•ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በተለይ ካልፈቀደ በቀር ይግባኝ ባይ በይግባኝ ማመልከቻ ላይ ዘርዝሮ ያልገለጸውን አዲስ ነገር በማንሳት ወይም መሰረት በማድረግ ለመከራከር የማይችል ስለመሆኑ፡- •ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በይግባኝ ማመልከቻ ተዘርዝሮ ከተገለጸ ወይም ክርክር ከተነሳበት ውጭ በሆነ ነገር ወ/ሮ ለተብርሃን ያይንሸት እና አቶ የማነ በየነ X መስጠት የማይችል ስለመሆኑ፡የፍትሐብሕር ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 328 /2/፤328 /3/
No summary available.
ህዳር 28 ቀን 2010 ዓ/ም ዳኞች፡- አልማው ወል ሙስጠፋ አህመድ አብርሃ መሰለ ጰውሎስ ኦርሺሶ ሰናይት አድነው አመልካች፡- ወ/ሮ ለተብርሃን ያይንሸት - የቀረበ የለም ከተባለ በኋላ ቀረቡ ተጠሪ፡- አቶ የማነ በየነ - የቀረበ የለም መዝገቡ ተመርምሮ ቀጥሎ ያለው ፍርድ ተሰጥቷል።
የክርክሩ ምክንያት የባልና ሚስት ንብረት ክፍፍልን የሚመለከት ነው። ጉዳዩ የተጀመረው በፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን የአሁን አመልካች ተጠሪ የነበሩ ሲሆን የአሁን ተጠሪ ደግሞ አመልካች ነበሩ። የአሁን ተጠሪ የግል እና የጋራ ንብረቶች ናቸው ያሉዋቸውን የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችን፣ የባንክ ገንዘብ እንዲሁም የኮንደሚኒየም ቤት ቁጠባ በተመለከተ አመልካች ተጠሪን ሳያገቡ የተመዘገቡ በመሆኑ የሥር አመልካች/የአሁን ተጠሪ/ የግል ንብረታቸው መሆኑን ገልጸው ቤቱም ያልደረሳቸው በመሆኑ መካፈል አይችሉም በማለት ውሳኔ እንዲሰጥበት ዳኝነት ጠይቀዋል።
የአሁን አመልካች /የሥር ተጠሪ/ በሰጡት መልስ የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችን በተመለከተ የግልና የጋራ ንብረቶች ናቸው ያሉዋቸውን በዝርዝር በማቅረብ እነዚህ ንብረቶች እንዲሁም በወጋገን ባንክ ያለው ገንዘብ እኩል እንዲካፈል፣ የማይንቀሳቀስ ንብረትን በተመለከተ አመልካች /የአሁን ተጠሪ/ በልጁ ስም በ40/60 የኮንደሚኒየም ቤት የቆጠበውን ገንዘብ ላካፈል ይገባል፣ ከ1997 ዓ/ም ጀምሮ በአመልካች ስም የተጠራቀመውን ገንዘብ ልንካፈል ይገባል በማለት ተከራክረዋል።
ጉዳዩን የተመለከተው የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተለያዩ ማስረጃዎችን እንዲቀርቡለት ካደረገ በኃላ የግልና የጋራ ንብረቶች ናቸው ባላቸው የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች፣ ወጋገን ባንክ ያለው ገንዘብ ላይ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን የኮንደሚኒየም ቤት በተመለከተ አመልካችና ተጠሪ ጋብቻ የፈጸሙት ጳጉሜ 2 ቀን 2002 ዓ/ም ሲሆን አመልካች /የአሁን ተጠሪ/ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ መቆጠብ የጀመሩት እ.ኤ.አ በ20/6/2013 ነው። ይህም ጊዜ ሲታይ አመልካች ለኮንደሚኒየም ቤት የቆጠቡት ገንዘብ ከተጠሪ ጋር በጋብቻ ውስጥ እንዳሉ ነው። በመሆኑም አመልካች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦል ቡልቡላ ቅርንጫፍ ከቆጠቡት ገንዘብ ከፊሉን ብር 7,227.23 /ሰባት ሺህ ሁለት መቶ ሃያ ሰባት ብር ከሃያ ሶስት ሳንቲም/ ለተጠሪ ይክፈሉ። የ40/60 ኮንደሚኒየም ቤት በተመለከተ የአሁን አመልካች /የሥር ተጠሪ/ በማስረጃ ስላላስረዱ ታልፏል በማለት ወስኗል።
