በትግራይ ክልል የጎጆ መውጫ ይዞታና ቤት የሚመለከትን ጉዳይ የቀበል መሬት ዳኝነት ኮሚቴ ጉዳዩን ተቀብሎ አይቶ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ በተሰጠዉ ዉሳኔ መብቴን ይነካል በማለት የመቃወሚያ ማመልከቻ ሲቀርብ የፍርድ መቃወሚያ ማመልከቻውን ተከትሎ የቀደመዉን ዉሳኔ የማጽደቅ ወይም የማሻሻል ወይም የመለወጥ ወይም የመሰረዝ ስልጣን ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ ያየው የቀበል መሬት ዳኝነት ኮሚቴ ስለመሆኑ፡- IX የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.358 ፣ 360(2)
No summary available.
ታህሳስ 23 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- 1.ዳኜ መላኩ 2. ተኽላት ይመሰል 3. ተፈሪ ገብሩ (ዶ/ር) 4. ቀነዓ ቂጣታ 5. ፀሐይ መንክር አመልካች፡- ወ/ሮ መረሳ አማረ - የቀረበ የለም ተጠሪዎች፡- 1.ቄስ ሃይለ ገብረ የቀረበ የለም 2. መቶ አለቃ ካልሃዩ ተስፋይ ይህ መዝገብ የተቀጠረዉ ለምርመራ ሲሆን ተመርምሮ የሚከተለዉ ፍርድ ተሰጥቷል።
ይህ የሰበር ጉዳይ የጎጆ መዉጫ ይዞታና ቤትን የሚመለከት ሲሆን ለችሎቱ ላቀርብ የቻለዉ የአሁን አመልካች የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.83091 በ19/09/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ እንዲታረምልኝ በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ መርምሮ ለመወሰን ነዉ።
የጉዳዩ መነሻ ሲታይ በተክዓ ቀበል መሬት ዳኝነት ኮሚቴ የአሁን አመልካች የመቃወም አመልካች፣የአሁን ተጠሪዎች ደግሞ የመቃወም ተጠሪዎች ሆኖ ሲከራከሩ ነበር።
የአሁን 2ኛ ተጠሪ በአሁን 1ኛ ተጠሪ ላይ ባቀረበዉ ክስ መነሻነት የቀበልዉ መሬት ዳኝነት ኮሚቴ ግራ ቀኛቸዉን በማከራከር በሰጠዉ ዉሳኔ የጎጆ መዉጫ ይዞታ ለአሁን 2ኛ ተጠሪ እንዲሆን የአሁን 1ኛ ተጠሪ ደግሞ የተሰራዉን ቤት ቆርቆሮዉን እና እንጨቱን አፍርሰዉ አንስተዉ እንዲወስዱ በማለት ወስኗል።፡ ከዚህ በኋላ የአሁን አመልካች የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.358 መሰረት የፍርድ መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን፣ የቀበልዉ መሬት ዳኝነት ኮሚቴ ጉዳዩን በማየት በሰጠዉ ብይን አመልካች ያቀረቡት የመቃወሚያ ማመልከቻ የብር 200,000 /ሁለት መቶ ሺህ/ ግምት ያለዉ የጎጆ መዉጫ ስለሆነ ኮሚቴዉ ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለዉም በማለት ማመልከቻዉን ዉድቅ በማድረግ ወስኗል።
የአሁን አመልካች በዚህ ብይን ቅር በመሰኘት ይግባኝ ለእምባ ኣላጀ ወረዳ ፍ/ቤት ያቀረቡ ሲሆን ፍ/ቤቱ ግራ ቀኛቸዉን በማከራከር በሰጠዉ ዉሳኔ የቀበልዉ መሬት ዳኝነት ኮሚቴ ይህን የጎጆ መዉጫ ክርክር ለማየት ስልጣን አለዉ በማለት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.341 መልሶለታል። ከዚህ በኋላ የአሁን አመልካች የይግባኝ ማመልከቻ ለማይጨዉ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት ያቀረቡ ቢሆንም ፍ/ቤቱ ይግባኙን ዉድቅ በማድረግ የሥር ዉሳኔ በማጽናት ወስኗል። የአሁን አመልካች አሁንም የሰበር አቤቱታ ለትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡ ቢሆንም ችሎቱ ይህ ጉዳይ ይግባኝ የሚባልበት አይደለም በማለት አቤቱታዉን ዉድቅ በማድረግ ወስኗል። አሁን የቀረበዉ አቤቱታ በዚህ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ለማስለወጥ ነዉ።
የአሁን አመልካች ባቀረቡት አቤቱታ የቀበልዉ መሬት ዳኝነት ኮሚቴ ግምት ያለዉን ንብረት ተቀብሎ ለመወሰን ስልጣን ሳይኖረዉ የተሰጠዉን ዉሳኔ በተመለከተ የሥር የክልል ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ እንዲሻርልኝ ወጪና ኪሳራ እንዲወሰንልኝ በማለት አመልክቷል።
