No summary available.
ቀን፡- 27/6/2010ዓ.ም ዳኞች፡- ዳኜ መላኩ ተኽላት ይመስል ተፈሪ ገብሩ (ዶ/ር) ቀነዓ ቂጣታ ፀሐይ መንክር አመልካች፡- ሼህ አደም ፋረስ ቀረቡ ተጠሪ፡- ሼህ ሙስጠፋ ፍላ ቀረቡ መዝገቡ መርምረን ተከታዩን ፍርድ ሰጥተናል።
ጉዳዩ በጋራ ንብረት ላይ ተደረገ የተባለዉ ስምምነት እንዲፈርስ የቀረበ ክስ የሚመለከት ክርክር ነዉ። ክርክሩ የጀመረዉ በቤ/ጉ/ክ/መንግስት የአሶሳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልካች በተጠሪ ላይ ባቀረቡት ክስ መነሻ ነዉ። አመልካች ባቀረቡት ክስም በአሶሳ ዞን አሶሳ ከተማ 03 ቀበል ክልል ዉስጥ በ 1000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አንድ ወፍጮ ቤት ህዳር 08 ቀን 1998 ዓ/ም በተደረገዉ ስምምነት በጋራ የያዙት ሲሆን ጥር 16 ቀን 2002 ዓ/ም በተፃፈዉ ዉል ንብረቱ ብር 90,000 ተገኝቶ አንዱ ወገን ንብረቱን እንዲያጠቃልል ስምምነት መደረጉን ከዚህ ገንዘብ ለጥገና ብር 20,000 ዉጪ ሆኖ ቀሪዉ 70,000 ለግራ ቀኙ የተከፋፈለ ሲሆን በግራ ቀኙ ስምምነትም ተጠሪ ለጊዜዉ ብር 15,000 ከፍለዉ ቀሪዉ 20,000 በሁለት ወር እንዲከፍሉ ስምምነት የተደረገ ቢሆንም ክፍያዉ አልተፈፀመም። የአመልካች ዕድሜ 80 ዓመት ሲሆን ዉሉም በዉልና ማስረጃ ያልተደረገ በመሆኑ ዉሉ ፈርሶ የንብረቱ ግምት አመልካች ከፍለዉ ንብረቱ እንዲያስቀሩ እንዲወሰን ጠይቋል።
ተጠሪ በበኩላቸዉ ባቀረቡት የመከላከያ መልስ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እንዲሁም በፍሬ ጉዳዩ መልስ ሰጥቷል። ባቀረቡት የመጀመሪያ መቃወሚያ ስምምነት ከተደረገ 6 ዓመት ያለፈዉ በመሆኑ በይርጋ እንደሚታገድ በፍሬ ጉዳዩ ደግሞ አመልካች የጠየቁት ቀሪ ክፍያ ብር 20,000 ለልጃቸዉ ወ/ሮ ሩቅያ አደም መክፈላቸዉን በመግለጽ ክሱ ዉድቅ እንዲሆን አመልክቷል።
መጀመሪያ ጉዳዩን የተመለከተዉ የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤትም በተጠሪ በኩል የቀረበዉን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ከመረመረ በኃላ ግራ ቀኙ ያደረጉት ዉል ጥር 15 ቀን 2002 ዓ/ም መሆኑን አመልካች የዉል ይሰረዝልኝ ጥያቄ ያቀረቡት በ 2008 ዓ/ም እንደሆነ በመግለጽ የፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ. 244/2/ እና የፍ/ሕ/ቁ. 1810(1) መሰረት በማድረግ የአመልካች ዉል ይሰረዝልኝ ጥያቄ የሁለት ዓመት ይርጋ ጊዜ ያለፈበት ነዉ በማለት በብይን ዉድቅ አድርጎታል። አመልካች በስር ፍ/ቤት ብይን ቅር በመሰኘት ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ እና ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት አላገኘም። የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበዉም የስር ፍ/ቤቶች ብይንና ትእዛዝ በመቃወም ለማሳረም ነዉ። አመልካች የካቲት 30 ቀን 2009 ዓ.