የአሁን አመልካች የአሁን ተጠሪ የግል ንብረቶች ናቸው ተብሎ በተሰጠው ውሳኔ፣ ከወጋገን ባንክ የአሁን ተጠሪ ጋብቻ ከመፍረሱ በፊት ያወጡትን 100,000.00 /አንድ መቶ ሺህ ብር/ ሳይወስን ያለፈው ያለአግባብ ነው፣ በልጅ ቀለብ ውሳኔ ላይ እንዲሁም የኮንደሚኒየም ቤት ምዝገባ የተደረገውና ቁጠባ የተጀመረው በጋብቻ ውስጥ በመሆኑና የኮንደሚኒየም ቤቱ ከጋብቻ ፍቺ ውሳኔ በኃላ የደረሰ ቢሆንም የንብረት ክፍፍል ጉዳይ በክርክር ላይ እያለ የደረሰ በመሆኑ ቤቱን በጋራ መካፈል ሲገባን የተቆጠበውን ገንዘብ ድርሻ የአሁን ተጠሪ ለአመልካች ይክፈሉ ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ ያለአግባብ ነው በማለት ይግባኝ ለፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዋል።
የይግባኝ ሰሚው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኙን ተቀብሎ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኃላ የቤት ቁሳቁሶች ላይ የተሰጠውን ውሳኔ በማጽናት፣ ከወጋገን ባንክ የአሁን ተጠሪ ያወጡትን ገንዘብ በተመለከተ ለትዳር ጥቅም እንደዋለ ባለማስረዳታቸው ግማሽ ብር 50,000 /አምሳ ሺህ ብር/ ለአሁን አመልካች እንዲከፍሉ፣ የልጅ ቀለብ ከአንድ ሺህ ብር ወደ ሁለት ሺህ ብር ከፍ በማድረግ እንዲሁም የኮንደሚኒየም ቤቱን በተመለከተ ምዝገባ የተደረገው ግራ ቀኙ ጋብቻ ውስጥ እያሉ መሆኑን፣ ለቤቱ ገንዘብ የተቆጠበውም በትዳር ውስጥ እያሉ በመሆኑ የአሁን ተጠሪ ከፍቺ ውሳኔ በኃላ ለኮንደሚኒየም ቤቱ የከፈሉትን ገንዘብ ግማሽ አመልካች መልሰው /ከፍለው/ ቤቱ የጋራ ላሆን ይገባል ሲል የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማሻሻል ወስኗል።
የአሁን ተጠሪ ከውሳኔዎቹ መካከል በባንክ ገንዘብ እና በኮንደሚነየም ቤት ላይ የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ለፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርበዋል። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኙን ተቀብሎ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኃላ የአሁን ተጠሪ ከባንክ ያወጡትን ገንዘብ ግማሽ ለአሁን አመልካች እንዲከፍሉ የተባለውን የውሳኔ ክፍል አጽንቶ የኮንደሚኒየም ቤቱን በተመለከተ አመልካች ለፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መልስ ሲሰጡ የተጠራቀመው ገንዘብ ድርሻ እንዲሰጠኝ በማለት የጠየቁ በመሆናቸው ከጠየቁት ዳኝነት ውጪ ቤቱን እንዲካፈሉ ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ ተገቢ አይደለም በማለት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በማጽናት የከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል።
ለዚህ የሰበር አቤቱታ ምክንያት የሆነውም የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በኮንደሚኒየም ቤት ላይ የሰጠው ውሳኔ ሲሆን አመልካች በሥር ፍርድ ቤት ተፈጽመውብኛል ያሉዋቸውን ዝርዝር የቅሬታ ነጥቦችን በጠበቃቸው በኩል አቅርበዋል።
