አንድ የሽያጭ ውል ያደረገ ወገን የተደረገው የሽያጭ ውል ያለመመዝገቡን የማይንቀሳቀስ ንብረት በእጁ ባስገባ 3ኛ ወገን ላይ በመቃወሚያነት ለማንሳት የማይችል ወ/ሮ እናኒ ተሰማ እና እነቄስ ገብረማርያም IV የሽያጭ ውል ያደረገ ወገን በውሉ መሰረት የማይንቀሳቀስ ንብረት ለ3ኛ ወገን ለማስተላለፍ የተከናወኑ ተግባራትን ሁሉ ለመቃወም የሚችለው የተደረገው የሽያጭ ውል የተመዘገበ ከሆነ ብቻ ስለመሆኑ፣ የፍ/ብ/ህ/ቁ. 2878
No summary available.
መስከረም 25 ቀን 2010 ዓ.ም ዳኞች፡- ረታ ቶሎሳ ተፈሪ ገብሩ ቀነአ ቂጣታ አብዬ ካሳሁን ፀሐይ መንክር አመልካች፡- ወ/ሮ እናኒ ተሰማ ቀረቡ ተጠሪ፡-
ጉዳዩየቀረበውን የአደአ ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁ. 44309 ሚያዚያ 26 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ፤ የምስራቅ ሸዋ መስተዳድር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ጥር 26 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ እንዲሁም የኦሮሚያ ብሕራዊ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ የካቲት 09 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ትዕዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ላታረምልኝ ይገባል በማለት አመልካች የካቲት 14 ቀን 2008 ዓ.ም የተጻፈ 04 ገጽ የሰበር አቤቱታ በማቅረባቸውነው።
ክርክሩ የቤት ሽያጭ ውልን የሚመለከት ሲሆን በአደአ ወረዳው ፍርድ ቤት የአሁን አመልካች ከሳሽ ተጠሪዎች ደግሞ ተከሳሾች በመሆን ተከራክረዋል።ለጉዳዩ መነሻ ምክንያት የሆነው አመልካች ሐምል 17 ቀን 2006 ዓ.ም የተፃፈ ክስ በአሁን ተጠሪዎች ላይ በማቅረባቸው ሲሆን የክሱ ይዘት በአጭሩ፡-1ኛ እና 2ኛ ተጠሪዎች የካቲት 01 ቀን 2003 ዓ.ም በተደረገ የቤት ሽያጭ ውል ለአሁን አመልካች በብር 32,000/ሰላሳ ሁለት ሺህ ብር/ የሸጡላቸውን በቢሾፍቱ ከተማ 01 ቀበል ውስጥ የሚገኝ በካርታ ቁጥር ኤ/05/026 የተመዘገበ በ105 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተሰራ ቤት በአንድ በኩል ቤቱን የሚመለከቱ ሰነዶችንና ስም ለማዞር የሚያስችል ውክልና ለአሁን አመልካች ከሰጡ በኋላ በልላ በኩል ከአሁን 3ኛ ተጠሪ ጋር ሰኔ 22 ቀን 2003 ዓ.ም በተደረገ የአከራካሪው ቤት ሽያጭ ውል መነሻነት ቤቱን ለ3ኛው ተጠሪ በመሸጥ ስመ ንብረቱ በ3ኛው ተጠሪ እንዲመዘገብ ያደረጉ በመሆናቸው፤ 4ኛው ተጠሪም ስለ ቤቱ በአግባቡ ሳያጣራ ስመ ንበረቱን በአሁኑ 3ኛ ተጠሪ መመዝገቡ ተገቢ ባለመሆኑ በ1ኛና 2ኛ ተጠሪዎችና በ3ኛው ተጠሪ መካከል የተደረገው የቤት ሽያጭ ውል ቀሪ ሆኖ በአመልካችና በ1ኛና 2ኛ ተጠሪዎች መካከል የተደረገው የቤት ሽያጭ ውል ተፈፃሚነት እንዲኖረው በመጠየቅ ያቀረቡት ክስ ነበር።
