የይዞታ ክርክርን በተመለከተ አንድ ተከራካሪ ወገን ካርታዉ እንደተሰረዘ እና በዚያ ካርታ ይዞታዉን ለመጠየቅ መብት እንደልለዉ ዉሳኔ ተሰጥቶ እያለ ተከራካሪ ወገን በመቀየር ክስ ስላቀረበ ብቻ የክርክሩ ጭብጥና ተከራካሪ ወገን ስለሚለያይ ከዚህ ቀደም ዉሳኔ ተሰጥቷል የሚያስብል አይደለም በማለት አዲስ ክስ ማቅረብ የማይችል ስለመሆኑ፡የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 5(1)
No summary available.
ታህሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡ ...1.ዳኜ መላኩ 2. ተኽላት ይመሰል 3. ተፈሪ ገብሩ (ዶ/ር) 4. ቀነዓ ቂጣታ 5. ፀሐይ መንክር አመልካች፡- .....አቶ ሱፍያን አቡበከር ቀርበዋል ተጠሪዎች፡- .....1.አቶ ክፍሉጋሼ የቀረበ የለም 2. ወ/ሮ ዘዉድ መኩሪያ ይህ መዝገብ የተቀጠረዉ ለምርመራ ሲሆን ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የይዞታ ክርክርን የሚመለከት ሲሆን ለችሎቱ ላቀርብ የቻለዉ የአሁን አመልካች የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.233491 22/9/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ መርምሮ ለመወሰን ነዉ።
የጉዳዩ መነሻ ሲታይ በአደኣ ወረዳ ፍ/ቤት የአሁን አመልካች 1ኛ የመቃወም ተጠሪ እና የአሁን ተጠሪዎች የመቃወም አመልካቾች፣ በዚህ ችሎት የክርክሩ ተካፋይ ያልሆነዉ የቢሾፍቱ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት አጄንሲ 2ኛ የመቃወም ተጠሪ ሆኖ ሲከራከሩ ነበር። የጉዳዩ መነሻ የአሁን አመልካች የቢሾፍቱ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት አጄንሲ ላይ ባቀረበዉ ክስ መሆኑን የሥር ዉሳኔ ግልባጭ ያሳያል።
የወረዳዉ ፍ/ቤት ከሳሽ እና ተከሳሽን በማከራከር በሰጠዉ ዉሳኔ በቢሾፍቱ ከተማ ቀበል 01 ክልል ዉስጥ የሚገኘዉን 9936 ካ.ሜ የሆነዉን ቦታ ተከሳሽ ለከሳሽ እንዲያስረክብ በማለት ዉሳኔ ሰጥቷል።
ይህን ዉሳኔ ተከትሎ የመቃወም አመልካቾች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.358 መሰረት ባቀረቡት አቤቱታ ለክርክር ምክንያት የሆነዉ ይዞታ የ1ኛ የመቃወም ተጠሪ የአቶ ሱፊያን አቡበከር ሳይሆን የእኛ ነዉ፣ ይዞታዉ ከእጃችን ወጥቶ አያዉቅም፣ በዚህ ጉዳይ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.163687 በ11/2/2006 ዓ.ም ዉሳኔ የሰጠ በመሆኑ 1ኛ የመቃወም ተጠሪ በተሰረዘ ካርታ መክሰስ መብት የለዉም፣ ስለዚህ የተሰጠዉ ዉሳኔ እንዲሻርልን በማለት ጠየቋል።
በዚህ የመቃወም ማመልከቻ ላይ 1ኛ የመቃወም ተጠሪ አቶ ሱፊያን አቡበከር ባቀረበዉ መልስ ለክርክር ምክንያት የሆነዉ ይዞታ በሕግ አግባብ የተሰጠኝ ነዉ፣ ካርታ አልተሰረዘም፣ ይዞታዉ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1996 ዓ.ም ግብር እየከፈልኩኝ ስጠቀምበት ነበር፣ የመቃወም አመልካቾች መብት ሳይኖራቸዉ ነዉ ይህን መሬት ወጥተዉ ያረሱት በማለት ተከራክሯል። 2ኛ የመቃወም ተጠሪ የብሾፍቱ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት አጄንሲ ባቀረበዉ መልስ ከዚህ በፊት የ1ኛ ተጠሪ ካርታ መሰረዙ ተረጋግጦ ከይዞታዉ መብት እንደልለዉ ዉሳኔ የተሰጠ በመሆኑ የ1ኛ ተጠሪ ክስ ተቀባይነት የለዉም በማለት ተከራክሯል።