የሰበር አቤቱታውን አጣሪው መርምሮ የኮንደሚኒየም ቤት ላይ ግልጽ የሆነ ክርክር አድርገው እያለ የሥር ፍርድ ቤት ያልተጠየቀ ዳኝነት የማለቱ እና ኮንደሚኒየም ቤቱ ምዝገባ ወቅት ግራ ቀኙ በጋብቻ ውስጥ የነበሩና ሲቆጥቡ ቆይተው የግራ ቀኙ ጋብቻ ፍቺ ተወስኖ የንብረት ክፍፍል ሳይደረግ የወጣ የኮንደሚኒየም እጣ በተመለከተ የኮንደሚኒየም ቤቱ የተጠሪ የመባሉ አግባብነት መጣራት ያለበት መሆኑ ስለታመነበት ጉዳዩ ለሰበር ችሎት ይቅረብ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ለተጠሪ ጥሪ ተደርጎላቸው በጠበቃቸው በኩል ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ/ም የተጻፈ መልስ አቅርበው የተከራከሩ ሲሆን የአመልካች ጠበቃም ሰኔ 5 ቀን 2009 ዓ/ም የተጻፈ የመልስ መልስ አቅርበዋል።
የነገሩ አመጣጥና የክርክሩ ሂደት በአጭሩ ከላይ የተገለጸውን የሚመስል ሲሆን አመልካች የኮንደሚኒየም ቤት ድርሻ እንዲወሰንላቸው በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያላነሱትን የከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰነው ባልተጠየቀ ዳኝነት ተብሎ በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሻረውን በተመለከተ የአሁን ተጠሪ በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በነበረው ክርክር በራሳቸው ይህንን አንስተው ተከራክረውበታል ወይስ ፍርድ ቤቱ በራሱ አንስቶ ነው ውሳኔ የሰጠው ? የሚል ጭብጥ ተይዞ ጉዳዩ እንደሚከተለው ተመርምሯል። የአሁን ተጠሪ ኮንደሚኒየም ቤቱን በተመለከተ ከጋብቻ በፊት መመዝገባቸውን፣ ቤቱም ያልደረሳቸው መሆኑን ገልጸው በንብረት ክፍፍል ግን ላካተት የማይችል የግል ንብረት ነው በማለት የፍድራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በነበረው የዳኝነት ጥያቄያቸው ላይ አንስተዋል። የአሀኑ አመልካች መልሳቸውን በጽሁፍ የመስጠት መብታቸው በሥር ፍርድ ቤት የታለፈባቸው ቢሆንም በቃል ክርክር ጊዜ የኮንደሚኒየም ቤቱ በጋብቻ ውስጥ በአሁን ተጠሪ ስም የተመዘገበ መሆኑንና የቁጠባ ገንዘብ መከፈል የጀመረውም በጋብቻ ውስጥ እያሉ መሆኑን ገልጸው የተጠራቀመው ገንዘብ ድርሻቸው እንዲወሰንላቸው ተከራክረዋል።
ጉዳዩን የተመለከተው የፍድራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአሁን ተጠሪ ለኮንደሚኒየም ቤት ምዝገባ የተመዘገቡት ግራ ቀኙ ከተጋቡ በኃላ በጋብቻ ውስጥ እያሉ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦል ቡልቡላ ቅርንጫፍ በአሁን ተጠሪ ስም በተከፈተው ሂሳብ ቁጥር መቆጠብ የተጀመረውም ግራ ቀኙ በጋብቻ ውስጥ እያሉ መሆኑን ገልጾ ከተጠራቀመው ብር 14,454.46 /አስራ አራት ሺህ አራት መቶ አምሳ አራት ብር ከአርባ ስድስት ሳንቲም/ ውስጥ ለአሁን አመልካች ብር 7,227.23 /ሰባት ሺህ ሁለት መቶ ሃያ ሰባት ብር ከሃያ ሶስት ሳንቲም/ የአሁን ተጠሪ ላከፍሉ ይገባል ሲል ወስኗል።
የአሁን አመልካች በይግባኝ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሄዱበትም የኮንደሚኒየም ቤት ምዝገባ የተደረገው እና ገንዘብ መቆጠብ የተጀመረው በጋብቻ ውስጥ እያሉ መሆኑን ገልጸው የኮንደሚኒየም ቤት ለአሁን ተጠሪ የደረሳቸው ምንም እንኳን የፍቺው ውሳኔ ከተሰጠ በኃላ ቢሆንም እጣ የወጣው በንብረት ክርክር ላይ እያሉ በመሆኑ ቤቱ የጋራ ንብረት ነው ተብሎ ላወሰን ይገባል በማለት ነው። የከፍተኛ ፍርድ ቤቱም ለውሳኔው መሰረት ያደረገው ይህንን ነጥብ እንደሆነ የውሳኔው ግልባጭ ያስረዳል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለማሻሻል ምክንያት ያደረገው አመልካች የኮንደሚኒየም ቤቱን ላካፈል ይገባል የሚል ዳኝነት በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስላላነሱ የመከራከሪያ ነጥብ ሆኖ ውሳኔ ያላገኘውን ፍሬ ነገር ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መስጠቱ አግባብነት የለውም የሚል ነው።