1ኛና 2ኛ ተጠሪዎች በአቀረቡት ክርክር ቤቱን ለአሁን አመልካች መሸጣቸውን አምነው 3ኛው ተጠሪ ከአመልካች ጋር በጋብቻ ውስጥ የነበሩ በመሆናቸው በወቅቱ ስሙ እንዲዞርላቸው የተደረገ መሆኑን ገልፀው ሲከራከሩ 3ኛው ተጠሪ በበኩላቸው አከራካሪውን ቤት አመልካች ከ3ኛ ተጠሪ ጋር ከተለያዩ በኋላ የገዙት ሆኖ እያለ ያላግባብ 3ኛው ተጠሪ ከ1ኛና 2ኛ ተጠሪዎች እንዲሁም ከ4ኛ ተጠሪ ጋር በመመሳጠር በስማቸው በማስመዝገብ የገዙት መሆኑን በመጥቀስ አመልካች ከ1ኛና 2ኛ ተጠሪዎች ጋር ያደረጉት የሽያጭ ውል ተቀባይነት ቢያገኝ እንደማይቃወሙ በመከራከር መልስ አቅርበዋል። 4ኛውም ተጠሪ በበኩላቸው የአመልካች ክርክር ቅን ልቦና የጎደለውና አከራካሪውን ቤት ከልዩ ልዩ ዕዳ ለማዳን የሚደረግ እንጂ አመልካች ከተጠሪ ጋር ባልና ሚስት በነበሩበት ወቅት በባላቸው ስም ቤቱን መመዝገቤ ስህተት የለበትም በማለት ተከራክሯል።
የ3ኛው ተጠሪ ሚስት የሆኑት ወ/ሮ ሕይወት አውድ ጣልቃ ገብተው ከ3ኛው ተጠሪ ጋር ከጥር 19 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ጋብቻ መስርተው ሲኖሩ ቆይተው በፍች የተለያዩ በመሆናቸው አከራካሪው ቤት የጋራ ሀብት ነው ተብሎ በፍርድ ቤት ተወስኖ ለመካፈል በሂደት ላይ የሚገኝ በመሆኑ የአመልካች ክስ አቤቱታ ውድቅ ላሆን ይገባል በማለት ክርክር አቅርበዋል።
በጣልቃ ገቢዋ አቤቱታ ላይ መልስ እንዲሰጡበት የታዘዙት 1ኛና 2ኛ መልስ ሰጭዎች የአከራካሪው ቤት ስመ ንብረት የተመዘገበው በ3ኛው ተጠሪ ስም በመሆኑ የጣልቃ ገብ አቤቱታ ተቀባይነት ቢያገኝ እንደማይቃወሙ ሲከራከሩ 3ኛው ተጠሪ በበኩላቸው አከራካሪው ቤት አመልካች የገዙት የግል ሀብታቸው ሆኖ እያለ 3ኛው ተጠሪ በማሳሳት በስማቸው ያስመዘገቡት በመሆኑ አከራካሪው ቤት የአመልካች ሀብት ነው ተብሎ ቢወሰን ተቃውሞ እንደልላቸው ተከራክረዋል። 4ኛው ተጠሪ ከጣልቃ ገብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የልላቸው መሆኑን ጠቅሰው አቤቱታቸው ውድቅ እንዲሆን አመልክተዋል።
ጉዳዩን በመጀመሪያ ደረጃ የተመለከተው የአደአ ወረዳ ፍርድ ቤትምየግራቀኙን ወገኖች የቃልክርክርእናማስረጃዎችበመመርመር አመልካች ከ1ኛና 2ኛ ተጠሪዎች ጋር የቤት ሽያጭ ውል አድርጌአለሁ ቢሉም የተመዘገበ የቤት ሽያጭ ውል የልለ በመሆኑ አቤቱታቸው ተቀባይነት የለውም፤ጣልቃ ገብ ከአከራካሪው ቤት ድርሻ አለኝ በማለት ያቀረቡት አቤቱታም በዚህ መዝገብ የተያዘው ክርክር የንብረት ክፍፍል ጉዳይ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም በማለት የአመልካችንም ሆነ የጣልቃ ገብን ክርክር ባለመቀበል ወስኗል።
አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅርበመሰኘትለምስራቅ ሸዋ መስተዳድር ዞን ከፍተኛፍርድ ቤት ይግባኝ በማቅረባቸውፍርድ ቤቱተጠሪዎችን አስቀርቦ ሲያከራክር ቆይቶ እንዲሁም አከራካሪውን ቤት በ3ኛው ተጠሪ ዕዳ ምክንያት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በወጣ ሀራጅ ገዝቸዋለሁ ያሉትን አቶ ሀይሉ ሳህልን በጣልቃ ገብነት ወደ ክርክሩ አስገብቶ ግራቀኙንአከራከሮሲያበቃ አከራካሪው ቤት 1ኛና በ2ኛ ተጠሪዎች ከአመልካች ጋር የካቲት 01 ቀን 2003 ዓ.ም በአደረጉት የሽያጭ ውል ለአመልካች መሸጣቸው ተረጋግጧል። በልላ በኩል ሰኔ 22 ቀን 2003 ዓ.ም በተደረገ የቤት ሽያጭ ውል አከራካሪው ቤት ለ3ኛ ተጠሪ ተሽጧል። ይህ ቤት የ3ኛ ተጠሪና የወ/ሮ ሕይወት አውድ የጋራ ንብረት ለመሆኑ በፍድራል ፍርድ ቤት 3ኛ ተጠሪና ወ/ሮ ሕይወት አውድ በአደረጉት የጋብቻ ሀብት ክርክር ተረጋግጧል። ከ3ኛ ተጠሪ ዕዳ ጠያቂ የሆኑ በርካታ ሰዎችም ቤቱን በፍርድ ቤት አስከብረው ክርክር እያደረጉ ቆይተዋል። የአሁን አመልካችም 3ኛ ተጠሪ ከገንዘብ ጠያቂዎች ጋር ሲከራከሩ የ3ኛው ተጠሪ ሚስት ነኝ፤
ድርሻም በአከራካሪው ቤት ላይ አለኝ በማለት ጣልቃ ገብተው ክርክር ሲያደርጉ ቆይተዋል። ስለሆነም አከራካሪው ቤት በ3ኛው ተጠሪ ተመዝግቦ እንደሚገኝ ያውቁ ነበር። አከራካሪው ቤት በብር 240,000/ሁለት መቶ አርባ ሺህ ብር/ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በጨረታ ተሸጦ አቶ ሀይሉ ሳህል የተባሉት ገዝተውታል። ስመ ንብረቱም በአቶ ሀይሉ ሳህል ስም ተመዝግቦ ይገኛል። በመሆኑም አመልካች የካቲት 01 ቀን 2003 ዓ.ም የተደረገው ውል ፀንቶ ሰኔ 22 ቀን 2003 ዓ.ም የተደረገው ውል እንዲፈርስ ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት ያለው አይደለም በማለት በውጤት ደረጃ የአደአ ወረዳ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አፅንቶታል። አመልካች በዚሁ ውሳኔ ቅር በመሰኘትና መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በማለት ለማሳረም ለኦሮሚያ ብሕራዊ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም።
አመልካች ይህንን የሰበር አቤቱታ ያቀረቡት የሥር ፍርድ ቤቶች ዳኝነት መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈፅሞበታል በሚል ሲሆን አቤቱታቸው በአጭሩ፡- አመልካች ከ1ኛና 2ኛ ተጠሪዎች ጋር የካቲት 01 ቀን 2003 ዓ.ም ያደረጉት የቤት ሽያጭ ውል እያለ 1ኛና 2ኛ ተጠሪዎች ከ3ኛ ተጠሪ ጋር ያላግባብ ያደረጉት ሽያጭ የቤት ውል መነሻ ተደርገው በተከናወኑት ተግባራት የተነሳ አመልካች መብቴን እንዳጣ የተደረገ በመሆኑ የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ተሽሮ አከራካሪው ቤት ለአመልካች ይገባል ተብሎ ላወሰንልኝ ይገባል በማለት ያቀረቡት ነው።