የሰበር አጣሪ ችሎት ጉዳዩን በማየት ፣የሥር ፍ/ቤቶች ተገምተዉ ያልቀረበዉን ንብረት በመጀመሪያ ያየዉ ፍ/ቤት ስልጣን አለዉ በማለት የመወሰናቸዉ አግባብነት ለመመርመር ሲባል አቤቱታዉ ያስቀርባል በማለት ተጠሪዎች መልስ እንዲሰጡ ባዘዘዉ መሰረት ተጠሪዎች የየራሳቸዉን መልስ አቅርበዋል። ተጠሪዎች ባቀረቡትም መልስ አመልካች ያቀረቡት አቤቱታ ዉድቅ እንዲደረግ በዝርዝር ተከራክሯል። የአሁን አመልካች የመልስ መልስ አቅርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥ ከላይ የተመለከተዉ ሲሆን ይህ ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር አግባብነት ካላቸዉ የህግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንዲሁም አቤቱታዉ ያስቀርባል ሲባል ከተያዘዉ ጭብጥ አንጻር እንደሚከተለዉ መርምሮታል። እንደመረመርነዉ የአሁን አመልካች በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.358 መሰረት ያቀረቡት የመቃወሚያ ማመልከቻ በአሁን ተጠሪዎች መካከል ሲካሄድ ቆይቶ የተሰጠዉ ዉሳኔ መብቴን ይነካል በማለት ነዉ።
በዚህ መሰረት ይህን የፍርድ መቃወሚያ ማመልከቻን ተቀብሎ የማየት እና የቀደመዉን ዉሳኔ መለወጥ የሚችለዉ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.358 ሥር እንደተመለከተዉ ራሱ ፍርዱን የሰጠዉ አካል ነዉ። በዚህ ጉዳይም የቀበልዉ መሬት ዳኝነት ኮሚቴ ለክርክር ምክንያት የሆነዉን የጎጆ መዉጫ እና ቤት በተመለከተ ዉሳኔ የሰጠ አካል እስከሆነ ድረስ ይህን የሕግ ድንጋጌ መሰረት በማድረግ፣ አመልካች ባቀረቡት የፍርድ መቃወሚያ ማመልከቻ ተከትሎ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.360 /2/ መሰረት የቀደመዉን ዉሳኔ የማጽደቅ ወይም የማሻሻል ወይም የመለወጥ ወይም የመሰረዝ ስልጣን አለዉ። የቀበልዉ መሬት ዳኝነት ኮሚቴዉ በዚህ አግባብ አስቀድሞ የሰጠዉን ዉሳኔ የሚያጸድቀዉ ወይም የሚያሻሽለዉ ወይም የሚለዉጠዉ ወይም የሚያሰርዘዉ የአሁን አመልካች ያቀረቡትን አቤቱታ ተቀበሎ ጉዳዩን ያየ እንደሆነ ብቻ ነዉ። ኮሚቴዉ አመልካች ያቀረቡትን መቃወሚያ የማየት ስልጣን የለኝም በማለት ከጀምሩ ዉድቅ የሚያደርግ እንደሆነ አስቀድሞ የሰጠዉን ዉሳኔ በተመለከተ ምንም ሳይባል እንዳለ ስለሚሆን ከላይ የተመለከቱት የሕግ ድንጋጌዎችን ዓላማ የሚቃረን ይሆናል። የቀበልዉ መሬት ዳኝነት ኮሚቴ የፍርድ መቃወሚያ ማመልከቻዉን ተቀብሎ ግራ ቀኛቸዉን ከአከራከራቸዉ በኋላ አስቀድሞ የሰጠዉን ዉሳኔ የሚያጸድቅበት ወይም የሚያሻሽልበት ወይም የሚለዉጥበት በሕግ በተመለከተዉ አግባብ ሲሆን፣ ይህን የሚያደርገዉ በስልጣን ወይም በልላ ሕጋዊ ምክንያት ላሆን ይችላል። ስለሆነም ኮሚቴዉ አመልካች ያቀረቡትን የመቃወሚያ ማመልከቻ ተቀብሎ አስቀድሞ የሰጠዉ ዉሳኔ ምን መሆን አለበት በሚለዉ ነጥብ ላይ ዉሳኔ ላሰጥበት ይገባል እንጂ ከጅምሩ ማመልከቻዉን ለመቀበል ስልጣን የለኝም በማለት አስቀድሞ ስለሰጠዉ ዉሳኔ ምንም ሳይል መተዉ አግባብ አይደለም። የሥር የወረዳዉ ፍ/ቤት ይህን ሁኔታ በመገንዘብ የቀበልዉን መሬት ዳኝነት ኮሚቴ አመልካች ያቀረቡትን መቃወሚያ የማየት ስልጣን አለዉ በማለት የሰጠዉ ዉሳኔ ተገቢ ነበር። በመሆኑም የሥር የክልል ሰበር ሰሚ ችሎት ይህን የወረዳዉ ዉሳኔ ይግባኝ የሚባልበት አይደለም በማለት አመልካች ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ ዉድቅ በማድረግ የሰጡት ዉሳኔ በአግባቡ ነዉ።
ሲጠቃለል የሥር የሰበር ሰሚ ችሎት በዚህ ጉዳይ የሰጠዉ ዉሳኔ በሕግ አግባብ ነዉ ከሚባል በስተቀር መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ነዉ ለማለት ስለማይቻል የሚከተለዉ ተወስኗል።
የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ.83091 በ19/09/2008 ዓ.ም የሰጠዉ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያልተፈጸመበት ስለሆነ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.348 /1/ መሰረት ጸንቷል።
የዚህ ዉሳኔ ግልባጭ ለሥር ፍ/ቤቶች ይድረስ።
ግራ ቀኛቸዉ በዚህ ችሎት የደረሰባቸዉን ወጪና ኪሳራ የየራሳቸዉን ይቻሉ።
No topics extracted.