ም ባቀረቡት የሰበር አቤቱታ ተጠሪ የአመልካች ዕድሜ መግፋት ተጠቅሞ ያታለሉ በመሆኑ ዉሉ እንዲሰረዝ የቀረበዉ ጥያቄ ዉድቅ መደረጉ በአግባቡ አለመሆኑን ይህ ቢታለፍ ቀሪ ክፍያ ብር 20,000 የመጠየቅ መብት ላታለፍ እንደማይገባ በመግለጽ የሥር ፍ/ቤቶች ብይን እንዲሻር ጠይቋል። ጉዳዩ ያጣራዉ ችሎትም የሥር ፍ/ቤት ጭብጥ አመሰራረትና የፍ/ሕ/ቁ. 1810 ለተያዘዉ ጭብጥ ያለዉ አግባብነት ተጠሪ ባሉበት ለመመርመር ለዚህ ችሎት ያስቀርባል ብሐል። ተጠሪም በ 10/11/2009ዓ.ም የተፃፈ መልስ ያቀረቡ ሲሆን መሰረታዊ ይዘቱም የሥር ፍ/ቤቶች የአመልካች ዉል ይሰረዝልኝ ጥያቄ በይርጋ ዉድቅ ማድረጋቸዉ ተገቢ መሆኑን ቀሪ ብር 20,000 በሴት ልጃቸዉ ወይዘሪት ሩቅያ አደም በኩል የተላከላቸዉ በመሆኑ የስር ፍ/ቤት ዉሳኔ እንዲጸና ጠይቀዋል። አመልካች አቤቱታቸዉን የሚያጠናክር የመልስ መልስ አቅርቧል።
የጉዳዩ አመጣጥም አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለፀዉ ሲሆን እኛም የስር ፍ/ቤቶች የሰጡት ብይንና ትእዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት መሆን አለመሆኑን መርምረናል።
እንደመረመርነዉም አመልካች ከተጠሪ ጋር ህዳር 8 ቀን 1998ዓ/ም ባደረጉት ስምምነት 1000 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈዉ ወፍጮ የጋራ ያደረጉ መሆኑን የተካደ ጉዳይ አይደለም። በልላ በኩል አመልካች እና ተጠሪ ጥር 16 ቀን 2002ዓ.ም በተፃፈ ዉል ንብረቱ ብር 90,000 ዋጋ እንዳለዉ በመገመት አንዱ ወገን እንዲያጠቃልለዉ ተስማምተዋል። በዚህም መሰረት ተጠሪ የአመልካች ድርሻ ብር 35,000 ከፍለዉ እንዲጠቀልሉት ስምምነት መደረጉን መዝገቡ ያሳያል። ከመዝገቡ እንደተረዳነዉ አመልካች በአንድ በኩል ዉሉ እንዲሰረዝ ሲጠይቁ በልላ በኩል ደግሞ ቀሪዉ ገንዘብ ብር 20,000 ያልተከፈላቸዉ ስለመሆኑ ካደረጉት ክርክር መገንዘብ ችለናል። አመልካች ዉሉ እንዲሰረዝ ለመጠየቅ መነሻ ያደረጉት ዕድሜያቸዉ ከ 80 ዓመት በላይ ከመሆኑም በላይ የንግድ ልምድም የለኝም በሚል ስለመሆኑ መዝገቡ ያሳያል። በመርህ ደረጃ ዉል ለአንድ ወገን የበለጠ ጥቅም ይሰጣል በሚል እንደማይፈርስ ነገር ግን ፈቃድ የተገኘዉ በዕድሜ መግፋት ወይም የንግድ ልምድ ዕዉቀቱ ማነስ ካለና በሕላና ግፍ መስሎ ከታየ ዉሉ የሚሰርዝበት ሁኔታ መኖሩን የፍ/ሕ/ቁ. 1710(1) እና (2) ድንጋጌዎች ያስገነዝበናል። የዉሉ ይሰረዝልኝ ጥያቄ መቅረብ ያለበትም በሕጉ በተደነገገዉ ጊዜ ገደብ ዉስጥ መሆን ያለበት ሲሆን በተያዘዉ ጉዳይ ስምምነት የተደረገዉ ጥር 2002 ዓ/ም ሲሆን የዉል ይሰረዝልኝ ክስ ያቀረበዉ ሚያዝያ 10 ቀን 2008 ዓ.