ሰበር አጣሪው ችሎቱም መዝገቡን መርምሮ አመልካች ከ1ኛና 2ኛ ተጠሪዎች ጋር በፈፀሙት የቤት ሽያጭ መነሻነት ውክልናና ሰነዶችን ተረክበው እያለ 1ኛና 2ኛ ተጠሪዎች ለ3ኛው ተጠሪ እንደገና ቤቱን መሸጣቸው አግባብነቱ ላጣራ ይገባል በማለት አቤቱታው ለሰበር ያስቀርባል በማለቱ ተጠሪዎች የሥር ክርክራቸውን በማጠናከር መልስአቅርበዋል። አመልካችም የመልስ መልስ አቅርበዋል።
ክርክሩ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ተጠናቋል። እኛም አቤቱታው ለሰበር ያስቀርባል ከተባለበት ነጥብ አንጻር ጉዳዩን እንደሚከተለው መርምረናል። ከመዝገብ ምርመራው መገንዘብ እንደተቻለው አከራካሪውን ቤት በተመለከተ የካቲት 01 ቀን 2003 ዓ.ም በአመልካችና በተጠሪ መካከል የሽያጭ ውል ተደርጎ እንደነበር፤ ሰኔ 22 ቀን 2003 ዓ.ም ደግሞ በ3ኛ ተጠሪና በ1ኛና 2ኛ ተጠሪዎች መካከል ልላ የሽያጭ ውል መደረጉን፤ 3ኛ ተጠሪ ሚስታቸው ከነበሩት ወ/ሮ ሕይወት አውድ ጋር ፍች ሲፈፅሙ ይኸው ቤት የባልና ሚስት የጋራ ሀብት ነው ተብሎ በፍርድ ቤት መወሰኑን፤3ኛው ተጠሪ ከልሎች ገንዘብ ጠያቂዎች ጋር ባደረጉት ክርክር ተፈርዶባቸው አከራካሪው ቤት በጨረታ ተሸጦ አቶ ሀይሉ ሳህል የተባሉት ግለሰብ ገዝተው ስመ ንብረቱ በአቶ ሀይሉ ሳህል ስም ተመዝግቦ እንደሚገኝ የተረጋገጠ ከመሆኑም በላይ የአሁን አመልካች በ3ኛው ተጠሪና በገንዘብ ጠያቂዎቹ መካከል በፍድራል ፍርድ ቤቶች በተደረገው ክርክር ከ3ኛው ተጠሪ ጋር ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ባልና ሚስት ሆነን እየኖርን በመሆኑ አከራካሪው ቤት የአመልካች ድርሻ ያለበት ነው በሚል በ2004 ዓ.ም ወደ ክርክሩ ጣልቃ ገብተው መከራከራቸውን የሥር ፍርድ ቤት ያረጋገጠው ፍሬ ነገር ከመሆኑም በላይ ይህ ችሎትም የፍድራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መዝገብ የሆነውን አስቀርቦ ተገንዝቧል።
በሥር ፍርድ ቤት የተረጋገጡ ፍሬ ነገሮችን መሰረት አድርገን እንደመረመርነው 3ኛው ተጠሪ ከአመልካች ጋር ባልና ሚስት ሆነው ባሉበት ጊዜ አከራካሪውን ቤት በባል ስም የተመዘገበ ነው ከሚባል በስተቀር 3ኛው ተጠሪ የአመልካችን ቤት ያላግባብ በስማቸው አስመዝግበዋል ለማለት የሚበቃ ምክንያት የለም። ምክንያቱም አመልካች ራሳቸው በ2004 ዓ.ም አከራካሪው ቤት የአመልካችና የ3ኛው ተጠሪ ንብረት ስለመሆኑ አምነውበዚሁ ቤት ላይ ያላቸውን ድርሻ ከ3ኛው ተጠሪ ገንዘብ ጠያቂዎች ለማስቀረት ሲከራከሩ ለመቆየታቸው በፍድራል ፍርድ ቤት መዝገብ ውስጥ የሚገኙ ማመልከቻዎች ያስረዳሉ።