የአደኣ ወረዳ ፍ/ቤት የግራ ቀኛቸዉን ክርክር በመመርመር በሰጠዉ ዉሳኔ ለክርክር ምክንያት የሆነዉ ይዞታ በተመለከተ ለ1ኛ የመቃወም ተጠሪ የተሰጠዉ ካርታ ያልተሰረዘ መሆኑን ማህደሩ ያረጋግጣል፣ የመቃወም አመልካቾች በይዞታዉ ላይ ባለመብት ቢሆኑም መሬታቸዉን ለልላ ሰዉ አሳልፈዉ የሰጠዉን አካል ከሶ ከሚጠይቁ በስተቀር 1ኛ የመቃወም ተጠሪ በሕገ ወጥ መንገድ ይዟል የሚያስብል ስላልሆነ፣ ከዚህ በፊት የተሰጠዉ ዉሳኔ የሚያፈርስ ምክንያት ስለልለ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሀ/ቁ.360/1/ መሰረት ጸንቷል። የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት የቀረበለትን ይግባኝ ዉድቅ በማድረግ የሥር ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል።
የሥር የመቃወም አመልካቾች በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት የሰበር አቤቱታ ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡ ሲሆን ችሎቱ ግራ ቀኛቸዉን በማከራከር በሰጠዉ ዉሳኔ ከዚህ በፊት ይህ ችሎት በመ.ቁ.163687 በ11/2/2006 ዓ.ም በሰጠዉ ዉሳኔ ለ1ኛ ተጠሪ አቶ ሱፊያን አቡበከር ካርታ ቀሪ ሆኖ የተሰረዘ መሆኑን፣ ይዞታዉ በእጁ ሳይኖር ግብር መክፈሉ ብቻ ባለመብት እንደማያደርገዉ እና አቶ ሱፊያን በዚህ ይዞታ ላይ መብት የለዉም በማለት የሥር ፍ/ቤቶችን ዉሳኔ በመሻር ዉሳኔ ሰጥቶ እያለ የሥር ፍ/ቤቶች በዚህ ጉዳይ ድጋሚ አጣርተዉ ዉሳኔ መስጠታቸዉ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነዉ በማለት የሥር ፍ/ቤቶችን ዉሳኔ በመሻር ወስኗል።
የአሁን የሰበር አቤቱታ የቀረበዉ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ለማስለወጥ ነዉ።
የአሁን አመልካች በ3/5/2009 ዓ.ም በተጻፈ የሰበር አቤቱታ፡ ለክርክር ምክንያት የሆነዉ ይዞታ ብሾፍቱ ከተማ በሕግ አግባብ የተሰጠኝ ካርታም ተሰጥቶኝ እና ከ1983 ዓ.ም ስጠቀምበት የነበረ ሆኖ ሳለ፣ ለአመልካች የተሰጠ ካርታ ያልተሰረዘ መሆኑን ተረጋግጦ እያለ፣ በዚህ ጉዳይ ከዚህ በፊት ዉሳኔ ተሰጥቷል የተባለዉ እና አሁን የቀረበዉ ክርክር የተለያዩ ጭብጦችና ተከራካሪ ወገኖች በመሆኑ አስቀድሞ ዉሳኔ ተሰጥቷል የሚያስብል ነገር በልለበት የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲታረምልኝ ኪሳራ እንዲወሰንልኝ በማለት በዝርዝር አመልክቷል።
የሰበር አጣሪ ችሎት ጉዳዩን በማየት ፣በዚህ ጉዳይ ከዚህ በፊት ዉሳኔ ያገኘ ጉዳይ ነዉ በማለት ዉሳኔ የመስጠቱን አግባብነት ለመመርመር ሲባል አቤቱታዉ ያስቀርባል በማለት ተጠሪዎች መልስ እንዲያቀርቡ ባዘዘዉ መሰረት ተጠሪ በ5/7/2009 ዓ.ም በተጻፈ መልስ፡ በዚህ ጉዳይ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠዉ ዉሳኔ የሕግም ሆነ የፍሬ ነገር ስህተት የልለዉ በመሆኑ እንዲጸናልን ወጪና ኪሳራ እንዲወሰንልን በማለት በዝርዝር ተከራክሯል። የአሁን አመልካች የመልስ መልስ አቅርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ ተመለከተዉ ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኛቸዉን ክርክር አግባብነት ካላቸዉ የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንዲሁም አቤቱታዉ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘዉ ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለዉ መርምሮታል። እንደመረመርነዉ የአሁን አመልካች ከዚህ ቀደም ይህን ይዞታ በተመለከተ የአሁን ተጠሪዎችን ጨምሮ በአራት ሰዎች ላይ ክስ አቅርበዉ ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.163687 በ11/2/2006 ዓ.ም በሰጠዉ ዉሳኔ ለአሁን አመልካች የተሰጠዉ ካርታ የተሰረዘ መሆኑን በሥር ፍ/ቤት የቀረበ ማስረጃ እንደሚያረጋግጥ በማመልከት፣ ይዞታዉም በአመልካች እጅ ሳይገባ እስከ 2004 ዓ.ም ግብር መክፈሉ ባለመብት እንደማያደርገዉ እና አመልካች በተሰረዘ ካርታ ይዞታዉን በተመለከተ ክስ ማቅረብ አይችልም በማለት ዉሳኔ የሰጠ መሆኑን የሥር ዉሳኔ ግልባጭ ያመለክታል።
