመካከላችን የኮንዶሚኒያም ቤት ሽያጭ ዉል በሕግ በተከለከለዉ የጊዜ ገደብ ዉስጥ በመደረጉ ለተጠሪ መተማመኛ እንዲሆናቸዉ ይህን የብድር ዉል ፈረምኩኝ እንጂ የተበደርኩት ገንዘብ የለም የሚል ነዉ። አመልካች ባቀረበዉ ክርክር ለተጠሪ የኮንዶሚኒያም ቤት በመሸጥ ገንዘብ ከመቀበል ዉጭ በዚህ የብድር ዉል ምንም ዓይነት ገንዘብ አልተቀበልኩም በማለት በመከራከር ላይ ይገኛል። ይህ ከሆነ ደግሞ የአሁን አመልካች እና ተጠሪ መካከል የኮንዶሚኒያም ቤት ሽያጭ ዉል ተደርጓል ወይስ አልተደረገም? ይህ የብድር ዉል ከኮንዶሚኒያም ቤት ሽያጭ ዉል ጋር ግንኙነት አለዉ ወይስ የለዉም? ሁለት ዉሎች አሉ ወይስ የሉም? የዉሎቹ ቁርኝት ወይም ግንኙነት ምንድን ነዉ? የሚሉት ነጥቦች ከግራ ቀኛቸዉ በሚቀርበዉ ክርክርና ማስረጃ መመርመር የሚገባቸዉ ጉዳዮች ናቸዉ።
ይህ ከሆነ ደግሞ የሥር ፍ/ቤቶች አመልካች የመከላከያ ክርክሩን እንዲያቀርብ ላፈቅዱለት የሚገባቸዉ የሚያመለክት ነዉ።
ሲጠቃለል የሥር ፍ/ቤቶች በዚህ መሰረት አመልካች የመከላከያ መልስ እንዲያቀርብ በመፍቀድ ሙሉ የመከላከያ ክርክሩን እንዲያቀርብ በማድረግ ተገቢዉን ማጣሪያ በማድረግ ዉሳኔ መስጠት ሲገባዉ አመልካች ያቀረበዉን የመከላከያ ማስፈቀጃ ማመልከቻ ዉድቅ በማድረግ የሰጡት ዉሳኔዎች መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመባቸዉ ስለሆኑ የሚከተለዉ ተወስኗል።
የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመ.ቁ.234216 በ28/6/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ እና ይህን ዉሳኔ በማጽናት የፍድራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በመ.ቁ.176598 በ14/11/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመባቸዉ ስለሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348 /1/ መሰረት ተሽሯል።
የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የተዘጋዉን መዝገብ በማንቀሳቀስ በፍርድ ሐተታዉ በተመለከተዉ አግባብ መደበኛ የክርክር አመራር ሰርዓት ተከትሎ የአሁን አመልካች የመከላከያ መልስ እና ክርክሩን እንዲያቀርብ በማድረግ፣ በሕጉ አግባብ ግራ ቀኛቸዉን በማከራከር በማጣራት ተገቢ ነዉ ያለዉን ዉሳኔ እንዲሰጥበት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.343 /1/ መሰረት ተመልሶለታል።
የዚህ ዉሳኔ ግልባጭ ለሥር ፍ/ቤቶች ይድረስ።
ግራ ቀኛቸዉ በዚህ ችሎት የደረሰባቸዉን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸዉን ይቻሉ።
ነሐሴ 11 ቀን 2008 ዓ.ም የተሰጠዉ የአፈጻጸም እግድ በዚህ ዉሳኔ ተነስቷል። ይጻፍ።
No topics extracted.