የአሁን አመልካች ለዚህ ሰበር ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ ላይ እንዲሁም በመልስ መልሳቸው የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ተጠሪው አመልካች የኮንደኒየም ቤት ያካፍለኝ ብላ በሥር ፍርድ ቤት አልጠየቀችም የሚል በይግባኝ ቅሬታው አላቀረበም፣ የይግባኝ ሰሚው ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዚህ ዓይነት ቅሬታ በጽሁፍም በቃልም ያከራከረው ነገር የለም። ይህ በሆነበት ሁኔታ ፍርድ ቤቱ በተጠሪ /በሥር ይግባኝ ባይ/ በኩል በይግባኝ ቅሬታ ላይ ያልተነሳውን አንስቶ መወሰኑ የሥነ ሥርዓት ህጉን ድንጋጌ የተከተለ አይደለም በማለት ተከራክረዋል። ይህን የቅሬታ ነጥብ እውነታ ለማረጋገጥ ይህ ችሎት የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍ/ይ/መ/ የሆነውን አስቀርቦ ተመልክቷል። የአሁን ተጠሪ /የሥር ይግባኝ ባይ / ለፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረቡት ቅሬታ ከመልስ ሰጪዋ /ከአሁን ተጠሪ / ጋር ከፍቺ በኃላ በተደረገ የንብረት ክፍፍል ከጋብቻ በፊት በይግባኝ ባይ በተደረገ የኮንደሚኒየም ቤት ምዝገባ፣ ከጋብቻ መፍረስ በኃላ በወጣልኝ እጣ በተፈጸመ ክፍያ ምክንያት የተገኘን የኮንደሚኒየም ቤት እንዲሁም ጋብቻው ጸንቶ ባለበት ጊዜ ከአስተዳደር አካል በተሰጠው ትዕዛዝ ምክንያት መልሶ ምዝገባ መደረግን ብቻ ምክንያት በማድረግ የኮንደሚኒየም ቤት የጋራ ነው ተብሎ በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ መወሰኑ አግባብ ስላልሆነ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሸሮ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ትዳሩ ፀንቶ በነበረበት ወቅት ከተቆጠበው ገንዘብ ላይ ድርሻዋን እንድትወስድ በማለት የወሰነውን የውሳኔ ክፍል በማጽደቅ የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ አሻሽሎ እንዲወስንልኝ እጠይቃለሁ የሚል እንደሆነ የክርክሩ ሂደት እንዲሁም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በግልጽ ያሳያል።
የአሁን ተጠሪ በጠቅላይ ፍርድ ቤት በነበረው ክርክር በኮንደሚኒየም ቤቱ ላይ ብቸኛ ባለመብት ያደርገኛል በማለት ያቀረቡት የመጀመሪያው ነጥብ በ1997 ዓ/ም መመዝገባቸውን ሲሆን ሁለተኛው ሰኔ 4 ቀን 2006 ዓ/ም ጋብቻ ፈርሶ ሚያዚያ ወር 2007 ዓ/ም እጣ ወጥቶላቸው ውል መዋዋላቸውን ነው።