የአሁን አመልካች ከዚህ ዉሳኔ በኋላ ባቀረበዉ አዲስ ክስ ካርታዉ እንዳልተሰረዘ እና የብሾፍቱ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ኤጄንሲ ይህን ይዞታ እንዲያስረክበዉ ዳኝነት በመጠየቁ፣ ኤጄንሲዉ የአመልካች ክስ ተቀባይነት እንደልለዉ በመግለጽ ቢከራከርም፣ የሥር ፍ/ቤት ለአመልካች የተሰጠ ካርታ እንዳልተሰረዘ እና ኤጄንሲዉ መሬቱን እንዲያስረክብ ዉሳኔ ሰጥቷል። የአሁን ተጠሪዎች ደግሞ ይህን ዉሳኔ በመቃወም የመቃወሚያ ማመልከቻ አቅርበዉ ቢከረከሩም፤ የሥር ወረዳ ፍ/ቤት እና ከፍተኛ ፍ/ቤት አስቀድመዉ ካርታዉ እንደተሰረዘ እና ለክርክር ምክንያት በሆነዉ ይዞታ ላይ ዉሳኔ ተሰጥቷል በማለት ያቀረበዉን መቃወሚያ በማለፍ ዉሳኔ መስጠታቸዉን መገንዘብ ይቻላል። ነገር ግን የክልል ሰበር ሰሚ ችሎት ይህን ሁኔታ በመገንዘብ የአሁን አመልካች ከዚህ ቀደም ዉሳኔ በተሰጠበት ጉዳይ አዲስ ክስ ማቅረብ እንደማይችል መወሰኑን የሥር ዉሳኔ ያሳያል።
በዚህ መሰረት ይህ ችሎት ጉዳዩን እንደመረመረዉ የአሁን አመልካች ከዚህ ቀደም የአሁን ተጠሪዎችን ጭምሮ በአራት ሰዎች ላይ ክስ አቅርበዉ ዉሳኔ የተሰጠበትን ጉዳይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.5 /1/ መሰረት ድጋሚ አዲስ ክስ የሚያቀርብበት የሕግ አግባብ የለም። የአሁን አመልካች ካርታዉ እንደተሰረዘ እና በዚህ ካርታ ይዞታዉን ለመጠየቅ መብት እንደልለዉ ዉሳኔ ተሰጥቶ እያለ ተከራካሪ ወገን በመቀየር የብሾፍቱ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት አጄንሲ ላይ ክስ ስላቀረበ ብቻ የክርክሩ ጭብጥና ተከራካሪ ወገን ስለሚለያይ የዚህን ድንጋጌ መስፈርት አያሟላም፣ ከዚህ ቀደም ዉሳኔ ተሰጥቷል የሚያስብል አይደለም በማለት ያቀረበዉ ክርክር ተቀባይነት የለዉም። ስለዚህ የአሁን አመልካች ያቀረበዉ ክስ ከዚህ ቀደም ዉሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ ስለሆነ አዲስ ክስ ለማቅረብ አይችልም።
ሲጠቃለል የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የአሁን አመልካች ያቀረበዉ ክስ ከዚህ በፊት ዉሳኔ በተሰጠበት ጉዳይ ነዉ በማለት የሥር ፍ/ቤቶች ዉሳኔ በመሻር አመልካች ያቀረበዉን ክስ ዉድቅ በማድረግ የሰጠዉ ዉሳኔ በሕግ አግባብ ነዉ ከሚባል በስተቀር መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስላልሆነ የሚከተለዉ ተወስኗል።
የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ. 233491 22/9/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ትዕዛዝ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያልተፈጸመበት ስላልሆነ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ.348 /1/ መሰረት ጸንቷል።
የዚህ ዉሳኔ ግልባጭ ለሥር ፍ/ቤቶች ይድረስ።
ግራ ቀኛቸዉ በዚህ ችሎት የደረሰባቸዉን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸዉን ይቻሉ።
No topics extracted.