በልላም በኩል ሲታይ አከራካሪው ቤት ወደ ሶስተኛ ወገኖች በመተላለፍና የፍርድ ቤት ውሳኔም አርፎበት በአሁኑ ጊዜ ለአቶ ሀይሉ ሳህል በሀራጅ ተሸጦ ስመ ንብረቱ ከ3ኛው ተጠሪ ወደ አቶ ሀይሉ ሳህል ተላልፎ የሚገኝ ለመሆኑ የሥር ፍርድ ቤት ያረጋገጠው ፍሬ ነገር ነው። በፍትሐ ብሕር ህጉ አንቀጽ 2878 ሥር እንደተመለከተው አንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ በሶስተኛ ወገኖች መቃወሚያ ሆኖ እንዲነሳ ከተፈለገ ውሉ በማይንቀሳቀስ መዝገብ መፃፍ አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም አመልካች በወቅቱ ባላስመዘገቡት ሽያጭ መነሻነት ህጉን ተከትሎ ቤቱን ለ3ኛው ወገን ለማስተላላፍ የተከናወኑ ተግባራትን ሁሉ ላቃወሙ የሚችሉበት አግባብ አይኖርም ።
ለማጠቃለል ከአጠቃላይ የክርክር ይዘት መገንዘብ የሚቻለው አመልካች ከ3ኛ ተጠሪ ጋር ባልና ሚስት ሆነው እስከ 2004 ዓ.ም የቆዩ መሆናቸውን ሲሆን አከራካሪው ቤት በ3ኛው ተጠሪ ስም የተመዘገበውም አመልካች ከ3ኛ ተጠሪ ጋር ባልና ሚስት ሆነው ባሉበት ጊዜ ነው። በልላም በኩል ሲታይ አከራካሪው ቤት ወደ ሶስተኛ ወገን እጅ የገባ በመሆኑ አመልካች የካቲት 01 ቀን 2003 ዓ.ም ያደረጉት የሽያጭ ውል አለመመዝገቡ አከራካሪውን ቤት በሂደት ወደ እጃቸው በአስገቡት ሶስተኛ ወገኖች ላይ መቃወሚያ ሆኖ መነሳት የሚገባው ባለመሆኑ የሥር ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ የፈፀሙት መሰረታዊ የህግ ስህተት አልተገኘም። ስለሆነም ተከታዩን ወስነናል።
የአደአ ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁ. 44309 ሚያዚያ 26 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ውሳኔ፤ የምስራቅ ሸዋ መስተዳድር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ጥር 26 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠውውሳኔ እንዲሁም የኦሮሚያ ብሕራዊ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ የካቲት 09 ቀን 2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጠው ትዕዛዝ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈፀመበት ሆኖ ባለማግኘታችን በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 348(1) መሰረት አፅንተነዋል።
የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔያቸው የፀና መሆኑን እንዲያውቁት የዚህ ችሎት ውሳኔ ግልባጭ ይተላለፍላቸው።
በዚህ ችሎት ክርክር ለወጣ ወጭና ኪሳራ ግራቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ።
በዚህ ችሎት የተሰጠው እግድ ተነስቷል፤ይጻፍ።
No topics extracted.