ከላይ የተመለከተውን በፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የነበረውን የአሁን ተጠሪን ክርክር ስንመለከት ክርክር ያስነሳውን የኮንደሚኒየም ቤት የአሁን አመልካች ይገባኛል ወይም ድርሻ ይሰጠኝ የሚል ክርክር በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያላነሱትን የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል የሚል ቅሬታ በይግባኝ ማመልከቻም ሆነ በቃል ክርክር ወቅት የተነሳ ነገር አልነበረም። የሥር ይግባኝ ባይ /የአሁን ተጠሪ/ በይግባኛቸው ያላነሱትን አዲስ ነገር የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት በራሱ አንስቶ መወሰን ይችላል ወይ? የሚለውን አግባብነት ካለው የፍትሓብሕር ሥነ ሥርዓት ህግ ድንጋጌ አንጻር መመልከት አስፈላጊ ነው። ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በተለይ ካልፈቀደ በቀር ይግባኝ ባዩ በይግባኝ ማመልከቻው ላይ ዘርዝሮ ያልገለጸውን አዲስ ነገር በማንሳት ወይም መሰረት በማድረግ ለመከራከር አይችልም ሲል የፍትሓብሕር ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 328 /2/ ይደነግጋል። ከዚህ በተጨማሪ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በማመልከቻው ተዘርዝሮ ከተገለጸው ወይም ክርክር ከተነሳበት ውጭ በሆነ ነገር ፍርድ መስጠት እንደማይችል የፍትሓብሕር ሥነ ሥርዓት ህጉ አንቀጽ 328 /3/ በአስገዳጅነት ደንግጓል።
ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ ከላይ እንደተገለጸው የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአሁን ተጠሪ በይግባኝ ማመልከቻ ላይ ዘርዝረው ያልገለጹትን መሰረት በማድረግ አመልካች የኮንደሚኒየም ቤት ይገባኛል ሲሉ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያልጠየቁትን ዳኝነት መሰረት በማድረግ የከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ተገቢ አይደለም ሲል የደረሰው ድምዳሜ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም የሚከተለው ውሳኔ ተሰጥቷል።
1.የፍድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍ/ይ/መ/ቁ.130707 ታኅሳስ 12 ቀን 2009 ዓ/ም ግራ ቀኙን የሚያከራክረውን የኮንደሚኒየም ቤት በተመለከተ የሰጠው ውሳኔ በፍትሓብሕር ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 348 /1/ መሰረት ተሽሯል።
2.የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠው ልላው የውሳኔ ክፍል ፀንቷል።
3.የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ. 168169 ሚያዚያ 26 ቀን 2008 ዓ/ም ክርክር የተነሳበትን ቤት በተመለከተ የሰጠው ውሳኔ ፀንቷል።
4.በቱሉ ዲምቱ ቁጥር 2 ሳይት ብሎክ 362 የሚገኘውና የሆነው በተጠሪ ስም የተመዘገበው የኮንደሚኒም ቤት የአመልካችና የተጠሪ የጋራ ንብረት ነው ተብሎ ተወስኗል። ስለሆነም ቤቱን ግራ ቀኙ በዓይነት እኩል እንዲካፈሉ፣ በዓይነት እኩል ለመካፈል የማይቻል ከሆነና ግራ ቀኙ ከተስማሙ የቤቱን ዋጋ አንደኛው ወገን የልላኛውን ወገን ድርሻ በገንዘብ በመክፈል ቤቱን እንዲያስቀር፣ በዚህ ካልተስማሙ ቤቱ በሀራጅ ተሸጦ ገንዘቡን እኩል እንዲካፈሉ ብለናል።
5.የዚህን ችሎት ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
6.የውሳኔው ግልባጭ ለሥር ፍርድ ቤቶች ይድረሳቸው።
7.መዝገቡ ውሳኔ ስላገኘ ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ።
No topics extracted.