ም መሆኑን መዝገቡ ያሳያል። አንድ ተዋዋይ የዉል ይሰረዝልኝ ክስ ዉሉ የማይረጋበት ምክንያት ከቀረቡት ጊዜ ጀምሮ በሁለት ዓመት ዉስጥ ማቅረብ ያለበት መሆኑን በፍ/ሕ/ቁ.1810(1) ተመልክቷል። ከዚህ አንፃር አመልካች የዉል ይሰረዝልኝ ክስ በሁለት ዓመት ጊዜ ዉስጥ አለማቅረባቸዉን መዝገቡ ያሳያል። ከዚህ በተያያዘ የአመልካች የዳኝነት ጥያቄ ግልጽነት የልለዉ መሆኑን ተመልክተናል። ምክንያቱም አመልካች ብር 20,000 እንዲከፈላቸዉ የጠየቁ ሲሆን በልላ በኩል ደግሞ የተጠሪ ድርሻ ብር 35,000 ከፍለዉ ንብረቱ እንዲያስቀሩ ዳኝነት መጠየቃቸዉን ካቀረቡት ክርክር መገንዘብ ችለናል።
No topics extracted.
አመልካች ከተጠሪ ጋር ፈፀምኩት ያሉትን ዉል ችግር ያለበት ከሆነ ዉሉ ይሰረዝ ብለዉ ከሚጠይቁ በቀር በተለየ አግባብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያቀረቡት ክርክር የህግ መሰረት የለዉም። አመልካች ክሱን መብታቸዉን ለማስከበር በህጉ የተመለከተዉ የሁለት ዓመት ጊዜ ገደብ ጠብቀዉ ያላቀረቡት በመሆኑ የስር ፍ/ቤት በብይን ዉድቅ ማድጋቸዉ የሚነቀፍ ሆኖ አልተገኘም።
አመልካች ያቀረቡት የዉል ይሰረዝልኝ ክስ በይርጋ ዉድቅ መደረጉ ተገቢ ቢሆንም አመልካች የጠየቁት ብር 20,000 ያልተከፈላቸዉ ከሆነ ተገቢዉን ዳኝነት ከፍለዉ ክስ የማቅረብ መብታቸዉ ላጠበቅ ይገባ ነበር። በመሆኑም የስር ፍርድ ቤቶች ዉል ለማሰረዝ ያቀረበ ክስ ዉድቅ ማድረጋቸዉ በዉጤት ደረጃ መሰረታዊ የህግ ስህተት የልለበት ቢሆንም አመልካች አለኝ የሚሉትን ቀሪ ገንዘብ የመጠየቅ መብታቸዉ ግን ላጠበቅ ይገባል። በዚህም ተከታዩን ወስነናል።
በቤ/ጉ/ክ የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍረድ ቤት በፍ/መ/ በ25/09/2008 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት የሰጠዉ ብይን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በፍ/ይ/መ/ በ24/2/2009 ዓ.ም የሰጠዉ ትእዛዝ የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በፍ/ሰ/መ/ በ5/05/2009 ዓ/ም የሰጠዉ ትእዛዝ በዉጤት ደረጃ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበት አይደለም በማለት አጽንተናል።
አመልካች ከተጠሪ ጋር አደረጉት ባሉበት የጋራ ሀብት በአንድ ወገን የመጠቅለል ዉል ያልተከፈለኝ ያሉትን ብር 20,000 ስልጣን ባለዉ ፍርድ ቤት ክስ የማቅረብ መብታቸዉ ይህ ዉሳኔ አያግዳቸዉም ብለናል።
ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ። መዝገቡ ተዘጋ ወደ መ/ቤት ተመለሰ።